ይግባኝ ምንድን ነው? የሚለው በወንጀልም ሆነ ፍትሐብሄር ጉዳዮች ስነ ሥርዓት ሕግ ቀጥተኛ ፍቺ ባይሰጠውም የሕግ መዝገበ ቃላት “በበላይ ፍርድ ቤት የተሰጠ እና አንድን ፍርድ ወይም ውሣኔ በመቃወም ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ በማቅረብ የፍርድ ቤት ውሳኔን /ፍርድ/ እንዲጣራ የሚደረግበት ወይም ሊለውጥ የሚችልበት ሥርዓት ነው” በሚል ብያኔ ሰጥቶታል::
በተመሳሳይ ታዋቂው የሕግ ኘሮፌሰር አለን ሲለን የይግባኝ ትርጉም አንድ ተከራካሪ ወገን በበታች ፍርድ ቤት የተሰጠን ፍርድ እንዲሠረዝ ወይም እንዲሻሻል በመጠየቅ ይግባኝ ሰሚ ለተባለ ፍርድ ቤት አቤቱታ የሚቀርብበት ሥርአት መሆኑን ነው የሚያስገነዝቡት::
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የክልል ዐቃቤ ሕግ አቶ ስማቸው አያሌው እንደሚገልፁት ጠቅለል ብሎ ሲታይ ይግባኝ በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በተሰጠ ፍርድ ወይም ውሳኔ ቅሬታ ያለበትን ወገን ቅሬታውን በሕጉ ስልጣን ለተሰጠው የበላይ ፍርድ ቤት አቅርቦ በማሳየት ውሳኔ እንዲሻር፣ እንዲለወጥ ወይም ውድቅ እንዲሆን ዳኝነት የሚጠይቅበት ሥርዓት ነው ይላሉ::
ይግባኝ መብት ነው ሲባልም ይህንን የሚጠቅሱ በርካታ የሕግ መሠረቶች ስላሉት ነው::
ለምሳሌ በኢፊዴሪ ሕገ መንግሥት ላይ አንድ የተከሰሰ ሰው ክርክሩ በሚታይበት ፍርድ ቤት የተሰጠ ትዕዛዝ ወይም ፍርድ ላይ ስልጣን ላለው ፍርድ ቤት ይግባኝ የማቅረብ መብት እንዳለው በአንቀፅ 26 ንኡስ ቁጥር 06 ላይ ተደንግጐ እናገኛለን::
በተጨማሪም በፍትሐብሄር ሕግ ስነ ሥርዓት ሕጋችን አንቀፅ 325 ንኡስ ቁጥር 01 ላይም ማንኛውም ተከራካሪ ወገን በበታች ባለ የፍትሐብሄር ስነ ሥርዓት ፍርድ ቤቶች ፍርድ ተሠጥቶ /የመጨረሻ ውሳኔ/ ተወስኖ ባለቀ ጉዳይ ላይ ይግባኝ ማቅረብ እንደሚችል ተደንግጓል::
በተመሳሳይ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ሥርዓት ሕጉ አንቀስ 181 ላይ የተፈረደበት ተከሳሽ፣ ተከሳሽ ነፃ በመውጣቱ ወይም በመለቀቁ መክንያት ይግባኝ ሊባል እንደሚችል ያስቀምጣል::
ኢትዮጵያ ተቀብላ በፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ሰነድ ላይም ይግባኝ መሠረታዊ ሰብዓዊ መብት እንደሆነ ተቀምጧል::
አቶ ስማቸው እንደሚሉት ከላይ በጠቀስናቸው ማሳያዎች የሕግ ድጋፍ አግባብ ይግባኝ መሠረታዊ እና በሕጉ ሙሉ ድጋፍ ያለው መሆኑን መገንዘብ እንደሚቻል ነው::
የይግባኝ አላማ
ይግባኝ የሚባልባቸው መሠረታዊ ዓላማዎች አራት ናቸው እነርሱም፡-
- በስር ፍርድ ቤት የተሠሩ (የተፈፀመ) ስህተት ማለትም የፍሬ ነገር ወይም የሕግ ስህተት ካለ ለማረም፣
- የፍርድ ቤቶችን አሠራር ቁጥጥር ለማድረግ፤ የፍርድ ጥራትን ለማሻሻል እና ለመቆጣጠር ከሚረዱ መንገዶች አንዱ በመሆኑ::
- በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ተመሳሳይ ውሳኔ (በተለይ በወንጀል ጉዳዮች) እንዲሰጥ ለማድረግ::
- ስነ ሥርዓታዊ ፍትሕን ለማስፈን፤ መብቱ የተጣሰ ተከራካሪ ወገን ለበላይ ፍርድ ቤት ጉዳዩን አስቀርቦ የተፈረደበትን ፍርድ እንዲሻሻል በማድረግ የመደመጥ መብቱን የሚያስከብርበት ዓላማ በመሆኑ ነው::
ባለሙያው አቶ ስማቸው ይግባኝ በፍትሐብሄር እና በወንጀል ለተከሰሱ ጉዳዮች መቅረብ እንደሚችል ሕጉን ጠቅሰው ገልፀውልናል:: ቀጥሎ ደግሞ ይግባኝ በፍትሐብሄር እና በወንጀል ጉዳይ እንዴት እንደሚቀርብ በዝርዝር ይገልፁልናል::
የፍትሐብሔር ይግባኝ
የፍትሐብሔር ስነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 327 የይግባኝ ማመልከቻ ይዘት ምን መምሰል እንዳለበት ደንግጓል:: በስነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 323 ንኡስ ቁጥር 02 መሠረት ደግሞ ይግባኝ የሚቀርበው ይግባኝ የሚባልበት ጉዳይ ላይ ውሳኔ በተሰጠ በ60 (ስልሳ) ቀናት ውስጥ እንደሆነ ነው::
ይግባኝ በ60 ቀን ውስጥ ያልቀረበ ከሆነ ግን ይግባኝ ባይ ይግባኝ የማቅረብ መብቱን ያጣል:: በአንፃሩ የይግባኝ ማቅረቢያ ጊዜው ያለፈበት አሳማኝ ምክንያት ያለው ሰው ይግባኙን በጊዜው ለማቅረብ ያልቻለበትን በቂ ምክንያት ከማስረጃዎች ጋር አያይዞ የፈቃድ ጥያቄ ማመልከቻ ማቅረብ እንደሚችል በስነ ሥርዓት ሕጉ ቁጥር 325 ተደንግጓል።
ይህ የፈቃድ ጥያቄ ማመልከቻ የይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት መዝገብ ቤት ሹም ይግባኙን በ10 ቀናት ውስጥ ማቅረብ አለበት::
በቂ ምክንያት ለሚለው በሕጉ የተሰጠ ዝርዝር ነገር የሌለ በመሆኑ የምክንያቱ በቂነት እንደየሁኔታው በፍርድ ቤቱ የሚመዘን እንደሆነ ባለሙያ አብራርተዋል:: ሆኖም አመልካቹ ይግባኙን በጊዜ ያላቀረበው በአመልካቹ ጠበቃ ወይም ነገረ ፈጅ ወይም በወኪሉ አለመቅረብ ምክንያት ከሆነ በቂ ምክንያት ተብሎ እንደማይወሰድና የይግባኝ መዝገብ እንዲከፈት የማይፈቀድ መሆኑን የፍትሐብሔር ስነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 326 ንኡስ ቁጥር 02 ደንግጓል::
የይግባኝ አቤቱታ ተቀባይነት የማያገኝበት ሁኔታ
ይግባኝ ከቀረበ በኋላ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ነገሩ የሚሰማበትን ቀነ ቀጠሮ ወስኖ ይግባኝ ባዩ ወይም ጠበቃው የሚያቀርቡትን ክርክር ከሰማ በኋላ የመጀመሪያው ደረጃ ፍርድ ቤት ፍርድ የሰጠበትን የመዝገብ ግልባጭ መርምሮ ፍርዱ ጉድለት የሌለበት መሆኑን ከተረዳ መልስ ሰጪውን ሳይጠራ ይግባኙን ዘግቶ አቤት ባዩን ሊያሰናብት ይችላል::
የወንጀል ጉዳይ ይግባኝ
