በምርት ለመካስ …

0
44

በክረምት በብዛት ማሳ በተፈጥሯዊዉ ዝናብ ምክንያት ለእርሻ ዝግጁ ሆኖ በሰብል  ይሸፈናል።  የደረቀው ለምልሞ፣ መሬቱም ወርዝቶ የሚታይበት ወቅት ነው።  አንዴ ክረምቱ ካለፈ፣ ላላፈ ክረምት ቤት አይሰራም ነው የሚባለው። ይሄን አስፈላጊ ወቅት በተገቢው  መንገድ ተጠቅሞ ለማልማት ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ዋነኛው ጉዳይ ነው።

“እንዳይኮተኩተው ዝናብ እየፈራ፣

በሐምሌ እንዳያርም ብርዱን እየፈራ፣

ልጁ ዳቦ ቢለው በጅብ አስፈራራ።” በማለት በክረምቱ ሰብሉን ማረም እና መንከባከብ ያልቻለ ሰነፍ አርሶ አደር በአቻዎቹ በሥነ ቃል እንዲህ ሸንቆጥ ይደረጋል። ዝናቡን እና ብርዱን ተቋቁሞ ሰብሉን በሚገባ የሚያርም፣ የሚኮተኩት እና የሚንከባከብ ታታሪ አርሶ አደር ደግሞ

“አረም አርማለሁ ሰብሉ እንዲፋፋ፣

የልጆች ማደጊያ ችግር እንዲጠፋ።” እያለ ሰብሉን እየኮተኮተ፣ እያረመ፣ ከተባይ እየተንከባከበ ክረምቱን በትጋት ያሳልፋል።

የመኸር የእርሻ ወቅት ለኢትዮጵያ ትልቁ የምርት ጊዜ ሲሆን በዓመቱ በአጠቃላይ ከሚመረተው ምርት 70 በመቶ የሚሆነው በዚህ ወቅት የሚለማ መሆኑን ከኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር ድረ ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ከ85 በመቶ በላይ ለኢትዮጵያ ዜጎች መተዳደሪያ የሆነው ግብርና እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ ሀገራት መሠረት ነው። በመሆኑም የ2017/18 የመኸር ሰብል ጥበቃ እና እንክብካቤ እንዴት ነው የሚለውን በምጣኔ ሀብት አምዳችን ልናስቃኛችሁ ወደናል። ወቅቱ አርሶ አደሩ ዝናብ እና ብርዱ ሳይበግረው ያለእረፍት የሚሰራበት ምሳውን ከቤቱ ሳይሆን በማሳው የሚመገብበት ወሳኝ ጊዜው ነው።

በኢትዮጵያ ክረምቱ ለግብርና ሥራ ተስማሚ በመሆኑ አርሶ አደሩ ከወትሮው በተለየ ሌት ከቀን በመሥራት የተሻለ ምርት ለማግኘት በትጋት የሚሠራበት ወቅት ነው። ከእነዚህ አርሶ አደሮች መካከል ደግሞ አርሶ አደር አበበ ፀጋ አንዱ ናቸው። አርሶ አደሩ በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ኮኪት ቀበሌ ነዋሪ ናቸው።

አርሶ አደሩ ሁሌም ለመኸር እርሻ ማሳቸውን በበጋው ወቅት በድግግሞሽ አርሰው ያዘጋጃሉ። በዚህ ወቅት ቀድመው አርሰው አለስልሰው ባዘጋጁት አሥር ሔክታር መሬት ላይ የተለያዩ ሰብሎችን እየዘሩ ነው። ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ ማሽላ ዘርተው እየተንከባከቡ ሲሆን ለጤፍ ዘር ደግሞ እየተዘጋጁ መሆኑን ነግረውናል። በዚህ ወቅትም አረም እያረሙ ይገኛሉ። እንዲሁም ድካማቸውን ለመቀነስ ፀረ አረም እንደሚጠቀሙም ገልፀዋል። የጉልበት ሠራተኛ እጥረት እንደገጠማቸው የተናገሩት አርሶ አደር አበበ በዚህም ምክንያት የፀረ አረም መድኃኒት እንዲጠቀሙ ተገደዋል።

በፀረ አረም ርጭት ወቅት የግብርና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክረ ሐሳብ ትፈፅማላችሁ? በማለት ለአቶ አበበ ጥያቄ አንስተን ነበር፤ እርሳቸው እንደሚሉት የፀረ አረም ርጭት ሲያካሂዱ በሰውነታቸው ላይ ጉዳት እንዳይደርስ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እና የመከላከያ መሳሪያዎችን ይጠቀማሉ። የፀረ አረም ኬሚካሎች በጤናቸው ላይ ጉዳት እንዳያመጣ የአፍ መሸፈኛ ጭንብል (ማስክ)፣ ኮፍያ፣ ጓንት፣ ቦት ጫማ እና ረጅም ሱሪ… ይጠቀማሉ። ነገር ግን ሌሎች አርሶ አደሮች ተገቢውን የመከላከያ አልባሳትን ሳይጠቀሙ ርጭት እንደሚያደርጉ ታዝበዋል። ለፀረ አረም መርጫ የሚያገለግሉ ዘመናዊ መርጫ መሳሪያዎች እና አልባሳት ቢመጡ መልካም ነው ብለዋል። “ፀረ አረም ጊዜን ይቆጥባል፤ በቶሎ አረሙ እንዲወገድ ያደርጋል” ነው ያሉት። በተደጋጋሚ የፀረ አረም መድኃኒት መጠቀም ግን በእርሻ መሬቱ ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ ነው የግል ሐሳባቸውን ያካፈሉን።

