አፍሪካ ከሌላው ዓለም በተለየ መልኩ ከዕድገት ወደ ኋላ ለምን ቀረች? የሚለው ጥያቄ ውስብስብ እና ዘርፈ ብዙ ነው። የአህጉሪቱን የዕድገት ጉዞ የገቱት የታሪክ፣ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የፖለቲካ እና የአካባቢ ሁኔታዎች ጥምረት እንጂ የአንድ ነጠላ ጉዳይ ብቻ አይደለም። አፍሪካ ሰፊ ናት፤ 54 ሀገራት አሏት:: ከአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን በላይ ሕዝብ እና የሚያስደንቅ የባህል፣ የቋንቋ እና የመሬት አቀማመጥ ባለቤትም ናት:: ታዲያ አፍሪካ በሰዎች ዘንድ ስትታሰብ ቀድሞ የሚመጣው ድህነቷ ነው::
በአፍሪካ እንዳታድግ ተጽእኖ ከፈጠሩት መካከል በጣም ግልፅ እና ገላጭ ከሆኑ ምክንያቶች አንዱ የመልካዓ ምድራዊ አቀማመጧ ነው። አህጉሪቱ ግዙፍ ናት፤ 30 ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎ ሜትር ትሸፍናለች:: ይህም ከእስያ ቀጥሎ ከዓለም ሁለተኛዋ ትልቋ አህጉር ያደርጋታል። ይሁንና የአፍሪካ ሰፊው ክፍል በረሃማ ነው:: 60 በመቶ የሚሆነው ግዛቷ በሰሃራ እና በካላሃሪ በረሃዎች የተሸፈነ ነው። እንዲሁም በርካታ ቦተዎቿ ወጣ ገባ የበዛበት በመሆኑ በግብርናው ዘርፍ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ላለመቻሏ እንደ አንድ ምክንያት ይጠቀሳል::
ኢንዲፔንደት (independent.co) ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው ብዙውን ጊዜ የሰው ልጅ መገኛ ተብላ የምትታወቀው አፍሪካ ድህነቷን ታሪክ ያላደረጉ ባልጠቀሙ የተፈጥሮ ሀብቶች የተሞላች አህጉር ናት። እንደተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (እ.አ.አ 2024) መረጃ በዓለም ላይ እጅግ ድሀ ከሚባሉት ከ46ቱ ያልበለጸጉ ሀገራት መካከል 33ቱ የሚኖሩባት የዓለም ድሃ አህጉር ሆና ቀጥላለች። እንደ ዓለም ባንክ መረጃ ከ1960ዎቹ ወዲህ ከአንድ ነጥብ ሦስት ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጭ እርዳታ ቢለገሳትም ድህነቷ አሁንም ቀጥሏል።
ሌላው ሊንክኢዲን (linkedin.com) ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው ለአፍሪካ ዕድገት መጓደል ትልቅ ምክንያት የሆነው የቅኝ ግዛት መዘዝ ነው። ከ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ጀምሮ እስከ 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት በአውሮፓ ኃያላን ቅኝ ግዛት ሥር ነበሩ:: ይህ ጊዜ ከ60 እስከ 80 ዓመታት ድረስ የዘለቀ ነው። የቅኝ ግዛት መዘዞች እጅግ በጣም ብዙ እና በጣም ጎጂ ነበሩ:: ቅኝ ገዥዎች ለመሰረተ ልማትም ሆነ ለተቋማት ልማት መዋዕለ ነዋያቸውን ፈሰስ ሳያደርጉ ከአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት አሟጠው ወደ ሀገራቸው ወስደዋል።
የአውሮፓ ኃያላን የዘፈቀደ ድንበሮች የአህጉሪቱን የዘር እና የባህል ክፍፍል ግምት ውስጥ አላስገቡም። በዚህም እስከ ዛሬ ድረስ የቀጠለ ውጥረትና ግጭት ፈጥሯል። ለምሳሌ በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን መካከል ያለው ድንበር ወይም እንደ ናይጄሪያ እና ሩዋንዳ ያሉ ሀገራት ውስጥ ያለው ውጥረት ሁሉም በቅኝ ግዛት ውሳኔዎች ላይ የተመሰረተ የድንበር አከላለል ውጤት ነው። ይህ ለአፍሪካ ሕዝብ ማሕበራዊ ትስስር ትኩረት አለመሰጠቱ በሀገራቱ መካከል አለመረጋጋት እና ግጭት እንዲፈጠር አስተዋጽኦ አድርጓል:: ይህም ለዕድገቷ የበለጠ እንቅፋት ሆኗል።
በተጨማሪም ከነጻነት በኋላ ብዙ የአፍሪካ ሀገራት የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሥርዓትን ሳይዘረጉ ቀርተዋል። የቅኝ ገዢ ኃይሎች ሆን ብለው በሀብት ማውጣት ላይ ያማከለ እንጂ ራሳቸውን የሚደግፉ ኢንዱስትሪዎችን አልፈጠሩም።
የአፍሪካ ሀገራት ነፃነታቸውን ሲያገኙ ወደ ዘመናዊ ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የሚያስችላቸውን አስፈላጊው መሠረተ ልማት፣ ዕውቀትና ተቋም ሳይኖራቸው ነበር። በዚህ ምክንያት ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ነፃነታቸውን ካገኙ በኋላ የተረጋጋ መንግሥት ለመገንባት፣ በትምህርት ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ወይም መሠረተ ልማት ለማስፋፋት ቢታገሉም አመርቂ ውጤት አላገኙም።
ለአብነትም በቤልጄየም ቅኝ ግዛት ስር የነበረችው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም ድሃ ከሆኑ ሀገራት መካከል ትመደባለች። የዓለም ባንክ የ2023 (እ.አ.አ) ሪፖርት እንደሚያመላክተው 63 በመቶ የሚሆነው ሕዝቧ በቀን ከሁለት ነጥብ 15 ዶላር ባነሰ ገንዘብ ኑሮውን የሚገፋ ነው። የመልካም አስተዳደር ጉድለት እና ሙስና አሁንም ድረስ የሀገሪቱ ከባድ ፈተናዎች ናቸው። በ2023 በወጣው በትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የሙስና አስተሳሰብ ጠቋሚ መረጃ መሰረት በዓለም ዙሪያ ከተዘረዘሩት 30 ሀገራት ውስጥ 18 የአፍሪካ ሀገራት በዝርዝሩ የተካተቱ ሲሆን ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎም አንዷ ናት። ይህ ሙስና አስፈላጊ የሆኑ ሀብቶችን የሚያሟጥጥ ከመሆኑም በላይ ዕድገትን ይገታል:: ለምሳሌ ናይጄሪያ በ1960 ነፃነቷን ካገኘችበት ጊዜ አንስቶ በሙስና ምክንያት 582 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር ገደማ እንደተመዘበረች ተዘግቧል። ሙስና የሕዝብን አመኔታ ከማበላሸቱም በላይ የውጭ መዋዕለ ንዋይን ያግዳል:: ባለሀብቶችን እንደ ትምህርት እና የጤና አገልግሎት ካሉ ወሳኝ መስኮች ያርቃል።
ሌላው አፍሪካ በድህነት እንድትዘፈቅ ካደረጓት ምክንያቶች መካከል እርዳታ ተጠቃሽ ነው:: አፍሪካ በ2021 እ.አ.አ 54 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር የልማት እርዳታ አግኝታ ነበር። አፋጣኝ እርዳታ የሚያስፈልግ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ በራስ የመተማመን መንፈስ ከማግኘት ይልቅ ጥገኛ መሆንን ያበረታታል። ለምሳሌ ማላዊ እ.አ.አ. በ2022 37 በመቶ የሚሆነውን በጀቷን የበጀተችው ከእርዳታ ባገኘችው ገንዘብ እንደነበር የአይ ኤም ኤፍ መረጃ ያሳያል።
እ.አ.አ በ2023 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀው በ2050 የአፍሪካ ሕዝብ ቁጥር በእጥፍ ወደ ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይገመታል። ይህ የሕዝብ ቁጥር መጨመር ለኢኮኖሚ ዕድገት ዕድል የሚያመጣ ቢሆንም ሥራ አጥነትን ይዞ ይመጣል የሚል ስጋትም አለ::
ኢንተርናሽናል ሌበር ኦርጋናይዜሽን በ2023 እንዳስታወቀው (ILO) በደቡብ አፍሪካ እና በናይጄሪያ ከ30 በመቶ በላይ የወጣቶች ሥራ አጥነት አለ። እንደ ዓለም ባንክ መረጃ ደግሞ አፍሪካ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የጉልበት ሠራተኛ ወደ ሥራ ለማስገባት በየዓመቱ 20 ሚሊዮን ሥራ አጥ ዜጎችን የሚያሳትፍ የሥራ ዕድል መፍጠር ያስፈልጋታል። ይሁንና አህጉሪቱ ይህን የሥራ ክፍተት ሳትሞላ በማህበራዊ አለመረጋጋት እና በድህነት ንረት አደጋ ላይ ትገኛለች።
ሌላው የአንድ ሀገር ዕድገት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክተው ትምህርት እንደሆነ ቢታወቅም በአፍሪካ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራበት አይደለም:: ሂውማን ራይትስ ዎች እንዳስታወቀው በአፍሪካ በተያዘው ዓመት( 2025) ዕድሜያቸው ከ6 እስከ 18 የሚሆኑ 98 ሚሊዮን ሕፃናት እና ወጣቶች ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው። ይህ የትምህርት ክፍተት አህጉሪቱ ለኢንዱስትሪ ዕድገት እና ፈጠራ አስፈላጊ የሆነ የተካነ ሠራተኛ የማፍራት አቅሟን ያደናቅፈዋል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ እንዳስታወቀው አህጉሪቱ ከዓለማችን የማዕድን ክምችት ውስጥ 30 በመቶ እና 65 በመቶ አርሶ አደሮች ቢኖሯትም አሁንም ችግር ላይ ትገኛለች። ሀብቷ ብዙ ጊዜ ለሙስና፣ ለግጭት እና ለኢኮኖሚ አለመረጋጋት ሲዳርጋት ይስተዋላል::
