በኢትዮጵያ የግብር አጀማመር ከመንግሥታት አመሠራረት ጋር የተቆራኘ እንደሆነ ታሪክ ያስረዳል። በሀገራችን የግብር ሥርዓት በአፄ ዘርዓያዕቆብ ተጀምሮ በአፄ ኃይለ ሥላሴ አዋጅ ወጥቶለት ማሻሻያዎች እየተደረጉበት አሁን እስከደረስንበት ዘመን ተሻግሯል። በወቅቱ ግብር የሚከፈለውም በጉልበት ወይም አገልግሎት በመስጠት፣ በዓይነት፣ አልፎ አልፎ ደግሞ በገንዘብ እንደነበር ድርሳናት ያስረዳሉ። መንግሥት በሕግ እና በመመሪያ ተመስርቶ ከሕዝብ እና ከድርጅት ገቢ የሚያገኝበት ዋነኛ መንገድ ነው። ይህም ለሀገር ልማት የሚውል የሀብት ምንጭ ሆኖ ያገለግላል።
በሀገራችን በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት እና በታክስ ሕግጋት መሠረት መንግሥት የተለያዩ የግብር ዓይነቶችን በመጣል ገቢ ይሰበስባል። ዜጎች ቤታቸውን በማከራየት፣ ዕውቀታቸውን በመሸጥ፣ በሥራ እና በሌላ መንገድ ከሚያገኘው ገቢ በሕግ በተቀመጠው አሠራር እና ሕግ መሰረት ግብር ይከፍላሉ።
ግብር የመንግሥት የልማት እና የማኅበራዊ አገልግሎት ዕቅዶች ማስፈጸሚያ፣ የሀገር ሉዓላዊነት ማስከበሪያ፣ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ እና የኅብረተሰቡን የመልካም አስተዳድር ችግሮች መፍቻ አይነተኛ መሳሪያ ነው።
በመሆኑም በአማራ ክልል ግብር መሰብሰብ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመረዳት በተለያዩ አካባቢዎች ግብር ወቅቱን ጠብቆ በመሰብሰብ ላይ ይገኛል። ለአብነትም የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር በበጀት ዓመቱ ግብር በወቅቱ እየሰበሰበ መሆኑን አስታውቋል። የብሔረሰብ አስተዳድሩ ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ፈጠነ ጥላሁን የግብር ከፋዩ ግንዛቤ እንዲያድግ አስፈላጊ የሚባሉ የቅስቀሳ ሥራዎች እንደተከናወኑ አስረድተዋል። ቀድሞ መረጃ የመሰብሰብ እና የማጥራት ሥራም ተከናውኗል። ይህን ተከትሎም ሐምሌ 01 ቀን 2017 ዓ.ም የበጀት ዓመቱ የግብር አሰባሰብ ሂደቱ በይፋ የተጀመረ መሆኑን አንስተዋል።
ግብር በወቅቱ እና በአግባቡ ካልተሰበሰበ አዳዲስ እና የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እንቅፋት መሆኑን በማንሳት ያለ ግብር ልማት እንደማይመጣም አስረድተዋል። “ግብር መቼም ቢሆን መቼም አይቀሬ እና በወቅቱ እንኳን ባይከፈል ዕዳ ሆኖ እንደሚቀጥል” ለበኵር ጋዜጣ በስልክ ተናግረዋል።
የማኅበረሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ እና መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት ግብር መሰብሰብ ቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል። የተሰበሰበው ግብር ደግሞ ለደመወዝ፣ ለመሠረተ ልማት ግንባታ (ለመንገድ፣ ለትምህርት ቤት፣ ለጤና ጣቢያ፣ ለሆስፒታል፣ ለንፁህ መጠጥ ውኃ፣ ለድልድይ፣ ለቴሌኮም፣ ለኤሌክትሪክ ኀይል አቅርቦት) እና ለሌሎች አገልግሎቶች እንደሚውል ነው ያስረዱት። የግብር አሰባሰብ ሂደቱ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲከናወን ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሠራ መሆኑን የጠቆሙት መምሪያ ኃላፊው በአሠራሩ ቅሬታ ያለው ግብር ከፋይ ቅሬታውን የሚያቀርብበት መንገድ እንዳለም አመላክተዋል።
እንደ መምሪያ ኃላፊው ማብራሪያ የገቢ አሰባሰቡን የተሻለ ለማድረግ አሠራርን ማዘመን፣ ባለሙያዎችን ማሰልጠን፣ ደረሰኝ በአግባቡ እንዲቆረጥ ማድረግ፣ የታክስ ማስከፈያ ምጣኔን ማሻሻል፣ ነጋዴው ባለበት ሆኖ እንዲከፍል ማድረግ፣ ግብር ከፋዮችን በደረጃቸው ማስከፈል፣ የግብር ከፋዩን ግንዛቤ ማሳደግ እና ሌሎች በትኩረት እየተሰራባቸው ያሉ መሰረታዊ ጉዳዮች ናቸው።
በብሔረሰብ አስተዳደሩ በ2017 በጀት ዓመት ከመደበኛ ገቢ እና ከከተማ አገልግሎት ለመሰብሰብ ከታቀደው 3 ቢሊዮን 148 ሚሊዮን 643 ሺህ 494 ብር ውስጥ 1 ቢሊዮን 980 ሚሊዮን 840 ሺህ 495 ብር መሰብሰቡን አቶ ፈጠነ ተናግረዋል፡፡ ዕቅዱን ሙሉ ለሙሉ ማሳካት ያልተቻለውም በክልሉ የተከሰተው የሰላም እጦት መሆኑን በምክንያትነት አስቀምጠዋል። በገቢ አሰባሰብ ሂደቱ በርካታ ፈተናዎች እና ጫናዎች እንደነበሩም አስታውሰዋል። ሆኖም በ2017 በጀት ዓመት የተሰበሰበው ግብር ከ2016ቱ በ449 ሚሊዮን 86 ሺህ 116 ብልጫ እንዳለው አመላክተዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ገቢዎች መምሪያ በ2018 በጀት ዓመት ግብርን በተሻለ ሁኔታ ለመሰብሰብ ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቆ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አቶ ፈጠነ አስረድተዋል። ከእነዚህ ቅድመ ዝግጅቶች መካከል እያንዳንዱ ነጋዴ ከአንድ ወር በፊት የሚከፍለውን የግብር መጠን ቀድሞ እንዲያውቅ እና ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርግ የመረጃ መለዋወጥ ሂደት እንደነበር መምሪያ ኃላፊው ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱ 3 ቢሊዮን 551 ሚሊዮን 983 ሺህ 432 ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል።
በብሔረሰብ አስተዳደሩ 20 ሺህ 223 የደረጃ ሐ፣ 2 ሺህ 162 የደረጃ ለ፣ 1 ሺህ 639 የደረጃ ሀ በአጠቃላይ አርሶ አደሩን ሳይጨምር 24 ሺህ 24 ነጋዴዎች እንዳሉ ተናግረዋል። እነዚህም በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ እንዲከፍሉ እየተደረገ ነው። ለአብነትም የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች (ከ20 ሺህ 223ቱ ውስጥ) ከ17 ሺህ በላይ ግብራቸውን በወቅቱ መክፈላቸውን ተናግረዋል። እስካሁንም 202 ሚሊዮን 70 ሺህ 704 ብር ተሰብስቧል።
ነጋዴው ግብሩን በአካል ተገኝቶ አሊያም በሞባይል ባንኪንግ እንዲከፍል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም አቶ ፈጠነ ጠቁመዋል። 11 ወረዳዎች ማስከፈል የሚገባቸውን ግብር እያስከፈሉ ነው። ለአብነትም ዚገም፣ ቻግኒ፣ ጓንጓ እና እንጅባራ ከተማ በግብር አሰባሰቡ የተሻለ አፈፃፀም ያላቸው አካባቢዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ፋግታ ለኮማ እና ዳንግ ከተማ ዙሪያ በፀጥታ ችግሩ ምክንያት አፈፃፀማቸው ዝቅተኛ ነው።
መምሪያ ኃላፊው እንዳስታወቁት ግብር በወቅቱ አለመክፈል ለቅጣት እና ለወለድ ይዳርጋል። በመሆኑም ”ግብር እና ሞት የማይቀር ዕዳ ነው” እንደሚባለው ግብር ከፋዩ በወቅቱ የተጣለበትን ግብር በመክፈል ለተጨማሪ ወጪ እንዳይዳረግ አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የግብር ትምህርት እና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ታዘባቸው ጣሴ ለበኵር ጋዜጣ እንደገለፁት ግብር ለአንድ ሀገር እድገት መሰረታዊ ጉዳይ ነው። በክልሉ የሚገኙ ግብር ከፋዮች የንግድ ትርፍ ግብር፣ የሥራ ግብር፣ የከተማ አገልግሎት ግብር፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ እና ሌሎች የግብር ዓይነቶችን እንደሚከፍሉም ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
ቢሮው በ2017 በጀት ዓመት በክልሉ ከመደበኛ 56 ነጥብ 15 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ከከተማ አገልግሎት 15 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በድምሩ 71 ነጥብ 65 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ከመደበኛ 53 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ፤ ከከተማ አገልግሎት ገቢ 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በድምሩ 60 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። ሰሜን ሽዋ ዞን፣ ዋግኸምራ እና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደሮች፣ ደቡብ ወሎ እና ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ በክልሉ በግብር አሰባሰቡ ከፍተኛ አፈፃፀም ነበራቸው፡፡ በአንፃሩ ደብረ ማርቆስ፣ ጎንደር ከተማ፣ አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ደብረ ታቦር እና ደሴ ከተማ ዝቅተኛ አፈፃፀም ያስመዘገቡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። በክልሉ የተከሰተው የሰላም እጦት በገቢ አሰባሰቡ ላይ ጫና አሳድሮ እንደነበር አስረድተዋል።
ቢሮው በ2018 በጀት ዓመት ከመደበኛ ገቢ 84 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ከከተማ አገልግሎት 15 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ማከናወኑን አብራርተዋል። ከተሠሩ ሥራዎች መካከልም የግብር አሰባሰብ ሥርዓቱን ከተለምዷዊ አሠራር ለማውጣት ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር አዲስ የኤሌክትሮኒክስ ታክስ አሥተዳደር ሥርዓት (ኢ-ታስ የዲጂታል አሠራር) በማበልጸግ ወደ ሥራ መገባቱን ነው የተናገሩት፡፡
የግብር ከፋዮችን ሙሉ መረጃ ወደ መተግበሪያው (ሲስተሙ) በማስገባት የሚከፈለውን የገንዘብ መጠን ለግብር ከፋዮች ቤታቸው ሆነው በሞባይል መልዕክት እንዲደርሳቸው ያደርጋል ብለዋል፡፡ ግብር ከፋዮች መልዕክቱ ከደረሳቸው በኋላ በሞባይል ባንኪንግ ወይም በአካል በባንክ መክፈል እንደሚችሉ ገልጸዋል። መተግበሪያው (ሲስተሙ) የክልሉን የግብር አሰባሰብ የሚያሻሽል መሆኑንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ታዘባቸው ማብራሪያ አዲሱ አሠራር የመደበኛ እና የከተማ አገልግሎት ገቢ አሰባሰብ ሂደትን በማዘመን የሕግ ተገዥነትን ያሳድጋል፤ የአገልግሎት አሰጣጥንም ያሻሽላል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ የግብር ከፋዮችን እንግልት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ሊፈታ የሚችል መሠረት የተጣለበት ነው። የግብር ከፋዩን ረጅም ሰልፍ እና ወረፋንም ያስቀራል፡፡
ያነጋገርናቸው ግብር ከፋዮችም ያረጋገጡልን ይህንኑ ነው፡፡ ነዋሪነታቸው በባሕር ዳር ከተማ የሆኑት ግለሰቦች ለበኵር ጋዜጣ በሰጡት አስተያየት በየዓመቱ የአከራይ ተከራይ ግብር ይከፍላሉ፡፡ ሁሌም ፋይል (የግል ማህደር) ለማስወጣት፣ የሚጠበቅባቸውን የግብር ገንዘብ በባንክ ለመክፈል፣ ማዘዣ ለማጻፍ እና ክፍያ ፈጽሞ ደረሰኙን ከግል ማህደራቸው ጋር ለማያያዝ ከሳምንት ላላነሰ ጊዜ ይመላለሱ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በዚህ ዓመት ግን የሚከፍሉት የግብር መጠን በሞባይላቸው ስለደረሳቸው በቀላሉ ያለምንም እንግልት እና የጊዜ ብክነት ክፍያ መፈፀማቸው አስደስቷቸዋል፡፡
ኢ-ታስን (የኤሌክትሮኒክስ ታክስ አስተዳደር ሥርዓት) በተመለከተ ከአንድ ሺህ በላይ በየደረጃው ያሉ ፈፃሚዎችን ለማብቃት በክልሉ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች የተግባር ስልጠና መሰጠቱን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ ስለ አዳዲስ አሠራሮች የግንዛቤ ማስጨበጥ በሁሉም የገቢ ተቋማት ውጤታማ የንቅንቄ መድረኮች ተካሂደዋል። በመድረኮቹ ከግብር ከፋዮች፣ ከአመራሮች፣ ከአጋር እና ባለድርሻ አካላት፣ ከተቋሙ ባለሙያዎች ጋር ውይይት ተካሂዷል።
በክልሉ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር የንግዱን እንቅስቃሴ ማቀዛቀዙ፣ ግብር ከፋዮች እንደፈለጉ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው መሥራት አለመቻላቸው፣ በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ አንዳንድ አስመጭዎች ደረሰኝ ለመስጠት ፈቃደኛ አመሆናቸው፣ ግብር ከፋዮች ለሸጡት ዕቃም ሆነ ለሰጡት አገልግሎት ደረሰኝ አለመስጠታቸው፣ ማኅበረሰቡ ለገዛው ዕቃም ሆነ ላገኘው አገልግሎት ደረሰኝ የመጠየቅ ልምዱ በሚፈለገው ደረጃ አለመሆኑ እና ሆን ተብለው የሚፈፀሙ የታክስ ስወራ በገቢ አሰባስቡ ላይ ተግዳሮቶች መሆናቸውን አብራርተዋል።
ዳይሬክተሩ ሐሳባቸውን ሲያጠቃልሉ ግብር በአግባቡ በመሰብሰቡ ለማኅበረሰቡ አስፈላጊ የመሠረተ ልማቶችን ለማሟላት አቅም የሚፈጥር መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የነሐሴ 12 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም