ባህር ውቅያኖሶች ሳይቀሩ በኢትዮጵያ የተጠሩበት ዘመን፣ አትላንቲክ እና ሕንድ ውቅያኖሶች ‘የኢትዮጵያ ውቅያኖስ’ የተባሉበት ጥንታዊ ካርታ፣ አብዛኛው የአፍሪካ ክፍል በ’ኢትዮጵያ’ የተሰየመበት ታሪክ ነበረ። የኢትዮጵያ የምስራቅ በሯ ሲከፈት ቀይ ባህር እና ሕንድ ውቅያኖስ ወለል ብለው የሚታዩበት፤ የምዕራብ በሯን ስንከፍተውም አትላንቲክ ውቅያኖስ እንደ ነሀስ እያበራ ተኝቶ የምናይበት ዘመን ነበረ። ወደ ሦስት አህጉራትን አንድ አድርጎ የሚያስተዳድር ሰፊ ስርወ መንግሥት፤ በዓለም የተፈሩ እና የተከበሩ ኃያላን ነገሥታት ነበሩ። የጥንት እና የዘመናዊው ዘመን የታሪክ ፀሀፍትም ይህን ሀቅ በዘመን አይሽሬ ብእራቸው ለትውልድ ከትበውት አልፈዋል።
ኢፎረስ የተባለው ግሪካዊ፣ “ኢትዮጵያውያን በእስያ እና በአፍሪካ የደቡብ ጠረፎች ላይ ይኖሩ እንደ ነበር ይታሰባል፣ ይህ የግሪካውያን የጥንት አስተሳሰብ ነበር፣” በማለት ከተናገረው በተጨማሪ፣ “ኢትዮጵያ በዓለም መጀመሪያ የተመሰረተች ሀገር ናት፤ ኢትዮጵያውያን በአማልክት ማምለክን ያስተዋወቁ እና ሕግን የመሰረቱ የመጀመሪያ ሕዝብ ናቸው፣” ያለው የቤይዛንታይኑ እስጢፋኖስ በወርቃማ ቃላት ያን የኢትዮጵያውያንን የታላቅነት ዘመን መስክሯል።
በአንደኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ ብቅ ያለው የኢትዮጵያ የኃያልነት ዘመን ማሳያ የሆነው የአክሱም ሥርወ መንግስት በዓለም ከነበሩት የወቅቱ ሀያላን አራት መንግሥታት ውስጥ እንደሚመደብ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክ ያሳያል። ኢትዮጵያ በዚህ ሩቅ ዘመን ላይ ከምስራቃዊው የሱዳን ጠረፍ እስከ ሞቃድሾ ድረስ በተንሰራፉት ወደቦቿ ላይ መርከቦቿ እየተገነቡ እና እየተነሱ ውቅያኖሶችን ያዳርሳሉ። አዶሊስ፣ ሚዲር፣ ታጁራ፣ ዘይላ፣ ገበዛ፣ በርበራ ከሚጠቀሱት ዋና ዋና ወደቦቿ ነበሩ። እነዚህ የባህር በሮቿን ከዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ጋር የተለያዩ ግንኙነቶችን ከማድረግ በተጨማሪ ከሀገር ውስጥ ለሚነሳው ረጅሙ የሲራራ የንግድ መስመር መዳረሻዎች ነበሩ።
በየብስ እና በባህር የሚከናወን ሁሉንም አህጉራት የሚያስተሳስር ረጅም የንግድ መስመር ከኢትዮጵያ ተነስቶ ሩቅ ምስራቅ ይደርሳል። በአፍሪካ በኩል ከደቡብ ኢትዮጵያ ከቦንጋ በመነሳት መዳረሻዎቹን በቀይ ባህር እና ሕንድ ውቅያኖስ በሚገኙ ወደቦች ላይ ያደርጋል። ከቦንጋ ተነስቶ ወደ ሰሜኑ እና ምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚያመሩ መስመሮች ነበሩ። ወደ ሰሜናዊው የኢትዮጵያ አቅጣጫ የሚያመራው የሲራራ መስመር የደቡብን፣ የወለጋን፣ የጎጃምን፣ የጎንደርን አካባቢዎች እየነካካ በአዘዞ እና በደብረታቦር ከተሞች ላይ ሁለት መገንጠያዎችን ይፈጥራል፤ አዘዞ የደረሰው መስመር ጎንደር ከተማን አልፎ በኤርትራ በኩል ምፅዋ ወደብ ላይ ሲጠናቀቅ፤ ከአዘዞ ወደ ምዕራብ የሚታጠፈው ደግሞ በመተማ በኩል ሱዳን ተሻግሮ በቀይ ባህር ጠረፍ፣ ፖርት ሱዳን ላይ ደርሶ ይቆማል። በደብረታቦር በኩል የቀረው መስመር የቤጌምድርን እና የወሎን አካባቢዎች እየጠቀለለ በአፋር በኩል አሰብ እና ዘይላ(ታጁራ) ከተባሉ ወደቦች ይደርሳል። ሁለተኛው ከቦንጋ የሚነሳው የሲራራ ንግድ መስመር ወደ ምስራቅ የኢትዮጵያ አቅጣጫ የተለያዩ ከተሞችን እየመሰረተ እና መንገድ እየጠረገ መዳረሻውን በአሁኗ ሶማሌላንድ የበርበራ ወደብ ላይ መዳረሻውን ያደረገ የንግድ እንቅስቃሴ ይፈፀም ነበር።
እነዚህ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ የደም ስር የሆኑ የንግድ መስመሮችን እና መዳረሻዎቻቸውን መቆጣጠር የቻለው የአክሱም ስርወ መንግሥት የቀይ ባህር የንግድ እንቅስቃሴ ላይ የዘመኑ ኃያል እና ጠንካራ መንግሥት ሆኖ ብቅ ካለበት አንደኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ጀምሮ እስከተዳከመበት አስረኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ቀጥሏል።
የአክሱም ሥርወ መንግሥት ከፊንቃውያን፣ ግሪካውያን፣ ከቤዛንታይን፣ ከሮማውያን፣ ከግብፃውያን፣ ከሕንዳውያን እና ከቻይናውያን ግዛቶች ጋር ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ነበረው። ‘ፐሪፕለስ ኦፍ ዘ ኤርትሪያን ሲ’ በተሰኘ ፀሀፊው ባልታወቀ ጥንታዊ መፅሀፍ ላይ እንደተጠቀሰው የኢትዮጵያ ዋና ወደብ የነበረችውን አዶሊስን የጠቀሰ ሲሆን በዚያም የባህር ጉዞ የሚያደርጉ የውጭ ሀገራት መርከቦች በማታ ጥቃት ከሚያደርሱ ስርአት አልበኞች ራሳቸውን ለመጠበቅ መልህቃቸውን ይጥሉባት ነበር። በአዶሊስ የቀለጠ ዓለምአቀፋዊ ንግድ ይካሄድባት የነበረና ከየአቅጣጫው በሚመጡ ነጋዴዎች ተጥለቅልቃ ማየት የተለመደ ነበር። አዶሊስ ወደ እርሷ ያለማቋረጥ ለሚጎርፉት ነጋዴዎቹ ከምታቀርብላቸው የዝሆን ጥርስ በልዋጭነት የተለያዩ የአልባሳት አይነቶችን፣ ጠርሙስ ነክ እቃዎችን፣ መገልገያ መሣሪያዎችን፣ የወርቅ እና የብር የጌጣጌጥ፣ መዳብ፣ እና ጥራት ያላቸውን የጦር መሣሪያዎች ለመስራት የሚያገለግሉ ከሕንድ የብረት ማእድን ታገኝ ነበር። ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የደም ስር የነበረችው አዶሊስ፣ ከምፅዋ አጠገብ የምትገኝ ወደብ ስትሆን፣ በድንጋይ የተገነቡ ቤቶች እና ሀውልቶች፣ አንድ ግድብ፣ እና በመስኖ የሚለማ እርሻ የሚገኙባት ቀልብን የምትገዛ ውብ ስፍራ መሆኗን መፅሀፉ ያወሳል።
በአክሱም ዘመን ኢትዮጵያ የራሷ የመገበያያ ሳንቲሞችን አሳትማ የምትጠቀም ብቸኛ አፍሪካዊት ሀገር የሚያስብላት ታላቅ ታሪክ ተመዝግቧል። ቀላል እና የተቀላጠፈ የንግድ ልውውጥ ለማካሄድ በማሰብ የራሷን ገንዘብ በማተም በሦሥተኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ በተግባር ላይ ያዋለችው ኢትዮጵያ በዓለማቀፉ የንግድ እድገት የራሷን አሻራ አሳርፋለች። የአክሱም የሳንቲም ገንዘብ በስራ ላይ መዋል በመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ ያለውን ሚና ጨምሮታል። አክሱም በአፍሪካ በኩል ያለውን የቀይ ባህር የንግድ እንቅስቃሴ በመቆጣጠር ለተወሰኑ ክፍለ ዘመናት ያለ ተቀናቃኝ በበላይነት መቀጠል መቻሉን ኮስሞስ የተባለ የባህር ላይ ነጋዴ፣ ክርስቲያን ቶፖግራፊ በሚል መፅሀፉ ላይ አስፍሮታል።
የኢትዮጵያ ታሪክ፣ በሚል ርእስ ማርከስ ሃሮልድ በፃፈው የታሪክ መፅሀፍ ላይ እንደተመላከተው፣ የአክሱም መንግሥት መነሳት እና በሀገር ውስጥ የባህር ዳርቻዎ ላይ የተቀዳጀው የበላይነት ከግብፅ አካባቢያዊ እና ከሮማውያን የዓለማቀፍ ኤኮኖሚ መነቃቃት ጋር የተቆራኘ ነበር። ከአገር ውስጥ የተለያዩ እቃዎችን በአዶሊስ ወደብ ለዓለማቀፍ ንግድ በማቅረብ እንዲሁም በምትኩ ሌሎች እቃዎችን በመገበያየት ጠንካራ የንግድ ትስስር ተፈጥሮ ነበር። እንዲሁም በርበራን በመጠቀም የኢትዮጵያ ነጋዴዎች የሕንድ ውቅያኖስን የንግድ መስመር በመቆጣጠር ወደ ሕንድ መሀል ሀገር ድረስ ገብተው ይነግዱ እና በምትኩም የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችን፣ እጣን ሸንኮራ አገዳ እና ሌሎች አይነት በርካታ ሸቀጣሸቀጥ ይዘው ይመለሳሉ። አክሱም በተለይ በዐፄ ካሌብ ዘመን እስከ የመን ተሻግሮ ግዛቱን በማስፋፋት በሁለቱም የቀይ ባህር ዳርቻዎች ላይ ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ የበላይነት መገንባት የተቻለበት የኢትዮጵያ የታላቅነት ዘመን መመዝገቡ በታሪክ ይታወሳል።
በ8ኛው ክፍለ ዘመን ላይ በአካባቢው የሙስሊም ሀገሮች ኃይል እያደገ መምጣት፣ ከቀይ ባህር እስከ ሕንድ ውቅያኖስ የነበረውን የኢትዮጵያ የመርከብ እንቅስቃሴ አዳከመው፤ ይህም የአክሱምን መንግሥት ባህሪ እየቀየረው መጣ። አክሱም ለዘመናት የባህል ተፅዕኖ ከነበራቸው እና ኢኮኖሚውን ካፀኑላት ከምስራቅ ሜዲትራኒያን ወዳጆቿ ጋር ነጠላት። ንግድ በመቀነሱ የጠረፋማው አካባቢ የኢኮኖሚያዊ ፋይዳውን አጥቷል፣ እንዲሁም አዶሊስ እና ሌሎች የንግድ ማዕከላት ቀስ በቀስ እየሟሸሹ ሄዱ። ተከትሎም የባህር ማዶ ግዛቶቹን ማስቀጠል የሚያስችል ወታደራዊ አቅም እና አስተዳደራዊ ብቃቱን የጎዳ አደገኛ የሆነ የገቢ መቀነስ ገጠመው። በአለም አቀፍ የነበረው ተፅዕኖ በትዝታ ብቻ ቀረበ። እናም በቀድሞ የሀገር ውስጥ ግዛቱ ላይ እንዲወሰን ተገደደ።
በዚህ ወቅት በዘመኑ እየገነኑ ከመጡት ኦቶማን ቱርኮች መነሳት ጋር ተያይዞ የአረቦች በሁለቱም የቀይ ባህር ዳርቻዎች ላይ የበላይነቱን ጠቅልለው የመያዝ ፍላጎት እያሳዩ መምጣት የአክሱምን ህልውና አደጋ ላይ ጣለው። አረብ ሀገራት በቀይ ባህር ዋነኛ ተገዳዳሪዎች በመሆን የቀይ ባህርን የኢትዮጵያ የንግድ ይዞታዎች በመውረራቸው፣ እና ከውስጣዊ የፖለቲካ አለመረጋጋት ችግሮች ጋር ተዳምሮ የአክሱም ህልውና በአስረኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ አከተመ።
የቀይ ባህር የበላይነቷን ያሳጣት የአለም የፖለቲካ አሰላለፍ እና የሀይል ሚዛን ለውጥ ከአክሱም ውድቀት ተከትሎ ለተቋቋመው የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ መንግሥታት ከባድ ዲፕማሲያዊ ጫናዎች ለማስተናገድ ተገደዋል። እስከ 13ኛው ክፍለ ዘመን የቆየው የዛግዌ ሥርወ መንግሥት ጠረፋማ አካባቢ ከአረቦችና ከኦቶማን ቱርኮች በሚደረግ የመስፋፋት እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ዳርቻ ይዞታዋን በተረጋጋ ሁኔታ መጠበቅ የተቸገረችበት እና ተደጋጋሚ በሆኑ የውጭ ትንኮሳዎችን ለመቀልበስ በርካታ የጦርነት ጊዜያትን አስተናግዳለች።
በመስቀል ጦርነቱ ወቅት አብዛኛው የአውሮፓ ግዛቶች በሙስሊም የኦቶማን ቱርኮች የተወረሩበት ጨለማ ዘመን በመሆኑ ግንኙነቷ ተቋርጦ ነበር። ይሁን እንጂ የኦቶማን ቱርኮች የኢትዮጵያን መሬት ለመውረር ያደረጓቸው ሙከራዎች በኢትዮጵያውያን ክንድ እየተመከቱ ስለመከኑ በጠረፍ ብቻ እንዲወሰኑ ግድ ብሏቸዋል። በርግጥ የባህር በሮቿን ይዘው ከውጭው ዓለም ጋር እንዳትገናኝ ያደርጓት የውጭ ጠላቶቿ በውስጥ ፖለቲካዋ ውስጥ እጃቸውን በማስረዘም ሀገሪቱን የማተራመስ ስልት ተከትለዋል። በዙሪያዋ ሙስሊም ጎረቤቶቿን በማስተባበር በጠላቶች የመክበብ ሴራ እየሸረቡ ሲረብሿት ቆይተዋል።
በ16ኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ ቱርኮች በምስራቁ በኩል አህመድ ግራኝን የጦር መሳሪያና ሌሎች ወታደራዊ ድጋፎችን በመስጠት ኢትዮጵያን እንዲወር አድርገዋል። በአህመድ ግራኝ ወረራ ወቅት የኢትዮጵያን ግዛት ለማስከበር ፖርቹጋሎች ድጋፍ በማድረግ መሳተፋቸው ከረጅም ዘመናት መቋረጥ በኋላ የኢትዮጵያና የአውሮፓ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደ አዲስ ጀምሯል።
ከ18ኛው እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ያለው ጊዜ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የእርስ በርስ ጦርነቶች የተዳከመችበት ነበር። በውስጥ የፖለቲካ አለመግባባት የተነሳ ደካማ ማዕከላዊ መንግሥት የተፈጠረበት እና ሀገሪቱ ከሰባ ዓመታት በላይ በቆየው በጎበዝ አለቆች በሚተዳደሩ በበርካታ ግዛቶች ተከፋፍላ ለከፍተኛ የመበታተን አደጋ የተዳረገችበት የዘመነ መሳፍንት ወቅት ተከስቷል። በተመሳሳይም ሀገሪቱን ለመውረር ያሰፈሰፉ ቅኝ ገዥዎች ዙሪያዋን ከበው ያስጨነቁበት አስቸጋሪ ወቅት ነበር።
ከ1840 ዓ.ም በኋላም ያሉት ሁኔታዎች መቀያየር ጀመሩ። ለዘመነ መሳፍንት ማብቃት ምክንያት እንደሆኑ እና የኢትዮጵያን አንድነት የታደጉ የሚባልላቸው ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ የተነሱበት ዘመን ብዙ ለውጦችን አስከትሏል። ዐፄ ቴዎድሮስ መሳፍንቶችን በጦርነት ካስገበሩ በኋላ ሀያል ሀገር ለመገንባት እቅድ ነበራቸው። ይሁን እንጂ ከውስጥ ከተጋረጡባቸው ተቃውሞዎች ጋር ከእንግሊዝ ጋር የተፈጠረው ውዝግብ የእርሳቸውን ሕይወት እና የሀገሪቱን ህልውና አደጋ ውስጥ አስገባ።
ግብፅ አጋጣሚውን በመጠቀም የኢትዮጵያ ጠላት ሆና ግዛቷን የማስፋፋት እንቅስቃሴ ማሳየት ጀመረች። በ1865 ዓ.ም የከኸዲቭ እስማይል ግብፅ ምፅዋን ተቆጣጥራ የራሷን አስተዳዳሪ አስቀመጠች።
በዚህ መካከል በዐፄ ዮሐንስ ላይ ምኒልክን በመደለል ከጀርባ የሚወጋቸው ጠላት የማድረግ አላማ ወጥና ተንቀሳቀሰች። በመሆኑም በ1875 ዓ.ም ላይ ግብፅ ሀረርን በመውረር ከሸዋ ወደ ጅቡቲ የተዘረጋውን የምኒልክን የንግድ መስመር ዘጋች። የምኒልክን የገቢና ወጪ የንግድ መስመር በማስተጓጎል አላማዋን ለማሳካት ተሯሯጠች። ከዚህም ሌላ ምኒልክን ለመደለል የጦር መሳሪያዎችን በስጦታ አቀረበች።
ግብፅ ለምታደርጋቸው ትንኮሳዎች ዐፄ ዮሐንስ እንደማይበገሩ ስታረጋግጥ በውጭ ሀገራት ቅጥረኛ የጦር ጠበብቶች የሚመራ ሰራዊት በ1875 ዓ.ም አዘመተች። የዘመቻው ዓላማ ዐፄ ዮሐንስን በማስወገድ በቀይ ባህር በስተምእራብ እና በመረብ ወንዝ በስተ ሰሜን ያለውን ግዛት ለመቆጣጠር ነበር። እናም ጉንደት ላይ በተደረገው ጦርነት የግብፅ ጦር ድል ሆነ። በዚህ ሳታበቃ ከወራት በኋላ ጉራእ ላይ ሌላ ዘመቻ ሞከረች። በዚህ ውጊያ የዮሐንስ ታላቁ ጄኔራል አሉላ የሚመራው ልዩ ሰራዊት የግብፁን ጦርነት በማያዳግም ቅጣት ድል አደረገው። ከዚህ በኋላ ግን ግብፅ ተስፋ ቆርጣ ተቀመጠች። ከደማቁ የጉራ ድል በኋላ ኢትዮጵያ ግዛቷን አስከብራ ኤርትራን በግዛቷ ውስጥ በማጠቃለል ፖለቲካዊ ድንበሯን የቀይ ባህር ዳርቻ ማድረግ እንደቻለች ራይሞንድ ጆናስ፣ ‘ዘ ባትል ኦፍ አድዋ’ በተሰኘ መፅሃፋቸው ላይ አስፍረውታል።
(መሰረት ቸኮል)
በኲር የነሐሴ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም