በባሕር ዳር ከተማ በተለይ በእረፍት ቀናቶች በርካታ ሰዎችን በአስፋልት እና በኮንክሪት መንገዶች ላይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ መመልከት እንግዳ አይደለም። ይህ ለምን ሆነ? ሲል አሚኮ በኵር ጋዜጣ የስፖርት ዝግጅት ክፍል በአስፋልት ላይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ያገኛቸውን ወጣቶች አነጋግሯል:: ከጋዜጣችን የስፖርት ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረገው ወጣት ኃይለ እየሱስ ተስፋ በከተማዋ በቂ የስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራ አለመኖሩን ይናገራል።
ዳግማዊ ምንሊክ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆነው ኃይለ እየሱስ በክፍለ ከተማቸው በቂ እና ደረጃቸውን የጠበቁ የማዘውተሪያ ስፍራ እንደሌለም ይናገራል። በባሕር ዳር ከተማ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ እጥረት በመኖሩ አስፋልት ላይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ተገደናል ብሏል። ይህ ደግሞ ለአካል ጉዳት እየዳረጋቸው እንደሆነ አልሸሸገም።
አስፋልት እና ኮንክሪት ጠንካራ በመሆናቸው በእነዚህ ቦታዎች ላይ የሚደረጉ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ለአጥንት መሰንጠቅ፣ ለመገጣጠሚያ ህመም እና ለሌሎች ከባድ ጉዳቶች ያጋልጣል። አስፋልት ላይ መንገድ ዘግቶ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ የትራፊክ ፍሰቱንም ያስተጓጉላል። ወጣቶች ልምምድ ለማድረግ የሚጠቀሙባቸው መንገዶች ለተሽከርካሪዎች ክፍት በመሆናቸው ለከፍተኛ የትራፊክ አደጋ ያጋልጣቸዋል። ይሁን እንጂ በባሕር ዳር ከተማ መሰል ተግባራት ሲከናወኑ በስፋት ይታያል።
ከጥቂት ዓመታት በፊት በየቀበሌው ብዙ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ እንደነበር የሚያስታውሰው ወጣቱ ከተማው መስፋቷን እና የሕዝብ ቁጥር መጨመርን ተከትሎ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ እጥረቱ ተፈጥሯል ነው ያለው። ይህን ተከትሎም ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚያደርገው የኅብረተሰብ ክፍልም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል፤ የክረምት ውድድሮችንም ለማቋረጥ ተገደዋል።
በከተማዋ በቂ እና ምቹ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ አለመኖር ወጣቶች በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ያላቸውን ተሰጥኦ እንዳያሳድጉ እና በውድድሮች ላይ ተሳታፊ እንዳይሆኑ እንቅፋት ፈጥሮባቸዋል። “በየክፍለ ከተማ እና ቀበሌዎች ያሉት የማዘውተሪያ ስፍራዎችም ሜዳቸው የተስተካከለ እና ምቹ አይደለም፤ ወጣቶች ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት አማራጭ ቦታ ሲያጡ ደግሞ ወደ ተለያዩ ሱሶች እና የወንጀል ድርጊቶች የመግባት እድላቸው ከፍ ይላል” ሲል ወጣቱ ያብራራል።
ምቹ የስፖርት ማዘውተሪያ ካለ ማኅብረሰብ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ይነሳሳል። ታዲያ የከተማ አስተዳደሩ ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ በቂ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ማዘጋጀት እና ያሉትን ሜዳዎች ማስተካከል አለበት የወጣት ኃይለ እየሱስ ተስፋ አስተያየት ነው።
ያነጋገርነው ሌላኛው ወጣት ደህንነት ከፌ ደግሞ “በከተማዋ ያሉ መዝናኛ ፓርኮች (Green Areas) በውስጡ አነስተኛ የስፖርት ማዘውተሪያ ያካተተ ቢሆንም ህጻናትን እንጂ ወጣቶችን ታሳቢ ያደረገ አይደለም” ብሏል። እናም በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ ክፍት ቦታዎችን በማጥናት ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ አገልግሎት እንዲውሉ ማመቻቸት እና አስፈላጊውን ቁሳቁስ ማሟላት ያስፈልጋል ነው ያለው ወጣቱ።
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የስፖርት ማዘውተሪያዎችን እና ሁለገብ የወጣቶች ማዕከላትን መገንባት ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባዋል፤ የከተማዋ የልማት ዕቅዶች እና የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችንም ያካተቱ መሆን እንደሚኖርባቸው ነው ሀሳቡን ያጠናከረው።
የግል ባለሀብቶችን በስፖርት ዘርፍ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እና ማበረታታት ያስፈልጋል ነው የተባለው። ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ሊስፋፋ የሚችለውም ምቹ እና በቂ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ሲኖር በመሆኑ ተቋማት የስፖርት መሰረተ ልማቶችን በመገንባት እና በማሟላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ወጣት ደህንነት ከፌ ጠቁሟል።
በባሕር ዳር ስድስት ክፍለ ከተሞች እና 27 የከተማ ቀበሌዎች አሉ። በከተማ አስተዳደሩ በአብዛኞቹ ክፍለ ከተሞች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ አለ። ይሁን እንጂ በቂ አይደሉም፤ የጥራት ጉድለቶች እንዳሉባቸውም የከተማ አስተዳደሩ ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ቶማስ ታምሩ ለበኩር የስፖርት ዝግጅት ክፍል ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች አስተዳደርን ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 729/2004 ዓ.ም ኀብረተሰቡ በሚኖርበት፣ በሚማርበት እና በሚሠራበት አካባቢ ሁሉ በስፖርት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳታፊ የሚሆንበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት ይላል።
ይህንንም ለማሳካት የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች በየአካባቢው በብዛት እና በጥራት እንዲስፋፉ እና እንዲጠበቁ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ሰነዱ ያትታል። የመንግሥት ፖሊሲ፣ የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ስትራቴጂክ ዕቅዶችም የኀብረተሰቡን ተሳትፎ ለማሳደግ የስፖርት መሰረተ ልማቶችን መስፋፋት እንዳለባቸው ያብራራል።
ሃያ ሦስተኛው የአማራ ክልል የስፖርት ምክር ቤት ጉባኤ ሲካሄድ የክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ በቀበሌ አንድ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ እና በወረዳ ወይም በክፍለ ከተማ ደግሞ ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚመች መለስተኛ ስቴዲየም እና ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ለማዘጋጀት እየተሠራ መሆኑ መገለጹ አይዘነጋም:: የክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮው ይህን ይበል እንጂ ተቋሙ በሚገኝበት ከተማ አሁን ላይ በቂ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ የለም:: ያሉትም ጥራታቸውን የጠበቁ እንዳልሆኑ የከተማ አስተዳደሩ ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ቶማስ ታምሩ መስክረዋል። ለአብነት ጥሩ የሜዳ ንጣፍ ሳር፣ የተመልካች መቀመጫ ወንበር እና የመሳሰሉት ሌሎች አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች የተሟሉላቸው አይደሉምም ብለዋል።
በባሕር ዳር ከተማ አንዳንድ ቀበሌዎች ላይ ሁለት እና ከዚያ በላይ የማዘውተሪያ ስፍራዎች ያሉባቸው ቀበሌዎች እንዳሉ አቶ ቶማስ የተናገሩ ሲሆን አንዳንዶቹ ጋር ደግሞ ምንም የማዘውተሪያ ስፍራ እንደሌለ ጠቁመዋል።
“ከተማዋ እየሰፋች እና እያደገች በመሆኗ በቂ እና ጥራት ያለው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ለማዘጋጀት እየተሠራ ነው። በተለይ ደግሞ ያሉትን ምቹ እና ጥራታቸውን የጠበቁ ለማድረግ ከከንቲባ ጽ/ቤት ጋር የተጀመሩ ሥራዎች አሉ ብሏል። ከከተማዋ ማስተር ፕላን ጋር በማጣጣም ያሉትንም ክፍት ቦታዎች በመለየት ማዘውተሪያ ስፍራ በሌለባቸው አካባቢዎች ለማዘጋጀት ለከተማ አስተዳደሩ ጥያቄ አቅረበናል” ብለዋል አቶ ቶማስ ታምሩ።
የከተማ አስተዳደሩ ምላሽም አዎንታዊ መሆኑን ነው አቶ ቶማስ የነገሩን። የከተማዋ የልማት ፕሮጀክቶች እና የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች የስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራዎችን ታሳቢ እንደሚያደርጉም ጭምር ነው የተናገሩት።
አሁን ላይ የኮሪደር ልማት እየተሠራ ባለበት አካባቢ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ የለም። በቀጣይ ግን የኮሪደር ልማቱ በሚነካቸው አካባቢ ያሉትን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች አብረው ከኮሪደሩ ጋር እንዲለሙ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ጠይቋል። ከተማ አስተዳደሩም ይህን ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነ ተነግሯል። አዲስ የማዘውተሪያ ስፍራ ሲዘጋጅ ነባሮችንም ምቹ የማድረግ ሥራ ይሠራልም ተብሏል።
በባሕር ዳር ከተማ የሚታየው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ እጥረት አፋጣኝ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው። ችግሩን ለመፍታት የመንግሥት፣ የማህበረሰቡ እና የሚመለከታቸው ሌሎች አካላትን የተቀናጀ ጥረት ይጠይቃል። ይህም ጤናማ፣ አምራች እና ከሱስ የጸዳ ትውልድን ለመፍጠር ያስችላል።
የሚመለከታቸው አካላት በከተማዋ ያለውን ችግር በመለየት ለመፍትሄው የበኩላቸውን ድጋፍ ማድረግ እና ክትትል ማካሄድ ይኖርባቸዋል። የማህበረሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ እና በማስተባበር ያሉትን የስፖርት ስፍራዎች ለመንከባከብ እና ለማሻሻል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይገባቸዋልም።።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የነሐሴ 12 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም