ራሱን የሚያፀዳው መስታዉት

0
69

በቻይና የዚጂያንግ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ተራመራማሪዎች በውስጡ በተቀበሩ ቀጫጭን የኤሌክትሪክ ኃይል አስተላላፊ ሽቦዎች ንዝረት ራሱን በራሱ ማፅዳት የሚችል ስስ መስታዉት መስራታቸውን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት አስነብቧል፡፡

እስከአሁን በየአገራቱ በተገነቡ ረዣዠም ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች የተገጠሙ መስታዉቶች ሲቆሽሹ፣ ከዚህም ባሻገር በበረሀ መካከል የተተከሉ የፀሀይ ኃይል መሰብሰቢያ ንጣፎችን ለማፅዳት አስቸጋሪ እና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ ሆነው ቆይተዋል፡፡ ለተጠቀሰው ችግር መፍትሄ የቻይና የተመራማሪዎች ቡድን ከማናቸውም ዓይነት ውኃም ሆነ ኬሚካል  በፀዳ መልኩ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ራሱን የሚያፀዳ መስታዉት መስራት ችሏል፡፡

ተመራማሪዎቹ ዜሮ ነጥብ 62 ሚሊ ሜትር ቅጥነት ወይም ስስ በሆነ ብርሃን አስተላላፊ መስታዉት ውስጥ የተዘረጉ ቀጫጭን ኤሌክትሪክ አስተላላፊ ገመዶች ተቃራኒ  የኤሌክትሪክ ኃይል ሲያገኙ በሚፈጥሩት ንዝረት የአቧራ ቅንጣቶቹ እንዲረግፉ ነው ያደረጉት፡፡

ራሱን በራሱ የሚያፀዳው መስታዉት ተቃራኒ ከሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ሲገናኝ የሚፈጠረው ንዝረት ብናኞቹን ይበትናቸዋል ነው የተባለው – በድረ ገጹ፡፡

ግኝቱ በስፋት አገልግሎት ላይ ለሚገኙ ከፀሀይ ኃይል መሰብሰቢያ የመስታዉት ንጣፎች፣ የተሽከርካሪ መስታዉት፣ በመስታዉት ለተሸፈኑ የችግኝ ማፍያ ወይም “ግሪን ሀውስ” እንዲሁም ለሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች ተፈላጊነቱ የጐላ መሆኑ ነው የተብራራው፡፡

አዲሱን ራሱን የሚያፀዳውን መስታዉትን የሰሩት ባለሙያዎች መስታዉቱ የኤሌክትሪክ ኃይል መስኩ ሲለቀቅ ወይም ማልሚያ ማጥፊያውን በመጫን ሲከፈት መስታዉቱ ላይ ለማረፍ የተጠጉ ቅንጣቶች እንደሚርቁም ባለሙያዎቹ አስረድተዋል፡፡

በመጨረሻም የመስታዉቱ ራሱን የማፅዳት አቅሙ 90 በመቶ መሆኑ መረጋገጡንም ነው ድረ ገጹ በማደማደሚያነት ያስነበበው፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የነሐሴ 12 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here