ለትውልድ የተተወ ርስት

0
38

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የስፖርት ጋዜጠኛ ነው፤ ስፖርት በህትመት ሚድያ እንዲዘገብ ያደረገ እና ቀዳሚ የቀጥታ ስርጭት አስተላላፊ ጋዜጠኛ ጭምር ነው። ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች በዓለም አቀፍ መድረክ ተደማጭነት ሊኖራቸው እንደሚችል በተግባር ያሳየ፣ ሙያውን እንደነብሱ የሚወድ፣ ታላላቅ የአውሮፓ የስፖርት የመገናኛ አውታሮችን በብቃት ያገለገለ፣ ከኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ እስከ ዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ፣ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እስከ አፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በብቃት እና በእውቀት ያገለገለ ሰው ነው- ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ።

የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኝነት ሲነሳ እንደ ንጋት ኮከብ ደምቆ የሚታየው ይህ ስም ነው። እርሱ ጋዜጠኛ ብቻ አልነበረም፤ ግዙፍ ራሱን የቻለ ተቋም ጭምር እንጂ። በሺዎች ለሚቆጠሩ የስፖርት ጋዜጠኞች መፈልፈልም ምክንያት ነው። የስፖርት ጋዜጠኝነት አባት ብቻ ሳይሆን የማያልቀው የስፖርት ፍቅር ምልክትም ነው።

ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ የተወለደው በአዲስ አበባ ከተማ በ1927 ዓ.ም ነው። ታሪኩ የሚጀምረውም የአዲስ አበባ ልብ በነበረችው ፒያሳ ነው። በእርሱ ዘመን ስፖርት በተለይ እግር ኳስ የከተማው ወጣቶች መነጋገሪያ እና መዝናኛ ነበር። ይህም ወደፊት ሊጓዝበት ላሰበው የህይወት መስመር መሰረት እንደጣለለት የፒያሳ ልጅ በሚለው መጽሐፉ ያትታል።

ፋቅሩ ኪዳኔ የጋዜጠኝነትን ሙያ ከመቀላቀሉ በፊት የሰውነት ማጎልመሻ ትምህርት መምህር ሆኖ ማገልገሉን የግል የታሪክ ማህደሩ ያስነብባል። በ1943 ዓ.ም ኢትዮጵያ እና ሱዳን ያደረጉት ጨዋታ ታላቁን የስፖርት ጋዜጠኛ ወልዷል። በአዲስ አበባ ስቴዲየም ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጨዋታዎችን ለማድረግ ቀነ ቀጠሮ ተይዟል። በአቶ ይድነቃቸው የሚመራው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከማስታወቂያ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ጨዋታውን በሬዲዮ በቀጥታ ስርጭት ለማስተላለፍ ወስነዋል።

በዚያ ዘመን ህዝቡ የስፖርት  መረጃ የሚደርሰው ከጋዜጣ በአጭር ዘገባ ወይም ከሰው አፍ ይሰማ እንደነበር  የኒውስ ሴንትራል ዶት አፍሪካ መረጃ ያስነብባል። ታዲያ ይህን ጨዋታ በብቃት ያስተላልፈዋል ተብሎ እምነት የተጣለበት ደግሞ ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ ነው። ጉምቱ የስፖርት ሰው ማይክራፎን በእጁ በመጨበጥ በኢትዮጵያ ስፖርት እና የመገናኛ ብዙኃን ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል። ስመጥሩ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ የስፖርት ጋዜጠኝነት ምን ያህል ኃይል እንዳለው ያሳየበት ታሪካዊ ቀን እንደነበረ መረጃዎች አመልክተዋል።

ከዚያም በኋላ የኢትዮጵያ ማስታወቂያ ሚኒስቴር የቀጠረው የመጀመሪያው የስፖርት ጋዜጠኛ መሆን ችሏል። በኢትዮጵያ ራዲዮ የስፖርት ፕሮግራሞችን መሥራት እና የቀጥታ ስርጭቶችን ማስተላለፍ ጀመሯል። ፕሮግራሙ ሳምንታዊ ሲሆን የሀገር ውስጥ ውድድሮችን ውጤት፣ ስለተጫዋቾች መረጃ እና ዓለም አቀፍ የስፖርት ክስተቶችን ያካተተ ነበር።

በወቅቱ የነበሩት አዲስ ዘመን እና ኢትዮጵያ ሄራልድ ለስፖርቱ ትኩረት አይሰጡም ነበር። ታዲያ ፍቅሩ ኪዳኔ እነዚህ ጋዜጦች የራሳቸው የስፖርት ዓምድ እንዲኖራቸው አድርጓል። የመጀመሪያውን የስፖርት ዓምድ ጽሁፍንም በማዘጋጀት ማበረታታት ችሏል። በሀገራችን የስፖርት ዜና በህትመት ሚዲያ ቦታ እንዲያገኝ ብርቱ ትግል በማደረግ በር ከፍቷል።

ስፖርቱ ባግባቡ ካልተመራ እና ካልተደራጀ የሚዘገብ ነገር እንደማይኖር ጠንቅቆ የተረዳው ጋዜጠኛ ፍቅሩ በስፖርት አስተዳደር ውስጥም በንቃት ተሳትፏል። ከሀገር ውስጥ እስከ ዓለም አቀፍ የስፖርት ተቋማትን በብቃት እና በእውቀት  ማገልገሉን የኢትዮጵያ ራዲዮ መረጃ ያመለክታል። የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ በመሆን አሻራውን አስቀምጦ አልፏል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና ብስክሌት ፌዴሬሽንን በመምራት አደረጃጀቱን እና የውድድር ስርዓቱን ማዘመኑንም መረጃዎች ይነገሩናል። ሀገራችን በ1960 እና 1968 ዓ.ም የአፍሪካ ዋንጫ ስታዘጋጅ ቁልፍ ሚና ከተጫወቱት መካከል አንዱ ነው።

የስፖርት ጋዜጠኝነትን ተቋማዊ ማድረግም ችሏል። የስፖርት ጋዜጠኝነት እንደ ሙያ እንዲታወቅ፣ የጋዜጠኞች መብት እና ጥቅም እንዲከበር እንዲሁም ሙያዊ ስነ ምግባር እንዲዳብር ጋዜጠኞችን በአንድ ማህበር አሰባስቧል። የመጀመሪያው የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዝዳንት በመሆንም አገልግሏል። እንደ አፈ ታሪክ የሚነገረው የታላቁ የስፖርት ጋዜጠኛ ገደል በሀገር ውስጥ ብቻ የተወሰነ አልነበረም። በኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኝነትን መስረት ከጣለ እና ተቋማዊ እንዲሆን ካደረገ በኋላ በዓለም አቀፍ የስፖርት ጋዜጠኝነት ታሪክም አሻራውን አስቀምጧል።

እንግሊዘኛ እና ፈረንሳይኛ ቋንቋን እንደ አፍ መፍቻው አማረኛ አቀላጥፎ መናገሩ በአውሮፓ ታላላቅ የስፖርት መገናኛ ብዙኃን ዘንድ በብርሃን እንዲፈልግ አድርጎታል። በኦሎምፒክ ኮሚቴ እና በአውሮፓ ታላላቅ የብዙኃን መገናኛ አውታሮች ተጽዕኖ ፈጣሪ ሲሆን ጊዜ አልፈጀበትም። በዓለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አማካኝነት የሚታተመውን “ኦሎምፒክ ሪቪው” የተሰኘውን መጽሔት ዋና አዘጋጅ ሆኖ ሠርቷል። ይህን ቦታ በዓለም ላይ ላሉ የስፖርት ጋዜጠኞች በቀላሉ የማያገኙት ቦታ ሲሆን የጋዜጠኛውን ብቃት እና ተቀባይነት እንደሚያሳይ የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ድረገጽ ያስነብባል።

ከዚህ ኃላፊነቱ ጎን ለጎን ለፈረንሳይ ዝነኛ የስፖርት ጋዜጦች ሌኪፕ (L’Equipe) እና ፍራንስ ፉትቦል (France football) የአፍሪካ ስፖርት ጉዳዮች ዘጋቢ በመሆን አገልግሏል። በአውሮፓውያን ዐይን ይታይ የነበረውን የአፍሪካ ስፖርት ገጽታ በትክክለኛ መረጃ እና ጥልቅ ትንታኔ በመቀየር ትልቅ ሥራ ሠርቷል። እንደ ቢቢሲ (BBC) ፣ ቪኦኤ ((VOA) እና ዶይቼ ቬለ (DW) ላሉ ግዙፍ የመገናኛ አውታሮች በቋሚነት አገልግሏል።

ፍቅሩ ኪዳኔ ለአፍሪካ ስፖርት የነበረው ፍቅር እና ተቆርቋሪነት በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF) ውስጥ በነበረው የረጅም ጊዜ አገልግሎት አሳይቷል። በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF) ውስጥ በልዑክነት እና ለቀድሞው የካፍ ፕሬዝዳንት ለነበሩት ኢሳ ሃያቱ የቅርብ አማካሪም ሆኖ መሥራቱን መረጃዎች አመልክተዋል። የአፍሪካ እግር ኳስ በዓለም መድረክ ጠንካራ ድምጽ እንዲኖረው፣ የአፍሪካ ዋንጫ ተወዳጅ እንዲሆን እና አፍሪካ በዓለም ዋንጫ ያላት ተሳትፎ እንዲጨምር ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ኮንትኔታል ስፖርት (Continental sport) የተሰኘ ጋዜጣ በእንግሊዘኛ እና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎች የሚታተም የራሱን ወርሃዊ መጽሔት በማቋቋም የአፍሪካን ስፖርት ታሪክ እና ተግዳሮቶች ለዓለም አሳውቋል። ለዚህ ጥረቱም የአፍሪካ ስፖርት እውነትኛ አምባሳደር የሚል ስም ተሰጥቶታል። በአጠቃላይ ለስፖርቱ ላበረከተው አስተዋጽኦ በርካታ ሽልማቶችን ያገኘ ሲሆን የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበር (ኢ.ስ.ጋ.ማ) በ2010 ዓ.ም የህይወት ዘመን ተሸላሚ ክብር መሰጠቱ የሚታወስ ነው።

ዕውቁ ጋዜጠኛ ዛሬ ላይ በሀገራችን በሺዎች የሚቆጠሩ የስፖርት ጋዜጠኞችን፣ የስፖርት አስተዳዳሪዎችን እና  አፍቃሪዎችን ፈጥሯል። ወጣት የስፖርት ጋዜጠኞችን በመምከር፣ የዕውቀት ሽግግር በማድረግ እና በማበረታታት ብዙዎች በሙያቸው እንዲጸኑ ማድረግ ችሏል።

እርሱ ጋዜጠኛ ብቻ አልነበረም፤በደራሲነትም ይታወቃል።  ታሪክን በብዕሩ የመቅረጽ ልዩ ችሎታ ነበረው:: “የፒያሳ ልጅ” የተሰኘ መጽሐፉ የደራሲነት ችሎታውን ያሳየበት ድንቅ መጽሐፍ መሆኑን ብዙዎች ይመሰክሩለታል። በ1960ዎች እና 70ዎች የአዲስ አበባ ከተማን ህይወት፣ የወጣቱን ባህል፣ ሙዚቃ እና የፋሽኑን ዓለም በህያው ቃላቶቹ ሰልሎልናል። “የስፖርት ጨዋነት ምንጮች” የተሰኘ መጽሐፍም በማሳተም ስፖርት ከውድድር ባለፈ ሰብዓዊ እሴቶችን ማስተማሪያ መድረክ መሆኑን አሳይቷል።

የቀድሞው ጋዜጠኛ ለሙያው ፍቅር እና ክብር የነበረው፣ ለወጣቶች አርአያ የሆነ፣ ቀጥተኛ እና ሀቀኛ ሰው ነበር። አንጋፋው ጋዜጠኛ በተወለደ በ87 ዓመቱ በ2015 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቶናል። ድምጹ ግን በኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ ውስጥ ለዘላለም ያስተጋባል፤ በብዕሩ ያኖረው አሻራም በትውልዶች እየተነበበ ይኖራል።

ለመጀመሪያ ጊዜ ስፖርት በጋዜጣ እንዲዘገብ ያደረገውን እና የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ የሰፖርት ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔን እኛም በጋዜጣችን ሠላሳኛ ዓመት በዓል እንዲህ ዘክረነዋል::

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የነሐሴ 19 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here