ኢትዮጵያ በመንግሥታቱ ማኅበር 

0
76

የኢትዮጵያን ታሪክ በሚያስገነዝቡ ድርሳናት ላይ እንደተገለጸው የልጅ ኢያሱ የንግሥና ዘመን  ከ1906 እስከ 1909 ዓ.ም የዘለቀ ነበር። ቀጣዩም የንግሥት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት ተብሎ ከ1909 እስከ 1922 ዓ.ም ድረስ ቀጥሏል። እዚህ ላይ ልብ መባል ያለበት ጉዳይ አለ። የንግሥና ዘመኑ የንግሥት ዘውዲቱ ተብሎ ይገለጽ እንጂ ኢትዮጵያ በሁለት ዘውድ ጫኝ ነገሥታት  ተመርታለች።

 

የልጅ ኢያሱ የንግሥና ዘመን ከሶስት ዓመታት በላይ እንዳይቆይ ተደርጎ ተጠናቀቀ። በ1909 ዓ.ም ዘውዲቱ ንግሥተ ነገሥታት፣ ተፈሪ መኮንን ደግሞ ራስ ተብለው አልጋወራሽ ሆኑ። ክንውኑ ግን ያልተለመደ አይነት ነበር። በኢትዮጵያ ታሪክ የተለመደው ወግ እና ስርዓት ንጉሠ ነገሥት ከተሾመ በኋላ ቆይቶ በተሿሚው ንጉሠ ነገሥት ፍላጎት እና ምርጫ ነበር አልጋወራሽ የሚሰየመው። የዘውዲቱ እና የተፈሪ ሹመት ግን “በህዝቡ ምርጫ” በሚል በሌሎች ምርጫ በአንድ ቀን ተከናውኗል።

 

ይህ የሆነበት ምክንያት ልጅ ኢያሱ ሲሻር የተለያዬ የምርጫ ፍላጎት ያለው ሁለት ጎራ በመፈጠሩ ነው። ስለዚህ ራስ ተፈሪ በነበራቸው አውሮፓ ቀመስ ትምህርት እና በተራማጅነታቸው የአውሮፓውያኑ ምርጫ ሆኑ። ዘውዲቱ ደግሞ የኢትዮጵያውያኑ ወግ አጥባቂ የመኳንንት ቡድን ምርጫ ነበሩ። ይህ በዘመነ መሳፍንት ጊዜ ብቻ የተተገበረ እና ያልተለመደ የሁለት ባንድ የአሿሿም ዘዴ የዘውዲቱን የአስተዳደር ጊዜ ያልተለመደ ያደርገዋል።

 

ዘውዲቱን ለሥልጣን ያበቃቸው ብቸኛ መመዘኛ የአፄ ሚኒልክ ቀጥተኛ ልጅ መሆናቸው ነው። የሸዋ መኳንንት ምርጫ የሆኑትም የቀድሞውን የምኒልክን ወግ እና ስርዓት እንደማይጥሱ እምነት ስለተጣለባቸው ነው። ራስ ተፈሪም የንጉሥ ሳህለ ሥላሴ ዝርያ ያላቸው እና የአፄ ሚኒልክ የአክስታቸው የልጅ ልጅ ስለሆኑ፣ በዘር ሐረግ ረገድ ለዘውዱ የልጅን ያህል ባይሆንም የማይተናነስ ቅርበት ነበራቸው። ነገር ግን የአልጋ ወራሽነቱን ሥልጣን ያገኙት በዘር ቆጠራ ብቻ ሳይሆን የአውሮፓውያንን ቋንቋ ስለሚናገሩ እና የቆንሲሎች ወዳድ ስለነበሩ ነው። ቀስ በቀስም ከአልጋ ወራሽነት ወደ ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴነት ተሸጋግረው፣ በመጨረሻም ንጉሠ ነገሥት ሆነዋል።

 

በዚህ አካሄዳቸውም የዘውዲቱን ሥልጣን በእርጋታ ከላያቸው ላይ እየገፈፉ ሥልጣን አልባ ባለሥልጣን አደረጓቸው። ይህም የሆነው ዘውዱቱ የአስተዳደር ልምድ ያልነበራቸው፣ ካብነት ትምህርት ያለፈ የዘመናዊ ትምህርት ዕውቀት ስላልነበራቸው ነው። በመሆኑም አጠቃላይ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን እና የሃገሪቱን የውጭ ፖሊሲም ሆነ የአስተዳደር ስራ አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ ከደጋፊዎቻቸው ጋር ያከናውኑ ነበር።

 

