ከክብር መውረድ

0
66

የሰው ክብር ወይም ሰውነት የሚለካው ረቂቅ በሆኑ እሴቶች ነው፡፡ ከእነዚህ የሰው ክብር መለኪያ ረቂቅ እሴቶች ደግሞ  ለሕሊና ታማኝ መሆን እና በራስ ላይ እንዲፈጸም የማይፈለግን ነገር በሌሎች ላይ አለመፈጸም ተጠቃሽ ናቸው፡፡

 

ብዙ ሰዎች እነዚህን እሴቶች ጠብቀው፣ ከሰውነት የክብር ማማቸው ሳይወርዱ ሕይዎታቸውን ይመራሉ፡፡ አንዳች ተግባር ለመፈጸም ሲነሱ ከሕሊናቸው ጋር ይማከራሉ፤ ‘ይሄን ተግባር ለመፈጸም አስቤያለሁ፤ ለመሆኑ ይሄ ልፈጽመው ያሰብሁት ተግባር ሌሎችን ይጎዳል? በእኔ ላይ እንዲፈጸምስ እፈቅዳለሁ?’ ብለው ራሳቸውን ይጠይቃሉ፡፡ ጠይቀውም ሊፈጽሙት ያሰቡት ተግባር ሕሊናቸውን የማይጎረብጠው፣ በእነሱ ላይ ቢፈጸም የማይቃወሙት መሆኑን ሲያረጋግጡ ብቻ ያሰቡትን ድርጊት ይፈጽማሉ፡፡

እነዚህን መሰል እሴቶቻችን አሁን ላይ ክፉኛ እየተሸረሸሩ፣ ወዳለመኖርም እየተሸጋገሩ ይገኛሉ፡፡ ለሕሊና መታመን ብሎ ነገር ጥያቄ ውስጥ ወድቋል፡፡ ክቡሩ የሰው ልጅ በራሱ እንዲፈጸሙ የማይፈልጋቸውን ተግባራት በሰው ላይ ሲያደርግ፣ በዚህም ከነበረበት የክብር ወይም የሰውነት ማማ ሲወርድ ይታያል፡፡

 

ከእነዚህ የሰውን ልጅ ከክብር ማማው እያወረዱት ካሉት ተግባራት ውስጥ ደግሞ ስርቆት አንዱ ነው፡፡ የሰው ልጅ ጥሮ ግሮ፣ በላቡ በወዙ  ያፈራውን ገንዘብም ሆነ ሀብት እንዲሁም ንብረት ሌላ እንዲወስድበት ፈጽሞ አይፈልግም፡፡ ሆኖም “የእኔን አትንኩብኝ!” እያለ ወገኖቹን ሲመነትፍ፣ መንትፎም ከክብር ማማ ወርዶ ሲፈጠፈጥ ይስተዋላል፡፡  ይህን ጽሑፍ ልጽፍ እያሰብሁ ባለሁበት ባለፈው ሳምንት  በከተማችን ያየሁት አሳዛኝ ክስተት ለዚህ አባባሌ እውነትነት ሁነኛ ማስረጃ ነው፡፡  በተጠቀሰው ሳምንት ባንዱ ዕለት ጧት ወደ መሥሪያ ቤቴ ለመሄድ ታክሲ ልሳፈር ስል  አንድ ወጣት ገና በማለዳው ሲሰርቅ እጅ ከፍንጅ ተይዞ ሰው ከብቦ ሲደበድበው ተመለከትሁ፡፡ አንዱ ይረግጠዋል፤ ሌላኛው በድንጋይ ይነርተዋል፤ ይገፈትረዋል፤ ዙሪያውን ከብቦ ትርኢቱን የሚመለከተውም በምሬት፣ “በለው!… የታባቱ ሠርቶ አይበላም?!… በዚህ ዕድሜው እንዴት ይሰርቃል?!…” እያለ ተደባዳቢውን ያበረታታል፡፡ እውነት ለመናገር ሁኔታው በጣም አሳዛኝ ነበር፡፡

 

ሰው ወጣቱን ሌባ ሲደበድበው ለብዙ ጊዜ የተጠራቀመ ምሬት ያለበት ይመስላል፡፡ ሁሉም የልቡ እስኪደርስ  ረግጦ ረግጦ ሲለቀው ወጣቱ ሌባ ከወደቀበት ተነስቶ በጭቃ የተጨማለቀ ጋቢውን አንገቱ ላይ እየጠመጠመ፣ “አሁንስ መረረኝ! ሁለተኛ እዚህ አካባቢ አልመጣም!” ሲል ሰማሁት፡፡ ወጣቱ ይህን ሲናገር ሌብነት ሱስ እንደሆነበት ተረዳሁ፡፡ ምክንያቱም ያን ያህል ርግጫ፣ ጡጫ… ቀምሶ፣ ከሰውነት ክብር ወርዶ፣ ተዋርዶ፣ በጭቃ ተጨማልቆ፣  “ሁለተኛ እዚህ አካባቢ አልመጣም!” አለ እንጂ ሁለተኛ “አልሰርቅም” አላለም፡፡ ሌብነት ሱስ ስለሆነበት ቦታ ቀይሮ ለመስረቅ እንዳሰበ አባባሉ እያሳበቀበት ከፊታችን ተሰወረ፡፡

