የእንስሳት አፍቃሪዎች ቁጣ

0
63

በቻይና የሊያኒንግ ከተማ ኗሪው  ውኃ በተሞላ የኘላስቲክ  ሳጥን ህይወት ያላቸውን ዓሣዎች ይዞ ሲያሽከረክር፤ በተመለከቱ እንስሳት አፍቃሪዎች ዘንድ ቁጣ መነሳቱን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ  ለንባብ አብቅቶታል፡፡

“የኤል9” ቅንጡ የቤት መኪናዋ ባለቤት በተሽከርካሪው የፊት  “ኮፈን” ላይ በተገጠመ የኘላስቲክ ሳጥን መጠናቸው  ከፍ ከፍ ያሉ ዓሣዎችን ይዞ እንደተንቀሣቃሽ የዓሳ ገንዳ ማሽከርከሩ ጨካኝነቱን ያሳያል ሲሉ ነው የከሰሱት – የእንስሳት አፍቃሪዎች፡፡

የቻይናዊውን ተሽከርካሪ በማህበራዊ ሚዲያ የተመለከቱ በሰው ሰራሽ ክሂሎት የተቀናበረ ቢመስላቸውም ባለስልጣናቱ የተቀናበረ ሳይሆን  እውነተኛ መሆኑን ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡

 

ግለሰቡ ለቀረበበት ክስ  ምላሽ ዓሣ ለማጥመድ በሄደበት ወቅት መያዣ እቃ ስላልነበረው በአጋጣሚ በተሽከርካሪው ላይ ባለ ባዶ ኘላስቲክ ሣጥን ውኃ ሞልቶ ዓሣዎቹን እንዳኖረበት አስረድቷል፡፡

ብልሀተኛው ቻይናዊ አሽከርካሪ በወቅቱ ለችግሩ ጥሩ መፍትሄ የዘየደ ቢመስለውም ወደ ከተማ ሲገባ ከተመልካቾች ቁጣ፣ ትችት ማስተናገዱን  ተናግሯል፡፡ ከሁሉም በላይ ተሽከርካሪዋ በተመልካቾች ተቀርፃ በማህበራዊ ድረ ገጽ በመታየቷ ቁጣ እና  ጭካኔውን የሚመጥን  እርምጃ እንዲወሰድበት የሚጠይቅ መረር ያለ አስተያየት አጋርተዋል – ተመልካቾች፡፡

 

ተመልካቾቹ ባነሱት የክስ ሀሳብ በመጀመሪያ ደረጃ የኘላስቲክ ሳጥኑ የተሽከርካሪው ሞተር በሚገኝበት “ኮፈን” ላይ በመገጠሙ ውሀውን ሊያሞቀው ወይም ሊያፈላው ስለሚችል ዓሣዎቹን ያሰቃያል ሲሉ ሞግተዋል፡፡ ከዚህም በላይ የኘላስቲክ ሳጥኑ ጠባብነት ዓሣዎቹን አጨናንቋል፤ ፍጥረታቱን በነፃነት የሚያኖር አይደለም ሲሉ ያስቆጣቸውን የክስ ሀሳብ አዳብረዋል።

 

በጥቂት ቀናት ውስጥ ማህበራዊ ድረ ገፆችን ያጨናነቀው የዓሣዎች ጉዳይ፤  የሊያኑንግ ከተማ ትራፊክ ፓሊስንም ትኩረት ስቧል፡፡

የከተማዋ ትራፊክ ፓሊስ የባለንብረቱን ተሽከርካሪ ገምግሟል፣ ፈትሿል፤ በደረሰበት ማጠቃለያም ግለሰቡ ለዓሣ መያዣ የተጠቀመበትን የኘላስቲክ  ሳጥን ይዞ ህዝብ በሚበዛበት አውራ ጐዳና ላይ ለማሽከርከር ብቁ አለመሆኑንም ነው የጠቆመው፡፡

ግለሰቡ ላይ የተወሰደው ርምጃ ወይም የተወሰነበት ቅጣት በድረ ገጹ ይፋ ባይሆንም በፓሊስ በኩል ተሽከርካሪዋ ላይ የተገጠመው የዓሣ መያዣ ህገወጥ መሆኑ ነው የተገለጸው።

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የሐምሌ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here