ጤናን በፈጣን ርምጃ

0
37

አዛውንቶች በየዕለቱ በደቂቃ ከአስራ አራት ርምጃ ጀምረው እየጨመሩ በፍጥነት መጓዝ ከቻሉ አካላዊ ጥንካሬ እና ጤናቸው ትርጉም ባለው መልኩ እንደሚሻሻል ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ  አስነብቧል::

በቺካጐ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የተመራ አዲስ ጥናት እንዳመላከታው በእድሜ የገፉ አዛውንቶች ከአዝጋሚ ርምጃ ተላቀው ፍጥነታቸውን እንዲጨምሩ ማስቻል ንቁ እና ጠንካራ ሆነው  ቀሪ ህይወታቸውን እንዲያሳልፉ ያስችላቸዋል::

 

በቺካጐ ዩኒቨርሲቲ የሰመመን ልዩ ባለሙያው ዶክተር ዳኔል ሩቢን አዛውንቶች ከቀዶ ጥገና ጋር ተያይዞም ችግሮች እንደሚስተዋሉባቸው ነው ያስረዱት:: መገለጫዎቹም- ያልታሰበ ክብደት መቀነስ፣ የእንቅስቃሴ ዝግመት ወይም መቀሰስ፣ የድካም ስሜት እና ከአካል እንቅስቃሴ መገታት የመሳሰሉት ናቸው::

ምልክቶቹን ያረጋገጡት ባለሙያዎቹ ለችግሩ መፍትሄ ለመሻት በፍጥነት  እና በለመዱት መልኩ የሚራመዱትን በመለየት ፍጥነታቸውን የመመዝገብ እና የመቀመር ተግባር አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል ::

 

ለዚህም ፈጣን ርምጃ በአዛውንቶቹ ላይ የሚያሳድረውን በጐ ተፅዕኖ ወይም መሻሻል ለመከታተል “speed test” የተባለ ስማርት የእጅ ስልክ መተግበሪያን ፈጥረዋል- አጥኚዎቹ:: መተግበሪያው የርምጃ ቁጥርን ወይም ብዛቱን፣ ፍጥነትን ወይም የጊዜ ልኬታውን ማሳየት እንዲችል ተደርጐም ነው የበለፀገው::

 

ዶክተር ዳኔል ሩቢን ለርምጃ  ፍጥነት መመዝገቢያነት የተዘየደው መተግበሪያ ከትክክለኛነቱ ባሻገር ለሁሉም ተደራሽ እና ለተጠቃሚዎቹም ምቹ ሆኖ መዘጋጃቱን ገልጸዋል።

በተግባራዊ ሙከራው ፈጣን የእግር ጉዞ ያደረጉ አዛውንቶች አካላቸው ተፍታቶ እና ጤናቸው  ተጠብቆ መገኘቱን ጥናቱ አረጋግጧል።

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የነሐሴ 5  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here