የመሠረተ ልማት አዋጅ

0
68

ሀገራት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው ከሚያከናውኗቸው ሥራዎች ሙስጥ መሠረተ ልማት አንዱ  ነው:: ለሕዝብ መኖር ወሳኝ  የሆነውን መሠረተ ልማት አቅም በፈቀደ መጠን ለማስፋፋት ከፍተኛ ክትትል እና ጥበቃ ይፈልጋል:: በጉዳዩ ዙሪያ የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ  አቶ ደረጀ ቁምላቸውን አነጋግረናል፤ ዐቃቤ ሕጉ እንዳሉት አንደ ታዳጊ  ሀገር በውስን ሀብት ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት የሚሆኑ መሠረተ ልማቶች በየጊዜው ለተለያዩ ጉዳቶች /ስርቆቶች/ ሲዳረጉ ይስተዋላል::

 

አቶ ደረጀ እንደገለጹት መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ሲደርስ መልሶ ለመጠገን ከፍተኛ ወጪ ከመጠየቃቸው ባሻገር ማኅበረሠቡ ተገቢ አገልግሎት እንዳያገኝ ትልቅ እንቅፋት ይፈጥራል:: ታዲያ ይህንን  በመሠረተ ልማት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት በማስቀረት  ተገቢውን አገልግሎት ለሕዝብ ለመስጠት መሠረታዊ የሚባሉ የሕግ ማዕቀፎች ወጥተው ሥራ ላይ ውለዋል::

 

“መሠረተ ልማት ሲባል ምንድን ነው?” ለሚለው ዐቃቤ ሕጉ ሲያብራሩ የኢፌዴሪ አስፈፃሚ አካላት ሥልጣን እና ተግባር መወሰኛ አዋጅ ቁጥር 1263/2014 ንኡስ ቁጥር 2 መሠረት ሥልጣን እና ተግባሩ ወደ ከተማ ልማት እና መሠረት ልማት ሚኒሥቴር ከመተላለፉ በፊት በተቀናጀ መሠረተ ልማት ማስተባበሪያ ኤጀንሲ አዋጅ ቁጥር 807/2006 አንቀፅ 21 ትርጉሙ ተዘርዝሮ ሰፍሯል:: አዋጁ ከመሬት በላይ ወይም ከመሬት በታች ያለ መንገድ፣ የባቡር ሀዲድ፣ የአውሮፕላን ማረፊያ፣ የቴሌኮሙኒኬሽን መስመር፣ የኤሌክትሪክ ኀይል፣ የመስኖ አውታር ግንባታ፣ የውኃ ወይም የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችንም የሚጨምር በማለት ትርጉም ሰጥቶታል::

 

በዚህ ሕግ አተረጓጐም ሌሎች ለሕዝብ አገልግሎት የሚውሉ ግንባታዎችንም ወደ መሠረተ ልማት የሚጨምር ይሆናል:: በሌላ በኩል አዋጅ ቁጥር 464/1997 የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የኤሌክትሪክ  እና የቴሌ አውታሮች   ምንድን ናቸው? ለሚለው ትርጉም ሲሰጥ የኤሌክትሪክ ኀይል አውታር ማለት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዘርፍ ኀይል ከማስተላለፍ እና ከማመንጨት ጋር አገልግሎት ላይ የዋለ ወይም እንዲውል የታቀደ መሣሪያ፣ የመሣሪያው ተገጣጣሚ ሽቦ፣ ምሰሶ፣ …  ናቸው::

የቴሌኮሙኒኬሽን አውታር የሚባለው ደግሞ ከቴሌ ኮሙኒኬሽን ሥርዓት (ሲስተም) ጋር በተያያዘ አገልግሎት  ላይ የዋለ እንዲሁም የታቀደ ማንኛውም ተገጣጣሚ አካላት፣ ሳተላይት፣ ኦኘቲካል ፋይበር፣ ታወር፣ የቴሌ አንቴና፣ ሽቦ፣ ኬብል፣ ምሰሶ ወይም ከማንኛውም አሠራር ጋር የተያያዘ እንደሆነ አዋጁ ትርጉም ሰጥቶ በዝርዝር  እንዳስቀመጣቸው ባለሙያው አብራርተዋል::

 

በጠቅላላው እነዚህ የመሠረተ ልማት ዘርፎች በመዋቅራዊ እና አገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ ለሁለት ተከፍለው ይቀመጣሉ:: እነዚህም የኤሌክትሪክ (የኀይል)፣ የመጓጓዣ /የትራንስፓርት/፣ የግንኙት እንዲሁም  የውኃ እና ፍሳሽ መሠረተ ልማቶች በመባል እንደሚጠሩ ባለሙያው  ገልፀዋል::

 

በሀገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 13 ላይ በፌዴራል ደረጃም ሆነ በክልል መንግሥት ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈፃሚ እና ሕግ ተርጓሚ አካላት እነዚህ የማሕበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ የመሠረተ ልማት ተቋማትን የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ይደነግጋል:: በየትኛውም መንገድ መሠረተ ልማትን ከማስፋፋት ባሻገር አስፈፃሚ አካላት በመሠረተ ልማት  ምክንያት የሌላውን መሠረተ ልማት ጉዳት ማድረስ እንደማይገባቸው በአዋጅ ቁጥር 857/2006 እና አዋጅ ቁጥር 1363/2014 ላይ ሰፍሯል:: ይህም መሠረተ ልማቶች  ከመጀመራቸው በፊት ከከተማ ልማት እና መሠረተ ልማት ሚኒሥቴር፣  በፌዴራል ደረጃ ሥራውን በሚያካሄዱበት ወቅት ደግሞ ከሌሎች የመሠረተ ልማት ተቋማት ፈቃድ ማግኘት እንደሚገባቸው በአዋጁ ተቀምጧል:: የመሠረተ ልማት ሥራ ከመጀመሩ በፊት በየደረጃው ያሉ የፌዴራልም ሆነ የክልል አስተዳደር አካላትም  ለቴሌኮሙኒኬሽን እና ለኤሌክትሪክ ኀይል የማሳወቅ ኃላፊነት አለባቸው::

 

ባለሙያው አቶ ደረጀ እንደሚሉት በመሠረተ ልማት ላይ በተለያዩ አካላት ስርቆት ከተፈፀመባቸው ወይም በጉዳት  ከተቆራረጡ   ድርጊት ፈጻሚውን ተጠያቂ ያደርጋል:: ይህን ተከትሎም በመሠረተ ልማት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመጠበቅ እና ለመከላከል በወጣው አዋጅ 464 /1997 ማንም ሰው የሀገር ደህንነትን በሚጎዳ መልኩ መሠረተ ልማት ላይ የስርቆት ድርጊት የፈፀመ እንደሆነ፣ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ እና አገልግሎቱ እንዲቋረጥ ያደረገ እንደሆነ  በወንጀል ሕጉ  በበለጠ ካላስቀጣ በስተቀር ከአምስ እስከ 20 ዓመት ፅኑ እስራት እንደሚቀጣ ተደንግጎ ይገኛል::

 

ባለሙያው እንደሚያብራሩት የወንጀል ድርጊቱ መሠረተ ልማት እየተሠራ እያለ በቸልተኝነት የሌላ መሠረተ ልማት የጎዳ እንደሆነ ደግሞ ቅጣቱ ከአምስት ወር እስከ አምስት  ዓመት በሚደርስ እስራት እንዲቀጣ ይወስናል:: መሠረተ ልማት የሚዘረጋ ሎደር፣ የግንባታ መኪና እና ሌሎችም በቸልተኝነት ሥራቸውን እየሠሩ  መስመር ቢቆርጡ፣ ፖል ቢገጩ፣ …. አስቦም ይሁን ሳያስብ  ቢያደርገው ቀድሞ  ጥንቃቄ ማድረግ የሚጠይቅ በመሆኑ ተጠያቂ ከመሆን እንደማያማልጥ የዐቃቤ ሕግ ባለሙያው አስረድተዋል:: ሌላው በወንጀል የሚያስጠይቀው ባልታወቀ አካል ተሰርቆ /ተቆርጦ/ እንዲሁም  ተሸሽጎ የተቀመጠ የኤሌክትሪክ ኀይል /አውታር/ ዕቃ የሸሸገ በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 6 መሠረት ያስቀመጠ፣ የደበቀ፣ የሸጠ፣ ለመሸጥ፣ ለመለወጥ የረዳ እና ያገናኘ እንደሆነ እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና በገንዘብ እስከ 20 ሺህ ብር ገንዘብ  እንደሚቀጣ አስቀምጧል::

 

በሀገሪቱ አጠቃላይ ያሉ መሠረተ ልማቶች የፌዴራል ጉዳይ እንደሆኑ ያነሱት አቶ ደረጀ፤ በክልል ደረጃ ወንጀል ተፈጽሞ ቢገኝም የመጀመሪያ ደረጃ ሳይሆን የመጨረሻ ውሳኔን ክልሎች ፌዴራልን ወክለው መከታተል አለባቸው:: መሠረተ ልማት በሀገሪቱ አጠቃላይ የተዘረጋ ነገር  ስለሆነ የማሕበረሰቡን እንክብካቤ ይፈልጋል  የሚሉት ባለሙያው፤ ምጣኔ ሃብት ሲወድም ደህንነት እና ሀገራዊ ጉዳት ስላለው እና መንግሥት ብቻ ጠብቆ የሚያድናቸው ባለመሆኑ ሁሉም ማሕበረሰብ ሲዘረፉ ተከታትሎ ማስረጃ በማቅረብ እና በመጠበቅ ቅንጅታዊ አሠራር እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል::

 

የህግ አንቀጽ

መሠረተ ልማትን ለመጠበቅ የወጡ ሀገር ዓቀፍ የሕግ ማዕቀፎች፡-

 

  • የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ለማኅበረሰቡ መሟላት እንደሚገባ ስላስቀመጠ መነሻ ይሆናል፡፡
  • የኢፌዴሪ ወንጀል ሕግ፤ የባቡር መጓጓዣ /ትራንስፖርት/ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1048/2019
  • የኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 985/2008
  • የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 761/2004
  • የቴሌ ኮሙኒኬሽን እና ኤሌክትሪክ አውታሮችን ደህንነት ለመጠበቅ የወጣው አዋጅ 464/1997
  • የኢነርጂ አዋጅ ቁጥር 810/2006 ተደንግገው ይገኛሉ፡፡

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የሐምሌ 21 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here