 

አስቀድሞ፣ “እስካልተያዙ ድረስ መስረቅም ሥራ ነው” እንደተባለው ስርቆት ለብዙዎች አንዱ መተዳደሪያ ዘዴ ሆኗል፡፡ ወጣቱ ሌባም በድርጊቱ ተጸጽቶ ከእንግዲህ አልሰርቅም ያላለው ስርቆትን መተዳደሪያው ስላደረገው ነው፡፡

ይህንን አሳዛኝ ትርኢት ባየሁ በሦሥተኛው ቀን ከታክሲ ወርጄ ወደ መሥሪያ ቤቴ ሳመራ ፖሊሶች አንድን ወጣት አምበርክከው ተመለከትሁ፡፡ ጠጋ ብየ ወጣቱን ከብቦ ከቆመው ሰው መሀል አንዱን ስጠይቅ ሲሰርቅ ተይዞ ነው አሉኝ፡፡ ወደ መሥሪያ ቤት ለመግባት ቸኩየ ስለነበር መጨረሻውን ሳላይ ሄድሁ፡፡

 

ስርቆት የሌቦች መተዳደሪያ ዘዴ በመሆኑ በየቦታው ሲፈጸም መመልከት እንዲህ የተለመደ ሆኗል፡፡   ስልቱም ቢሆን በየጊዜው “እያደገ” እና እየተቀያየረ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ስርቆትን መተዳደሪያው ያደረገ መንታፊ በየዕለቱ ሰውን እንዴት አታልሎ፣ አፍዝዞ፣ አደንዝዞ… መስረቅ እንዳለበት ሲጠበብ ውሎ ሲጠበብ ያድራል፡፡ እግር ረግጦ “ይቅርታ” በማለት ተጋፍቶ ተሻሽቶ መመንተፍ የተለመደ እና ብዙ “የተሠራበት” ዘዴ ሆኗል፡፡ እኔን ጨምሮ በዚህ ዘዴ ለዚያውም በተደጋጋሚ ያልተመነተፈ ይኖራል ብየ አላስብም፡፡  ካለም እሱ አንድም ሲበዛ ጠንቃቃ ወይም ዕድለኛ ነው ማለት ይቻላል፡፡

 

ተሽከርካሪያቸውን የተበላሸባቸው ይመስል መንገድ ላይ አቁመው እየጎረጎሩ ባጠገባቸው የሚያልፍን እግረኛ፣ “ጋሼ እሱን ድንጋይ አቀብለኝማ!…” ብለው ተቀብለው እግረኛው ጉዞውን ሊቀጥል ሲል፣ “አዝዤህ ሳልሸኝህ እንዴት እሄዳለሁ?…” በሚል ማታለያ በእጅ በእግር ገብተው ወደ ተሽከርካሪያቸው አስገብተው ኪስ መበርበር የለመዱ ሞጭልፎች አጋጥመውኝ በጊዜ ስለነቃሁባቸው ከመመንተፍ መዳኔን አስታውሳለሁ፡፡

 

አንዱ ወዳጄ ደግሞ በእግሩ እየሄደ እያለ ተሽከርካሪያቸውን እያበረሩ አምጥተው እሱ ጋ ሲደርሱ እንዳቆሟትና በሰባዎቹ አጋማሽ የሚገመቱ ተሳፋሪ ቁልፍ የወደቀባቸው በማስመሰል ጥለው አቀብለኝ ብለውት እንዳቀበላቸው፣ ካቀበላቸው በኋላ ግን ሽማግሌው፣ “ፀሐይ ነው እንሸኝህ” እንዳሉት፣ እሱም ሽማግሌ ስለሆኑ መቼም አይሰርቁኝ ብሎ ገብቶ ሽማግሌው ስልኩን አዘናግተው እንደወሰዱበት  አጫውቶኛል፡፡

 

ምናልባት አንድ ዓመት ሳይሆነው አይቀርም፤ ድርጊቱ ከተፈጸመ፡፡ አርባ ሜትር ያስፋልት መንገድ ጠርዝ ይዤ እያዘገምሁ ነው፤ ከቤቴ ወደ መሥሪያ ቤቴ፡፡ ከፊት ለፊቴ በቅርብ ርቀት አንድ ጋቢ የለበሰ ሰው በስልክ እያወራ ይጓዛል፡፡ ድንገት ሦሥት እግር ( ባጃጅ) ስትበር መጥታ በመጣችበት ፍጥነት አልፋኝ ሄደች፡፡ በስልክ እያወራ ከነበረው ሰውየ ስትደርስ ተሽከርካሪዋ ውስጥ የነበረ ሞጭላፊ ስልኩን ነጠቀው፡፡ በዚህ ቅጽበት ባለስልኩ፣ “ኧሮ ስልኬ!… ስልኬ!…” እያለ እሪታውን እያቀለጠው ጋቢውንም ጫማውንም እያንጠባጠበ ሦሥት እግሯን ተከትሎ ሮጠ፤ ሆኖም  ተሽከርካሪዋም ፍጥነቷን ጨምራ ስለበረረች ድካሙ ሁሉ ከንቱ ሆኖ መቅረቱ ትዝ ይለኛል፡፡

 

ታክሲ ውስጥ ከገባችሁ በኋላ ልብሳችሁ ላይ ቆሻሻ ደፍተው ጋሼ ልብስህ ቆሽሿል በማለት አስወልቀው የሚመነትፉ ሌቦችም ያጋጥማሉ፡፡ የእናንተን ባላውቅም እንዲህ ዓይነቶቹ ሞጭልፎች እኔን አጋጥመውኛል፡፡

እንደ አማኝ ሁሉ ቤተ ክርስቲያን ግቢ ዘልቀው በመግባት ነጠላቸውን ወይም ጋቢያቸውን አጣፍተው፣ የጸሎት መጽሐፍ ዘርግተው አማኝ መስለው የሚመነትፉም አይታጡም:: እንዲሁ ዓይነት ቁጭ በሉዎችን በጸበል ቦታ  ብትሄዱም አታጧቸውም:: ሰው ነጠላም ይሁን ጋቢ አጣፍተው ለብሰው፣ የጸሎት መጽሐፍ ዘርግተው ሲያያቸው እምነት ይጥልባቸዋል:: እምነት ስለሚጥልባቸውም፣ “ጸበል አስቀድቼ እስክመጣ፣ ልጅ አቁርቤ እስክመለስ ጠብቂልኝ፤ ጠብቅልኝ…” እያለ የያዘውን ሁሉ በአደራ ትቶላቸው ይሄዳል:: ሲመለስ ግን ባደራ ያስቀመጠውን ዕቃም እነሱንም በቦታቸው አያገኛቸውም:: ሀገር አማን ብሎ ልብሱን እንዲሁም ጫማውን አወላልቆ አስቀምጦ ጸበል ተጠምቆ ሲወጣ ልብሱንም ሆነ ጫማውን እየተመነተፈ ነጠላ እና ጋቢ ለምኖ ለብሶ፣ በባዶ እግሩ ጠጠር እየወጋው… ወደ ቤቱ የተመለሰውን ቤቱ ይቁጠረው::  ጫማውን አውልቆ በር ላይ በመተው ወደ ቤተ እምነት የገባ አማኝም ሲመለስ ጫማውን ካገኘ ዕድለኛ ነው ከሚባልበት የሌቦች ዘመን ላይ ደርሰናል:: በቤተ እምነት ግቢ የሚፈጸመው ስርቆት ክቡሩ የሰው ልጅ ሰብዕናውን በነዋይ እንዲሁም በቁስ ፍቅር ምን ያህል እንዳስገዛ ወይም ከክብር ማማው እንደወረደ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው::

 

ሌቦች ሕጻናትን በመደለል ለስርቆት መላካቸው ደግሞ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተለመደ የመጣ የምንተፋ ዘዴ ነው:: ሕጻናቱ፣ “ጋሼ የስፖርት ስጠን!” በማለት ሳሎን ድረስ ሰተት ብለው ይገባሉ:: የዋሁ አባዎራም እውነት መስሎት፣ “የክለባችሁ ስም ማን ይባላል? ስንት አባላት አሉት? ከእነማን ጋር ነው የምትጋጠሙት?” እያለ ከተወሰኑት ሕጻናት ጋር ሲያወጋ ሌሎቹ ሕጻናት ከወጣት ሌቦች በተሰጣቸው ትዕዛዝ መሠረት ጠረጴዛ ላይ ያለን ስልክ ጨምሮ ያገኙትን ሁሉ መነታትፈው ይወጣሉ::

 

ሕጻናቱ ከመንታፊ ወጣቶች በሚሰጣቸው ትዕዛዝ መሠረት የመኪና መለዋወጫ ዕቃዎችን ሳይቀር በጠራራ ፀሐይ ፈትተው ለመንታፊ ወጣቶች እንደሚሰጡ፣ ወጣት ሌቦች መንገደኛን ሰዋራ ቦታ ላይ አስቁመው ለመዝረፍ ሲታገሉ ኪስ በመበርበር ያገኙትን ለቃቅመው ለዘራፊዎች እንደሚያቀብሉ የወንጀል ድርጊቱ የተፈጸመባቸው ሲናገሩ ማዳመጥ እየተለመደ መጥቷል::

ሱቅ የሆነ ዕቃ ጠይቆ ባለሱቆቹ ዕቃውን ሊያመጡ ዞር ሲሉ ባንኮኒ ላይ የተቀመጠን ስልክ መንትፎ በኪሱ ካደረገ በኋላ፣ “በቃ ተወው! በቃ ተይው!” ብሎ የሚሄደው ጩሉሌም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ መጥቷል::

 

ሌብነት እንደ ቴሌ እንዲሁም ባንክ  ያሉ ተቋማትን ሳይቀር እየፈተነ  ይገኛል::  “የምንደውለው ከቴሌ ነው፤ የባንክ ሠራተኞች ነን…” እያሉ በተቋማቱ ሠራተኞች ስም የሚያጭበረብሩ ሌቦች እየተበራከቱ በመምጣታቸው ተቋማቱ ሕብረተሰቡ እንዳይታለል በተደጋጋሚ በማሳሰብ ላይ  ናቸው:: የተቋማቱን ማሳሰቢያ ተቀብሎ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ከሁላችንም የተቋማቱ ደንበኞች የሚጠበቅ ግዴታ ነው፡፡

 

ሌቦች ስርቆትን መተዳደሪያቸው ስላደረጉት ለስርቆት ሲጠበቡ ውለው እያደሩ፣ በየዕለቱ አዳዲስ የስርቆት ስልት እየፈጠሩ ሲመነትፉን እኛ ተሰራቂዎቹም ላለመሰረቅ መጠበብ ያለብን ይመስለኛል፡፡ “ሌባ አታልሎ እንዳይመነትፈኝ ምን ዓይነት የጥንቃቄ ርምጃ መውሰድ አለብኝ?” ብለን ራሳችንን መጠየቅ፣ በተቻለን መጠንም ጠንቀቅ ማለት ግድ ይለናል፡፡ የየግል ጥንቃቄያችን እንደተጠበቀ ሆኖ ለችግሩ በጋራ ዘላቂ መፍትሄ ልንሻም ይገባል፡፡ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለመሻት ደግሞ ሌብነት ይህን ያህል ለምን ተስፋፋ ብሎ ማጠየቅ እና የችግሩን መሠረታዊ ምክንያት መረዳት ያስፈልጋል፡፡

 

ብሪታኒካ ዶት ኮም ላይ ያገኜሁት መረጃ እንደሚጠቁመው ሰዎች ስርቆትን በተለያዩ ምክንያቶች ያዘወትራሉ፡፡ ከእነዚህ የስርቆት ምክንያቶች አንዱ፣ ምናልባትም ዋነኛው ደግሞ በሱስ መጠመድ እንደሆነ መረጃዉ ይጠቁማል፡፡ በመረጃው ላይ እንደተመለከተው በመጠጥ፣ በጫት፣ በቁማር… ሱስ የተጠመደ ሰው ያንን ሱሱን ለማስታገስ ገንዘብ የግድ ስለሚያስፈልገው ስርቆት ላይ ይሰማራል፡፡ ስለሆነም ስርቆትን በዘላቂነት ለመከላከል ሱስ አማጪ የሆኑትን ነገሮች ማስወገድ እንደሚያስፈልግ ድረ ገጹ ይገልጻል፡፡

 

ድረ ገጹ ይህን ሲል ባይነ ሕሊናየ ከተማችንን ቃኜኋት፡፡ ከተማችን ከንጋት እስክ ምሽት መጠጥ በሚጨለጥባቸው መጠጥ ቤቶች ተወራለች፡፡ ቁማር እንዲሁም ጫት ቤቶችም በየስርቻው አሉ፡፡ እነዚህ መጠጥ፣ ጫት እንዲሁም ቁማር ቤቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ እና ስልቱን እየቀየረ ለመጣው ስርቆት አባባሽ ምክንያቶች እንደሆኑ መገንዘብ አይከብድም፡፡ እናም ችግሩን ለማቃለል ይቻል ዘንድ ማኅበረሰቡ ላለመሰረቅ ማድረግ ያለበት ጥንቃቄ እንደተጠበቀ ሆኖ የሚመለከተው አካል እነዚህን ቤቶች መፈተሽ፣ ፈትሾም ሥርዓት ማስያዝ ይኖርበታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እናንተስ ምን ትላላችሁ?፡፡

(ቦረቦር ዘዳር አገር )

በኲር የሐምሌ 21  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here