“ዳኙ ገላግለን!…” – ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ

0
43

“ዳኙ ሊመታ ነው!… ዳኙ ገላግለን!…ወይኔ ዳኙ አገባ!… ደንሶ አገባ ዳኙ!… ቀኝ አሳይቶ ግራ!… ግራ አሳይቶ ቀኝ!… በጣም አስደናቂ ግብ ነው!… ሕዝቡ ወደ ሜዳ እየገባ ነው!… ተመልካቹም እንደተመኝኋት አገኝኋት እያለ ነው!… ችቦ በራ!… ስቴዲየሙ ተንቀለቀለ!…”

ይህ ድምጽ ከ37 ዓመታት በፊት ታህሳስ 17 ቀን 1980 ዓ.ም ኢትዮጵያ የምሥራቅ እና የመካከለኛው አፍሪካ ዋንጫን ስታነሳ ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ ያስተጋባው ድምጽ ነው። ይህም በእግር ኳስ ታሪክ ከብዙ የእግር ኳስ አፍቃሪ ጆሮ  የማይጠፋ ድምጽ ነው።  ድምጹም በብዙ የስፖርት መሰናዶዎች ዘንድ መግቢያ ወይም ማጀቢያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። ደምሴ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ እንዲታወስ ካደረጉት ዘገባዎች መካከልም ይህ ክስተት ትልቁን ድርሻ ይይዛል።

 

ከአሥራ ሦስት ዓመታት እድሜው ጀምሮ ለስፖርት ጋዜጠኝነት ልዩ ስሜት እና ፍቅር ነበረው፤ ለአብዛኞቹ የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች አርአያም ተመሳሌትም ነው። ኢትዮጵያ የ15ኛውን የምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ ስታነሳ በደስታ ፈንጥዟል። ብርቅዬ አትሌቶቻችን በአራቱም የዓለም ማዕዘን የሀገራቸውን ሰንደቅ አላማ ከፍ ሲያደርጉ የደስታ ሲቃ እየተናነቀው ዘግቧል። ከሞስኮ እስከ ባርሴሎና፣ ከአትላንታ እስከ ሲዲኒ፣ ከአቴንስ እስከ ቤጂንግ ኦሎምፒክ የአትሌቶቻችንን ድል ለሕዝቡ አብስሯል።

ደምሴ ዳምጤ የአትላንታን፣ የአቴንስን እና የቤጂንግ ኦሎምፒክን ቦታው ድረስ በመጓዝ በሬዲዮ ለሕዝብ ጆሮ አድርሷል። በተጨማሪም  ሦስት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን ቦታው ድረስ ተጉዞ ዘግቧል። አትሌት ምሩጽ ይፍጠር እ.አ.አ በ1980 በሞስኮ ኦሎምፒክ በአምስት እና አስር ሺህ ርቀት ድርብ ድል ሲቀዳጅ ድሉን ያበሰረው ደምሴ ዳምጤ ነው። ከጭላሎ ተራራ ግርጌ  ያስተጋባው  የደምሴ ድምጽ  ኃይሌ ገብረ ስላሴን ወደ ሩጫው ዓለም እንዲገባ ምክንያት ሆኖታል።

 

በሊቢያ የተዘጋጀውን 13ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ በቀጥታ በሬዲዮ በማስተላለፍ  በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ የመጀመሪያው የስፖርት ጋዜጠኛ ነው። የስፖርት የቀጥታ ስርጭትን ወደ ላቀ ምዕራፍ ያሸጋገረ የለውጥ ፈር ቀዳጅ ጋዜጠኛ ነው። እስካሁን ድረስ የማይረሱ በርካታ ስፖርታዊ ሁነቶችን እና ክስተቶችን ለአድማጭ ተመልካች አድርሷል።

በስፖርቱ ምክንያት ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፏል፤ ብዙ ዋጋም ከፍሏል። ስቴዲየሞች በእግር ኳስ ተመልካቾች ጢም ብለው ሲሞሉ እና ኦና ሲሆኑ ተመልክቷል። የብሄራዊ ቡድናችን ተጫዋቾች ከሀገር ወጥተው አንመለስም ሲሉ፣ በተደጋጋሚ የብሄራዊ ቡድኑ ሽንፈት እና በፌዴሬሽኑ አመራሮች አለመግባባት ምክንያት ብሄራዊ ቡድኑ በፊፋ ቅጣት የአልጋ ቁራኛ ሆኗል። ጉምቱው ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ ለ40 ዓመታት ያህል ስለስፖርት እና ስፖርተኞች ብቻ ሲያወራ ኖሯል።

