የዓየር ብክለት የመተንፈሻ አካላትን ብቻ ሣይሆን የአዕምሮ ጤናን በማወክ በጤና ላይ የከፋ ጫና እንደሚያሳድር ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ለንባብ አብቅቶታል፡፡
በእንግሊዝ የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች ባደረጉት ምርምር እንዳረጋገጡት ከተሽከርካሪ እና ከፋብሪካዎች የሚለቀቀው በካይ ጢስ ከባቢ አየርን በመበከል የአዕምሮ ህመም ተጋላጭነትን ይጨምራል፡፡
የአዕምሮ ጤና ችግር የሆነው የመርሳት በሽታ ወይም “አልዛሂመር” በ2025 እ.አ.አ በዓለማችን 57 ነጥብ አራት ሚሊዮን ሰዎችን እንዳጠቃ ግመታቸውን ይፋ አድርገዋል። በ2050 እ.አ.አ የተጠቂዎቹ ቁጥር ሦስት እጥፍ አድጐ 152 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሊደርስ ይችላል ሲሉ ነው ያሳሰቡት፡፡
በተመራማሪዎቹ የተደረገው ግምገማም በአየር ብክለት እና በአዕምሮ ጤና መናጋት መካከል ያለውን አሳሳቢ ግንኙነት አጉልቶ ያመላከተ መሆኑም ነው የተጠቆመው፡፡
ከሁሉም በላይ የአየር ብክለት በጣም ደቂቅ ለሆኑ እና ጥቀርሻን ለመሳሰሉ በካይ ትነቶች ዳርጐ የአዕምሮ ህመም ተጋላጭነትን እንደሚጨምር ደርሰውበታል፡፡
ግኝቱ የአየር ብክለትን መሰረት አድርጐ ከ29 ሚሊዮን መረጃ ሰጪዎች የተሰበሰበ ምላሽ እና ከተካሄዱ 34 ጥናቶች ውጤት የተቀመረ ነው፡፡ በዚሁ መሠረትም ጥቃቅን በዓይን የማይታዩ የብክለት መንስኤዎችን መጠን በመጨመር በከተማ እና በአቅራቢያው የጤና ችግርነቱ ጐልቶ መከሰቱን ነው ያሰመሩበት – ተመራማሪዎቹ፡፡
ከተሽከርካሪ እና ፋብሪካዎች የሚለቀቅ በካይ ጢስ ከመተንፈሻ አካላት አልፎ ወደ ደምስር በመግባት በጭንቅላት ውስጥ የደም ዝውውርን በማገድ ለአዕምሮ ጤና እክል፣ ከሁሉም በላይ ለመረሳት በሽታ እንደሚዳርግ ተገልጿል።
ጥናቱ በአብዛኛው ከፍተኛ እና መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት የተሰበሰበ መረጃን መሰረት ያደረገ መሆኑን የጠቀሱት ተመራማሪዎቹ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሃገራት ውጤቱ ሊለያይ እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡
በአጠቃላይ ሁነቱ የህዝብ ጥያቄ ሊያስነሳ እንደሚችል የተጠቆመ ሲሆን አልፎም ለእድሜ ልክ የመርሳት አደጋ ሊዳርግ፣ ለታዳጊ እና ህፃናትም ዳፋው የከፋ እንደሚሆን ተጠቁሟል።
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሐምሌ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም