በኔይማር ወጥመድ የገባዉ ባለተሰጥኦ

0
130

ላሚን ያማል በኔይማር ጁኔር፣ በሊዮኔል ሜሲ እና በክርስቲያኖ ሮናልዶ ደረጃ ትልቅ ተሰጥኦ እና ክህሎት እንዳለው ብዙዎች ይናገራሉ። የእነዚህ ባለተሰጥኦ የእግር ኳስ ተጫዋቾች አልጋ ወራሽ እንደሚሆንም ብዙ ተወርቶለታል። ያማል ከላሜሲያ አካዳሚ የተገኘ ድንቅ ባለተሰጥኦ ነው፤ ግቦችን ያስቆጥራል፣ ግብ የሚሆኑ ኳሶችንም ለቡድን ጓደኞቹ አመቻችቶ ያቀብላል፤ አንድ ለአንድ የትኛውንም ተጫዋች ማለፍ የሚችል አስደናቂ ተሰጥኦ ያለው ሲሆን በተጋጣሚ ቡድን ላይ ሽብር የሚፈጥር ፈጣን እና ባለክህሎት ታዳጊ ነው።

ያማል በቅርቡ 18ኛ ዓመት የልደት በዓሉን አክብሯል። ይህን ተከትሎም ሕጋዊ የሆነ የረጅም ጊዜ የውል ስምምነት ከየትኛውም ክለብ ጋር መፈራረም የሚያስችለውን ዕድል አግኝቷል። እንደዚህ ዓይነት እድል ያገኘበትን የልደት በዓሉን ሲያከብር ግን በርካታ የእግር ኳስ ባለሙያዎችን እና ደጋፊዎችን ያነጋገር ሁነት ተፈጥሯል።

 

ያማል በቅርቡ ላከብረው የልደት በዓል ዝግጅት ድንኮችን (በጣም አጫጭር ሰዎችን)፣ ሞዴሎችን እና ሌሎች ታዋቂ ሰዎች እንዲገኙ ገንዘብ መክፈሉን መረጃዎች አመልክተዋል። ታዲያ የስፔን መንግሥትም የአካል ጉዳተኞችን እና የሴቶችን መብት ተጋፍቷል በሚል ምርመራ ጀምሮበታል። በእርግጥ የልደት በዓሉን ብቻ ሳይሆን የእረፍት ጊዜውን ያሳለፈበት መንገድም በእግር ኳስ ህይወቱ ላይ አደጋ ሊፈጥር የሚችል አካሄድ እየተከተለ ስለመሆኑ እየተነገረ ይገኛል። በእረፍት ቀኑ ወደ ብራዚል አቅንቶ ኔይማርን መጎብኘቱም አይዘነጋም።

የልደት በዓሉን ምክንያት በማድረግ የጭፈራ እና የዳንኪራ መድረክ ማዘጋጀት ከአርአያው ኔይማር ጁኔር የኮረጀው ተግባር መሆኑን ፕላስ ስፖርት አስነብቧል። ኔይማር ጁኔርን በርካታ ታዳጊ የእግር ኳስ ተጫዋቾች አርአያ አድርገው ዘርፉን ተቀላቅለዋል፤ አሁንም እየተቀላቀሉ ነው። ሜዳ ውስጥ በሚያሳያው ድንቅ የእግር ኳስ ክህሎት በመማረክ ታላቅ የእግር ኳስ ተጫዋች የሆኑ በርካቶች ናቸው።

 

ከእነዚህ መካከል ብራዚላዊው የክንፍ ተጫዋች ሮድሪጎ፣ ጀርመናዊው አማካይ ጀማል ሙሲያላ፣ እንግሊዛዊው የጨዋታ አቀጣጣይ ኮል ፓልመር፣ ኔዘርላናዳዊው ዣቪ ሲሞኒ እና ፈረንሳያዊው ዴሲሬ ዶዌ ብራዚላዊው ባለተሰጥኦ ሜዳ ውስጥ የሚያከናውናቸውን ተግባራት አርአያ አድርገው ታላቅ ደረጃ የደረሱ ተጫዋቾች ናቸው። በአንጻሩ ደግሞ እንደ ላሚን ያማል ያሉ ታዳጊዎች ሜዳ ውስጥ ባለው ተግባሩ፣  ከሜዳ ውጪ በሚያሳየው ባህሪው እና በሚከተለው የአኗኗር ዘይቤ የሚማረኩ፣ ተማርከውም የሚከተሉት አሉ።

 

የኔይማር ጁኔር ተጽእኖ ከብራዚላውያን የእግር ኳስ ባለተሰጥኦዎች አልፎ አውሮፓን ተሻግሮ በአራቱም የዓለም ማዕዘን አርፏል። ወጣቶችም ድንቅ የእግር ኳስ ክህሎቱን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የኔይማር ህይወቱን በመኮረጅ ከሜዳ ውስጥ እና ከሜዳ ውጪም ተግባራዊ ለማድረግ ሲሞክሩ ይስተዋላል። ይህ ደግሞ በተጫዋቾች የእግር ኳስ ህይወት  አደጋ እንዳይፈጥር ብዙዎች ስጋት አድሮባቸዋል።

ኔይማር ሜዳ ውስጥ አስመስሎ መውደቅ የተካነበት እንደሆነ የሜል ስፖርት መረጃ ያስነብባል። ይህንን መጥፎ የሜዳ ላይ ልማድም ኬሊያን ምባፔ፣ ሊዊስ ስዋሬዝ፣ አርያን ሮበን፣ አሽሊ ያንግ እና ብሩኖ ፈርናንዴዝን የመሳሰሉት ይጠቀሙበታል እየተባለ ይኮነናሉ። ከሜዳ ውጪም የብራዚላዊው ባለተሰጥኦ ተጽእኖ በወጣት ተጫዋቾች ዘንድ እጅግ የጎላ ነው።

 

ኔይማር ጁኔር በትውልዱ ካሉ ባለተሰጥኦ የእግር ኳስ ተጫዋቾች መካከል የሚጠቀስ ቢሆንም ባሎንዶር ሳያሸንፍ የአውሮፓን ምድር በመልቀቅ ወደ ልጅነት ክለቡ አምርቷል። አቅሙን አውጥቶ እና ተሰጥኦውን በሚገባ እንዳይጠቀምበት ተደጋጋሚ ጉዳትም መሰናክል እንደሆነው አይዘነጋም። በዋናነት ግን ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ትኩረት ማድረጉ፣ ፓርቲ በማዘጋጃት ዳንኪራ ማብዛቱ፣ በየጊዜው ለጋዜጣ እና ለመጽሔት የፊት ገጽ ማድመቂያ የሚሆኑ አነጋጋሪ እና አወዛጋቢ ጉዳዮች ላይ መሳተፉ የእግር ኳስ ህይወቱን አበላሽቶታል። ከሙያው ይልቅ ዝናውን እና የአኗኗር ዘይቤው ላይ ትኩረት ማድረጉ እግር ኳሱን እንዲዘነጋ ምክንያት ሆኖታል። በዚህ ድርጊቱም በርካቶች ይኮንኑታል። የቀድሞ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ሩድ ጉሌት እና ፍራንክ ሌባኦፋንን የመሳሰሉ የቀድሞ ተጫዋቾች የፕሮፌሽናል ተጫዋች ስነ ምግባር የለውም  ይሉታል።

ኔይማር የእህቱን ልደት ለማክበር ጉዳት ገጥሞኛል እስከማለት የደረሰ ተጫዋች ነው፤ ታዲያ ለሙያው የማይታመን የስነ ምግባር ችግር ያለበት ተጫዋች እንደሆነም የቀድሞ ተጫዋቾች ይናገራሉ። አብዝቶ መዝናናትን የሚወደው ኔይማር በመጨረሻም በአውሮፓ ምድር በእግር ኳሱ ዓለም የሚታወስበት አንድም ትልቅ የግል ሽልማት ሳያሸንፍ የእግር ኳስ ምዕራፉን ለመደምደም ተቃርቧል።

 

በፓርክ ደ ፕሪንስ ቆይታው ካሳየው ክህሎት ይልቅ ባዘጋጀው የዳንኪራ ድግስ ብዙዎች እንደሚያስታውሱት ጎል ዶት ኮም አስነብቧል። የፓርቲ ድግስ በማሰናዳት የሚታወቀው ኔይማር “የድግስ ሰው” የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶታል። ብራዚላዊው ኮከብ በፓሪስ የምሽት ክለቦች የማይጠፋ ተጫዋች እንደነበረ ጭምር ጎል ዶት ኮም አመልክቷል።

የኔይማር የልጅነት አርአያ የሀገሩ ልጅ ሮቢንሆ ቢሆንም እግር ኳስን መረዳት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ግን ሌላኛው ብራዚላዊ ሮናልዲንሆ ጎቾ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲናገር ተደምጧል። ሮናልዲንሆ በእግር ኳስ ታሪክ የላቀ ተሰጥኦ ካላቸው ተጫዋቾች አንዱ እንደነበር አይዘነጋም። ይሁን እንጂ ከእግር ኳስ ውጪ ባሉ ጉዳዮች መጠመዱ የእግር ኳስ ህይወቱን አክሽፎታል። ዳንኪራ  መውደዱ እና ያልተገራ ስነ ምግባር መያዙ በእግር ኳሱ እንዳይታወስ አድርጎታል። ይህም እግር ኳስ ካቆመ በኋላ የገንዘብ ችግር እንዲገጥመው ምክንያት ሆኖታል። ኔይማር ጁኔር የሮናልዲንሆን መንገድ መከተሉ በተጠበቀው ልክ በእግር ኳስ ህይወቱ እንዳይደምቅ መሰናክል ሆኖታል። ያማል ደግሞ የኔይማርን መንገድ እየተከተለ ነው ሲሉ ብዙዎች ተናግረዋል።

 

የተጫዋቾች አርአያ (ተምሳሌት) የሚሆን በእግር ኳስ ብቻ ሳይሆን በግል ህይወታቸው ላይም አሉታዊ ተጽእኖ ያሳርፋል። በእግር ኳስ ስፖርት ሁሉም አርአያ የሚሆኑ ስፖርተኞች በጎ ተጽእኖ አይኖራቸውም። አንዳንድ ተጫዋቾች ምንም እንኳ ክህሎት እና ተሰጥኦ ቢኖራቸውም ለወጣት አትሌቶች ግን አርአያ የሚሆን ባህሪ ወይም የአኗኗር ዘይቤ የላቸውም። ጥቂቶች በስነ ምግባራቸው እና በሙያቸው ብቁ መሆናቸው ለሌሎች ተምሳሌት ሲሆኑ አንዳንዶች ደግሞ ሜዳ ውስጥ በሚያሳዩት ያልተገባ ባህሪ እና የግል ህይወታቸው ምክንያት አርአያ መሆን አይችሉም።

ሊዮኔል ሜሲ እና ክርስቲያኖ ሮናልዶ ለዓመታት ስማቸውን እና ዝናቸውን ጠብቀው በወጥነት የተጫወቱበት ሚስጥር ለሙያቸው መታመናቸው ፣ ሥራቸውን ማክበራቸው እና እግር ኳሱ ላይ ትኩረት ማድረጋቸው እንደሆነ ጎል ዶት ኮም  ያስነብባል። የ18 ዓመቱ ያማል እና ኔይማር ጁኔርን የሚያመሳስላቸው የፓርቲ ድግስ መውደዳቸው መሆኑን ፖላንዳዊ ግብ ጠባቂ ዊችኒ ሲዝኒ ተናግሯል። “ሁሉም የራሱ የሆነ ህይወት መንገድ አለው፤ ላሚን ያማል ግን እየሄደበት ያለው መንገድ ቀይ መብራት ያለው ነው” ሲል የእግር ኳስ ህይወቱ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ስጋቱን አስቀምጧል።

 

የዘንድሮው የያማል የልደት ድግስ በ2020 እ.አ.አ ኔይማር 28ኛ ዓመቱን ሲያከብር ከነበረው ጋር ይመሳሰላል ተብሏል።ድግሱ የታቀደ እና ረጅም ጊዜ የታሰበበት በመሆኑ ያማል የኔይማርን መንገድ እየተከተለ ስለመሆኑ በአስረጅነት አቅርበዋል። እንደ ሜል ስፖርት ዘገባ የታዳጊው ያልተገባ መንገድ ያላማረው የካታላኑ ክለብ በእጅጉ ተጨንቋል። ገና በደንብ ያልታየው ክህሎት እንዳይከስም ስጋት ገብቶታል። ያማል ከኔይማር የእግር ኳስ ህይወት የሚጠቅመውን ብቻ ሳይሆን የማይጠቅመውንም እየወሰደ መሆኑን ሜል ስፖርት ያትታል። የያማል የልደት ድግስ ባርሴሎናን ብቻ ሳይሆን የስፔንን ባለስልጣናትንም አስጨንቋል።

 

ታዳጊ ተጫዋቾች የኔይማርን የእግር ኳስ ህይወት ሳይሆን አኗኗር እና ዝናን አርአያ የሚያደርጉ እየበዙ መሆናቸውን የስፔን የወጣት ተጫዋቾች አሰልጣኝ ጋቢኖ ካራሞን ተናግሯል። ያማል ገና ታዳጊ በመሆኑ በአካል ብቃት እና በአዕምሮ መብሰል ይጠበቅበታል። ቤተሰቦቹ፣ የቅርብ ሰዎች እና ባለሙያዎች ስለጠንካራ የሥራ ባህል ሊያስተምሩት እንደሚገባ አስተያየቱን ያስቀመጠው የቢቢሲ ስፖርት አምደኛ ጊሊየም ባሌጉ ነው። አሁን ላይ ያማል በካምፕ ኑ የዐስር ቁጥር መለያ ተሰጥቶታል። በካታላኑ ክለብ ቤትም የሜሲን ሌጋሲ ለማስቀጠል ከኔይማር ወጥመድ ማምለጥ ይጠበቅበታል።

በሀገራችንም ለሙያቸው የማይገዙ፣ ከእግር ኳስ ስነ ምግባር ውጪ የሆነ ድርጊት የሚፈጽሙ ተጫዋቾች ጥቂት አይደሉም። አንድ ዓመት በወጥ አቋም ተጫውተው በቀጣይ ዓመት ያንን ምርጥ አቋም ለመድገም ሲሳናቸው መመልከት እንግዳ አይደለም። ዝና እና ገንዘብ የአኗኗር ዘይቤያቸውን እና ትኩረታቸውን  ሲያስቀይራቸው መመልከትም በኢትዮጵያ እግር ኳስ አዲስ አይደለም። ።

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የሐምሌ 21 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here