ግዙፉን ኩባንያ የረታዉ ግለሰብ

0
39

በአርጀንቲና ከመዲናዋ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ ብራጋዶ በተሰኘች ከተማ ቀረፃ ሲያካሂድ በነበረ የጐግል ኩባንያ ካሜራ ያለፈቃድ በግቢው ውስጥ ከፊል እርቃኑን የሚያሳይ ምስል ተቀርጾ መለቀቁን የተመለከተው ግለሰብ ፍርድ ቤት ከሶ መርታቱን ኤንዲቲቪ ድረ ገጽ   አስነብቧል፡፡

 

በሙያው ፖሊስ የሆነው ግለሰብ በጐግል ተሽከርካሪ ላይ በተጫነ ካሜራ ተቀርፆ  ምስሉ በመገናኛ ብዙሃን  በመለቀቁ በስራ ቦታ ባልደረቦቹ፣ በመኖሪያ ቀጣናው  ጐረቤቶቹ እንደተሳለቁበት   አመልክቷል፡፡

ኩባንያው ምስሉን በድረ ገጽ ሲለቅ የቤት ቁጥሩን እና የጐዳናውን ስም ሳያደበዝዝ ለእይታ ማብቃቱ ማንነቱ ተለይቶ መዘባበቻ እንዳደረገውም ነው ከሳሹ በምሬት ያስረዳው፡፡

 

ግራ ቀኙን ያከራከረው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ግለሰቡ ባልተገባ ሁኔታ  ከቤቱ ውጪ መታየት አልነበረበትም በሚል በ2019 እ.አ.አ ክሱን ውድቅ አድርጐት ነበር፡፡ ኃላም የግለሰብ መብቴ ተጥሷል ሲል  ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ በመጠየቁ የከሳሽ ተከሳሽ   ክርክር መቀጠሉን ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡

 

ከፍተኛው ፍርድ ቤትም ጉዳዩን በጥልቀት መርምሮ ግራቀኙን አከራክሯል፤ ጐግል ኩባንያ የግለሰቡ የግቢ አጥር ቁመቱ ማጠሩ በካሜራ እይታ ውስጥ ሊገባ እንዳስቻለው ቢከራከርም የአጥሩ ከፍታ  አንድ ሜትር ከ80 ሳንቲ ሜትር መሆኑን ከሳሽ በምላሽነት አቅርቧል፡፡

ከፍተኛው ፍርድ ቤት ማንም ሰው  እርቃኑን እንደተፈጠረ ለዓለም መታየት እንደማይሻ በመንቀስ ጐግል  የግለሰቡን ማንነት እንዳይታወቅ፣ የከሳሽን ፊት እና የተሽከርካሪው ታርጋ እንዳይለይ የማደብዘዝ መመሪያውን በአግባቡ ቢፈፅምም የጐዳናው መለያ ቁጥር መታየቱ   ግለሰቡን መለየት እንደሚያስችል ነው የደመደመው፡፡

በመጨረሻም የቦነሳይረስ ብሔራዊ የሲቪል ይግባኝ ሰሚ  ፍርድ ቤት ጐግል ኩባንያ 12 ሺህ ዩሮ ወይም 1,884,000 ብር እንዲከፍል የወሰነበት መሆኑን ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የነሐሴ 5  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here