የወንጀል ጉዳይ ክርክር የሚደረገው የወንጀል ተጎጂን በመወከል በዐቃቤ ሕግ እና ወንጀል በመፈፀም በተጠረጠረ ተከሳሽ መካከል ነው፤ ፍርድ ቤት በሚሰጠው ውሳኔ ላይ ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ወይም ተከሳሽ ቅሬታ ሊኖራቸው ይችላል። ይህም ቅሬታ በተከሳሽ የሚቀርብ ከሆነ የተወሰነብኝ የጥፋተኝነት ውሳኔ ተገቢ አይደለም ወይም የተላለፈብኝ ቅጣት ተገቢ አይደለም ወይም ተመጣጣኝ አይደለም በማለት ሊቀርብ የሚችል ነው:: ዐቃቤ ሕግ ደግሞ ተከሳሽ በነፃ በመለቀቁ ወይም ዝቅተኛ ቅጣት በመወሰኑ ቅሬታ ካለው ይግባኝ ማለት ይችላል።
ባለሙያው እንደሚገልፁት ከሳሽም ይሁን ተከሳሽ የዋስትና መፈቀድ ወይም መከልከል ላይ፣ የዋስትና መጠን መብዛት ወይም ማነስ ላይ ይግባኝ ሊሉ ይችላሉ።
በመሆኑም ከሳሽም ይሁን ተከሳሽ ጉዳዩን ያየው ፍርድ ቤት በሰጠው የመጨረሻ ፍርድ ወይም ውሳኔ ላይ ቅሬታ ካለው ይግባኝ ማለት ይችላል።
ይግባኝ የማይቻልባቸው ሁኔታዎች
በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ሥርዓት ሕጉ ቁጥር 184 እንደተደነገገው በስነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 94 መሠረት ቀጠሮ መስጠት ወይም አለመስጠት፣ በቁጥር 131 መሠረት ስለሚቀርብ መቃወሚያ፣ በቁጥር 146 መሠረት ማስረጃን ስለ መቀበል ወይም ስላለመቀበል ፍርድ ቤት በሚሰጠው ትዕዛዝ ላይ ይግባኝ ለማለት አይቻልም።
ይሁን እንጅ የጥፋተኝነት ውሳኔ በተሰጠበት ለጊዜው በመልቀቅ ወይም በነፃ መልቀቅ ፍርድ ተሰጥቶ ይግባኝ በተባለበት ጊዜ እነዚህ የተሰጡት ትዕዛዞች ይግባኝ ለማለት ምክንያቶች ለመሆን ይችላሉ።
ውሳኔ በተሰጠበት ጉዳይ ይግባኝ ስለማለት
የተፈረደበት ሰው በጥፋተኛነት ውሳኔ እና በቅጣቱ ላይ ይግባኝ ማለት ይችላል። ነገር ግን ተከሳሽ የተከሰሰበትን ወንጀል ያመነ ሆኖ በእምነቱ መሠረት ጥፋተኝነቱ ከተወሰነ በኋላ ስለቅጣቱ ልክነት ወይም ሕጋዊ ላለመሆኑ ይግባኝ ማለት እንጂ የጥፋተኝነት ውሳኔ በተሰጠበት ላይ ይግባኝ ማለት አይችልም። ዐቃቤ ሕጉ ወይም የግል ከሳሹ ፍርድ ቤት በሚሰጠው ለጊዜው በመልቀቅ ወይም ነፃ በመልቀቅ ፍርድ ላይ ወይም ቅጣቱ በቂ አይደለም በማለት ይግባኝ ማለት እንደሚችል በስነ ሥርዓት ሕጉ ቁጥር 185 ስር ተደንግጎ ይገኛል።
የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ስልጣን
ይግባኙ በሚሰማበት ጊዜ በጉዳዩ ውስጥ ለመግባት በቂ ምክንያት የሌለ መስሎ ከታየው ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ይግባኙን ያሰናብተዋል። በጉዳዩ ለመግባት በቂ ምክንያት ያለ በመሰለው ጊዜ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የሚከተሉትን ተግባራት እንደሚፈፅም በቁጥር 195 ስር ተደንግጓል።
ተከሳሹን ነፃ በመልቀቅ ወይም ለጊዜው በመልቀቅ በተሰጠ ትዕዛዝ ይግባኝ የተባለ ሲሆን ትዕዛዙን ሰርዞ ስልጣን ያለው ሌላ ፍርድ ቤት ጉዳዩን እንደገና እንዲያይ ማዘዝ ይችላል:: ጥፋተኛ ነው ብሎ እንደ ሕጉ ሊፈርድበትም ይችላል፤ ይግባኝ የቀረበው ጥፋተኛ ነው በተባለበት ውሳኔ እና በቅጣት ላይ ከሆነ፣ ጥፋተኛ ነው የተባለበትን ውሳኔና ቅጣቱን ሰርዞ ተከሳሹን በነፃ ሊለቅ፣ ፍርዱን ለውጦ ወይም ሳይለውጥ ቅጣቱን ሊያፀና፣ ሊጨምር ወይም ሊቀንስ ይችላል።
ይግባኝ የቀረበው ጥፋተኛ ነው በተባለበት ውሳኔ ላይ ብቻ ከሆነ ፍርዱና ቅጣቱን ሰርዞ ተከሳሹን በነፃ ሊለቅ ይችላል።
በስነ ሥርዓት ሕጉ ቁጥር 195 ንኡስ ቁጥር 03 ስር እንደተደነገገው ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ነው የተባለበትን ውሳኔ አፅንቶ ቅጣቱን የለወጠ እንደሆነ ወይም ቅጣቱን አፅንቶ ጥፋተኛ ነው የተባለበትን ውሳኔ የለወጠ እንደሆነ ጥፋተኛ ነው በተባለበት ወይም ቅጣቱ እንዲለወጥ በተወሰነው ላይ ብቻ ለሁለተኛ ጊዜ ይግባኝ ለማለት ይቻላል።
በሌላ በኩል ለይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የቀረበው ይግባኝ ስለ ተፈረደባቸው ብዙ ሰዎች የሚመለከት ሆኖ ይግባኝ ያለው ግን አንድ ሰው ብቻ በሆነ ጊዜ በይግባኝ የተሰጠው ፍርድ ይግባኝ ባዩን የሚጠቅም በሆነ ጊዜ እና ተከሳሾቹ ይግባኝ ቢሉ ኖሮ በፍርዱ እነሱም ሊጠቀሙ ይችሉ ነበር የሚያሰኝ ሲሆን ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የሚሰጠው ፍርድ ይግባኝ ላላሉት ሰዎች ይግባኝ እንዳሉ ተቆጥሮ ይፈፀምላቸው ለማለት ያስችላል:: ይህም በስነ ሥርዓት ሕጉ ቁጥር 196 ንኡስ ቁጥር 01 ሥር ተደንግጓል። ይሁንና ይግባኝ ባዩ ላይ ጉዳት የሚያመጣበት ከሆነ ይግባኝ ባላሉ ሰዎች ላይ አይፈፀምም።
በአጠቃላይ በወንጀል ጉዳይ የሚቀርብ ይግባኝ በመጀመሪያ ደረጃ ጉዳዩን አይቶ ፍርድ ወይም ውሳኔ በሰጠው ፍርድ ቤት ፍርድ ወይም ውሳኔ ላይ የሚቀርብ ቅሬታ ሲሆን ይህም በከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ወይም በተከሳሽ ሊቀርብ ይችላል።
የህግ አንቀጽ
- በኢፊዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 26ይግባኝ የማቅረብ መብት፡፡
- በፍትሐብሄር ሕግ ስነ ሥርዓት ሕጋችን አንቀፅ 325 ተወስኖ ባለቀ ጉዳይ ይግባኝ የመቅረብ መብት፡፡
- የስነ ሥርዓት ሕጉ ቁጥር 332 ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ለጉዳዩ እልባት እስከሚሰጥ ድረስ የሥር ፍርድ ቤት ፍርድ አፈፃፀም ታግዶ
እንዲቆይ ሊያዝ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡
- በስነ ሥርዓት ሕጉ ቁጥር 335 ደግሞ አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ መሟላት ከተቻለ ብቻ አፈፃፀም እንደሚታገድ፡፡
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የሐምሌ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም