በርካታ ሀገራት በአፍሪካ በግጭት ላይ ይገኛሉ፡፡ ታዲያ እነዚህ ሀገራት ከዓመት ዓመት ከግጭት ቀጣና ይወጣሉ ተብሎ ሲጠበቅ በግጭት አዙሪት ውስጥ ነው የሚሽከረከሩት፡፡ በአህጉሪቱ በተነሱ ግጭቶች ከፍተኛ ውድመት ከደረሰባቸው ሀገራት መካከልም ሱዳን፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኢትዮጵያ፣ እና የሳህል ቀጣና ሀገራት ይጠቀሳሉ፡፡
ሱዳን
ከሁለት ዓመት በፊት (እ.አ.አ ሚያዚያ 2023) የጀመረው የሱዳን የርስ በርስ ጦርነት መቋጫ አልተገኘለትም። በሀገሪቱ ጦር መሪ በጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃን እና በፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች (አር ኤስ ኤፍ) መሪ በጄኔራል መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሚቲ) መካከል በስልጣን ሽኩቻ ምክንያት የሚደረገው ጦርነት ሀገሪቱን ከባድ ዋጋ አስከፍሏታል፤ እያስከፈላትም ነው።
በሀገሪቱ በተከሰተው ግጭት ከ150 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን 12 ሚሊዮን ያህሉ ደግሞ ቀያቸውን ለቀው መሰደዳቸውን ከቢቢሲ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ 30 ነጥብ አራት ሚሊዮን ሰዎች ሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡
ጦርነቱ ከ50 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላትን ምሥራቅ አፍሪካዊቷን ሀገር (ሱዳንን) ምስቅልቅሏን አውጥቷል። ከሀገሪቱ ሕዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ለረሃብ መጋለጡን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይፋ አድርጓል። ጾታዊ ጥቃት የጦርነቱ መገለጫዎች እስኪመስሉ ድረስ ተፈጽመዋል።
መረጃው ይፋ እንዳደረገው ምን እየተካሄደ እንደሆነ በቅጡ መገንዘብ የማይችሉ ሕፃናት በታጠቁ ኃይሎች ተደፍረዋል፤ የችግሩም ገፈት ቀማሽ ሆነዋል። መሠረተ ልማቶች ወድመዋል። ለህዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ከጥቅም ውጪ ሆነዋል።
በአሁኑ ወቅት የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሉ የራሱን መንግሥት አቋቁሟል። የሀገሪቱ ጦር ደግሞ የካርቱምን ክፍሎች መልሶ ተቆጣጥሯል። ግጭቱ ግን በተለይ በዳርፉር እና በኮርዶፋን ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ የአፍካ ሕብረት ሱዳንን ሊከፋፍል ስለሚችል አዲስ ለተቋቋመው የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይል መንግሥት የትኛውም ሀገርም ሆነ ተቋም እውቅና እንዳይሰጥ አሳስቧል፡፡
ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ
ዴሞክራቲክ ሪብሊክ ኮንጎን ጭካኔ የተሞላበት የቤልጂየም ቅኝ ግዛት (እ.አ.አ 1885-1960) የተፈጥሮ ሀብቶቿን በዝብዞ ጠንካራ ተቋማት እንዳይኖራት አድርጓል። ከነጻነት በኋላ በሀገሪቱ የነበረው ሁኔታ ለዓመታት ደካማ፣ የተከፋፈለ እና ለመፈንቅለ መንግሥት የተጋለጠ ነበር።
የሞቡቱ ሴሴ ሴኮ አገዛዝ (1965-1997 እ.አ.አ) ሥርዓታዊ ሙስና የነገሰበት፣ ሰላማዊ ሕዝባዊ ተቃውሞን የሚያፍን እና በመልካም አስተዳደር ዕጦት የሚታመስ ነበር።
እ.አ.አ በ1994 በሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ የተሳተፉ የሁቱ ሚሊሻዎች ወደ ምሥራቃዊ ኮንጎ መሸሻቸው የሩዋንዳን እና የኡጋንዳን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት አስከትሏል።
በተፈጥሮ ማዕድናት በበለጸገችው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ (በኮባልት፣ ወርቅ፣ አልማዝ እና ቆርቆሮ ማዕድናት መክበሯን ልብ ይሏል) የታጠቁ ቡድኖች የማዕድን መገኛ ስፍራዎችን ለመቆጣጠር ይዋጋሉ። ሀብቷም እርግማን የሆነባት ይመስል ሰላሟን አሳጥቷታል።
ከቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው ከ100 በላይ አማፂያን እና የሚሊሻ ቡድኖች በምሥራቃዊ የሀገሪቱ ክፍሎች ይንቀሳቀሳሉ። ለአብነትም ኤም 23 (M23)፣ ከእስልምና አክራሪነት ጋር የተገናኘው ኤ ዲ ኤፍ (ADF) እና ማይማይ (Mai-Mai) ቡድኖች ውስጥ ብዙዎች እየተሳተፉ ነው።
ታዲያ በዚህ ምክንያት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ተበራክተዋል። የሕፃናት ወታደሮች ምልመላ እና የመብት ጥሰት ማብቂያ ያለው አይመስልም፡፡
መረጃው አክሎ እንዳብራራው በሰሜን እና ደቡብ ኪቩ እንዲሁም በኢቱሪ ግዛቶች የማያቋርጥ ውጊያ አለ። የታጠቁ ኃይሎች ግፍ ይፈጽማሉ፣ ጅምላ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር እንዲሁም አፈና ተበራክቷል። ከስድስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ዜጎቿ ተፈናቅለዋል። ረሃብ፣ በሽታ እና የሕክምና አገልግሎት እጦት ተንሰራፍቷል። ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ርዳታ ከሚደርግላቸው ቀዳሚ ሀገራት ተርታም ተሰልፋለች።
ከጥቂት በመንግሥት ቁጥጥር ከሚደረግባቸው ዋና ዋና ከተሞቿ ውጪ በሁሉም የመንግሥት እርከኖች በሚባል ደረጃ ሙስና ተስፋፍቷል። በቂ የመሠረተ ልማት አውታር ባለመኖሩ ሕዝቧ ተማርሯል። ደካማ የጤና ጥበቃ ሥርዓት በመኖሩ ምክንያት ሀገሪቱ በተደጋጋሚ በኢቦላ፣ ኮሌራ እና ወባ በመሳሰሉ ወረርሽኞች ትጠቃለች።
ይህ በእንዲህ እያለ አንደርስታንዲንግ ዋር ዶት ኦርግ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መንግሥት እና በሩዋንዳ የሚደገፉት ኤም 23 አማጽያን በአሜሪካ እና በኳታር በሚመራው የቀጣናዊ የሰላም ማዕቀፍ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተኩስ አቁም ስምምነት በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ እ.አ.አ ሐምሌ 19 ቀን 2025 ተፈራርመዋል። አዲሱ ስምምነት ለወደፊት የሰላም ንግግሮች ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር በግጭቱ ውስጥ የተሰማሩ ኃይሎች የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ የሚያስችል ነው ተብሏል።
ሁለቱ ወገኖች የማረኳቸውን እስረኞች ለመፍታት መተማመን ላይ ደርሰዋል፡፡ ስምምነቱ ተኩስ አቅሙን የሚያፈርሰውን አካል የሚቀጣ ቅድመ ሁኔታን ባያካትትም ነገር ግን ኳታር የስምምነቱ ስኬታማነት በዋነኛነት በሁለቱም ወገኖች ላይ ስለመሆኑ አስታውቃለች።
ሮይተርስ የኮንጐ መንግሥትን ዋቢ በማድረግ እንደዘገበው ስምምነት ላይ ለመድረስ የአሜሪካ ግፊት በጣም ጠንካራ ነበር። ሆኖም ግጭቱ ሊቀጥል እንደሚችል ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት። ኤም 23 የተኩስ አቁም ስምምነትን ከፈረመ በኋላ በሰሜን ኪቩ በሚገኙ በተለያዩ አካባቢዎች ከኮንጎ መንግሥት ደጋፊ የዋዛለንዶ ሚሊሻ ተዋጊዎች ጋር ጠብ ፈጥሯል።
የኤም 23 ቃል አቀባይ ላውረንስ ካኑካ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መንግሥት በምሥራቃዊው የሀገሪቱ ክፍል ውስጥ ወታደሮችን እና ከባድ መሳሪያዎችን በሁሉም ግንባሮች በማሰማራት እና በደቡብ ኪቩ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት በማድረስ የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት ተላልፏል ሲሉ ወቅሰዋል።
ኢትዮጵያ
በኢትዮጵያ የጦርነት ዋና መንስኤዎች ውስብስብ የብሔር ግጭት፣ የፖለቲካ ስልጣን ሽኩቻ፣ የታሪክ ቅሬታዎች እና የሃብት ፉክክር እንደሆኑ ነው አንደርስታንዲንግ ዋር ዶት ኦርግ ላይ ያገኘነው መረጃ የሚጠቁመው።
በአውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር በ1995 የተዋቀረው የኢትዮጵያ የብሔር ፌደራሊዝም ሥርዓት በክልሎች ማንነት ላይ የተመሠረተ ትልቅ የራስ ገዝ አስተዳደርን ይሰጣል። ታዲያ የሕገ መንግሥቱ አወቃቀር የብሔር እኩልነትን ያመጣል ተብሎ ቢታሰብም አሁን ላይ ግን ጫፍ የወጣ ብሔርተኝነትን በመፍጠር በቡድኖች መካከል ጥቃትን ማስከተሉ ነው የተገለጸው። በክልሎች መካከል የተቀሰቀሰው የግዛት ውዝግብ ፖለቲካዊ አለመረጋጋትን ፈጥሯል።
የሰሜኑ ጦርነትን (2020 – 2022 እ.አ.አ) ጨምሮ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች የቀጠለው ብጥብጥ እና ግጭት ሀገሪቱን ዋጋ እያስከፈላት ነው፡፡ ብጥብጦች ውዱን እና አይተኬውን የሰው ልጅ ሕይወት እየቀጠፉ ናቸው፡፡
ወደፊት ሀገሪቱን ወደነበረችበት የቀደመ ሰላሟ ለመመለስ ሁሉን አካታች ሀገራዊ ውይይት መደረግ እንዳለበት በዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ግፊት እየተደረገ ነው፡፡ ይህን ተከትሎ ሀገራዊ የምክክር መድረኮች እየተካሄዱ ይገኛሉ፡፡ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ውጪ አማራጭ እንደሌለ ተፋላሚ ወገኖች ሊገነዘቡ ይገባልም ተብሏል፡፡
የሳህል ቀጣና
ወርልድ ፖፑሌሽን ሪቪው (worldpopulationreview.com) ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው ሳህል ተብሎ በሚጠራው ክልል በዋነኝነት 10 ሀገራት (ሴኔጋል፣ ጋምቢያ፣ ሞሪታኒያ፣ ጊኒ፣ ማሊ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ኒጀር፣ ቻድ፣ ካሜሩን እና ናይጄሪያ) የሚካተቱ ሲሆን ቡርኪናፋሶ፣ ኒጀር እና ማሊ ግጭት ውስጥ ይገኛሉ። በሀገራቱ የሚከሰቱ እና አሁንም ድረስ የቀጠሉት ግጭቶች መነሻቸው በተለያዩ ጎሳዎች መካከል ለረዥም ጊዜ በመሬት እና በንብረት ላይ የዘለቁ አለመግባባቶች ናቸው።
በደካማ አስተዳደር እና የፖለቲካ አለመረጋጋት የሚታሙት አብዛኛዎቹ የሳህል ሀገራት ዜጎቻቸው በደካማ የመንግሥት ተቋማት አሠራር፣ ሙስና እና ውጤታማ አስተዳደር እጦት ይሰቃያሉ። ይህም ታጣቂ ቡድኖችን ፈጥሯል።
በቀጣናው ባሉ ግጭቶች ሰፊ መፈናቀል ተከስቷል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሰብዓዊ ርዳታ ጠባቂ ሆነዋል፡፡
እንዲሁም በሽብርተኝነት ስማቸው ከሚጠቀስ ቡድኖች ጋር ማለትም ከአልቃይዳ እና ከአይ ኤስ ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂ ቡድኖች አለመረጋጋትን እና ብጥብጥን በማስፋፋት አባላትን በአካባቢው በመመልመል ላይ መገኘታቸው ቀጣናው ሰላም እንዲያጣ ምክንያት ሆኗል።
በሀገራቱ ተንሰራፍቶ የሚገኘው ከፍተኛ ድህነት ቅሬታዎችን አባብሶ በመንግሥታቸው ላይ እንዲያምጹ እና ወደ ታጠቁ ኃይሎች ፊታቸውን እንዲያዞሩም በር ከፍቷል።
ድርቅ፣ በረሃማነት እና የውኃ እንዲሁም የግጦሽ መሬት ፉክክር በአርብቶ አደር እና አርሶ አደሮች መካከል ያለውን ግጭት አባብሷል። የውጭ ወታደራዊ ጣልቃገብነቶች (የፈረንሳይ፣ ቻይና፣ ሩሲያ…) እና የጂኦፖለቲካዊ ፍላጎቶችም አካባቢያዊ እንቅስቃሴዎችን እንዳወሳሰቡት ይነገራል።
በሳህል ቀጣና ውስጥ በሚፈጠሩ ግጭቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፣ ሚሊዮኖች የሀገር ውስጥ መፈናቀል ደርሶባቸዋል፤ ወይም ወደ ሌላ ሀገር ለስደት ተዳርገዋል። በግጭቶች ምክንያት የግብርና ሥራዎች በመስተጓጎላቸው እና በገበያ መቋረጥ ምክንያት የምግብ ዋስትና እጦት እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ተባብሷል።
የመሠረተ ልማት ውድመት፣ የንግድ እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ፣ ውስን ኢንቨስትመንት እና የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ሀገራቱን እየናጣቸው ነው። ብጥብጡ ወደ ጎረቤት ሀገሮች በመስፋፋቱ ሰፊውን አካባቢ እንዳይረጋጋ አድርጎታል። በቀጣናው ድንበር ዘለል ሽብርተኝነት እና የጦር መሣሪያ ዝውውር ጨምሯል። የጎሳ መለያየት እና የማሕበረሰብ ግንኙነት መፈራረስ ተባብሷል። በመንግሥት እና በጸጥታ ኃይሎች ላይ ያለው እምነት ተዳክሟል። ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፤ ወይም ወድመዋል። የተጓተቱ የልማት ፕሮጀክቶች እና የተዳከሙ ተቋማት ተበራክተዋል።
ታዲያ በሳህል ቀጣና ውስጥ ለሚገኙ ሀገራት የሕግ የበላይነትን እና አስተዳደርን ማጠናከር፣ የዴሞክራሲ ተቋማትን መደገፍ እና ሙስናን መዋጋት፣ ለውጤታማ ፖሊስ እና ፍትሕ የፀጥታ ሴክተርን ማሻሻል፣ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይት፣ ሁሉንም ብሔረሰቦች እና ማኅበረሰቦች በሰላማዊ ድርድር ላይ ማሳተፍ፣ ታሪካዊ ቅሬታዎችን መፍታት እና ብሔራዊ እርቅን መፈጸም፣ የፀረ ሽብርተኝነት እና የደኅንነት ትብብር፣ የታጣቂ ቡድችን ትስስር ለመቁረጥ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ትብብርን መጠየቅ መፍትሔዎች መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ላይ ያገኘነው መረጃ ያትታል።
(ሳባ ሙሉጌታ )
በኲር የሐምሌ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም