የሳናኔ ደሴት ብሔራዊ ፓርክ በታንዛኒያ ኃይቅ ላይ ባለ ባህረ ሰላጤ ይገኛል፡፡
ሳናኔ ደሴት ስያሜውን ያገኘው ሳናኔ ቻ ዋንዲ ከተሰኘ ዓሣ አጥማጅ ቀዳሚ ባለይዞታዋ ነው፡፡ በኋላም መንግሥት ለባለይዞታው ካሳ በመክፈል በ1964 እ.አ.አ የመጀመሪያው የመንግሥት መካነ እንስሳት አድርጐ ከልሎታል፡፡
የፓርኩ የመጀመሪያ ልኬታ ዜሮ ነጥብ ሰባት ካሬ ኪሎ ሜትር ነበር፤ ኋላ ላይ ሳናኔ ብሔራዊ ፓርክ በስተደቡብ የሚገኙ ሁለት ትንንሽ ደሴቶችን አካቶ ስፋቱ ወደ አንድ ነጥብ 32 ኪሎ ሜትር ስኬዌር ሊያድግ ችሏል፡፡
የፓርኩ ምስረታ የዱር እንስሳት ጥበቃን በቪክቶሪያ ኃይቅ ለሚገኘው የሙዋንዛ ወደብ ኗሪዎች ለማስተማር እና መዝናኛነቱን ለማስተዋወቅ ነበር፡፡ በ2013 እ.አ.አ ቀጣናው ወደ ፓርክነት ሲያድግ ሁለት ነጥብ 20 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ተለክቷል፡፡
ፓርኩ በቅርበት ከምትገኘው የሙዋንዛ ከተማ ደቡብ ዕራብ ሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የተከለለው፡፡ ወደ ፓርኩ ለማምራትም በዓየር ማጓጓዣ ከዳሬሰላም ወይም ከኪሊ ማንጃሮ ዓየር ማረፊያ በአውራጐዳና ከአሩሻ፣ ዳሬሰላም፣ ኪጐማ፣ ታቦራን መነሻ ማድረግ ይቻላል፡፡
ሳናኔ ደሴት ፓርክ በጃልባ፣ በእግር በመንቀሳቀስ በቪክቶሪያ ኃይቅ ላይ የሚገኙ ዓእዋፍን ለመመልከት፤ ፎቶ ግራፍ ለመነሳት፣ የቪዲዮ ቀረፃ፣ ለሰርግ፣ ለልደት የተለያዩ ዝግጅቶችን ለመከወን ተመራጭ ነው፡፡
በሳናኔ ደሴት ብሔራዊ ፓርክ ከ40 በላይ የዓዕዋፍ ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡፡ ዓእዋፉን ለመመልከት ከህዳር እስከ መጋቢት ያሉት ወራት ይምከራሉ፡፡
ከሰኔ እስከ ነሀሴ ደረቅ ወቅት በመሆኑ ለመዝናናት አቀበት ቁልቁለቱን ለመመልከትም ይመረጣል፡፡
በፓርኩ ከሚገኙ የዱር እንስሳት ቀጭኔ፣ የሜዳ አህያ፣ ከርከሮ፣ የሜዳ ፍየል፤ ከተሣቢ -ዓዞ እና የተለያዩ የእባብ ዝርያዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በፓርኩ ክልል ለጐብኚዎች ጊዜያቸውን ለማርዘም የሙዋንዚ ሴረን ሆቴል፣ ኪሊማንጃሮ ሆቴል፣ ሴዳር ሆቴል ሙዋንዛ እና የሳናኔ ደሴት ማረፊያ ሰፈር በማስተናገጃነት ያገለግላሉ፡፡
ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ታንዛኒያ ቱሪዝም፣ ሳናኔ ብሐራዊ ፓርክ ድረገፆችን እንዲሁም ዊኪፒዲያን ተጠቅመናል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሐምሌ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም