የቬትናም መንገድ

0
62

ከዋናው ደቡብ ምስራቅ እስያ ክፍለ አህጉር ምስራቃዊ ቀጠና ላይ የምትገኘው ቬትናም በሰሜን ቻይና፣ በደቡብ እና በምስራቅ የቻይና ባህር፣ የታይላንድ ባህረ ገብ በደቡብ ምእራብ እንዲሁም በምእራብ ካምቦዲያ እና ላኦስ ያዋስኗታል። ዋና ከተማዋ ሃኖይ በሰሜን በኩል ስትገኝ የሀገሪቱ ትልቋ ከተማ ሆቾ ሚንህ (የቀድሞዋ ሳይጎን) ከተማ በደቡብ የሀገሪቱ ክፍል ይገኛሉ።

 

ጥንታዊ የስልጣኔ አሻራ ያላት ቬትናም የተለያዩ የውጪ ወራሪዎችን ያስተናገደች፣ በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ የተራዘመ ጦርነት ሰለባ የሆነችበት እና ከ1946 እስከ 1967 ዓ.ም ለሁለት ሀገርነት የተከፈለችበት አስከፊ ዘመናት ነበሯት። ይሁንና በ1967 ዓ.ም ዳግም ውህደት ከፈጠረች በኋላ በ1968 ዓ.ም  ሐምሌ 1967 ዓ.ም አንዲት ሕብረተሰባዊት የቬትናም ሪፐብሊክን እስከመመስረት ደርሳለች። እናም የመከፋፈል መጥፎ ታሪኳን አስወግዳ አዲስ የለውጥ እና  የብልፅግና ታሪክ የጀመረችው ቬትናም የበኩር የታሪክ አምድ ርእሰ ጉዳያችን ናት፤ መልካም  ንባብ።

 

የቬትናም ሕዝብ አመጣጥን በተመለከተ የሚታወቀው በአንፃራዊነት ጥቂት ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ በታሪክ ውስጥ የተከሰቱት “ላክ” ሕዝቦች በሚል መጠሪያ ሲሆን እነርሱም አሁን ሰሜናዊ ቬትናም በሚገኝበት በሬድ ሪቨር ረግረጋማ ስፍራ ይኖሩ ነበር። አንዳንድ ተመራማሪዎች እንደሚሉትም ላኮች ቬት ከሚባሉ ሌሎች ሕዝቦች ጋር ቅርብ ዝምድና ነበራቸው። ቬቶችም ከያንግዚ ወንዝ እስከ  ሬድ ወንዝ ድረስ ባለው የምስራቅ እስያ ጠረፋማ ክልል በአንደኛው ሚሊኒዬም ወቅት ይኖሩ ነበር። ሌሎች ደግሞ ይህን አስተሳሰብ ሲሞግቱት የአሁኗ ዘመናዊት ቬትናም ሕዝብ በደቡብ ምስራቅ እስያ ክፍለ አህጉር ከሚገኙ ቻይናዊ ካልሆኑ ሕዝቦች ጋር በርካታ የባህል እና የቋንቋ ባህሪያትን እንደሚወራረሱ በማስረዳት ነው። የሆነው ሆኖ ቬትናም የተባለች ሀገር እጅግ ውስብስብ ከሆነ የጎሳዎች ቅይጥ የተመሠረተች ሀገር እንደሆነች ይነገራል።

 

ነገር ግን በ1910ዎቹ የተካሄዱት የከርሰ ምድር ቁፋሮ ግኝቶች በአሁኑ ሰሜን ቬትናም ውስጥ የጥንት ስልጣኔ ሊኖር እንደሚችል አመላክተዋል። ከ1950ዎቹ ጀምሮ የከርሰ ምድረ ቁፋሮ ባለሙያዎች የዚህን ስልጣኔ እውነትነት ለማረጋገጥ በርትተው ሰርተዋል። ከ4000 ቅ.ዓ በፊት የሚጀምር ስልጣኔ የነበረ መሆኑን አረጋግጠዋል።

 

ቬትናም የጥንታዊ ስልጣኔ መገኛ ብትሆንም በርካታ የውጪ ወራሪዎች ሰለባ ሆና የቆየች ሀገር ናት። ቻይና፣ ፖርቹጋል፣ ፈረንሳይ እና ጃፓን እየተፈራረቁ ወረራ ፈፅመውባታል። ቻይና ከአንድ ሺህ ዓመታት በላይ ቬትናምን ግዛቷ አድረጋት ቆይታለች። የዚህ ሚሌኒዬም የመጀመሪያው አጋማሽ የወረራ ወቅት የተቋረጠው ታይ ሳች የተሰኘ ታዋቂ የነፃነት ታጋይን መገደል ተከትሎ በተነሳ ታላቅ አመፅ  ነበር። የቬትናም ሕዝብ በመተባበር አመፁን ቢያቀጣጥሉትም የማታ ማታ ግን አልተሳካም። የዚህ ሚሌኒዬም ሁለተኛው አጋማሽ ወረራ የበለጠ ቬትናምን ያንበረከከ ነበር። ማንኛውንም  አይነት የቬትናማውያን አመፅ እንዳይኖር የሚገድብ ህግ በመፅደቁ፤ ነገር ግን ቬትናማውያን ከቻይና የቅኝ ግዛት ቀንበር ለመላቀቅ   ትግላቸውን ቀጠሉ።  በዚህም በ931 ዓ.ም ቬትናም ከቻይና ነፃነቷን አገኘች።

 

ከአስረኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ቬትናም  “የደቡብ ዘመቻ” ተብሎ የሚታወቅ የመስፋፋት ዘመቻን ወደ ደቡብ አድረጋለች። ይህን የመስፋፋት ዘመቻ እያደረገች ጎን ለጎን ከቻምፓ እና ከሞንጎል መንግሥታት ጋር ሉአላዊነቷን ለማስከበር ስትታገል ነበር። ለሀገሩ ዳር ድንበር ብርቱ ትግል በማድረግ ሀገሩን ከእነዚህ ወራሪዎች  የጠበቀው የቬትናም ሕዝብ እጅግ ሀገሩን  ወዳድ ተጋዳይ መሆኑን ታሪኩ ያስረዳል። ጠላቶቻቸውን  አንበርክከው መልሰዋልና።

 

ከ16ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ እስከ 18ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ ባለው ጥቂት ክፍለ ዘመናት ቬትናም እፎይታ እና የፀና  ሀገራዊ ውህደት የተቀዳጀችበት ነበር። በመካከል ለስልጣን የሚፎካከሩ የሰሜኑ እና የደቡቡ ክፍል ቤተሰቦች የእርስ በርስ ጦርነት ቢያደርጉም ንጉየን የተባለው የመጨረሻው የቬትናም ስርወ መንግሥት ከ1794 እስከ 1875 ዓ.ም ድረስ ሀገሪቱን አስተዳድሯል። ከዚያም ቬትናም የተጎናፀፈችው አጭር የሰላም ጊዜ ወዲያውኑ በ19ኛው ክፍለ ዘመን  አጋማሽ ላይ በፈረንሳይ የባህር ኃይል አዛዦች ጣልቃ ገብነት ተስተጓጎለ።

 

በ1847 ዓ.ም የፈረንሳይ ጣልቃ ገብነት በቬትናም ላይ የተፋጠነበት እና በ1850 ዓ.ም ደግሞ በአድሚራል ሪጋውልት ዲ ጀኑሊ የሚመራ የጦር መርከበኛ  ሀይል ቱራንን መክበብ ጀመረ እና የዳ ናንግ የባህር ዳርቻን ተቆጣጠረ። ይህ ክስተት ደግሞ የ1854 እና 1866 ዓ.ም ቬትናምን የፈረንሳይ  ግዛት ያደረጉ ስምምነቶች  የተፈረሙበትን እውነታ አስከተለ።

 

የፈረንሳይ ኢንዶ ቻይና የተባለ  አዲስ መልካዓምድራዊ ክልልም በይፋ ተመሰረተ። በዚህ አዲስ ግዛት ውስጥ ቬትናም፣ ላኦስ እና ካምቦዲያ የተካተቱበት በቬትናም ታሪክ ውስጥ አዲስ የታሪክ ዘመንን ያመላከተ ሆኖም ተመዘገበ። ለአስተዳደራዊ  ጉዳዮች ይመች ዘንድ በፈረንሳይ የቅኝ አገዛዝ ዘመን  ቬትናም ወዲያዉኑ ለሶስት ተከፈለች። ቶንኪን በሰሜን፣ በመሀል በኩል አናም እና በደቡብ ኮቺንቺና ይባሉ ነበር።

የብሔራዊ ሉዓላዊነትን የደፈረው ይህ ድርጊት የቬትናም አርበኞችን በፈረንሳይ ላይ በቁርጠኝነት ለትግል እንዲነሱ አደረገ።  ከሰሜን እስከ ደቡብ በሀገሪቱ  ከተሞች አያሌ አመፆች ተከናወኑ። የቬትናማውያን በፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ላይ የተቀጣጠለው የነፃነት ትግል ከአርሶ አደር አማፂያን እስከ ምሁራን የተካተተበት ሰፊ ተቃወሞ ነበር። ነገር ግን ግቡን ማሳካት አልቻለም።   በመሆኑም የሁለተኛው የዓለም ጦርነት እስካበቃበት ጊዜ ድረስ ቬትናም ነፃነቷን አላገኘችም ።

 

ከ1932 እስከ 1937 ዓ.ም በተካሄደው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ጃፓኖች አካባቢውን ተቆጣጠሩ እና የፈረንሳይ ኢንዶቻይና ግዛት እንዲያከትም አደረጉ። የጃፓኖች በፈረንሳይ እግር መተካት ለቬትናም ሕዝብ ሰላም  አላመጣለትም፤ በተቃራኒው ጃፓን የራሷን አዲስ ግዛት መሰረተች እና ቬትናማውያንን ዳግም ተገዢ አደረገ። በጃፓን ሰራዊት እና በፈረንሳይ ሰራዊት መካከል በመጋቢት 2 ቀን 1937 ዓ.ም ላይ የተካሄደው ግጭት ትልቅ ቀውስ  አስከተለ፤ የፈረንሳይን ሽንፈትም  አበሰረ።

 

መጋቢት 7 ቀን 1937 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥት ባኦ ዳይ ከጃፓኖች ጋር በማበር የሀገሪቱን ነፃነት እና ዳግም ውህደት አወጀ። ነሀሴ 1937 ዓ.ም ላይ ደግሞ የቀድሞው የኢንዶ ቻይና ኮሚንስት መሪዎች ህብረት “ቬት ሚንህ” የተባለ ሀይል ከጃፓን ጋር ግልፅ ግጭት ውስጥ ገባ። በመስከረም 1937 ዓ.ም ላይ ሀኖይ ከተማ ውስጥ ባ ዲንህ አደባባይ ላይ ሆ ቺሚንህ የቬትናም ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ነፃነትን አወጀ። በዚሁም ሆ ቺ ሚንህ  የቬትናም ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚደንት ሆነ። ንጉሠ ነገሥት ባኦ ዳይ በመሸነፉ የሀገሪቱ የመጀመሪያው የሪፐብሊክ መንግሥት ልዩ አማካሪ እንዲሆን  ተደረገ።

 

የቬትናማውያን ደስታ ብዙ መዝለቅ አልቻለም። ምክያቱም በፈረንሳይ እና በቬትሚንህ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ያፈራረመው የ1946 ዓ.ም የጄኔቫው ጉባኤ በሌላ በኩል ቬትናም ወደ ሁለት ሉዓላዊ ሀገርነት እንድትከፈል ውሳኔ አሳልፎ ነበር። በዚህ መልኩ ቬትናምን የለቀቀችው ፈረንሳይ በቬትናም ሁለት ሀገሮች እንዲፈጠሩ መንገድ ጠረገች። በሰሜን ሆ ቺሚንህ የሚመራት የቬትናም ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በደቡብ ደግሞ ንጎ ዲንህ ዳየም የሚመራው የቬትናም ሪፐብሊክ የተባሉ ሁለት የተለያዩ መንግሥታት በቬትናም ምድር ተፈጠሩ። የሰሜኑ ኮሚንስት መንግሥት የደቡብን ብሔርተኝነት እንዲቃወም ውግንናውን ከሶቭየት ሕብረት ጋር ያደረገ እና ከቻይና ድጋፍ ይደረግለት ነበር። እንዲሁም የአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል ለደቡብ ቬትናም ድጋፍ በመስጠት ጣልቃ ገባ። በዚህ መልኩ የአንድ ሀገር ሰዎች የኃያላን ርእዮተ ዓለማት ሰለባ ሆነው ለሁለት ተከፈሉ። አሜሪካ ኮሚኒዝም ወደ ሌሎች ሀገራት እንዳይስፋፋ በመስጋት የደቡቡን መንግሥት መደገፉን ቀጠለች። ከዚያም አሜሪካ ሰሜን ቬትናምን በመጋቢት ወር  1957 ዓ.ም   በቦምብ ደበደበች። ይህ ድብደባ የቬትናም ጦርነት የመጀመሩን ክብሪት የጫረ ክስተት ነበር።

 

አሜሪካ በቀጥታ ሰራዊቷን በማዝመት የጦርነቱ ተዋናይ ሆነች። በሰሜን ቬትናም ላይ የጀመረችው የቦምብ ድብደባ እስከ 1960 ዓ.ም ድረስ አላቆመም። ጦርነቱም እስከ 1971 ዓ.ም ድረስ ቀጥሎ ነበር። ነገር ግን የቬትናም አርበኞች ከአሜሪካ ሰራዊት ጋር የጀመሩትን ትንቅንቅ አጠነከሩት። አሜሪካ ሰራዊቷን በየጊዜው እንድትጨምር ብትገደድም  የቬትናማውያኑን ትግል መቋቋም አልቻለችም። ይልቁንም አሜሪካውያኑ በታሪካቸው ያላዩት ሽንፈት እና ውርደት በቬትናም ምድር ላይ ገጠማቸው። በመቶ ሺዎቹ የሚቆጠሩ ወታደሮቿ ሙት እና ቁስለኛ ሆኑ። መንግሥት ከውስጥም ከውጭም የተቃውሞውን ጫና መቋቋም አልቻለም። የማታ ማታም አሜሪካ ደቡብ ቬትናምን ራስሽ ተወጭው ብላ በችግር ውስጥ  እንዳለች ለብቻዋ ትታት እስከ 1967 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ቬትናምን ለቃ ወጣች። በ1967 ዓ.ም የሰሜኑ መንግሥት የደቡብ ቬትናምን መዲና የቀድሞዋን ሴጎን ከተማ ከተቆጣጠረ እና በቬትናማውያን ዘንድ እንደ ብሔራዊ ጀግና በሚቆጠረው ሆቺ ሚንህ ስም ከሰየሟት በኋላ የቬትናም ጦርነት አበቃ። በዚሁ ዓመትም ቬትናም ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ተዋሃደች። ሁለቱ ሪፐብሊኮች አንድ ሆነው አንዲት የቬትናም ሶሺያሊስት ሪፐብሊክ እንዲመሰረት ፈቅደው፣ ሀኖይ ከተማ መናገሻቸው እንድትሆን ወሰኑ።

 

