ግን ምን ሆነን ነው?

0
34

ዐዉቀነዉም ይሁን ሳናዉቀዉ የሀገራችን ቋንቋ፣ ባህል፣ ጥበብ እና ሌሎች የማንነት መለያዎቻችን  እየተሸረሸሩ በመሄድ ላይ ናቸው::  ኢትዮጵያ ቅኝ ያልተገዛች፣ ሉአላዊነቷን አስከብራ፣ ታፍራ እና ተከብራ የኖረች ሀገር ናት:: ይሁንና አሁን አሁን ዜጐቿ በአውሮፓውያኑ ባህል፣ ቋንቋ፣ አልባሣት፣  ሌሎች ወግ እና ልማዶች በእጅ አዙር ቅኝ ተገዥ ለመሆን ዳርዳር እያሉ ይመስላል። እናም ቆም ብለን ራሳችንን መጠየቅ እና ለጥያቄያችን መልስ መፈለግ ከምንገደድበት ደረጃ ላይ ደርሰናል::

እኛ ኢትዮጵያውያን የራሣችን የሆነ ባህል፣ ቋንቋ አመጋገብ እና የምግብ ዝግጅት፣ ህክምና፣ አለባበስ እና አልባሳት፣ አጊያጊያጥ፣ የእደ ጥበብ ውጤቶች፣ ቤት እና የቤት ቁሳቁስ አሰራር ደንብ እና ሥርዓት ባለ ሀብቶች እንዲሁም ባለ ፀጋዎች ሆነን ሳለ ያሉንን  ሐብቶች በአግባቡ ባለመጠቀም እና ባለማስፋፋት ይልቁንም አንዳንዶቹ እንዲጠፉ ቀሪዎቹ ደግሞ እንዲደበዝዙ እና እንዲረሱ ብሎም በሌላ ሀገር ባህል እና ወግ እንዲተኩ መንገዶችን ሁሉ የዘረጋን የሩቅ ናፋቂዎች ሆነናል። ግን ምን ሆነን ነው?

እኛ ኢትዮጵያውያን የራሳችን ቋንቋ፣ ፊደል እና የአፃፃፍ ስልት ያለን ሆነን  እያለ ይህን ሐብት በመተው የውጭ ሀገር ቋንቋ ናፋቂ እና አድናቂ ሆነናል:: ልጆቻችንም የራሳቸውን ቋንቋ ችላ ብለው እንግሊዝኛ እና ሌሎች ቋንቋዎችን እንዲማሩ የማንከፍለው ዋጋ የለም:: ተምረው በቋንቋው መናገር ሲችሉ ደግሞ ልጆቻችን በዕውቀት የመጠቁ አድርገን በመቁጠር ደስታችን ወሰን የለውም። ግን ለምን?

ለመሆኑ የትኛው ሀገር ነው የራሱን ቋንቋ ረስቶ እና አጥፍቶ በሌላ ሀገር ቋንቋ የተጠቀመ እና የተከበረ? እኛ የናቅነውን ቋንቋችንን ሌሎች ሀገራት አክብረውት በየዩኒቨርሲቲዎቻቸው ማስተማር መጀመራቸውን እያየን እኛ ከቋንቋችን ይህን ያህል ለመራቅ የፈለግነው  ለምንድነው?

በየስብሰባው እና በጽሑፎቻችን መካከል የውጭ ቋንቋ ካልደባለቅን ዐዋቂ የሆንን የማይመስለን አላዋቂዎች፤ ቋንቋ የማንነት መገለጫ እና መከበሪያ መሆኑን የረሣን ዝንጉወች ሆነናል። ግን ምን ሆነን ነዉ?

በየጊዜው የሚተላለፉ እና በየቦታዉ የሚሰቀሉ ልዩ ልዩ ማስታወቂያዎች ጉራማይሌነት ደግሞ በእጅጉ ገራሚ እና አሳቃቂ ናቸው:: ከሰሞኑ በከተማችን የአሸንዳ በአል ልዩ ዝግጅት ለማዘጋጀት ያቀደ አንድ ድርጅት እንዲህ ብሎ ማስታወቂያ ሰቅሎ አየሁ፤ እስኪ እናንተም አንብቡት፤

X… Event presenter

Vip singer  and D J    ……..

መግቢያ ዋጋ 300 ብር

Vip – 500  ብር

ይላል:: እና ከዚህ ማስታወቂያ ምን ታዘባችሁ ? እኔማ የየትኛው  ሀገር መግባቢያ ይሆን የሚል ጥያቄ አጭሮብኛል።  ባህላዊ በዓል እንዲህ ነወይ የሚከበረው? ግን ምን ሆነን ነው?

