“የመሃል ሜዳ ሆስፒታል 30 በመቶ እንኳ ግብዓቶች አልነበሩትም”

0
49

በሰሜኑ ጦርነት ከፍተኛ ውድመት የደረሰባቸውን የአጣዬ እና የወልድያ ሆስፒታሎችን ከሌሎች አጋሮቻቸው ጋር ሆነው ድጋፍ አድርገዋል:: በኮቪድ 19 ወቅትም ለሀገራቸው ድጋፋቸው አልተለየም፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተራድኦ ድርጅት ሆስፒታል አማካኝነት በመላው ሀገራችን የሚሰራጭ 40 ጫማ (feet) ኮንቴነር የሕክምና ቁሳቁስ እና አልባሳት ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻቸው ጋር በመሆን እረድተዋል:: ለመሃል ሜዳ አጠቃላይ ሆስፒታል እና በሰሜን ሸዋ ለሚገኙ አምስት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ217 ሚሊዮን በላይ ብር የሚያወጡ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርገዋል::

የተወለዱት በሰሜን ሸዋ ዞን መሃል ሜዳ (መንዝ መናገሻ) ነው:: ትምህርታቸውን እስከ ሰባተኛ ከፍል ድረስ በመሃል ሜዳ ተከታትለዋል:: ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ከተማ አቅንተው እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ተምረዋል:: የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ አውስትራሊያ ሄደዋል:: በዚያ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በዱር እንስሳት ፎቶግራፍ ሳይንስ እና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማዕድን ጂኦሎጂ ይዘዋል፤ የዚህ ሳምንት የበኩር አንግዳችን የተሸሪክ ተመራማሪ እና ጸሐፊ፣ ፕሮፌሽናል የዱር እንሰሳ እና የተፈጥሮ የፎቶግራፍ ባለሙያ እንዲሁም ጂኦሎጂስት ልዑል ሰገድ እርገጤ ናቸው:: በማኅበረሰብ ግልጋሎት እና በጎ አድራጎት ዙሪያ ያደረግነው ቆይታ እነሆ:: መልካም ንባብ!

ወደ በጎ አድራጎት እና የማኅበረሰብ ግልጋሎት ሊገቡ ያስቻለዎት ምክንያት ምንድን ነው?

የሰው ልጅ ሲያድግ በአካባቢው የሚያየው ነገር ይኖራል:: ሌላ አካባቢ ደግሞ ሄዶ ሲኖር የተለየ ነገር ያያል:: የሚያየውን ነገር የአደገበት አካባቢ እንዲኖረው ይፈልጋል፤ መለወጥ የሚፈልጋቸው ነገሮችም ይኖራሉ:: ከሀገር ከወጣሁ ከሁለት ዓመት በኋላ አባቴ ነው የመጀመሪያውን ጥያቄ፡የጠየቀኝ፤ እሱም ሰው ስትሆን የአያቶችህን ትምህርት ቤት የመሃል ሜዳ ሆስፒታል እንዲሁም ማኅበረሰብህን እና ሀገርህን ኢትዮዽያን አትርሳ፤ በአቅምህ እርዳ ነበር ያለኝ:: እሱም በአቅሙ ለአካባቢው የአስፓልት መንገድ እንዲሠራ፣ ለከተማው የ24 ሰዓት የመብራት አገልግሎት እንዲያገኝ፤ በመንገድ፣ ሆስፒታል፣ ትምህርት እና የመሳሰሉት እንዲሟሉ ከኅብረተሰቡ ጋር ሆኖ ይታገል ነበር፤ በአጠቃላይ የአካባቢውን እና የመሃል ሜዳን እድገት እና ለውጥ ይመኝ ነበር:: እሱ ማድረግ የሚገባውን ነገር አድጎ ጨርሶ አልፏል።

እኔም አባቴ የሚያደርገው ነገር ከልጅነት ጀምሮ ከኔው ጋር አድጎ ስለነበር ዛሬ ላይ እንድደርስ አድርጎኛል:: ሆስፒታሉን እና በአካባቢው ያሉ ትምህርት ቤቶችን (በመሃል ሜዳ እና ዙሪያው)  በሚቻለኝ አቅም ሁሉ እንድረዳ ጠይቆኛል:: በተለይ ሆስፒታሉ በኅብረተሰቡ እና በዎርልድ ቪዢን የተገነባ እንደሆነ፣ አባቴም በዚህ ሂደት ውስጥ ዋነኛውን ድርሻ ይዞ እንዳሠራ ፣ የሕክምና መሣሪያዎች ከውጪ ሲመጡ በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ እንደነበር እና እቃዎቹም ከሆስፒታሉ ሳይደርሱ ወደ ሌላ አካባቢ በጉልበት እንደተወሰዱ አባቴ ይነግረኝ ነበር:: ይህ ቁጭት እንዳለ ሆኖ ከሀገር ስወጣ ደግሞ የማየው በጎ ነገር ሁሉ በሀገሬ እንዲኖር እመኝ ነበር::

የመሃል ሜዳ አጠቃላይ ሆስፒታል ብዙ ነገሮች የሚጎሉት ነበር:: የሕክምና መሣሪያዎች አልተሟሉለትም ነበር:: አልጋዎቹ ጥቂት እና ካርቶን የተነጠፈባቸው ነበሩ:: በአጠቃላይ ተገቢውን አገልግሎት ለማኅበረሰቡ እየሰጠ አልነበረም::

የስረደጅ የመጀመሪያ ደረጃ ሙሉ ሳይክል ት/ቤት ደግሞ ዓመታዊ በጀቱ 4000 ብር ብቻ ነበር፤ ይህም ለቾክ እና ለሰሌዳ ማጥፊያ መግዣ ብቻ የሚመደብ ነው:: መንዝ ጌራ ምድር ወረዳ የሚገኙ ሌሎች አራት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም እንደዚሁ ተመሳሳይ ችግር ነበረባቸው፤ ትምህርት ቤቶቹ በጣም ከከተማ የራቁ ናቸው፤ አይደለም ለመኪና ለበቅሎ እንኳን ጥሩ የሚባል የጠጠር መንገድ የላቸውም፤ አራቱም ት/ቤቶች ከ200- 500 ብር ነው ዓመታዊ በጀታቸው:: በዚህ ምክንያት መምህራንም ተማሪዎችም ይቸገሩ ነበር:: ይህንን ሀገር ቤት እያለሁ አስተውል ነበር:: ነገር ግን ምንም ጠንካራ ሠራተኛ ብሆን ይህን ሥር የሰደደ ችግር ለመፍታት አቅም አልነበረኝም::

ለመሃል ሜዳ አጠቃላይ ሆስፒታል እና ለሌሎች በአካባቢው ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች ድጋፍ አድርገዋል፤ ድጋፉን እንዴት ጀመሩት? የነበረውስ ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?

አውስትራሊያ ገብቼ ሁለት ዓመት እንደቆየሁ ትምህርቴን እየተማርኩ ጥሩ ሥራ ያዝኩ:: አባቴ ይለኝ የነበረው ነገር አልተረሳኝም፤ ቃል የዕምነት እዳ ስለሆነ:: በዚህ በውጭ ካሉ የአካባቢው ተወላጆች ጋር ምን ማድረግ እንችላለን በሚል ውይይቶችን አካሄድኩ:: አብዛኛው ሰው በራሱ ሕይወት ላይ ነው ማተኮር የሚፈልገው:: ስለሆነም ተባባሪ ማግኘት ከባድ ነበር:: በዚህ ምክንያት ብቻየን መንቀሳቀስ ጀመርኩ::

በመጀመሪያ መሃል ሜዳ እና አካባቢው ቀዝቃዛ ነው፤ ሞቀ ከተባለ እስከ 16 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ነው፤ በአንዳንድ ወቅት ደግሞ ከዜሮ በታች ስድስት ይወርዳል፤ የመሃል ሜዳ አጠቃላይ ሆስፒታል ማዋለጃው ማሞቂያ የለውም፤ በዛ ወቅት የተወለዱ ሕጻናት በብዛት ይሞታሉ:: የማዋለጃ እና የታካሚ አልጋዎች በቁጥር ትንሽ እና እንደ ድሃ ልብስ የተቀደዱ ነበሩ:: ጉዳዩ መፈታት የነበረበት በመንግሥት ነበር፤ መንግሥት አልደረሰለትም:: በሰሜኑ ጦርነትም ጉዳት ደርሶበታል፤ ተዘርፏል፤ ኮርኒስ ሳይቀር ቀዳደው ነው የሄዱት:: ስለሆስፒታሉ እና መሟላት ስላለባቸው ነገሮች የሆስፒታሉን አመራሮች ሳማክር፣ በፎቶግራፍ የተደገፉ መረጃዎችን ላኩልኝ::

በቅድሚያ የማዋለጃ ክፍል ማሞቂያ መሣሪያዎችን ነው መሰብሰብ የጀመርኩት:: ቀጥሎም ሌሎች የሕክምና መሣሪያዎችን ለማሰባሰብ የዘርፉ ዕውቀት ያስፈልጋል:: በመሆኑም ቤተሰቦቼ የመሃል ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ነርሲንግ ዳይሬክተር ከሆኑት ከአቶ መርከብ ባልከው ጋር አስተዋወቁኝ:: ሆስፒታሉ 30 በመቶ እንኳ ግብዓቶች አልነበሩትም፤ ይሄንን በፎቶ አስደግፈው መረጃ ሰጡኝ:: በባዶ ነበር ያንን ትልቅ ስም የያዘው:: በዋናነት ከአቶ መርከብ ጋር እየተመካከርን የሚያስፈልጉትን ቁሳቁሶች ሰበሰብኩ::

ለመሃል ሜዳ አጠቃላይ ሆስፒታል ድጋፍ ከተደረጉት የህክምና ዕቃዎች መካከል ዳይሌሲስ ማሽን ብዛት ሦስት፣ ዲጂታል ኤክስሬይ ዊዝ ፍሮሎስኮፒ ብዛት አንድ፣ አንስቴዥያን ማሽን ብዛት ሰባት፣ የሕፃናት ሟሞቂያ ብዛት 41፣  ዘመናዊ የአምቡላንስ አልጋ ብዛት ሁለት፣ ኢንፊውቭን ማሽን ብዛት 11፣ አይ.ሲ.ዩ ማሽን ብዛት 14፣ ደረጃቸውን የጠበቁ በኤሌክትሪክ በቻርጅ እና በሪሞት የሚሠሩ አልጋዎች ብዛት 43፣ አልትራሳወንድ ብዛት አምስት፣ አይ .ሲ.ዩ. ማሽን ብዛት አምስት፣ ኢኮ እና ኢሲጅ ማሽን ብዛት ስድስት፣ ዊልቸር፣ ልዩ ልዩ ክራንች፣ አልጋዎች፣ ደረጃ ሰባት (seven star) የህሙማን አንሶላ፣ ዘመናዊ ፍራሾች እና ሌሎች ብዛት ያላቸው የህክምና እቃዎች ይገኙበታል::

ትምህርት ቤቶቹን በተመለከተ ደግሞ እኔ ምንም ከተማ ብማርም ገጠር ላይ ያለውን ችግር አውቃለሁ፤ እሱን መሠረት አድርጌ ምን ምን ድጋፍ ትፈልጋላችሁ ብዬ ጠየቅኩ:: ትምህርት ቤቶቹን ለማገዝ ሀሳብ ሳቀርብላቸው አላመኑኝም ነበር፤ የምነግራቸው ነገርም ቅዠት ነበር የሚመስላቸው:: እንኳን በገጠሩ በከተማ ባሉ ትልልቅ ትምህርት ቤቶችም መደረግ የማይችሉ ነገሮችን ነበር ሳነሳላቸው የነበረው:: የማይሆን ተስፋ እንደማላሲዛቸው ነግሬ አግባባኋቸው:: “ስናይ እናምናለን” የሚል አቋም ነበራቸው:: ከእነሱ ጋር እየተመካከርኩ አስፈላጊ ግብዓቶችን መሰብሰብ ቀጠልኩ:: እነሱ ጠይቀውኝ የነበረው እንደ ቾክ፣ እስክርቢቶ፣ ደብተር ከተቻለ ጫማ እና ልብስ ነበር:: እኔ ያሰብኩት እንደ ዲጂታል ላይብራሪ ያሉ ትልልቅ ነገሮችን ነው:: ይህ ለእነሱ ሕልም ነው:: በእርግጥ በአብዛኛው የሀገራችን ክፍል ይህ እንደ ቅዠት ሊቆጠር ይችላል:: ትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ ያሉ ሰዎች ሳይቀር ጉዳዩን ሲሰሙ ትንሽ ተገርመው ነበር፤ ምክንያቱም አካባቢው እጅግ በጣም ከከተማ ሩቅ ነው::

በፎቶ የምልክላቸውን ቁሳቁሶች እያሳየሁ፣ ሞራል እየሰጠሁ ቆየሁ:: መብራት ስለሌለው የፀሐይ ኃይል ማመንጫ አሟላሁ፤ ከዚያ ዴስክቶፖች፣ ላፕቶፖች፣ ፕሮጀክተር፣ ቴሌቪዢን ሞኒተር (እስከ ስምንተኛ ክፍል ላለው ትምህርት ቤት) ነጭ ሰሌዳ፣ የስፖርት ቁሳቁስ አሰባስቤ አስረከብኩ:: ለተማሪዎችም መለያ ልብሶችን አቀረብኩ::

በአጠቃላይ ለመሃል ሜዳ አጠቃላይ ሆስፒታል፣ ለስረደጅ  የመጀመሪያ ደረጃ ሙሉ ሳይክል ትምህርት ቤት እና ሌሎች ተጨማሪ አራት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ217 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደርጓል:: ይህም ሌሎች ወጪዎችን ሳይጨምር ነው::

ድጋፉን የሚያሰባስቡበት መንገድ ምን ይመስላል?

ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ተራድኦ ድርጅት ሥር የቤተክርስቲያኗም ልጆች ሆነ ከቤተክርስቲያን ውጪ ያሉ ልጆች ተሰባስበን 40 ጫማ ኮንቴነር መድሐኒት በኮቪድ ወቅት ልከን ነበር:: በኋላ በሰሜኑ ጦርነት ውድመት ለደረሰባቸው ለአጣዬ እና ለወልድያ ሆስፒታሎች ድጋፍ አድርገናል:: ይህ ተሞክሮ ነበረኝ::

የመሃል ሜዳ አጠቃላይ ሆስፒታልን እና ትምህርት ቤቶቹን ግን በግሌ ነው ድጋፉን የማደርገው:: አብዛኞቹን ቁሳቁሶች በጨረታ ነው የምገዛቸው:: አንዳንድ ጊዜ እርዳታ እጠብቃለሁ:: ብዙ መርዳት የሚፈልጉ ሰዎች እና ድርጅቶች አሉ:: ነገር ግን ይሄን የአወኩት በግሌ ከ90 ከመቶ በላይ ቁሳቁሶቹን ገዝቼ ከጨረስኩ በኋላ ነው:: ከጅቡቲ ቃሊቲ ከዚያ እስከ መጨረሻ መዳረሻው ቁሳቁሶቹን ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ አውጥቶ ያጓጓዘልኝ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ነው::

እቃው ወጪው ብቻ ሳይሆን መሰብሰቡም ብዙ ውጣ ወረድ አለው:: ከአንድ ግዛት ወደ ሌላ ግዛት  በመኪና ከ1700 ኪሎ ሜትር በላይ እየተጓዝኩ ነበር የምሰበስበው፤ ምክንያቱም የአውሮፕላን ወጪ እጅግ ውድ ስለሆነ ማለት ነው፤ ደርሶ መልስ 3400 ኪሎ ሜትር እያሽከረከርኩ እጓዝ ነበር:: ሀገሩ ሰላም፣ መንገዱ ጥሩ፣ የምነዳቸው መኪናዎች ምቹ ስለሆኑ እንጂ 3400 ኪሎ ሜትር ቀላል አይደለም፤ ከኢትዮጵያ ግብጽ መጓዝ እንደማለት ነው:: በዚህ መንገድ  ተሰብስበው ነው ለህዝባችን አገልግሎት እንዲሰጡ የተደረገው::

በዚህ ሁሉ ሂደት የገጠሙ ችግሮች ምን ምን ናቸው?

አድካሚ ረዥም ርቀት ተጓጉዞ ቁሳቁሶችን መሰብሰቡ አንዱ አስቸጋሪ ነገር ነበር:: ትልቁ ችግር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ከመጣ በኋላ ነው:: ሁሉም ተቋማት የየራሳቸው መመሪያ እና አሠራር አላቸው:: ነገር ግን አብዛኞቹ ተቋማት የተንዛዛ እና ምቹ ያልሆነ ቢሮክራሲ አላቸው:: እቃዎቹ ጅቡቲ ደርሰው የመጨረሻ መዳረሻቸው ለመግባት ስምንት ወራት ነው የፈጀባቸው:: በስምንት ወራት ውስጥ ብዙ አገልለግሎቶች መስጠት እየቻሉ በአየር ላይ ቆይተዋል::

