ዝናብ እና አበቦች ያገኙት የበረዶ አሳሾች

0
59

በሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ (አርክቲክ) ባለፉት ወቅቶች የነበረን ግግር በረዶ ለማጥናት የተንቀሳቀሰው የተመራማሪዎች ቡድን አበባ የለበሰ ቀጣና እና የቀለጠው በረዶ በጐድጓዳ ስፍራዎች ኩሬዎችን ፈጥሮ መመልከቱን ሳይቴክ ዴይሊ ድረ ገጽ በነሀሴ ወር መባቻ ለንባብ አበቅቶታል::

በለንደን የሚገኘው የኩዊን ሜሪ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በ2025 የካቲት ወር ወደ ሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ (አርክቲክ) አቅንተው ነበር:: የጉዟቸው መነሻ በቀጣናው ባለፉት ወቅቶች የነበረን በረዶ ለመመልከት ያለመ ነው:: የተመራማሪዎቹ ቡድን በቦታው እንደደረሰ ግን ዝናብ፣ በዛፍ እና ቁጥቋጦ አልባ ቀጣና  አበባ የለበሰ የሣር ምድር ነው ያገኙት::

ቡድኑ ወደ አርክቲክ ቀጣና ሲያመራ  ቀደም ብሎ በነበራቸው ግንዛቤ መሠረት ለክልሉ ተስማሚ የሆኑ ወፈር ያሉ ጥጥነክ አልባሳት፣ የእጅ ጓንት፣ ለጭንቅላታቸው ልባስ የሹራብ ኮፍያ የመሳሰሉትን የጓዛቸው አካል አድርገው ነበር::

የቡድኑ መሪ ዶ/ር ጃምስ ብራድሊ እና አባላቱ  ግን አዲስ እውነታን ታዝበዋል፤ቀዝቃዛው ዓየር ቀርቶ  በሙቀት  በረዶው ሟምቶ፣ ጐድጐድ ባሉ ስፍራዎች ኃይቆችን እንዲሁም ቀጣናው አበባ ሳር እና ቅጠላ ቅጠል ለብሶ ማየታቸውን ነው ያረጋገጡት:: ሁኔታው አስደንጋጭ መሆኑንም የቡድን አባላቱ ሪፓርት አመላክቷል::

በአርክቲክ “ቮልባርድ” ቀጣና ሙቀቱ ከዓለም አቀፍ አማካይ  ከእጥፍ  በላይ  መጨመሩንም አረጋግጠዋል::

ከተመራማሪዎቹ ቡድን አንዷ የዶክትሬት ተማሪዋ ላውራ ሞላሬስ እንደተናገሩት የጉዟቸው ዓላማ አዲስ የወረደ በረዶን ሰብስቦ የመሟሚያ ጊዜውን ለመገምገም ነበር፤ ግን መጠኑ በጣም አነስተኛ ሆኖባቸዋል:: ይህም የናሙና አሰባሰብ እቅዳቸውን አስተጓጉሎባቸዋል::

ቡድኑ በአርክቲክ ስነ ምህዳር ሰፊ ለውጥንም አስተውሏል:: በአዲሱ  የአርክቲክ ቀጣና የሙቀቱ መጨመር የዱር አራዊቱን ህልውና አደጋ ላይ መጣሉንም ጭምር::

በመጨረሻም በአርክቲክ በተስተዋለው ለውጥ ላይ ምርምር ያደረጉት በጣሊያን ኔኘልስ ዩኒቨርሲቲ “ጂኦ ማይክሮ ባዮሎጂስት” ዶና ቶ ጊቮናሌ የተከሰተው ለውጥ የሚያስከትለውን የጉዳት ደረጃ ለማሰቀመጥ የመረጃ እጥረት  በመኖሩ መቸገራቸውን ጠቁመዋል:: በማጠቃለያነትም “አርክቲክ ዓይናችን እያየ መቀልበስ ወደማይቻል ደረጃ እየተሸጋገረ ቢሆንም በምናቀርባቸው እና በምናስተላልፋቸው መልእክቶች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል” ነው ያሉት::።

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የነሐሴ 12  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here