ጥቂት ምሁራንን ከጎናቸው አሰልፈው የአስተዳደር እንቅስቃሴውን የገፉበት ልዑል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ ከ1909 እስከ 1922 ዓ.ም ካከናወኗቸው ተግባራት ውስጥ ኢትዮጵያን የመንግሥታቱ ማኅበር አባል ማድረጋቸው ይጠቀሳል። በ1915 ዓ.ም ኢትዮጵያ የአባልነት ማመልከቻዋን ስታስገባ ጠንከር ያለ ተቃውሞ ገጥሟት ነበር። “በውስጧ የባሪያ አገዛዝ አለ፤ ግድያ እና ዝርፊያ አለ፤ የግዛቷ ወሰን በደንብ የተከለለ አይደለም፤ በግዛቷ ላይ የመንግሥታቱ ማኀበር የሚያዘውን ህግ ልታስፈፅም አትችልም … የሚሉት ዋና ዋናዎቹ የመቃወሚያ ነጥቦች ነበሩ።

 

የአልጋወራሹን የአስተዳደር ስራ ያዩ ሃገራት ደግሞ ድጋፍ ሰጡ። አልጋ ወራሹም የባሪያ አገዛዝ በህግ እንደተሻረ እና ሃገራቸውም ሰላም መሆኗን አስረዱ። በመሆኑም በሚያዝያ ወር 1916 ዓ.ም ኢትዮጵያ በልዑል አልጋ ወራሹ ጥረት የመንግሥታቱ ማኀበር አባል ሃገር ለመሆን ቻለች።

ኢትዮጵያ የመንግሥታቱ አባል ሃገር ከሆነች በኋላ ወዲያውኑ በሚያዝያ ወር አልጋ ወራሹ መኳንንቱን አስከትለው፤ በተመቻቸላቸው የጉብኝት ፕሮግራም የፈረንሳይን፣ የቤልጂየምን፣ የስዊድንን፣ የኢጣሊያን፣ የእንግሊዝን፣ የግሪክን … ዋና ከተሞች ተዘዋውረው ጎበኙ። ከየሃገራቱ መሪዎች ጋርም እየተወያዩ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን አጠናከሩ። የመንግሥታቱን ማኀበር መቀመጫ ጄኔቫን ጎበኙ።

 

ኢትዮጵያ የመንግሥታቱ ማኀበር አባል ሃገር መሆኗን ተከትሎ ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ አውሮፓን ተዘዋውረው በመመልከታቸው በምሁራኑ ዘንድ አድናቆት ተቸራቸው። ጉብኝቱ ለኢትዮጵያውያኑ ልዑካን ቡድንም ብዙ ግንዛቤን ያስጨበጠ ነበር። ልዑል አልጋ ወራሹም በጉብኝታቸው ወቅት ያዩትን ስልጣኔ ሃገራቸው ላይ ተግባራዊ ማድረግ ጀመሩ፤ አዳዲስ ስራዎችም መከናወን ቻሉ። በርካታ ኢትዮጵያውያንም እየተመለመሉ ለትምህርት ወደ አውሮፓ ተላኩ። ትምህርት ቤቶችም በአዲስ አበባ እና በየጠቅላይ ግዛቱ እንዲከፈቱ ተደረገ።

 

መጋቢት 24 ቀን 1922 ዓ.ም ንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ በ53 ዓመታቸው  ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፤ የንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥትም ፍፃሜው ሆነ።

ኢትዮጵያ የመንግሥታቱ ማኅበር አባል ሃገር እንድትሆን  ጥረት ያደረጉት ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ፤ ቀዳማዊ ነጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ስላሴ ተብለው  በብቸኝነት  ንግሥናቸው ቀጠለ።

 

በ1928 ዓ.ም የኢጣሊያ መንግሥት  በቅኝ ግዛት ለመያዝ በሰሜን እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክፍል ጦርነት ጀመረ። በዘመናዊ የጦር መሳሪያ፣ በአውሮፕላን እና በመርዘ ጋዝ በመታገዝም ከፍተኛ ጉዳት አደረሰ። መሸነፍን አሜን ብለው የመቀበል ታሪክ የሌላቸው ጀግና ኢትዮጵያዊያን በአርበኝነት ዱር ቤቴ ብለው በመሰባሰብ መፋለማቸውን ቀጠሉ። የመንግሥታቱ ማኅበር ድርጊቱን ከመቃወም ያለፈ ድጋፍ ግን ማድረግ ሳይችል ቀረ።

 

በጦርነቱ ምክንያት ከሃገር የወጡት አፄ ኃይለ ሥላሴም በ1929 ዓ.ም ጀኔቫ ላይ በተካሄደው የመንግሥታቱ ማኀበር ስብሰባ በመገኘት በሃገራቸው ላይ የጣሊያን ወረራ ያስከተለውን ጉዳት በዝርዝር ማስረዳት ቻሉ። “ትልቁ አሳ ትንሹን አሳ ይዋጠው ብላችሁ ብትፈርዱ ነገ በእናንተ ደርሶ ታዩት የለምን!” ብለውም ተናገሩ። ይህ ንግግራቸው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ላስከተለው እልቂት እንደ ትንቢት ተቆጠረላቸው።

ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ቆራጥ ተጋድሎ የኢጣሊያን ወረራ አሸንፋ ላለም ጥቁር ሕዝብ የነፃነት ጮራን ፈነጠቀች። ለቅኝ ግዛት ያልተንበረከከች መሆኗንም መላው ዓለም መገንዘብ ቻለ።

 

ኢትዮጵያ በመላው ዓለም ዘንድ ከፍ ብላ እንድትታይ ቀዳማዊ ሃይለ ሥላሴ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። የሃገራቸው ባህል እና ቋንቋ በዓለም ላይ ጎልቶ እንዲታይ ጥረዋል። አለባበሳቸው ኢትዮጵያዊ፤ ንግግራቸውም አማርኛ ነበር።

 

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስብሰባ ላይ ሲገኙ ንግግራቸው በአማርኛ ነበር። ይህን የሚያደርጉት ደግሞ እንግሊዝኛ መናገር አቅቷቸው አይደለም። እንዲያውም ከእንግሊዘኛ በላይ ፈረንሳይኛም አሳምረው ያዳምጣሉ፤ አቀላጥፈውም ይናገሩበታል።

 

በ25ኛው ዓመት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምስረታ በዓል ላይም በአማርኛ ባደረጉት ንግግር “ድርጅቱ የተመሠረተበትን አላማ በትክክል እየፈፀመ አይደለም፤ በዚህ የተነሳ ከመጠናከር ይልቅ የመዳከም አዝማሚያ ይታይበታል” በማለት በድፍረት ሃሳባቸውን ገልጸዋል። የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

 

ኢትዮጵያ በመንግሥታቱ ማኅበር /በዛሬው ስያሜ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት/ ቀዳሚዋ አፍሪካዊት ሃገር ናት። በተለያዩ ሃገራት የሚከሰቱ ግጭቶችን በሰላም ለመፍታት ድርጅቱ የሚሰጣትን የሰላም አስከባሪነት ተልኮም በብቃት በመፈፀም ላይ ትገኛለች።

ምንጭ ፦ ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ በተክለ ጻድቅ መኩሪያ

–      የኢትዮጵያ የአምስት ሺህ ዓመት ታሪክ፣ ካልተዘመረለት ኢያሱ እስከ ተዘመረለት ኢህአዴግ መፅሐፍ ፪ ፣ በፍስሐ ያዜ ካሴ

–      የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ከመጀመሪያው እስከ አሁኑ ዘመን፣ በዓለማየሁ አበበ

 

ሳምንቱ በታሪክ

ዐፄ ናዖድ

 

ሰለሞናዊውን የኢትዮጵያ ስርዋ መንግሥት ከተቋረጠበት በማስቀጠል ረገድ ግንባር ቀደም ከነበሩት ንጉሥ ዩኩኖ አምላክ በኋላ በርካታ ነገሥታት በሰሎሞናዊው ዙፋን ላይ ወጥተዋል። ከእነዚህ መካከልም አንዱ ዐፄ ናዖድ ይጠቀሳል። ለሰባት ወራት ብቻ በስልጣን ላይ ቆይተው ከሞቱት ከንጉሥ ዳግማዊ አምደ ፂዮን ተከትለው በ1488 ዓ.ም አንበሳ በር በሚል ስመ መንግሥታቸው ወደ ስልጣን የወጡት ንጉሠ ነገሥት ናዖድ ለአስራ ሦስት ዓመታት የቆየው መንግሥታቸው ያበቃው ሐምሌ 24 ቀን 1500 ዓ.ም  ነበር።

ከዳውሮው ባላባት ሴት ልጅ ንግሥት እሌኒ ሞገሳ ጋር ተጋብተው ወልደው ከብደዋል። የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ከቱርክ መራሽ አረቦች ወረራ መታደግ የቻሉ ታላቅ ንጉሥ የነበሩት ዐፄ ናዖድ የነገሥታት ልጆች ከስምንት ዓመት እድሜያቸው በኋላ በግሸን አምባ በግዞት እንዲታሰሩ የሚደረግበትን አሰራር ያስቀሩ ናቸው።

ምንጭ- የኢትዮጵያ ታሪክ፣ በአባ  ጋስፓረኒ እና የጥንቷ ኢትዮጵያ ትንሳኤ ታሪክ፣ በመሪ ራስ አማን በላይ

 

 

ሔነሪ ፎርድ

 

ሐምሌ 21ቀን 1967 ዓ.ም የዓለማችን እውቁ የፎርድ መኪና አባት የሚባለው ሔነሪ ፎርድ የተወለደበት ነበር። ሚሽገን ውስጥ በዲርቦርን ታወን ሺፕ የተወለደው ፎርድ ለሰራተኞች በቀን የ5 ዶላር ምንዳን ለመጀመሪያ ጊዜ በስራ ላይ ያዋለ እውቅ አሜሪካዊ ነው።

 

ምንጭ፣ ሂስትሪሮፕሌስ

  (ጥላሁን ወንዴ)

በኲር የሐምሌ 21  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here