ትልቁ ችግር የነበረው ጉምሩክ ላይ ሳይሆን የኢትዮጵያ ምግብ እና መድሃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ላይ ነበር:: እቃዎቹ ያገለገሉ ስለነበሩ ባለሥልጣኑ ባለው መመሪያ ምክንያት ነው ችግሩ የተፈጠረው:: ተነጋግሮ ነገሮችን በአጭሩ መፍታት እየተቻለ ነገር ግን ሞራል የሚነኩ እና ተነሳሽነትን የሚያሳጡ ሁኔታዎች ነበሩበት:: ጥቅም የመፈለግ አዝማሚያዎችም ነበሩ፤ የተቋሙ ኃላፊዎች በመጨረሻ ስለ ጉዳዩ ከሰሙ በኋላ ወዲያው ተፈጣጥኖ አልቋል:: ትምህርት ሚኒስቴር እና የጤና ሚኒስቴር ላይ ምንም ችግር አልገጠመኝም:: ጉምሩክ ላይም የተወሰነ ቢሆንም ብዙ ችግር አልነበረም፤ ነገር ግን ከቀበሌ ጀምሮ ኃይለኛ ማስረጃ ይጠይቃሉ:: ለወደፊቱ ብዙ ነገሮችን ተምሬበታለሁ::

በሌላ በኩል የመሃል ሜዳ እና አካባቢው ማኅበረሰብ “የሆስፒታሉ አምባሳደር ይሁን!” የሚል ሀሳብ አንስቶ ከቃለ ጉባዔ ጋር ጉዳዩ ወደ ክልል ተልኮ ነበር:: ነገር ግን እስካሁን ምላሽ አላገኘም:: ለሆስፒታሉ የበለጠ ድጋፍ ለማግኘት እና ተዓማኒነትን ለማግኘት እውቅናው አስፈላጊ ነው:: የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም የእውቅና ደብዳቤ ሊሰጠኝ የክልል ማረጋገጫ ተጠይቆ እስካሁን ምላሽ አልተሰጠውም፤ ይህ በፍጥነት ሊፈጸም ይገባል እላለሁ::

መንግሥት በውጪ ያሉ ሀገራቸውን መርዳት የሚፈልጉ ሰዎችን የሚያማርሩ አሠራሮችን ማስተካከል አለበት:: ሰው ተማሮ ከዚህ በኋላ በጭራሽ ብሎ መውጣት የለበትም:: ይህ ከሆነ በዕውቀት፣ በገንዘብ፣ በቁሳቁስ እና በሌሎች ሀብቶች ሀገራቸውን ለመርዳት፣ ሕዝባቸውን ከችግር ለማላቀቅ የሚፈልጉ ብዙ ዜጎች አሉ:: ሀገራችንም በደንብ ካገዝናት ከችግሯ የምትላቀቅበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም::

ለወደፊት ያሰቡት ነገር ካለ?

እንደ ፈጣሪ ፈቃድ በሆስፒታሉ እና በትምህርት ቤቶቹ እንዲሁም በሌሎች የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተለያዩ ነገሮችን ለማድረግ በእቅድ ይዣለሁ:: ከታች ያሉ ተቋማት ወደ ላይ የሚያድጉባቸውን ሥራዎች ለመሥራት አስቤያለሁ፤ ለምሳሌ የጤና ኬላዎችን ወደ ጤና ጣቢያ ከዚያም ወደ ክሊኒክ እያለ ወደ ላይ ማሻሻል አንዱ ዓላማዬ ነው:: ከመሃል ሜዳ አልፎ ወረዳ እና ክልል ላይ ለመሥራት እቅዱ አለ፤ እየተነጋገርናቸው ያሉ አካላትም አሉ::

“ገሎ መፎከር ይሻላል”  እንደሚለው የሀገሬ ሰው መሬት ላይ ወርዶ በተግባር ሲሠራ ቢወራ ይሻላል ብየ ነው እንጂ ብዙ ነገሮች አሉ:: በታሪክ፣ በሃይማኖት፣ በባሕል፣ በዱር ሃብት፣ በተፈጥሮ ሃብት፣ በመልክዓ ምድር እና በሌሎች ዘርፎች ላይ እንደ ክልል ብቻ አይደለም እንደ ሀገር ብዙ ነገር እያሰብኩ ነው:: ትልልቅ ፕሮጀክቶች አሉ:: እነዚህ ፕሮጀክቶች መሬት ላይ ይወርዳሉ ብየ አስባለሁ::

ሥራዎች ሲሠሩ ለብቻ ከሚሆን በትብብር ቢሆን የበለጠ ስኬታማ ይሆናሉ:: ሀገራቸውን እንዴት ላግዝ ሕዝቤን እንዴት ልርዳ ብለው የሚያስቡ ብዙ በውጪ እና በሀገር ውስጥ ያሉ ሰዎች አሉ:: ከእነሱ ጋር በመጣመር የተሻለ ሥራ መከወን ይቻላል:: መንግሥት ቢሮክራሲውን ክፍት ካደረገው የበለጠ ለመሥራት ሀሳቡ አለ:: ሀገራችን ትልቅ አቅም እና ሀብት አላት:: አብዛኞቹ ሀገራት ላይ ብትሄድ ብዙ ነገር አንድ ላይ አታገኝም፤ ኢትዮጵያ ግን ባሕሉን፣ መልክዓ ምድሩን፣ ታሪኩን፣ ሃይማኖቱን እና ሌሎች እሴቶችን በአንድ ላይ የምታገኝባት ሀገር ናት:: ለምሳሌ ኬንያ ብትሄድ የዱር እንስሳትን እና የማሳይ ጎሳን ባሕል አይተህ ነው የምትመለሰው:: ግብጽ ብትሄድ ፒራሚድ ነው የምታየው:: እስራኤል ብትሄድ ታሪክ እና ሃይማኖት ወይም ቴክኖሎጂ ነው የምታየው:: ኢትዮጵያ ግን ከዚህ በተጻራሪ ሁሉንም ነገር የምታገኝባት ናት:: ይህ በክልል የታጠረ አይደለም፣ በመላው ኢትዮጵያ ነው ያለው::

የፀጥታው ሁኔታ ችግር ከመፍጠሩ ውጪ ለመሥራት ምቹ ሁኔታ አለ:: ፀጥታው ከተስተካከለ ትልልቅ ፕሮጀክቶች አሉ፤ የሚታተሙ መጻሕፍትም ዝግጅታቸው ተጠናቋል:: እስከ 30 ዓመት የፈጁ በተለያዩ መስኮች ያተኮሩ ጥናቶችም ይቀርባሉ:: እነዚህ ሲወጡ ለሀገር ዕድገት የራሳቸውን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ:: በውጪም በሀገር ውስጥም ላሉ አቅሙ ላላቸው ኢትዮጵያዊያን ሕዝባችንን ከድህነት፣ ከመሃይምነት፣ ከስደት እና ሌሎች ችግሮች ተባብረን እናውጣው ስል መልዕክቴን አስተላልፋለሁ::

የሚያመሰግኗቸው አካላት ወይም ሰዎች ካሉ?

በቅድሚያ ሁሉን ላደረገ ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባው፤ በመቀጠል በዚህ ውጣ ውረድ ውስጥ እስከመጨረሻው ከጎኔ ላልተለዩኝ ለሃይማኖት አባቶቼ እና ለመላው ቤተሰቤ ላቅ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። በተጨማሪ ለዶ/ር አየለ ተሾመ የኢትዮዽያ ጤና ሚኒስቴር ዴታ፣ ለአቶ ጣልባቸው በቀለ የመንዝ ጌራ ምድር ዋና አስተዳዳሪ፣ ለአቶ ጌታቸር ባይሳሳው የመሃል ሜዳ ከተማ አስተዳዳሪ፣ ለአቶ ወርቅነህ ዘውዴ የመሃል ሜዳ አጠቃላይ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ፣ ለአቶ ወንድወሰን አድማሴ የመንዝ ጌራ ምድር ወረዳ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና በየደረጃው ለአሉ የሚንስቴር፣ የወረዳ፣ የክልል እንዲሁም የዞን መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች ላቅ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። በመጨረሻም ዶ/ር ቴዎድሮስ ክፍለ ዮሃንስ በደ/ብርሃን ዩንቨርስቲ የአስራት ወልደየስ ጤና ሳይንስ ካምፓስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ እንዲሁም ጠቅላላ ሐኪም፣ አቶ ማሙየ መንገሻ የደ/ብርሃን ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን፣ አቶ መርከብ ባልከው የመሃል ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል  ነርሲንግ ዳይሬክተር  እና አቶ ሽፈራው ግርማ የስረደጅ የመጀመሪያ ደረጃ ሙሉ ሳይክል ት/ቤት ርዕሰ መምህር፣ ላደረጉልኝ የማማከር እገዛ ማመስገን እፈልጋለሁ::

ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን!

እኔም አመሰግናለሁ!

 

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የነሐሴ 12 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ

በhttp:// www.ameco.et/Bekur

በቴሌግራም – https://t.me/bekur123 ላይ ማግኘት ይችላሉ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here