ለአብነትም በአህጉሪቱ ውስጥ ትልቋ የነዳጅ አምራች የሆነችው ናይጄሪያ እ.አ.አ ከ1960 ወዲህ ከ340 ቢልዮን በላይ የአሜሪካ ዶላር የነዳጅ ዘይት አገኝታለች፤ ሆኖም የዓለም ባንክ እንደገለጸው ከ40 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝቧ ከድህነት ወለል በታች ነው።
ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎም 24 ትሪሊዮን ዶላር የማዕድን ሀብት ቢኖራትም በሂውማን ዴቨሎፕመንት ጠቋሚ መረጃ መሰረት ከ191 ሀገራት መካከል 179ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
ዩ ኤን ዲ ፒ እ.አ.አ በ2023 ይፋ ባደረገው መረጃ በአፍሪካ አብዛኛውን ጊዜ የውጭ ሀገር ኩባንያዎች የተፈጥሮ ሀብት ማውጣትን ሥራ በበላይነት ይቆጣጠራሉ:: ትርፋቸውንም ወደ ሌላ ሀገር ስለሚልኩ ለአካባቢው ኢኮኖሚ አነስተኛ ጥቅም ነው እያስገኙ የሚገኙት።
ሌላው አፍሪካን ወደ ኋላ ካስቀሯት መካከል የአየር ንብረት ለውጥ ተጠቃሽ ነው:: አፍሪካ ከዓለም አቀፉ ግሪንሃውስ ጋዝ ልቀት ውስጥ ሦስት በመቶውን ብቻ የምታዋጣ ቢሆንም በአየር ንብረት ለውጥ ውጤት በእጅጉ ትሠቃያለች። በተደጋጋሚ በተለያዩ የአህጉሪቱ ሀገራት የተከሰቱ ድርቅ እና የጎርፍ መጥለቅለቅ ማሳያዎች ናቸው:: የዓለም ባንክ እንዳስታወቀው እ.አ.አ እስከ 2050 ድረስ 86 ሚሊዮን የሚሆኑ አፍሪካዊያን ከአየር ንብረት ጋር በተያያዙ ተፅእኖዎች ምክንያት ወደ ሌላ አካባቢ ሊሰደዱ ይችላሉ። 60 በመቶ የሚሆኑት በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ ሰዎችም ለአደጋ ይጋለጣሉ። የአየር ንብረት ለውጥ የምግብ አለመረጋጋት እንዲባባስ ያደርጋል፣ የውኃ እጥረት ያስከትላል እንዲሁም በሀብት ላይ የሚፈጠሩ ግጭቶች እንዲባባሱ ምክንያት ይሆናል:: ይህ ደግሞ ዕድገትን ያደናቅፍል።
እ.አ.አ. በ2015 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ ድህነትን ለማስወገድ የሚያስችሉ እና ለዘላቂ ልማት የሚያግዙ ግቦችን አስቀምጧል። ግቦቹም በ2030 በጤና፣ በትምህርት፣ በፍትሕ፣ በኢኮኖሚ ልማት እና በአየር ንብረት ለውጥ መሻሻል ላይ የሚያተኩሩ ናቸው። ሆኖም በዚህ ወቅት አፍሪካ እነዚህን ግቦች ለማሳካት መንገድ ላይ አይደለችም። ማሳያ የሚሆነውም አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ የከፋ የድህነት ደረጃ ላይ መገኘቷ ነው::
በተጨማሪም ለአፍሪካ ድህነት አስተዋፅኦ ካደረጉ ቁልፍ ምክንያቶች አንዱ በየጊዜው የሚያጋጥማት ከፍተኛ የሆነ የተማረ ሰው ኃይል ፍልሰት ነው። ይህም አህጉሪቱን ለልማት የሚያስፈልገውን የተማረ የሰው ካፒታል አሳጥቷታል። የሰለጠነ ሠራተኞች ፍልሰት በአካባቢው ኢንዱስትሪዎች ላይ ተጽእኖ በማሳደር የቴክኖሎጂ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገቶችን ያግዳል። ለአንድ ሀገር የሰለጠነ እና የተማረ ማሕበረሰብ መኖር ለዘላቂ ዕድገት ወሳኝ ነው።
በርካታ ተግዳሮቶች ያሉበት የአፍሪካ አህጉር የውጪ ብድርም ዕድገቷን ከገቱባት ምክንያቶች ውስጥ ተጠቃሽ ነው:: የአይ ኤም ኤፍ 2023 መረጃ እንደሚያሳየው የአፍሪካ ሀገራት በየዓመቱ 22 ቢሊዮን ዶላር እዳ ይከፍላሉ። ይሁን እንጂ በአፍሪካ ያለው የተትረፈረፈ ሀብት እና የወጣት ሕዝብ መበራከት የአህጉሪቱን የድህነት ታሪክ ሊቀይር ይችላል የሚሉ ተስፈኞች አሉ::
(ሳባ ሙሉጌታ )
በኲር የነሐሴ 12 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም


