ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ዓመታት የተካሄደው የሰሜኑ ጦርነት እና ከዚያም በኋላ በአማራ ክልል ውስጥ ተቀስቅሶ ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረው በትጥቅ የታገዘ ግጭት የትምህርት ዘርፉን ክፉኛ ፈትነውታል፡፡ ቀድሞውኑም 85 በመቶ ትምህርት ቤቶቹ ከደረጃ በታች በሆኑበት ክልሉ ያጋጠመው የሰላም እጦት ትምህርት ተቋማትን ለጉዳት ዳርጓል፡፡ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ እንዲሆኑ፣ መምህራን የሚፈለገውን ዕውቀት ለተማሪዎቻቸው እንዳይሰጡ አድርጓል፤ ለአብነትም በ2016 ዓ.ም ከሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ ሆነው ከርመዋል፡፡
በተመሳሳይ በ2017 ዓ.ም ብቻ በ10 ሺህ 997 ትምህርት ቤቶች ሰባት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር የክልሉ ትምህርት ቢሮ ቢያቅድም መመዝገብ የተቻለው ከሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ያልበለጡ ተማሪዎችን እንደነበር የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 10ኛ መደበኛ ጉባዔውን ባካሄደበት ወቅት ተጠቁሟል፡፡
በተማሪ ምዝገባ የዕቅዱን 40 በመቶ ማሳካት ቢቻልም ከተመዘገቡት ውስጥ ሲማሩ የከረሙት ግን ሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ተማሪዎች ብቻ ናቸው፡፡ ከአራት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ከትምህርት ውጪ መሆናቸውን በጉባዔው ተመላክቷል፡፡
የሰሜኑን ጦርነት ጨምሮ አሁንም ድረስ በቀጠለው ግጭት ስድስት ሺህ 187 ትምህርት ቤቶች በከፊል እና ሙሉ ለሙሉ ጉዳት እና ዝርፊያ አስተናግደዋል፡፡ በግጭቱ ምክንያት የተጎዱ ትምህርት ቤቶችም ከሁለት ሺህ በላይ እንደሆኑ ነው በምክር ቤቱ ሪፖርት የተመላከተው፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ የሰላም ችግሩ ልጆችን ከትምህርት እያራቃቸው መሆኑን የጠቆሙት ከዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የመጡት የክልሉ ምክር ቤት አባል ናቸው፡፡ የምክር ቤት አባሏ እንዳሉት ብዙ ተማሪዎች ለሁለት ዓመት በዘለቀው የሰላም ችግር ከትምህርት ውጪ ሆነዋል፡፡ ትምህርት የጀመሩትም ቢሆን ዓመቱን ሙሉ ሳያቋርጡ መማር አልቻሉም፡፡ ሲማሩ የከረሙትም እያስመዘገቡት ያለው የምዝና ውጤት በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህም ግጭቱ ምን ያህል ለሥነ ልቦና ጉዳት እየዳረጋቸው መሆኑን ማሳያ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት እና ደረጃ ለማሻሻል እየተሠራ ያለውን ሥራ ያደነቁት የምክር ቤት አባሏ፤ ነገር ግን አሁንም ከትምህርት ውጪ የሆኑ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ማምጣት ላይ መረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ለተሳካ የትውልድ ቅብብሎሽ አስተማማኝ ሰላም መፍጠር ላይ መሥራት እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡
ከምዕራብ ጎንደር መተማ አካባቢ የመጡት ሌላዋ የምክር ቤት አባልም ሐሳቡን ተጋርተዋል፤ ችግሩን በመቋቋም በ2017 የትምህርት ዘመን በከፍተኛ ጥረት እና ቁርጠኝነት ትምህርትን ማስቀጠል እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡ ዘርፉ የሁሉም ልማቶች መሠረት በመሆኑ ለተሳካ የትምህርት እንቅስቃሴ በትጋት እና በልዩ ርብርብ መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡
ሌሎች የምክር ቤቱ አባላትም ተመሳሳይ ሐሳብ በማንሳት ከችግሩ ለማላቀቅ ሁሉም እንዲረባረብ ጠይቀዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት ችግር ውስጥ የወደቀው ትምህርት በትውልድ ቅብብሎሽ ላይ እየፈጠረ ካለው ተጽእኖ ነጻ እንዲወጣ የትምህርት ጥራትን እና ተደራሽነትን ማሻሻል ላይ በትኩረት ሲሠራ መቆየቱን ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ተናግረዋል፡፡ አቶ አረጋ እንዳሉት የሰላም እጦቱ በተማሪዎች እና መምህራን ላይ የፈጠረው ወከባ ከፍተኛ ነው፤ ይሁን እንጂ ችግሩን በመቋቋም ትምህርትን በማስቀጠል በትምህርት ቁሳቁስ አለመሟላት ምክንያት ውጤታቸው እንዳይቀንስ በትኩረት ተሠርቷል፡፡
የክልሉ መንግሥት የሰላም ሁኔታው እንዲሻሻል የሚያደርጉ ሥራዎችን ከመሥራት ጎን ለጎን የመማሪያ ክፍል ገጽታዎችን ማሻሻል ላይ በትኩረት ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በዚህም አራት ሺህ 279 መማሪያ ክፍሎች በአዲስ መገንባታቸውን አቶ አረጋ አስታውቀዋል፡፡ ይህም የዕቅዱ 72 ነጥብ ሁለት በመቶ ነው፡፡
በሪፖርቱ እንደተመላከተው 16 ሺህ 647 መማሪያ ክፍሎችን መጠገን ተችሏል፡፡ በዓመቱ 57 ሺህ 223 መቀመጫ ወንበሮች (ኮምባይንድ ዴስክ) ማቅረብ ተችሏል፡፡ ይህም ለማቅረብ ከታቀደው አኳያ የ59 በመቶ ድርሻ ያለው ነው፡፡
ሕዝቡ መንግሥት የሰላም ችግሩን እንዲቀለብስለት ከመጠየቅ ባሻገር ለትምህርት ሥራው መሻሻል የነበረው አበርክቶ ከፍተኛ እንደነበር ርእሰ መሥተዳድሩ ገልጸዋል፡፡ በ2017 ዓ.ም በ11 ወራት ውስጥ አንድ ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር መሰብሰቡ ለሕዝቡ ተሳትፎ ቁርጠኝነት ማሳያ አድርገው አንስተዋል፡፡
ርእሰ መሥተዳድሩ እንደገለጹት የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በሁሉም የክፍል ደረጃዎች ያለውን የመማሪያ መጻሕፍት ጥምርታ አንድ ለአንድ ለማሳካት በትኩረት ሲሠራ ቆይቷል፡፡ እስካሁንም 30 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን መጻሕፍትን ማሰራጨት ተችሏል፡፡
በቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያለው የተማሪ መጻሕፍት ጥምርታን አንድ ለአንድ ማዳረስ መቻሉን ለግቡ ስኬት ማሳያ በማድረግ አንስተዋል፡፡ በአንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያለውን የተማሪ መጻሕፍት ጥምርታ አንድ ለሁለት ማዳረስን እንደ ግብ ተይዞ ሲሠራ መቆየቱን እና ይህንንም ማሳካት እንደተቻለ ነው አቶ አረጋ የጠቆሙት፡፡
የሰላም ችግሩ በትምህርት እንቅስቃሴ ላይ እያሳደረ ያለው ጫና ቀጣይነት እንዳይኖረው ከወዲሁ መረባረብ እንደሚገባ ርእሰ መስተዳደሩ አሳስበዋል፡፡ ትምህርት የማንኛውም ፖለቲካ ፍላጎት ማስፈጸሚያ መሣሪያ እንዳይሆን መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በትምህርት ሥራው ላይ ያጋጠመውን ፈተና በፍጥነት በመሻገር የትውልድ ቅብብሎሽን ለማስቀጠል የመንግሥት መዋቅሩ እና ሌሎች የሚመለከታቸው የትምህርት ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሠሩ እንደሚገባም አስታውቀዋል፡፡
በአዲሱ ዓመት በትምህርት ዘርፉ የተቃጣው አስነዋሪ ድርጊት ቆሞ ትምህርት ለትውልድ ቅብብልሾ የሚያበረክተው ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከወዲሁ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት መሥራት እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳደሩ አሳስበዋል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት በመሻገር የትውልድ ቅብብሎሹን ለማስቀጠል የትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት በትኩረት መሥራት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ግብዓትን ከወዲሁ ማሟላትም ለዓመቱ ትምህርት የተሻለ አፈጻጸም ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡ የትምህርት መሠረተ ልማትን ማሻሻል ይገባልም ነው ያሉት፡፡
ብቁ እና ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት ቅድመ አንደኛ ደረጃ ላይ መሥራት ላይ ማተኮር እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ ኅብረተሰቡ ለትምህርት የሚያደርገውን ተሳትፎ እንዲያሳድግ የሚያደርጉ ሥራዎች ላይም ትኩረት እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡
አማርኛ በአማርኛ
ቃጤ – ከቁና አነስ ያለ የእህል መስፈሪያ
ቅርቅፍት – ወጣ ገባ መንገድ
ቅርንጥስ – የተጣጣፈ አሮጌ ጨርቅ፤
ቅፍለት – ተከታትሎ የሚጓዝ የነጋዴ ግመል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የሐምሌ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም