በዓለም የጋዜጣ አሳታሚዎች ማሕበር እና በፀሃፊያን በተሰጣቸው እውቅና እና ይሁንታ ቀዳሚዎቹን አምስት ጋዜጦች እነሆ፡-አንደኛው በ1605 እ.አ.አ “ታዋቂ እና የማይረሱ” ዜናዎች በሚል በጆሃን ካርሎስ ለህትመት የበቃው ቀዳሚ ህትመትን ያሟሽ ሆኖ ተመዝግቧል::
በሁለተኛ ደረጃ ጀርመናዊው ሉካስ ሹልቴ “ኢቫስ” በሚል ስያሜ በ1609 እ.አ.አ ወቅታዊ ዘገባ እና በዓለም ዙሪያ ካሉ አገራት የተውጣጡ ዜናዎችን ለህትመት ያበቁበት ነው::
ሦስተኛው በ1618 እ.አ.አ በኔዘርላንድ ማንነቱ ያልተገለፀ አሳታሚ “ኮራንቴ” በተሰኘ ርእስ በዓለም የመጀመሪያ ሳምንታዊ “ብሮድሺት” ጋዜጣን አሳትሟል::
በአራተኛ ደረጃ በቀድሞዋ ደች በአሁኗ ኔዘርላንድ በ1618 እ.አ.አ አበርሃም ቬሮሄቨን በተሰኘ ሰው ይታተም የነበረ ጋዜጣ ነው::
ጋዜጣው በምዕራቡ ዓለም የተከናወኑ ሁነቶች ዜና፣ ሽሙጥ፣ የዝነኛ ሙዚቀኞች ህይወት ይቀርብበትም ነበር::
አምስተኛው በ1631 እ.አ.አ በፈረንሳይኛ “ላጋዜታ” በሚል ለህትመት የበቃ የመጀመሪያ ጋዜጣ ብቻ ሲሆን የመጀመሪያ መፅሄትም ነበር:: የህትመቱ ተፈላጊነት እና ተነባቢነቱ በእጅጉ መጨመሩም ተጠቁሟል:: ጋዜጣው በ1762 እ.አ.አ ፖለቲካዊ ዜና ላይ አተኩሮ “ጋዜታ ደፍራንስ” በሚል ስያሜ ቀጥሏል::
ምንጭ፡- ፔን ግሎባል ኢንክ::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የነሐሴ 19 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም