የፕሮጀክቶች አፈጻጸም መጓተት ለምን?

0
55

መሠረተ ልማት ለአንድ ሀገር ምጣኔ ሀብት ዕድገት እና የሕዝቡን መስተጋብር ለማቀላጠፍ አይነተኛ ሚና ይጫወታል። ይህም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ይሰጣል። ለአብነት የመንገድ መሠረተ ልማት የገጠሩን ማኅበረሰብ ከከተሜው፤ ሸማቹን ከሻጩ በቀጥታ በማገናኘት የተሻለ አገልግሎት እንዲኖር ያደርጋል። ይህም ለምጣኔ ሀብቱ ዕድገት ሁነኛ መንገድ ነው።

የአማራ ክልል መንግሥት የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረዥም ጊዜ የልማት እቅድ በማቀድ በፌደራል እና በክልሉ መንግሥት የልማት ፕሮጀክቶችን በማከናወን የክልሉን ምጣኔ ሀብት ዕድገት ለማፋጠን ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል።

 

የአብክመ ፕላንና ልማት ቢሮ ደግሞ በክልሉ የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶችን በመከታታል እና በመደገፍ ያሉበትን የአፈጻጸም ሁኔታ ክልላዊ ቅርጽ በያዘ መልኩ ሪፖርት በማዘጋጀት ለከፍተኛ የክልል አካላት እንዲገመገሙ የማድረግ ተግባር እና ኃላፊነት ተሰጥቶት እየሠራ ይገኛል። የፕላንና ልማት ቢሮ የፕሮጀክቶችን አፈጻጽም የመከታተል እና የመገምገም ኃላፊነት በክልሉ መንግሥት መወሰኛ አዋጅ ቁጥር 280/2014 ተሰጥቶታል፡፡

 

ፕሮጀክቶች ተጀምረው ሳይጠናቀቁ ረዥም ዓመታትን በማስቆጠራቸው፣ መንገዶች ተጀምረው በወቅቱ ሳይጠናቀቁ በመቅረታቸው፤ የመስኖ ግድቦች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ባለመገደባቸው በኢኮኖሚያዊ እና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደሩ ይገኛል። በሕዝብ ዘንድም የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምንጭ ሆነዋል።

 

በፕሮጀክቶች መጓተት ምክንያት ሕዝቡ ከፕሮጀክቶች ማግኘት ያለበትን ጥቅም በወቅቱ ሳያገኝ ለዓመታት ተሻግሯል። ለአብነትም የመገጭ ግድብ፣ ርብ እና ሌሎች የመስኖ ፕሮጀክቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡

በመሆኑም የመንገድ፣ የውኃ፣ የድልድይ፣ የትምህርት ቤት፣ የጤና፣ የቴሌኮም፣ የኤሌክትሪክ እና መሰል መሠረተ ልማቶችን በወቅቱ፣ በፍጥነት እና በጥራት በማጠናቀቅ ማኅበረሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄ መፍታት ግድ ይላል። እንዲሁም በየጊዜው የመንግሥት ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ያሉበትን ደረጃ መቃኘት፣ መገምገም፣ መረጃ እና ምክረ ሐሳብ ለሚመለከተው አካል ማቅረብ እንዲሁም በጥፋተኞች ላይ አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ መውሰድ ይገባል።

 

በፌደራል መንግሥት የሚሠሩ 61 የአስፋልት መንገዶች መኖራቸውን የተናገሩት በአብክመ ፕላንና ልማት ቢሮ የልማት ፕሮጀክቶች ክትትል እና ግምገማ ዳይሬክተር ወ/ሮ እናንየ ይብሬ 13ቱ በሰሜኑ ጦርነት ጊዜ ውላቸውን አቋርጠው አራት ዓመታትን አስቆጥረዋል። 12ቱ ደግሞ በክልሉ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር እና በተቋራጭ አቅም ውስንነት ምክንያት  ሥራቸውን አቋርጠዋል። 36 የሚሆኑት ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ እንዳሉም ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ አብራርተዋል። በመሆኑም ወቅታዊ የፀጥታ ችግሮችን በመቋቋም ምን ያህል ፕሮጀክቶች መቼ ተጀምረው መቼ ይጠናቀቃሉ? የት ዞን፣ የት ወረዳ የሚሉትን ቀድሞ በመለየት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል። ከዚህ በፊት የነበሩትን የፕሮጀክቶች መዘግየት ለመፍታት ጥብቅ የተጠያቂነት አሠራር በመዘርጋት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል። የፕሮጀክት ድልድሉ ፍትሐዊ እንዲሆን ጥረት እየተደረገ ይገኛልም ብለዋል።

