‘በመትከል ማንሰራራት’ በሚል መሪ መልዕክት በመላው ኢትዮጵያ የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡ ሐምሌ 24 ቀን 2017 ዓ.ም በተካሄደው መርሃ ግብር 700 ሚሊዮን ችግኞችን መትከልን ያለመ ነበር፤ ከ714 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ከዕቅዱ በላይ በመፈጸም በስኬት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡
294 ነጥብ አንድ ሄክታር መሬት ላይ ተከላ መካሄዱንም ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡ በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩም 29 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሕዝብ መሳተፉን ነው ያስታወቁት፡፡
በዕለቱም የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ አረንጓዴ አሻራቸውን በኮምቦልቻ ቱሉ አዳሜ አስቀምጠዋል፤ “የአየር ንብረት መዛባት ይፈትናት የነበረችው ኢትዮጵያ ዛሬ በአረንጓዴ አሻራ እየተፋለመችው ነው” ብለዋል፡፡ የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለረጅም ጊዜ የሚተገበር የስትራቴጂ አካል መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
የአየር ንብረት መዛባት የዓለም አንደኛው ችግር መሆኑን ያነሱት ርእሰ መስተዳድሩ ኢትዮጵያም ስትፈተን መቆየቷን ተናግረዋል፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥን ለማስተካከል ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የሐምሌ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም