ልጆች እና ንባብ

0
29

ልጆች እንዴት ሰነበታችሁ? ክረምቱ እንዴት ነው? ልጆች በዚህ ጽሑፍ ለወላጆች እና ለእናንተ ለልጆች ንባብ ያለውን ፋይዳ እና እንዴት የማንበብ ልምድን ማዳበር እንደሚቻል እንነግራችኋለን::

ልጆች በህይወታቸው ስኬታማ እንዲሆኑ ከሚያሰፈልጓቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ እና መሠረታዊው ነገር የማንበብ ክህሎት ነው:: ጥሩ የንባብ ችሎታ ያላቸው ልጆች መጻሕፍትን በማንበባቸው ትምህርታዊ ጥቅም ከማግኘትም ባሻገር ለዕድሜ ልክ ስኬት የሚያስፈልጉ ክህሎቶችንም ያገኛሉ:: ንባብ የቃላት አጠቃቀምን ያዳብራል፣ የትኩረት ጊዜን ይጨምራል እናም ጠንካራ አስተሳሰብን ያበረታታል:: ንባብ ለልጆች የሚከተሉት ዋነኛ ጠቀሜታዎች አሉት::

ንባብ በዓይነ ሕሊና የመሣል ችሎታን ያሳድጋል- ለምሳሌ አንድ ታሪክ ስታነቡ የገጸ ባሕርያቱ ድምፅ ምን ዓይነት ነው? መልካቸው ምን ይመስላል? አካባቢውስ ምን ዓይነት ነው? ደራሲው አንዳንድ ፍንጮችን ይሰጠን ይሆናል። የቀረውን የሚሞላው ግን አንባቢው ራሱ ነው።

ንባብ መልካም ባሕርያትን ለማዳበር ይረዳል- ልጆች ሲያነቡ የማገናዘብ እና ችግሮችን የመፍታት ችሎታቸው ይዳብራል። በተጨማሪም ልጆች ለማንበብ ትኩረታቸውን መሰብሰብ ያስፈልጋቸዋል። እንዲህ ማድረጋቸው እንደ ትዕግሥት፣ ራስን መግዛት እና የሌሎችን ስሜት መረዳት ያሉ ባሕርያትን ለማዳበር ይረዳቸዋል።

ንባብ በጥልቀት የማሰብ ችሎታን ያዳብራል- አንድ ሰው በሚያነብበት ጊዜ፣ ደራሲው ሐሳቡን ያዋቀረበትን መንገድ ለመረዳት ቀስ ብሎ ማንበብ ይችላል፤ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜም መለስ ብሎ ያነበበውን ነገር ይከልሳል። እንዲህ ማድረጉ ያነበበውን ነገር ለማስታወስ እና ከትምህርቱ ጥቅም ለማግኘት ይረዳዋል

ልጆች የማንበብ ባህላቸውን እንዲያሳድጉ የሚረዱ ነጥቦች እንደሚከተለው ቀርበዋል::

  1. ለልጆች ምቹ እና ለንባብ የሚያነሳሳ በመጻሕፍት የተደራጀ የማንበቢያ ቦታን ማዘጋጀት
  2. ልጆች በቤት ውስጥ ማንበብ እንዲችሉ እና የበትኛውም የተመቻቸ ቦታ ላይ እንዲያነቡ ማበረታታት
  3. አርዓያቸው (ምሳሌያቸው) በመሆን በልጆች ፊት ማንበብ
  4. በማንበብ እና በመኖር ውስጥ እውነተኛ ግንኙነትን መፍጠር፤ ማንበብ ለሕይወታቸው ያለውን አሰፈላጊነት መንገር፤
  5. ለንባብ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን በቤት ውስጥ ማሟላት ከብዙዎቹ ጥቂቶች ናቸው::

ምንጭ፡- ላይፍ ሀክ ድረ ገጽ፡፡

 

ተረት

ጥንቸል እና ዝንጀሮ

ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ደቃቃ ጥንቸል፤ እህል ውሃ ፍለጋ በጫካ ውስጥ ስትዘዋወር፤  አንድ  ዝንጀሮ    ታገኛታለች:: ጥንቸሏ ግዙፍ ስላልሆነች በየቅጠላ ቅጠሉ ውስጥ እየተሹለከለከች መሄድ  እንደምትችል ዝንጀሮ ያውቃል:: ሆኖም አንድ ምክር ሊመክራት ፈልጓል::

 

“እመት ጥንቸል! የረዥም ጊዜ ወዳጅነታችንን መሰረት በማድረግ ምክር ልለግስሽ እፈልጋለሁ” አላት::

ጥንቸልም “ምን ዓይነት ምክር?” ስትል ጠየቀችው

ዝንጀሮም “ይህን ጫካ አትመኝው:: ሰሞኑን አዳኞች መጥተው ለአውሬ ማጥመጃ የሚሆን ትላልቅ ጉድጓድ ሲቆፍሩ እኔ ዛፍ ላይ ሆኜ አይቻቸዋለሁ:: ስለዚህ ጫካው እንደድሮው ሰላም መስሎሽ ወዲህ ወዲያ አትበይ”

ጥንቸልም “አመሰግናለሁ:: ወጥመዱን የሰሩት ለእኔ አይመስለኝም:: እንደ አንበሳ፣ እንደ ነብር፣ እንደ ዝሆን ላሉት እንጂ እንደኔ ቀጫጫ ለሆነ ፍጡር አይደለም:: በአጋጣሚ ጉድጓድ ውስጥ ብወድቅም መውጫ ብልሃት አላጣም!” ትለዋለች::

ዝንጀሮም “እንግዲህ የወንድምነቴን መክሬሻለሁ:: ብታውቂ እወቂበት” አላትና ሄደ::

ጥንቸል እየተዘዋወረች ቅጠል መበጠሷን ትቀጥላለች:: ጥቂት እንደሄደች ዝንጀሮ እንደፈራው አንድ በቅጠል የተሸፈነ ትልቅ ጉድጓድ ውስጥ ሳታስበው ትወድቃለች:: ጉድጓዱ በጣም ጥልቀት ያለው በመሆኑ በጭራሽ በቀላሉ ልትወጣ የምትችልበት አይደለም:: ስለዚህ አላፊ-አግዳሚውን እንዲያወጣት ለመለመን ተገደደች:: “እባካችሁ አውጡኝ? እባካችሁ እርዱኝ?” እያለች መጮህ ጀመረች:: ጠቃሚ ምክርን መስማት እና ተግባራዊ ማድረግ ከሚመጣ ችግር ያድናል የሚለውን  ከተረቱ እንማራለን::

ምንጭ፡-  የኤዞኘ ተረቶች

ሞክሩ

  1. መኪና ወደ ቀኝ ሲታጠፍ የማይሽከረከረው ጐማ የትኛው ነው?
  2. ህይወት የለኝም፤ አምስት ጣት ግን አለኝ፤ እኔ ማን ነኝ?
  3. ሰዎች ይገዙኛል፤ ለመብላት፡፡ ሆኖም በፍፁም አይመገቡኝም:: እኔ ማን ነኝ?

መልስ

  1. ለቅያሬ የተያዘው
  2. የእጅ ጓንት
  3. የምግብ ሰሀን

ነገር በምሳሌ

– ራት በዳረጎት አይለወጥም- በጊዜያዊ ነገር መደለል ተገቢ አይደለም::

– ላም በረቱን የሰው ልጅ አባቱን አይረሳም፤

ሁሉም የራሱ የሆነውን አይዘነጋም::

– ሌሊት የምክር እናት-

ተኝተው ያሰቡት ነገር ጠቀሜታው ከፍያለ ነው፡፡

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የነሐሴ 19 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here