ሀያዎቹ!

0
69

መንፈሳዊ መጻሕፍት ዕድሜን ከተፈጥሮ ጋር አዛምደው ያቀርቡታል። ልጅነትን በነፋስ፣ ወጣትነትን በእሳት፣ ጎልማሳነትን በውኃ፣ አዛውንትነትን በመሬት መስለው ይገልጹታል። “ወጣት የነብር እጣት”  የሚለው የአበው ብሂል ይህ ዕድሜ ምን ያህል ጥንቃቄ የሚፈልግ እንደሆነ ያሳያል። እሳት የጥቅሙን ያህል ጉዳቱም አይጣል ነው። የብዙዎች ሕይወት መሠረቱ የሚጣለው በዚህ የእሳትነት ዕድሜ መጀመሪያ ሀያዎቹ ውስጥ ነው።

በዕድሜ የገፉ ሰዎች ወደ ኋላ ተመልሰው ማስተካከል ቢችሉ፤ እሠራበታለሁ ወይም ተሳስቼበታለሁ የሚሉት   እሳት ያለበትን የሀያዎቹን ትኩስ ወጣትነት ዕድሜ ነው።

 

በሀገራችን በአብዛኛው የ20ዎች ዕድሜ ድንገት ያልፋል። አሁን እኔ 30ዎች ውስጥ ገብቻለሁ።  ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ሥራ ላይ ነኝ። በሚያሳዝን መልኩ ይህ ዕድሜ  እንዴት እንደ ነፋስ እንደፈጠነብኝ የገባኝ ከሦስት ዓመታት በፊት ነበር። ሕይወት መብላት፣ መጠጣት፣ ተቀጥሮ መሥራት፣ ማግባት፣ መውለድ እና መሞት ይመስለኝ ነበር። እንዲያውም የምሞት አይመስለኝም ነበር።

 

አሁን ነው ሸምገል ያሉ ሰዎችን ሳይ ራሴን በማሰብ ማዘን እና ዕድሜ ቀልድ እንዳልሆነ የገባኝ። ይህን ጽሑፍ ሀገራዊ ቅርጽ ሰጥቼ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በማሳየት ነው የማቀርበው። የእኔ እና የሌሎች ጓደኞቼ የዕድሜ አረዳድ ችግር ያለበት ነው። የት እንደምሄድ ሳላውቅ ከዩንቨርስቲ ወጥቻለሁ። ወቅቱ ረድቶኝ ሥራ አገኘሁ። ሀያዎቹን  በቀልድ፣ በወሬ፣ በልማዳዊ ኑሮ፣ በአቅጣጫ ቢስ ሕይወት፣ ፈታ በማለት ጨርሻለሁ። ዕድሜ ቁጥር ብቻ  አይደለም። ዕድሜን ተከትለው የሚመጡ ኃላፊነቶች አሉ። ትዳር ይጀመራል። ልጅ ይመጣል። እነዚህ ነገሮች ትልቅ ትኩረት የሚፈልጉ ናቸው። በሠላሳ ዓመቱ ትዳር የሚጀምር ተቀጣሪ ወንድ ምን ዓይነት ሕይወት ይኖረዋል?

 

ሰዎች በሠላሳ ዓመት ዕድሜያቸው የተረጋጋ ገቢ፣ ሥራ፣ ሕይወት ሊኖራቸው የሚገባበት ጊዜ ነው። የሀገራችን እውነት ሌላ ነው። አንድ ታዳጊ ወጣት በሀያ ዓመቱ የኮሌጅ እና ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ያጠናቅቃል። ሥራ ፈልጎ ያገኛል። ሥራ ካለህማ ሚስት አግባ ይባላል፤ ያገባል። ልጅ እና ሚስቱን በበቂ ሁኔታ ማስተዳደር አይችልም። ትክሻው ይጎብጣል፤ ይቸገራል። ትልልቅ ሐሳቦችን ከማሰብ ይልቅ በልቶ ማደር እና ምናልባትም ከተሳካለት ለልጆቹ ቤት ሰርቶ ማለፍን ግቡ አድርጎ ይኖራል። በትንንሽ ድርጊቶች እና ሐሳቦች ይጠመዳል።

 

ያስተማሩት ወላጆቹን መደገፍ እና እንደ ሀገራችን ልማድ፤ ውለታ መመለስ ሲገባው ጤፍ ላኩልኝ የሚል ይሆናል። መሮጥ፣ ማሳካት፣ ማግኘት፣ መሆን የሚችልበት ሀያዎች ዕድሜ ሳይታወቅ አልፏል። ሥራ መቀየር ይፈልጋል ሚስቴስ፣ ልጆቼስ? ይላል። የተሻለ ሥራ ለመሥራት ይመኛል ገንዘብ ያጥረዋል። ያን ጊዜ እንደ አባቶቹ “ኧረ ልጅ ማሰሪያው ኧረ ልጅ ገመዱ፤ ጎጆማ ምን ይላል ጥለውት ቢሄዱ” ብሎ መብሰልሰል ይጀምራል። ልጅ ሀብት መሆኑ ቀርቶ መታሰሪያ ገመድ ይሆናል። አባቱ የጠላውን የድህነት ውርስ ልጁ መጣል ሲገባው ፊደል የቆጠረ ደሀ ይሆናል። ለልጆቹ ያንን ድህነትን ያወርሳል።

 

ዶክተር ሜግ ጄይ የተባለች ክሊኒካል ሳይኮሎጂስት “ዘ ዲፋይኒንግ ዲኬድ” በሚል ሀያዎቹ ውስጥ ያሉ አስር ዓመታት በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ ያላቸውን ጉልህ ሚና በመጽሐፍ አስቀምጣለች።

ብዙ ሰዎች የሀያዎቹን አስር ዓመታት መዝናኛ እና መቀለጃ አድርገው ማሳለፋቸውን በመኮነን ትጀምራለች። አንዳንዶች የሀያዎቹን ዕድሜ ለውጥ እና ዕድገት ሲጠቀሙበት ብዙዎች ማባከናቸው ጉዳቱ የሚያሳዝን ስለ መሆኑም ትናገራለች።

 

ጄይ  የሀያዎቹ ዕድሜ ለምን የሕይወት መሠረት እንደሆነ ትናገራለች። እሷ እንደምትለው በአሜሪካ 80 በመቶ የሚሆኑት ወሳኝ የሚሆኑት የሕይወት ክስተቶች በአማካይ በ35 ዓመት ዕድሜ ይከናወናሉ። ከግማሽ በላይ አሜሪካውያን በ30 ዓመት ዕድሜያቸው የወደፊት ትዳር አጋራቸውን አግብተው መኖር ይጀምራሉ።

ሌላው ጄይ የምትጠቅሰው ጉዳይ የአንጎል ዕድገት ጉዳይ ነው። “አንጎላችን ለጎልማሳነት ራሱን የሚያስተካክልበት  ሁለተኛው ጊዜ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ያልቃል” ብላለች። የሰው ልጆች የፊተኛው የአንጎል ክፍል (ፍሮንታል ሎብ) የሚያድገው እስከ 25 ዓመት ነው። ይህ የአንጎል ክፍል  የምክንያታዊነት ማዕከል ነው። 25 ዓመት ካለፈ በቀላሉ መለወጥ፣ መሻሻል፣ መማር ከባድ ይሆናል። በሀያዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚለወጥ ሰብዕና በጥሩ ወይም በመጥፎ ዕድሜ ልክ የመከተል ባህሪ አለው።

የሰው ልጆች በመጀመሪያው የሥራ ሕይወታቸው አስር ዓመታት የሚያገኙት ገንዘብ በቀሪው ዘመናቸው ከሚያገኙት በላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳውም ገልጻለች።

 

የሴት ልጅ የመውለድ አቅም በጣም ትክክለኛው ስነ ሕይወታዊ ጊዜ 28 ዕድሜ ላይ ነው። ከ35 ዓመታት በኋላ እየቀነሰ ይመጣል። በቸልተኝነት የባከነውን ሀያዎቹን ለማካካስም “ሴቶች በዚህ ጊዜ ሁለት ወይም ሦስት ልጆችን ለመውለድ  መሮጥ የሚጀምሩበት ነው” ስትል ጄይ ትናገራለች። በዚህ ምክንያት ሴቶች ሠላሳዎች ዕድሜ ውስጥ ከፍተኛ ጫና  ውስጥ ይገባሉ።  ሠላሳዎች እና አርባዎች ውስጥ የሚገኙ ሴቶች “ምን እየሰራሁ ነበር፣ ምን እያሰብሁ ነበር” ብለው ራሳቸውን አንደሚወቅሱ ባለሙያዋ ተናግራለች።

 

በሀያዎቹ ዕድሜ የምንይዛቸው ጓደኞች የወደፊት ሕይወታችንን የመወሰን ዕድላቸው ትልቅ ነው። በሀያዎቹ ዕድሜ የኖርንበት ቦታ የአኗኗር ዘይቤያችንን ይቀይሰዋል። በዚህ ዕድሜ የያዝናቸው የፍቅር አጋሮች መቼ፣ እንዴት እና ማንን እንደምናገባ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። በእነዚህ ዓመታት የምንሠራቸው ሥራዎች ለወደፊት የሥራ ሕይወታችን በር ይከፍታል ወይም ይዘጋሉ። የምንወስናቸው ገንዘብ ነክ  ውሳኔዎች የወደፊት ሕይወታችንን ያረጋጋሉ ወይም አደጋ ያመጣሉ።

 

የዚህ ዘመን ሰብዕናችን አቀራረጽ በእርጅና ዘመናችን የሚኖረንን የአዕምሮ ሰላም ይወስነዋል። ለስኬት የምንሰጠው አመለካከት  እውነተኛ ደስታ ወይም ኀዘን ይሰጠናል። በሀያዎቹ ዕድሜ መልካም ሰው መሆናችን በቀሪው ሕይወታችን መልካም ስምን ያጸናል።

እናም ጄይ “በከፍተኛ ደረጃ ሕይወታችን የሚወሰነው እየተከሰቱ መሆናቸውን ልብ በማንላቸው እጅግ ትልቅ ተጽዕኖ ባላቸው የሀያዎቹ ዓመታት ነው” ነው እንዳለችው ነው።

 

በግል ምልከታየ እና ሕይወቴ እንዳየሁት አፍላ መሥሪያ እና መማሪያ ዕድሜያችን መዝናኛ ሆኖ አልፏል። የሰለጠነው ዓለም ሀያዎቹን የእውቀት እና ሀብት መፍጠሪያ ያደርገዋል። እኛ ደግሞ መዝናናቱን ስንጨርስ ወደ መኖር ፊታችንን ጨፍጋጋ አድርገን እንገባለን። ሳንሰራ ከወላጆች ብር ተቀብለን እንዝናናለን። የእኛ ጊዜ ሲመጣ በሕይወት ጥያቄዎች ተሞልተን ትክሻችን ይጎብጣል። ሌላው ዓለም ገንዘብ ሠርቶ ይዝናናል። ለዚህ ማሳያ ቢሊየነሩ ቢልጌትስ ያለውን ሐሳብ ልጥቀስ። “በሀያዎች የዕድሜ ክልል በጣም በጣም ጥንክሬ ሠርቻለሁ። ለዚህ ነው አሁን ሚዛናዊ ሕይወት የምኖረው” ነበር ያለው።

 

ቢሊየነሩ ጃክ ማ “ከሀያ እስከ ሠላሳ ዓመት ዕድሜህ ነገሮችን በአግባቡ መሥራትን  ለመማር ጥሩ ኩባንያ ተቀላቀል። ጥሩ አለቃህን ተከተል” ይላል። ሀያዎች ዕድሜ ለነገ ስንቅ የሚሆን እውቀት ማግኛ ነው። ይህ ፍሬ የሚያፈራው ሠላሳዎች ውስጥ እና በኋላ ሊሆን ይችላል። አርባዎች ዓመታት  ቀደም ብለን በሀያዎች የዘራነውን የምንበላበት ነው። የመረጋጋት ዘመን ነው። ሀምሳ ዓመት መዝናኛ ነው። የተከማቸ ሀብት እየተመነዘረ የሕይወት ትርጉም እና አሻራ ማስቀመጥ ላይ የሚሠራበት ነው። ሽርሽር፣ ቦታዎችን መጎብኘት፣ ተፈጥሮን መመርመር፣ ሰው መርዳት እና ሌሎች ተግባራት ከዚህ ዕድሜ በኋላ ይመጣሉ። ከራስ በላይ ለሰው የምናስብበት እና የምንሰራበት ዕድሜ ይመጣል።

 

ፈላስፋው ካርል ዩንግ “ሕይወት ከ40 ዓመት በኋላ ይጀምራል፤ ከዚያ በፊት ያለው ምርምር እና ጥናት ነው” ያለው ሐሳብ  ለእኛም መሥራት ያለበት ነው። በሀያዎች ተዝናንተን በ50ዎች ከቤተሰቦቻችን ጋር የምንጎሳቆል ለምን እንሆናለን?

 

በመጨረሻም “ኢፍ ዩ ዎንት ቱ ቼንጅ ዘ ወርልድ  ዱ ኢት ዋይል ዩ አር ሲንግል፤ ዋንስ ዩ ሜሪድ ኢቭን ዩ ካንት ቼንጅ ዘ ቲቪ ቻናል” የምትባል ሐሳብ ጠቅሼ ልጨርስ። ዓለምን እቀይራለሁ ብለህ የምታስብ ከሆነ በላጤነትህ አድርገው፤ካገባህ በኋላ እንኳንስ ዓለምን የቴሌቪዥን ቻናልህን መቀየር አትችልም እንደማለት ነው።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የሐምሌ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here