ለሰላም መስፈን ሁሉም የቻለውን ያበርክት!

0
64

“የነበር ሲወራ ይመስላል ያልነበር…” ይሉት አባባል እንኳን ቀብራችን ሰርጋችን አላምር ላለን ለእኛ ይሰራል፡፡

ያኔ እንዲህ ነበርን፤ ሰበብ ፈልገን የምንደግስ፤ ሰበብ ፈልገን የምንጨፍርና ሳቅን የምንጋራ- የሰርግን ያህል ቀብራችን በሰው የተሞላና  አጀብ የበዛበት፤ ያዘነን  አጽናንተን  የምናረጋጋ ነበርን፡፡

በየጎዳናው የምንስቅ በ“እንዴት ነህ! በእንዴት ነሽ!” ቆመን ስናወራ የአንዳችን ጉዳይ ለአንዳችን የሚገደን፤ ምናገባኝ ሩቃችን ሰው ወዳድና  ደስተኞች ነበርን፡፡

ይኼው አሁን ምን ሆንን-  ሳቅ ብርቃችን፤ ነጋ ጠባ ስጋት  የከበበን በ”ምን ይሆን?” ሃሳብ የተዋጥን ብኩን፤ከነጭ ጥቁር የበዛብን፣ ከመደሰት ሃዘን ያጠላብን፣ ከተስፋ ይልቅ ስጋት ዙሪያችንን የከበበን ሆንን፡፡

በፊት ምክንያት ፈልገን የምንስቅ-አሁን ምክንያት ፈልገን የምናለቅስ ሆደ ባሻዎችና በናፍቆት የተሞላ እምባ ያዘለ ዓይን የያዝን ሆንን፡፡

ይህ ለምን ሆነ? ሰላም  ለምን አጣን? በሰላም ወጥቶ መግባት ብርቅ ከመሆኑ በፊት የግዱን መሽቶ ይነጋል ብለን ያለስጋት በተስፋ ተኝተን በደስታ የምንነቃ የነበርነው እንኳን የኛ የጎረቤትም ሰላም መሆን ለኛ ዋስትናችን ነበር፡፡ የኛ ብቻ ሳይሆን የሌሎች ወጥቶ መግባት  እና ሰላም መዋል ዋጋው  ከፍ ያለ ነበር፡፡ የዚህን ሰላም ዋጋ የተረዳነው  ግን ዘግይተን ነው፡፡ ይህ የገባን በሰበብ አስባቡ እየተሸረሸረ እየተሸረሸረ ከመጣው መደማመጥ እና ተጣልቶ መታረቅ እሴት ስንርቅ ነው፡፡

በህይወት እንዲህ ገጥሟችሁ አያውቅም? እያለ ምንም ያልመሰለን ስናጣው የቆጨን ነገር፣ እኛ ጋር እያለ ዋጋ ያልሰጠነው እና የጣልነው ነገር ከሰው ላይ ስናየው “ለካ እንዲህ ያምራል-እንዲህም ውብ ነበር”  ያስባለን የ ሰላም መታጣትም እንዲሁ ነው፤ የጸጥታን ውበት የምናውቀው የረብሻ ድምጽ ስንሰማ ነው፡፡

ወይም ደግሞ የሰላምን ዋጋ የተረዳነው እንደ አንዳንድ በዙሪያችን የነበሩ ሰዎች በፀብ፣ በሞት፣ ቦታ በመቀየር… ስንለያይ ዋጋቸውን እንደተረዳነው ዓይነት፡፡ አለመኖራቸው የፈጠረውን ክፍተት ማንም ሊሞላው እንደማይችል ስናውቅ እና ስናጣቸው ዋጋቸውን እንረዳለን፡፡

ይህን ህመም ደጋግመን ቀምሰነዋል፡፡ ጊዜ ሳንሰጣቸው፣ ሳንጠይቃቸው፣ ዋጋ ሳንሰጣቸው እና ሁሌም የሚኖሩ እየመሰለን ባጣናቸው ብዙ ሰዎች ብርቱ ህመም ታመናል፡፡

እንደዚያ ዓይነት ህመም የመታመምን ያህል ነው በሰላም እጦት መቀጣትም ህመሙ እጥፍ ነው፡፡ ሀገርን ያሳምማል፡፡ በሰላም ወጥቶ መግባት ይናፍቃል፡፡ እንዲሁ ተነስቶ ዛሬስ እዚህ ቦታ ደርሼ ልምጣ ማለት ሲቀር፣ እንኳን ሀገር እና ጓደኛ እናት አባትን ሄዶ መጠየቅ፤ መጠየቅ አይደለም ሲሞቱ መቅበር ሲቀር የሰላም እጦት ቅጣት ህመሙ እንዴት ቃላት እንደማይገልጸው አይተናል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በዚህ ሰዓት የሚጾመው ጾመ ፍልሰታን ብዙ አማኞች እንደሁሌው በየእምነት ተቋሙ ተሰብስበው አልከወኑትም፡፡ ያኔ ታዲያ

“የነበር ሲወራ ይመስላል ያልነበር

አምና ይኼን ጊዜ እንዴት እንዴት ነበር”

ብሎ በናፍቆት ያሳለፈውን ዛሬ በተመሳሳይ ወቅት ምእመኑ ተሰብስቦ እየከወነው ነው፡፡ ይህ አንዱ ማሳያ እንጅ በሰላም እጦት እንዳልነበር የሆነው ብዙ ነው፡፡

 

ለሰላም መስፈን ሁሉም የቻለውን ካላበረከተና ወደነበርንበት ካልተመለስን የምንከፍለው ዋጋ እጥፍ እየሆነ ይሄዳል፡፡ የሰላም  ፍላጎት በአንድ በኩል ፍላጎት ብቻ አይመጣም፡፡ ሁሉም ከልቡ እኩል ሲሰራ፣ እኩል ሲያበረክት ያኔ የናፈቅነው ሰላም ወደ እኛ ይመጣል፡፡

በኲር የነሐሴ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here