 

የታላቁ ጋዜጠኛ የሕይወት ታሪክ ከዚህ ይጀምራል። ደምሴ ዳምጤ በምሥራቅ ኢትዮጵያ ክልል በሐረርጌ ክፍለ ሀገር ልዩ ስሟ “ግራዋ” በተባለች አነስተኛ ከተማ በ1945 ዓ.ም ተወለደ። ደምሴ ዳምጤ በጋራ ሙለታ ግራዋ ከተማ ተወለደ እንጂ ያደገው ግን በድሬዳዋ ከተማ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትንም በድሬዳዋ ራስ መኮንን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጨርሷል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በከዚራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቋል።

ደምሴ ገና በለጋ እድሜው ተሰጥኦውን ፈልጎ በማገኘት የጋዜጠኝነትን ሙያ ተቀላቅሏል። ክብርን፣ ተወዳጅነትን እና ዝናን ያጎናጸፈው የስፖርት ጋዜጠኝነት ፍላጎት ያደረበት ገና የ13 ዓመት ታዳጊ እያለ እንደነበር ከኢትዮጵያ ሬዲዮ ያገኘነው መረጃ ያሳየል። በሙያው ልቆ ይታይ ዘንድ የጋዜጠኛ ሰለሞን ተሰማ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር።

 

የጋዜጠኝነት ህይወቱን ለማሳደግ ከአባቱ በሚሰጠው ገንዘብ ጋዜጣ በመግዛት ያነባል። ድምጹን ከፍ አድርጎ እንደ ሰለሞን ተሰማም በማንበብ ይለማመድ ነበር ተብሏል። እንዲሁም በልጅነቱ ከአባቱ ጋር ድሬዳዋ ስቴዲየም በመግባት ጨዋታዎችን የመመልከት ዕድል እንደነበረው የግል የታሪክ ማህደሩ ያስረዳል። ይህም ስኬታማ እና ታላቅ የስፖርት ጋዜጠኛ እንዲሆን አስችሎታል።

ከኢትዮጵያ ሬዲዮ የሚሰማቸውን ዘገባዎችም በትምህርት ቤት ውስጥ በእረፍት ሰዓት ለተማሪዎች ያቀርብ ነበር። ዘገባዎችን በመስማት ከሚወዱት ሰዎች መካከል መምህሩ የነበሩት እና በወቅቱ የሐረርጌ ክፍለ ሀገር የስፖርት መምሪያ ስፖርተኛ የነበሩት አቶ መላኩ ወልደሰማያት ነበሩ። እርሳቸውም የታዳጊውን ተሰጥኦ ዐይተው በመረዳት ከታዋቂው የስፖርት ጋዜጠኛ ሰለሞን ተሰማ ጋር አስተዋውቀውታል። ጋዜጠኛ ሰለሞን ተሰማ ታዳጊውን  አንድ የስፖርት ዘገባ ሠርቶ በፖስታ እንዲልክላቸው ያዝዙታል።

 

ደምሴ ዳምጤ የምሥራቅ በረኛ ፖሊስ  እና የድሬዳዋ ሲሚንቶ ያደረጉትን ጨዋታ ተመልክቶ ዘገባ ሠርቶ ይልክላቸዋል። ለኢትዮጵያ ሬዲዮ የላከው የመጀመሪያ ዘገባም መስከረም 12 ቀን 1962 ዓ.ም ተላልፏል። ይህም የዝነኛው ጋዜጠኛ ማርሽ ቀያሪ ክስተት እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮም በተከታታይ ሰባት ዓመታት በነጻ በድሬዳዋ የሚከናወኑ የስፖርት ሁነቶችን በመዘገብ ለኢትዮጵያ ሬዲዮ አድርሷል። በ1968 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሬዲዮ በቋሚነት በመቀጠር ወደ አዲስ አበባ ተዘዋውሯል።

ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤን በሬዲዮ መስማት ሜዳ ውስጥ በቀጥታ ጨዋታን ከመከታተል ያልተናነሰ ልብን ያሞቃል። ጋዜጠኛ ደምሴ ጥልቅ የሀገር ፍቅር የነበርው ባለሙያ ነው። ፍቅሩንም በሥራው በነበረው ትጋት አስመስክሯል።

ለሙያው የተሰጠ እና ራሱንም ለሙያው የሰጠ ጋዜጠኛ ነው። እ.አ.አ በ1992 በባርሴሎና ኦሎምፒክ ደራረቱ ቱሉ አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ ማጥለቋን ታሪክ ያወሳል:: ይህም በአህጉራችን በሴቶች የኦሎምፒክ ውድድር የመጀመሪያው ወርቅ በመሆን በታሪክ መዘገብ ሰፍሯል:: ውድድሩን በእኩለ ሌሊት የተከታተለው ደምሴ ተኝቶ እስኪነጋለት መታገስ አልቻለም።

 

ይህንን ዜና ለሕዝብ ለማድረስ ደምሴ ዳምጤ በወቅቱ  ከነበረው ከምኒልክ ሆስፒታል ወረድ ብሎ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ጣቢያ ወደ ሚገኝበት አቡነ ጴጥሮስ   ከጅብ ጋር ተጋፍቶ በእግሩ በመጓዝ በማለዳ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ድሉን አብስሯል።

ሌላው ከማይዘነጉ የደምሴ ትዝታዎች መካከል ኢትዮጵያ ባስተናገደችው የምሥራቅ እና የመካከለኛው አፍሪካ ውድድር የኢትዮጵያን ድል ያበሰረበት ስሜት ነበር:: በዚህ ውድድር ስምንት ሀገራት ነበር የተሳተፉት። ሀገራቱም ኢትዮጵያ፣ ዚምባብዌ፣ ዛንዚባር፣ ኬኒያ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ዛምቢያ እና ማላዊ ናቸው።

 

በዚህ መድረክ ለፍጻሜ የቀረቡት ኢትዮጵያ እና ዚምባብዌ ናቸው። የፍጻሜ ጨዋታውም ታህሣሥ 17 ቀን 1980 ዓ.ም ነበር የተከናወነው፤ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በተገኙበት።  ጨዋታው እንደተጀመረ የዚምባብዌ ብሄራዊ ቡድን ቀድሞ ግብ በማስቆጠር በአንድ ለባዶ መሪነት የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ተጠናቀቀ:: በሁለተኛው አጋማሽ  ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሽርፍራሪ ሴኮንዶች ሲቀሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በእጅ የተወረወረችዋን ወደ ግብ በመቀየር ዘጠና ደቂቃው በአቻ ውጤት ተጠናቋል:: በዕለቱ ጨዋታውን ሲያስተላልፍ የነበረው ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ  “ወይኔ!… ወይኔ!… ወይኔ ገብሬ!… ገብሬ የመታውን የዚምባብዌው ሁለት ቁጥር በራሱ ግብ ላይ … በራሱ ግብ ላይ ከመረብ አሳረፈ፤ በራሱ ግብ ላይ ከመረብ አሳረፈ!…” እያለ ጨዋታውን አስተላለፈ::

ጭማሪው ሠላሳ ደቂቃም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት ተጠናቋል:: በተሰጠው የመለያ ምትም ዳኛቸው ደምሴ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን አሸናፊ ያደረገችውን የመጨረሻዋን ግብ ሲያስቆጥር ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ በመግቢያው ላይ ያነበብነውን እስካሁን በብዙ ሰው ጆሮ የሚቃጭለውን የደስታ ስሜት አስተጋብቶታል:: ደምሴ በአርባ ዓመታት የጋዜጠኝነት ሙያው የአትሌቲክስ እና የእግር ኳስ ስፖርታችን ህያው ምስክር ሆኖ ዘልቋል።

ጉምቱ የስፖርት ጋዜጠኛ ባደረበት ህመም ከአስራ ሁለት ዓመታት በፊት በ60 ዓምቱ ነበር ህይወቱ ያለፈው። ለሀገራችን የስፖርት እድገት ላበረከተው የላቀ አስተዋጽኦ እኛም ታላቁን የስፖርት ጋዜጠኛ እንዲህ ዘክረነዋል::

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የነሐሴ 5 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here