 

በተለይም የመገጭ መስኖ ፕሮጀክት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው የገለፁት ዳይሬክተሯ ከ17 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት እና ለጎንደር ከተማ ሕዝብ የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ታልሞ ወደ ሥራ የተገባው የመገጭ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታው ለረዥም ዓመታት ተጓትቷል ብለዋል። ወደ ጣና ሐይቅ የሚገባውን ደለል በመከላከል ፋይዳው ከፍተኛ የሆነው ፕሮጀክቱ 45 ሺህ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎም ይጠበቃል።

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ አሁን ላይ በተሻለ ሁኔታ ክትትል እና ድጋፍ እየተደረገለት መሆኑን ጠቅሰዋል። እንደ ዳይሬክተሯ ማብራሪያ የቴክኒክ እና የጥራት ችግር እንዳይፈጠር ትኩረት ተሰጥቷል። ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅም ለሀገር ውስጥ ፍጆታ እና ለውጭ ምንዛሪ የተሻለ ምርትን በመጨመር ድህነትን ይቀንሳል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ነው። ከረዥም ዓመታት በፊት ተጀምረው ያልተፈፀሙ ፕሮጀክቶችንም በማጥናት ግንባታቸው እንዲከናወኑ እየተደረጉ መሆኑን አንስተው፣ ለዚህም የመገጭ ፕሮጀክት ሁነኛ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።

 

የተቋራጭ አቅም ውስንነት፣ የካሳ ክፍያ እና የወሰን ማስከበር ችግር፣ የፀጥታ ችግሩን ሰበብ በማድረግ አንፃራዊ ሰላም ባለበት አካባቢ እንኳን ገብቶ የመሥራት ፍላጎት አለመኖር፣ ተቋራጮች የሚፈለገውን የሰው ኃይል እና ማሽነሪ ይዘው አለመግባት፣ በቂ ግብዓት ይዞ አለመቅረብ እና መሰል ጉዳዮች ለፕሮጀክቶች መዘግየት መሠረታዊ ምክንያቶች መሆናቸውን በአብነት አንስተዋል።

ወ/ሮ እናንየ እንዳሉት ችግሩን ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው። ለስኬቱም በልዩ ሁኔታ ክትትል እና ድጋፍ እንዲሁም ቅንጅታዊ አሠራርን  ማጠናከር ይገባል።

የፕሮጀክቶቹን ዝርዝር አፈጻጸም የተናገሩት ወ/ሮ እናንየ የተጀመሩ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እና አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ እንዲሁም በጥራት እና በፍጥነት እንዲጠናቀቁ ቢሮው ከፍተኛ ክትትል እያደረገ ነው።

 

በቂ በጀት መመደብ፣ የነዳጅ አቅርቦት ችግርን መፍታት፣ ተቋራጮችን በሙሉ አቅማቸው ሳይቆራርጡ ወደ ሥራው ማስገባት፣ በሰበብ አስባቡ የማይሠሩትን የእርምት ርምጃ መውሰድ፣ ካልቻሉ በሌላ ተቋራጭ መተካት፣ ክትትል እና ድጋፍ ማድረግ፣ በባለቤትነት እንዲሠሩ ማድረግ፣ አሠራሮችን ማዘመን፣ … የመፍትሄ አቅጣጫዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ለዚህም ባለድርሻ አካላት በየጊዜው ክትትል እና ድጋፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

ተቋራጩ ለሥራው የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል እና ግብዓት እንዲያሟላ ማድረግ፣ ያለቀለት ዲዛይን ይዞ እንዲቀርብ ማድረግ፣ ግዥ ለመፈፀም የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓቱን ማሻሻል እንደሚገባም ጠቁመዋል። አማካሪዎችም ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዲሁም ልምድ እና ተሞክሮን ማምጣት ይጠበቅባቸዋል። በአጠቃላይ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች የክልሉ ትልቅ ሀብት በመሆናቸው ሁሉም አካል ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባ ጠይቀዋል።

 

ከዚህ ጋር በተያያዘ የመገጭ ፕሮጀክት በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ወደ አገልግሎት እንዲገባ የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርግ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አረጋግጠዋል፡፡ የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 10ኛ መደበኛ ጉባዔውን ከሐምሌ 19 እስከ 22 ቀን 2017 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ማካሄዱ ይታወሳል። በዚህ ወቅት ርእሰ መሥተዳድሩ የመንግሥትን የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።

 

በሪፖርታቸውም በበጀት ዓመቱ የተሠሩትን የመንገድ ሥራዎችን አቅርበዋል። አንድ ሺህ 210 ኪሎ ሜትር መንገድ መሠራቱንም ተናግረዋል። ከእነዚህም ውስጥ 132 ኪሎ ሜትር የሚሆው  የአስፋልት መንገድ፣ 15 ኮንክሪት ድልድዮች እና 24 ተንጠልጣይ ድልድዮች መገንባታቸውን አስታውቀዋል። ሌሎች ድልድዮችም አፈጻጸማቸው በጥሩ ደረጃ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። የክልሉን የመንገድ ሽፋን  ከ32 ሺህ 523 ኪሎ ሜትር ወደ 33 ሺህ 734 ኪሎ ሜትር ማድረስ ተችሏል ብለዋል። በበጀት ዓመቱ 18 ወረዳዎችን እና 221 ቀበሌዎችን በመንገድ ማስተሳሰር  እንደተቻለም አስገንዝበዋል።

 

በበጀት ዓመቱ ትኩረት የተሰጠው ሌላኛው ዘርፍ የመስኖ ልማት መሆኑን ነው ያነሱት። አቶ አረጋ እንዳስታወቁት በበጀት ዓመቱ 197 የመስኖ ፕሮጀክቶች የጥናት እና ዲዛይን ሥራ ተሠርቷል። 223 የመስኖ ፕሮጀክቶች ወደ ግንባታ ገብተዋል። 113 ፕሮጀክቶች ደግሞ ተጠናቅቀዋል። በበጀት ዓመቱ በንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦትም በትኩረት ተሠርቷል። ከ75 ነጥብ ሁለት አጠቃላይ ሽፋን ወደ 77 ነጥብ አምስት በመቶ ከፍ ማድረግ ተችሏል።

ሌላው በሪፖርታቸው ያነሱት በከተሞች ላይ የኮሪደር ልማት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ነው። ባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ደሴ እና ኮምቦልቻ የመጀመሪያ ምዕራፍ አጠናቅቀው ወደ ሁለተኛ ምዕራፍ ተሸጋግረዋል። የኮሪደር ልማት ለዘመናት ሰው እንዳያያቸው አድርገን በጉያችን የደበቅናቸውን መስህቦችን እና የኢንቨስትመንት አቅሞችን የገለጠ፤ ባሕር ዳርን ከጣና ሐይቅ ጋር ያስተሳሰረ፤ ጎንደርን እንደገና የሞሸረ፤ በእርጅና የቆየችውን ደሴን ዳግም ያስዋበ፤ ለኮምቦልቻ እና ለደብረ ብርሃን ከኢንዱስትሪ ከተማነታቸው ባሻገር የቱሪዝም ስጦታ ያበረከተ ነው ብለዋል። በቀጣይም ሌሎች መሠረታዊ ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲሠሩ ክትትል እና ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የሐምሌ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here