ከዚያ ወዲያ በጦርነት የደቀቀችውን ቬትናም መልሶ የማቋቋም እና አንድነቷን የማጠናከር ከፍተኛ ርብርብ ወደ ማድረግ ምእራፍ ተሸጋገረች። ከአጭር ጊዜ ማሽቆልቆል በኋላ እና  ከውህደቱ ጀምሮ ከተከተለው የኢኮኖሚ መረጋጋት   በ1972 ዓ.ም  ቬትናም ከኢኮኖሚያዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ችግሮቿ በፍጥነት ያነሳትን የኢኮኖሚ ፖሊሲ መተግበር ጀመረች። የቬትናም ፖሊሲ ከአለማቀፉ ማህበረሰብ ጋር ግንኙነቷን ማስፋት እና ማጠናከር ላይ ያተኮረ ነበር። በዚህም ጠንካራ እንቅስቃሴ ቬትናም ከብዙ መከራ በኋላ በቅርብ ዓመታት ሀገሪቱ የተረጋጋ ሰላም እና ኢኮኖሚ ባለቤት ለመሆን በቅታለች።

 

ሳምንቱ በታሪክ

ልብነ ድንግል ነጋሡ

ሰሎሞናዊው ስርወ መንግሥት ዳግም ወደ ክብሩ ከተመለሰ በኋላ፤  የመካከለኛው የታሪክ ዘመን ከኢትዮጵያ ነገሥታት ውስጥ አንዱ ናቸው፤ ልብነ ድንግል።

ልብነ ድንግል የዐፄ ናኦድ ልጅ ሲሆኑ የአባታቸውን መሞት ተከትለው በኢትዮጵያ የንጉሥ ዙፋን ላይ ሐምሌ 29 ቀን 1500 ዓ.ም  ዘውድ ደፍተው ለ32 ዓመታት ኢትዮጵያን የመሩ ንጉሥ ነበሩ።

የዐፄ ልብነ ድንግል የአስተዳደር ዘመን ከፊል ሰላም እና መረጋጋት የሰፈነበት እንዲሁም በከፊል በሁከትና በጦርነቶች የተሞላ ነበር። የንጉሡ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት በተረጋጋ ሰላም እና ደስታ የተሞሉ ነበሩ። ነገር ግን ቀሪዎቹ አስራ አምስት ዓመታት ግጭቶችን እና አለመረጋጋት የነገሰባቸው ነበሩ።

በሌላም በኩል ከአህመድ ግራኝ ጋር ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ ገብተው ነበር። ይህም ሽምብራ ኩሬ ላይ በተደረገው ጦርነት ዐፄው ድል ሆነው ዘመናቸው እንዳበቃ ታሪክ ያስረዳል።

ምንጭ-አባ ጋስፓሪኒ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ።

 

ኮሎኔል አስፋው ኃይለ ማሪያም

ሐምሌ 29 ቀን 1952 ዓ.ም በኮሪያ የተቀሰቀሰውን ግጭት ለማረጋጋት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ቡድን ላደረገው ጥሪ ፈጣን መልስ የሰጠችው ኢትዮጵያ ‘ቃኘው’ የተባለ ሰራዊቷን በተለያዩ ዙሮች ልካ እጅግ የተወደሰ አስገራሚ አስተዋጽኦ አበርክታለች።

በመሆኑም የ4ኛ ሻለቃ መሪ ሆነው የተሾሙት ኮሎኔል አስፋው የሚመሩትን ጦር በአግባቡ በማሰልጠን እና በማደራጀት የውጊያ ሞራሉ ተጠብቆ ተልዕኮውን እንዲወጣ  ጥረት አድርገዋል።

ለዚህ የቃኘው ውጤታማ ስራ ኬሌኔል አስፋው ስላበረከቱት ሚና የአሜሪካው ጄኔራል የምስጋና እውቅና የሰጡት ሐምሌ 29 ቀን 1952 ዓ.ም  ነበር።

ምንጭ-ሲሞን ስኮርዲለስ ‘ቃኘው’

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የሐምሌ 28 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here