አርሶ አደሩ እንደተናገሩት እንደ ከዚህ ቀደሙ የግብርና ባለሙያ በየማሳው እየተገኙ ሙያዊ ምክር እና ድጋፍ የማድረጉ ሁኔታ መቀዛቀዙን ገልፀዋል። ይህ የሆነውም በክልሉ በተፈጠረው የሰላም እጦት እንደሆነ ነው አርሶ አደር አበበ የተናገሩት።

ሌላው በስልክ ያነጋገርናቸው የምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ዙሪያ ወረዳ ቁጭ አካባቢ ነዋሪው አርሶ አደር አየለ አለሙ በ2017/18 የምርት ዘመን በአራት ሔክታር መሬታቸው የተለያዩ ሰብሎችን ዘርተው አብቅለዋል። በዚህ ዓመት የዝናብ ስርጭቱ የተስተካከለ በመሆኑ የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ተስፋ አድርገዋል። የእርሳቸውን ጨምሮ በአካባቢው ያለው የሰብል ቡቃያ በእጅጉ ያማረ መሆኑን ነው ለበኩር ጋዜጣ የተናገሩት።

አርሶ አደሩ እንደገለፁት የሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦቱ እየተሻሻለ ቢመጣም የዚህ ዓመት የዋጋ ጭማሪ ግን በግብርና ሥራቸው ላይ ፈታኝ አድርጎታል። ሆኖም ጫናውን ተቋቁመው ዘር መዝራታቸውን ነግረውናል። ሰብልን በወቅቱ አለማረም እና አለመንከባከብ ከፍተኛ የምርት መቀነስ እንደሚያስከትል አስረድተዋል። በመሆኑም የሚያስከትለውን የምርት መቀነስ በመገንዘብ ሁሌም ሰብላቸውን በወቅቱ ያርማሉ፣ ይኮተኩታሉ፣ ግብዓት ይጨምራሉ፣ ከወፍ ይጠብቃሉ፣ የተባይ አሰሳም ያደርጋሉ።

ከዚህ በተጨማሪም በእጅ ማረም ያልቻሉትን ሰፊ መሬት ላይ ሰብላቸውን ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ የፀረ አረም ርጭት ያከናውናሉ። አርሶ አደሩ ትክክለኛውን የፀረ አረም ከትክክለኛው የመሸጫ ቦታ እንደሚገዙ ነግረውናል። እንዲሁም የመጠቀሚያ ጊዜያቸውን የሚያሳዩ ፅሑፎችን በማየት አረጋግጠው እንደሚገዙ አስረድተዋል። አክሎም በፀረ አረም ርጭት ጊዜ ማድረግ የሚገባቸውን ጥንቃቄዎች አንስተዋል። ሰብሉን በአግባቡ ረጭተው ከጨረሱ በኋላ የተጠቀሙባቸውን ዕቃዎች እና አልባሳት በጥንቃቄ ያስቀምጣሉ። የፀረ አረሙን ዕቃ ከተጠቀሙ በኋላ ማቃጠል አሊያም መቅበር ቀዳሚ ተግባራቸው ነው።

አሁን ላይ በቆሎ፣ በርበሬ፣ ስንዴ፣ ጤፍ እና ዳጉሳ ዘርተው እየተንከባከቡ መሆኑን ነው የተናገሩት። በቆሎ፣ ዳጉሳ እና ስንዴ ላይ የፀረ አረም  ርጭት እንደሚያካሂዱ ነው ያከሉት። ጉልበትን፣ ወጭን እና ጊዜን ለመቆጠብ ሲሉ ነው የፀረ አረም መድኃኒት እየተጠቀሙ ያለው። ነገር ግን ፀረ አረም መድኃኒቱ የአፈር ለምነቱን እየቀነሰው ይመጣል የሚል ስጋት አላቸው። የመሬቱን ለምነት እና ጉዳት ለመከላከል ፀረ አረም ከመጠቀም ይልቅ ሌሎች አማራጮችን (አረምን በደቦ ወይም በወንፈል እና በጉልበት ሠራተኛ) ማረም ይመረጣል ብለዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በትስስር ገጹ እንዳስነበበው አሁን ላይ የግብርና ምርታማነትን እየተፈታተኑት የሚገኙ ችግሮች መካከል ተባይ፣ አደገኛ እና መጤ አረም፣ የዋግ በሽታ እና መሰል ችግሮች መሆናቸውን ጠቅሷል።

በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአረም መከላከል እና መቆጣጠር ባለሙያ አቡኔ ከበደ እንዳብራሩት አረም ባልተፈለገበት ማሳ ላይ የሚበቅል ማንኛውንም ሰብል እና እፅዋትን የሚጎዳ እና ከጥቅም ውጪ የሚያደርግ ነው። በከፍተኛ መጠን ዘር ማፍራታቸው፣ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መቋቋማቸው፣ በአፈር ውስጥ ለብዙ ጊዜ ተደብቀው መቆየታቸው እና ምቹ ሁኔታ ሲያገኙ መብቀል መቻላቸው የአረም ልዩ ባህሪ መሆኑን ጠቅሰዋል። ንፁህ ዘር መጠቀም፣ ማሳን በሚገባ ማዘጋጀት፣ ፀረ አረም ኬሚካልን መጠቀም፣ ኳራንታይንን (ቁጥጥር)ተግባራዊ ማድረግ እና አረሞች ወደ አካባቢያችን እንዳይገቡ ወይም እንዳይባዙ ማድረግ መሠረታዊ የአረም መከላከያ ዘዴዎች እንደሆኑ ተለይተዋል። የፀረ አረም መድኃኒቶች ከዘር በፊት የሚረጩ፣ ሰብሉ ከመብቀሉ በፊት የሚረጩ እና ከበቀለ በኋላ የሚረጩ ናቸው። መርጦ ገዳይ እና ጅምላ ገዳይ የፀረ አረም መድኃኒት መኖሩን አረጋግጠዋል።

አረም የሰብሉን ምግብ፣ ውኃ፣ አየር፣ የፀሐይ ብርሐን እና ሌሎችን ለሰብሉ አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን በመሻማት በሰብሉ እድገት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል። ከዚህ ባለፈም ለበሽታ እና ለተባይ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ምርታማነትን ይቀንሳል። እንዲሁም የምርት ጥራትን ያጓድላል። በመሆኑም አርሶ አደሩ አረምን ቀድሞ በመከላከል በእጅ በማረም መከላከል እንዳለበት መክረዋል።  አርሶ አደሩ የፀረ አረም ኬሚካል (መድኃኒት) መጠቀም ያለበት የመጨረሻ አማራጭ አድርጎ መውሰድ እንዳለበት ተናግረዋል።

እንደ ባለሙያዋ ማብራሪያ ፀረ አረም ኬሚካል አረም እንዳይበቅል ወይም ከበቀለ በኋላ የሚከላከል ነው።

የፀረ አረም መድኃኒት መጠቀም የመጨረሻ አማራጭ ቢሆንም ኬሚካሎችን (መድኃኒቶችን) እንደ ሰብል ዓይነቶች መጠቀም እንደሚገባም ባለሙያው መከረዋል፡፡ ፀረ አረም መድኃኒት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ካልተደረገለት ከፍተኛ ጉዳት በማስከተል ለሞት እና ለአካል ጉዳት እንደሚዳርግም ነው የሚያስረዱት። ከሰው አልፎ በእንስሳት፣ በውኃ እና በሌሎች ላይ ጉዳቱ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

አርሶ አደሩ ከሕጋዊ የፀረ አረም ኬሚካል አቅራቢዎች በመግዛት የግብርና ባለሙያዎች በሚሰጧቸው ምክረ ሐሳቦች በተባሉት ቀን፣ ሰዓት፣ የኬሚካል አይነት መጠቀም እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል፡፡ ፀረ አረም መድኃኒት በፈሳሽ፣ በዱቄት እና በጠጣር መልኩ ይዘጋጃል። በአስፈላጊው ጊዜ፣ በተመረጠው ቦታ እንዲሁም በተባለው መጠን የባለሙያ ምክረ ሐሳብ በመቀበል አረምን በመከላከል ምርትን ማሳደግ ተገቢ መሆኑንም ያነሳሉ። የተሟላ ትጥቅ፣ አልባሳት፣ ጫማ እና ሌሎች የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ማሟላት ተገቢ ነው ብለዋል።

አርሶ አደሩ ማሳን በየጊዜው ማሰስ፣ ተባይ ወይም በሽታ ከተከሰተ የተባዩን ዓይነት እና መጠን፣ ከሰብሉ ላይ ያሳረፈውን ችግር እና የመከላከል ሥራው ምን መሆን አለበት የሚለውን ከባለሙያ ጋር በመለየት የተቀናጀ የተባይ እና የበሽታ መከላከል ሥራዎች መሥራት እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል።

መረጃ

በእርሻ መሬት ላይ የሚታዩ አረሞች አደገኛ፣ መደበኛ፤ መጤ እና ወራሪ ተብለው ይመደባሉ።

አረም እንክብካቤ ባልተደረገለት ሰብል ውስጥ በመስፋፋት ሰብሉን ከምርት ውጭ የሚያደርግ ነው።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የነሐሴ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here