መውጫ መንገዱ እንዳይዘጋ

0
50

የምስረታ ዘመኑን 1987 ዓ.ም በበኵር ጋዜጣ ያደረገው የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን 30ኛ ዓመቱ ላይ ይገኛል፡፡ የክልሉ ሕዝብ የእረጅም ጊዜ የመልማት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ዓላማ አድርጎ የተቋቋመው ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅት በሁለት የቴሌቪዥን እና በሰባት የሬዲዮ ጣቢያዎች፣ በኵር ጋዜጣን ጨምሮ በአራት ጋዜጦች እና በተለያዩ የዲጅታል ሚዲያ አማራጮች ድንበር የለሽ መረጃን እያደረሰ ይገኛል፡፡ የምልክት ቋንቋን ጨምሮ በ12 ቋንቋዎች ዘገባዎችን ተደራሽ እያደረገ የሚገኘው አሚኮ ትምህርት ዋናው የክልላችን ብሎም የሀገራችን ከችግር የመውጫ መንገድ መሆኑን ተገንዝቦ በትኩረት ሲሠራ ቆይቷል፤ እየሠራም ይገኛል፡፡

አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ለትምህርት ትኩረት የሚሠጥ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር እየሠራ ይገኛል፡፡ የትምህርት ተሳትፎ እንዲያድግ፣ የትምህርት ቤቶች ደረጃ እንዲሻሻል፣ በመማሪያ ግብዓት የተሟሉ መማሪያ ክፍሎች እንዲኖሩ፣ የትምህርት ተደራሽነት እንዲሰፋ እና ጥራት እንዲረጋገጥ የሚያደርጉ ሥራዎችን ለይቶ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ እየሠራም ይገኛል፤ የተመዘገቡ ለውጦችም አስረጂ ናቸው፡፡

አሁንም በተለይ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ (ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ) ያጋጠሙ የሰላም መደፍረሶች በትምህርት እንቅስቃሴው ላይ እያሳደሩት ያለውን ተጽእኖ አጉልቶ በማሳየት ሁሉም ለችግሩ ማብቃት እንዲረባረብ በሚያደርጉ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል፡፡ በተለይ ከሐምሌ 2015 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ አማራ ክልል በሰላም እጦት ቀውስ ውስጥ እያለፈ ይገኛል፡፡ ችግሩ በክልሉ ሕዝብ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ ተጽእኖ ቢፈጥርም ለትውልድ ቅብብሎሽ መቀጠል ቀጥተኛ አስተዋጽኦ ባለው የትምህርት ሥራ ላይ ከፍተኛ ጫናን ፈጥሯል፡፡ የትምህርት ተቋማት ለተለያየ አይነት ጉዳት ተዳርገዋል፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ መረጃ እንደሚያመለክተው ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ አሁንም ድረስ በክልሉ የቀጠለው ግጭት ስድስት ሺህ 154 ትምህርት ቤቶችን ለጉዳት ዳርጓል፡፡ ይህም ወትሮውንም ከ85 በመቶ በላይ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች ለሆኑበት ክልሉ የትምህርት ጥራትን ዕውን ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” አድርጎታል::

የግጭቱ ዳፋ ከትምህርት ተቋማት ጉዳትም በላይ ነው:: በ2016 ዓ.ም በአጠቃላይ መማር ከነበረባቸው ከስድስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ውስጥ ከሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ የሚበልጡት ከትምህርት ውጪ ሆነው ከርመዋል:: በ2017 የትምህርት ዘመንም ከአራት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን የሚበልጡ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሲሆኑ በትምህርት ላይ የከረሙት ከሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን እንደማይበልጡ የክልሉ ምክር ቤት ከወርሀ ሐምሌ 19 ቀን ጀምሮ ባካሄደው መደበኛ ጉባኤው ወቅት አስታውቋል::

የሰላም እጦቱ የክልሉን የትምህርት ተሳትፎ ወደ ኋላ የሚጎትት፣ የትውልድ ቅብብሎሹም አደጋ ውስጥ እንዲወድቅ አድርጎታል:: ባለፉት ሁለት ዓመታት ከሰባት ሚሊዮን የሚበልጡ ተማሪዎች ከትምህርት ቤቶች እና ከመምህራን ጋር ሳይገናኙ መክረማቸውን ቁጥራዊ አኃዞች ያሳያሉ::

ከቁጥሩም በላይ ከዕድሜያቸው ላይ ሁለት ዓመታት የተቀነሰባቸው ተማሪዎች የሚያጋጥማቸው ስነ ልቦናዊ ጫና ከፍተኛ መሆኑ ነው:: በ2015 ዓ.ም የስድስተኛ ክፍል ትምህርቱን ያጠናቀቀው እና በምዕራብ ጎጃም ዞን ጃቢ ጠህናን ወረዳ ነዋሪ የሆነው አዲስ አበባው ከትምህርት ውጪ የሆነባቸውን ሁለት ዓመታት በቁጭት ያስታውሳቸዋል:: “ክልሉ ሰላም ሆኖ ትምህርት ባይቋረጥ ኖሮ በ2018 ዓ.ም ዘጠነኛ ክፍል እደርስ ነበር” በማለት ቁጭቱን ተናግሯል:: አሁን ላይ ዕድሜው 17 ዓመት ላይ እንደሚገኝ የተናገረው ተማሪዉ በዚህ ዓመት ትምህርት የሚከፈት ከሆነ የባከኑ ሁለት ዓመታትን እያሰበ የሰባተኛ ክፍል ትምህርቱን ለማስቀጠል መወሰኑን ተናግሯል:: “ዳግም ለሦስተኛ ዓመት ከትምህርት ውጭ ሆኜ መክረም አልፈልግም” የሚለው አዲስ ከሚኖርበት ገጠር ቀበሌ ወጥቶ ወደ ከተማ ሄዶ ትምህርቱን ለማስቀጠል ዕቅድ መያዙን ተናግሯል::

በክልሉ ትምህርት ቢሮ ሥር የሚገኙ የትምህርት ባለድርሻ አካላትም በ2018 የትምህርት ዘመን አንድም ተማሪ ከትምህርት ገበታ ውጪ እንዳይሆን ታሳቢ ያደረገ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እያከናወኑ ይገኛሉ:: የደቡብ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ በ2018  የትምህርት ዘመን 811 ሺህ 211 ተማሪዎችን ለመመዝገብ ማቀዱን የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ እና የትምህርት መምሪያ ኃላፊዉ ደስታ አሥራቴ ተናግረዋል::

ወላጆች ልጆቻቸው ለተጨማሪ ሦስተኛ ዓመት ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነው እንዳይከርሙ አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ እንደሚገባ አቶ ደስታ አስገንዝበዋል:: ሁሉም የትምህርት ባለድርሻ አካላት ተቋርጦ የቆየውን የትምህርት ስብራት በቁጭት መጠገን እና የመማር ማስተማር ሂደቱን ማስቀጠል  እንደሚገባም አሳስበዋል::

በ2017 የትምህርት ዘመን 623 ሺህ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ የሆኑበት የምሥራቅ ጎጃም ዞንም የአዲሡን የትምህርት ዓመት በተሳካ ሁኔታ ለማስኬድ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል:: ከዞኑ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ (ፌስቡክ) የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው በትምህርት ዘመኑ 790 ሺህ 374 ተማሪዎች ይመዘገባሉ:: ነሐሴ 19 ቀን ለሚጀምረው የተማሪ ምዝገባ ስኬታማነት ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል እንዲረባረብ ጥሪ ቀርቧል::

ሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ጸጋዬ እንግዳወርቅ በበኩላቸው በ2017 ዓ.ም 407 ትምህርት ቤቶች ተዘግተው መክረማቸውን ገልጸዋል:: በዚህም ምክንያት ከ380 ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን መከታተል ሳይችሉ ቀርተዋል:: ከትምህርት የራቁ ተማሪዎችም ለሕገ ወጥ ስደት፣ ለጉልበት ብዝበዛ እና ለሥነ ልቦናዊ ችግር ተጋላጭ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

እንደ ሀገር ተወዳዳሪ ለመሆን ተተኪውን ትውልድ በእውቀት፣ በክህሎት እና በአመለካከት የመገንባት ጉዞው በሰላም ዕጦት ምክንያት የተራዘመ ጉዳት እንዳያስከትል መሥራት እንደሚገባም ኃላፊው አስገንዝበዋል:: በ2018 የትምህርት ዘመንም 600 ሺህ ተማሪዎችን ለማስተማር ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል።  ከነሀሴ 19 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የተሟላ ምዝገባ በማካሄድ ከመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች መደበኛ ትምህርት ለማስጀመረ እየተሠራ ነው ብለዋል:: ማኅበረሰቡም ትምህርት ቤቶች ላይ የሚደርስን ጥቃት በማስቆም ሕጻናት ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 10ኛ መደበኛ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት ርእሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ የሰላም እጦቱ በትምህርት ሥራው ላይ እያደረሰ ያለው ጫና ማብቃት እንዳለበት አስገንዝበዋል:: ትምህርት የማንኛውም የፖለቲካ ፍላጎት ማስፈጸሚያ መሣሪያ እንዳይሆን የመንግሥት መዋቅሩ እና ሌሎች የሚመለከታቸው የትምህርት ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሠሩ እንደሚገባም አሳስበዋል::

በአዲሱ ዓመት በትምህርት ዘርፉ የተቃጣው አስነዋሪ ድርጊት ቆሞ ትምህርት ለትውልድ ቅብብልሾ የሚያበረክተው ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከወዲሁ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት መሥራት እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳደሩ አሳስበዋል:: ችግሩን በዘላቂነት በመሻገር የትውልድ ቅብብሎሹን ለማስቀጠልም የትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል::

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የነሐሴ 19  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here