የሌሎች ሃገራት ዜጎች የራሳቸው የሆነውን ሁሉ ጠብቀው እና ሣይጐድል በማስቀጠል ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር እና እንዲያድግ፣ ከዛም አልፎ ወደ ሌሎች ሀገራት በመላክ እና በማስተዋወቅ ባህላቸውን እና ቋንቋቸውን  እየሸጡ ይገኛሉ:: እኛስ?

እኛማ የውጭ ሀገር ባህል እና ቋንቋ ናፋቂ፣ ፈረንጅ አድናቂ ሆነናል:: ግን ምን ሆነን ነው?

እኛማ ቀደምት የሆኑ ጥበቦቻችን እየተዉን በዉጭ ሀገራት ዕዉቀት እና ባህል ለመኖር  የፈለግን እዚህ እዚያ የምንዉተረተር ብኩን ትዉልዶች እየሆንን ነዉ። ግን ለምን?

ከተዉናቸዉ ጥበቦች መካከል  አንዱ ከጥንት ጀምሮ ቅድመ አያቶቻችን ይጠቀሙበት የነበረውን እና አያሌዎች የተፈወሱበትን የባህል ሕክምና ሳይቀር አናንቀን እና አጣጥለን እነሱ የኛን መነሻ አድርገው ዘመናዊ መድኃኒት ሲያመርቱ እኛ ግን የራሳችንን ጥለን በነሱ ዘመናዊ ሕክምና ብቻ ተጠቃሚ ዜጐች ሆነናል:: ግን ለምን? በእርግጥ ዘመናዊ ህክምና አይጠቅምም፤ ጉዳትም  አለዉ እያልሁ  እንዳልሆነ ትረዱኛላችሁ።

የባህል ሕክምናችን ቀደምት አባቶቻችን እና እናቶቻችን እንደ አሁኑ ዘመናዊ ሕክምና ሳይጀምር በራሣቸው ጥበብ እና ዕውቀት በመታገዝ ፈዉሰዋል፤ አድነዋል። ዐዋቂዎቹ አባቶቻችንም መድኃኒቶችን ለመድኃኒትነት ያገለግላሉ ብለዉ  የእፅዋት አይነቶችን በመለየት ከእፅዋቱ ቅጠል፣ ግንድ እና ስራ ስር፣ ከእንስሳት ተዋፆዎች እንዲሁም ሌሎች የሰብል እና የማእድን አይነቶችን በመቀመም በህመም የተቸገረን ፈዉሰዋል፤ በአደጋ የተሰበረን ሰዉ ጠግነዋል።

ባህላዊ ህክምና ከሰዉ ልጆች  አልፎ እንስሳትም በበሽታ ሲያዙ ይድኑበታል:: ይህ ዕውቀታቸው ዛሬም ድረስ ያለ ቢሆንም እኛ ግን ላለመጠቀም የማንጠቅሰው ምክንያት የማናሳብበው ሰበብ የለም:: ግን ምን ሆነ ነዉ?  በእርግጥ በባህላዊ ሕክምና ዘርፍ የሚጠቀሱ ችግሮች እንዳሉ ቢታወቅም  ለምሣሌ፡- የመጠን፣ የልኬት እና ሌሎች ሁኔታዎች ጥያቄ ቢያስነሱም ህመም ፈዋሽነታቸውን ግን መካድ አይቻልም::

ያደጉ ሀገራት ሳይቀር በባህል ሕክምናው ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሰዋል:: እንዲያውም በአንዳንድ ሀገራት ከዘመናዊ ህክምናው ጐን ለጐን በእኩል ደረጃ፣ ቦታ እና እውቅና ተሰጥቶት ሕዝቡም በሚመርጠው ህክምና  ማለትም በባህላዊ ወይም በዘመናዊ እንዲታከም እድሎች ተፈጥረውለታል:: እኛስ?

እኛማ በአጉል ዘመናዊነት ይሁን አላዊቂነት የተነሳ የዘርፉን ጥበብ በቅጡ የማናውቅ በርካቶች ነን:: ግን ለምን ማንስ ይሆን ተወቃሹ? ህክምናው በኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን አገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ ባይቋረጥም እንደ አጀማመሩ ግን አላደገም፤ ተገቢው ድጋፍ እና ጥበቃም አልተደረገለትም፤ ለሕዝቡ ተገቢ የሆነ መረጃ እንዲኖረውም አልተደረገም:: ግን ለምን?

ከተማችን ውስጥ “ጊዜዋ” የሚባል መድኃኒት ቤት አየሁና በሥራ አጋጣሚ ያገኘኋቸውን ሀኪም ጊዜዋ ምንድን ነው በማለት ጠየቅኋቸው:: የሰጡኝን ምላሽ እንደወረደ ላስነብባችሁ፤ “ጊዜዋ በየጓሯችን የምትገኝ ትንሽ ተክል (እፀዋት)ስትሆን  ለብዙ የድንገተኛ ህመም ፈውስ የምትሰጥ ተክል ናት:: የተክሏን ቅጠል በመቀንጠስ እና በመጨመቅ ለታመመው ሰው በተለይም ለህፃናት በማጠጣት ከህመሙ በፍጥነት ማዳን ይቻላል:: እንዲያውም የኛ ማህበረሰብ እንዲህ  ይላል፤

ምነው ሞተ ልጅሽ!

ጊዜዋ የለም ወይ ደጅሽ!

ሲባል አልሰማሽም ወይ በማለት ታዝበውኛል:: የባህል ህክምና የላቀ ዕውቀት የሚጠይቅ እና ለበሽታዎችም ፍቱን መሆኑን ሕዝቡ ግንዛቤው ቢኖረውም መጠቀም ላይ ግን ገና ይቀረናል:: ግን በባህላዊ ህክምናን ሌሎች ሀገራትም ከዘመናዊ ሕክምና ጐን ለጐን በስፋት ይጠቀሙበታል፤ በበሳይንስም ተቀባይነት እንዳለው ይነገራል:: አንዳንድ ሀገራትም ዘርፉን አበልፅገው ትልቅ ደረጃ ላይ አድርሰውታል:: በህክምና ተቋማታቸውም ሁለቱንም ህክምናዎች በማሳለጥ ሕዝቡ በሚመርጠው እንዲታከም ዕድል አመቻችተውለታል::  እኛስ?

ሌላዉና ሀገራችንን በውጭ ሀገራት ከሚያስተዋውቋት መካከል አንዱ ደግሞ  የራሳችን የምግብ አዘገጃጀት እና ምግቦች ናቸው:: የምግብ ዝግጅት የየአካባቢውን ማህበረሰብ ባህል፣ ወግ፣ ልማድ እና ልዩ ዕውቀት የሚያሳይ ተግባር ነው:: በሀገራችን በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የየራሳቸው የሆነ ጣእም፣ ሽታ እና ቀለም የሚፈጥሩ የምግብ አዘገጃጀቶች አሏቸው:: በተለይም በምግብ ዝግጅቱ ላይ ምግብን በማጣፈጥ፣ ቀላል፣ ምቹ እና ተስማሚ እንዲሆን፣ እንዲሁም ሳይበላሽ ለረዥም ጊዜ እንዲቆይ  ለማድረግ የሰሩት “ምርምር “ ግን ልዩ ግርምትን ይፈጥራል:: አድናቆትን እና ክብርንም ያሳጣል። እኛስ ዛሬ እንዴት ነዉ ምግብ የምናዘጋጀዉ? ይዘቱን እና ጥቅሙን ተረድተን ነው? ወይስ በዘፈቀደ ቀደምቶቻችን ልዩ ልዩ ምግብና መጠጥን ለማዘጋጀት የተጠቀሙበት “ኬሚስትሪ”  እና ያለ ማቀዝቀዣ (ያለፍሪጅ) ሳይበላሹ እንዲቆዩ የሚያደርጉበት ልዩ ጥበብ ደግሞ ከሌላው ዓለማት ለየት ያለ ሆኖ ይገኛል።

ከእለት እለት እና ከዘወትራዊ ምግቦች በተረፈ ጊዜን፣ ጉልበትን  እና ብክነትን ለመቀነስ ምግቦች አንዴ ተዘጋጅተው ረዘም ላለ ጊዜ እንዲቆዩ የሚያስችለው ጥበብ ለትውልድ ቢሸጋገር ብክነትን ከመከላከል በመለስ ጤናማ ማህበረሰብን ለመፍጠር እገዛው የጐላ ነው በማለት አስበዉ እና ተጠበዉ ይህን ምርምር ፈጥረዋል::

ቀደምት አያቶቻችን ልጆቻችው በኬሚካል ያልተበረዘ ምግብ እና መጠጥን በመጠቀም የጤና እክል እንዳይገጥመን በማሰብ ይህን ዕውቀት ፈጥረውልን ይነስም ይብዛ እስካሁንም እየተጠቀምንበት ነው:: የዛሬዎቹስ? ዛሬማ ለልጆቻችን የሚበጁ ተፈጥሯዊ ይዘታቸውን ያልለቀቁ ምግቦችን ከመስጠት ይልቅ የታሸጉ ምግቦችን፣  የታሸጉ ጭማቂዎችን፣ በኬሚካል የበለፀጉ ጣፋጮችን በመመገብ የዘመንን  ሆነናል:: ይህ ተግባራችንም ቀስ በቀስ እንደሚጎዳን የተለያዩ የስርአተ ምግብ ባለሙያዎች አስታውቀዋል:: እናማ አጉል  ዘመናዊነትን ትተን ከጓሯችን ጐመን፣ ድንች ከእንቁላል እና ሌሎች እህሎችን ተጠቅመን፣ ጭብጦ፣ ገንፎ፣ ቂጣ እና አጥሚት አዘጋጅተን ልንመገብ ይገባል:: የልጆች አመጋገብ በአካላዊ እና   አእምሯዊ ጤና ላይ የሚያስከትለውን  ዳፋ ለማወቅ ያስችል ዘንድ “ሀገርን በአንድ ሺህ ቀናት” የሚለውን የወ/ሮ  ፍሬ ዓለም ሽባባውን መጽሐፍ እንድታነቡ እጋብዛችኋለሁ::

የሀገራችን ምግብ እና መጠጦች በስሪታቸው ከኬሚካል የፀዱ በመሆናቸው እነሱን በመጠቀም ልጆቻችንን መመገብ፣ እኛም መመገብ ጠቀሜታው የላቀ ነውና የውጪው ምግብ ቢቀርብን መልካም ነው::

ሌላው የትዝብቴ ማጠንጠኛ ደግሞ አልባሳታችን ነው:: ኢትዮጵያውያኑ በራሳቸው ዕውቀት ልዩ ልዩ አልባሳትን በማዘጋጀት  የቀን፣ የሌሊት፣ የዘወትር፣ የበዓላት (የክት) ልብስ በማዘጋጀት ዘመናትን ተሻግረዋል:: ይነስም ይብዛ አሁን ላይ አልጠፉም:: አልባሳቱ በራሳቸው ባለሙያዎች በመሠራታቸው ደግሞ የኢትዮጵያውያን አልባሳት በዓለም ሕዝብ ዘንድ መታወቂያ እና መከበሪያ ሆነዋል:: ይሁንና ይህ መለያችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበረዘ እና እየደበዘዘ ዛሬ ላይ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በዘመናዊ አልባሳት እየተተካ ነው:: ግን ለምን?

የባህል አልባሳትን መልበስ ባህሉን ከማስቀጠሉ በተረፈ በሥራው ላይ የሚሳተፉ በርካታ ባለሙያዎችን ገቢ የሚያሳድግ የሀገርን ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት የሚያፋጥን ነውና ትኩረት ልናደርግበት ይገባናል:: ይህ የዘመናዊ አልባሳት ወረራም ከከተማው አልፎ በገጠሩ አካባቢም በእጅጉ እየተስፋፋ ነው። ግን ምን ሆነን ነዉ?

ምን ስለጐደለን፣ ምን ስለሆንን ነው ሁሌ የሌላ ሀገር ባህል ፣ምግብ፣ አልባሳት እና ሌሎችን የምንከተለው? ከኛ ምን ጐድሎ ይሆን? እነዚህ  ጉዳዮች ትዝብት ላይ የሚጥሉ ብቻ ሳይሆኑ እርምት እና ሥራ የሚጠይቁ ናቸውና የራሳችን የሆኑት እንዲቀጥሉ እኛ በግንባር ቀደምትነት የምርቶቹ ተጠቃሚዎች ልንሆን ይገባል:: ሌሎች እንዲገለገሉባቸውም ጠቀሜታቸውን እና ባለመጠቀማችን የሚፈጠረውን ጉዳት ማስረዳት ይኖርብናል:: አለበለዚያ  እንዲያው በከንቱ ያደገ ሀገር እንዲኖረን መመኘት፣  የተሻለ ኑሮ ለመኖር መሻት እና  መፈለግ የሚሳካ አይሆንምና ምን ሆነን ነው? ለምን? በሚል ራሳችን መጠየቅ፣ ፈጥነን ለለውጥ መነሳት ይኖርብናል::

(ብርቱካን አትንኩት)

በኲር የነሐሴ 19 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here