“ትንሽ ርህራሄን ወደ ዓለም ለማምጣት እንትጋ”

0
21

በአሜሪካ ፕሮቪደንስ ፌዴራል ሂል ተብላ በምትጠራው አካባቢ  ነው ያደጉት – ፍራንክ ካፕሪዮ፡፡ ወላጅ አባታቸው የተሻለ ሕይወትን ፍለጋ ከጣሊያን የመጡ ስደተኛ  ነበሩ፡፡ ታዲያ ፍራንክ አባታቸውን በልጅነታቸው ጫማ በመጥረግ፣ ጋዜጣ እና ወተት  በማከፋፈል  ሥራ  ያግዙ ነበር።

የፍራንክ ካፕሪዮ አባት ግን ልጃቸው በልጅነታቸው በተለይም ወተት ማድረስ እና የወተት መያዣ እቃ የመሰብሰብ ሥራን ሲሠሩ ህይወታቸውን ሙሉ ይሄንን ላለመሥራት እና ከድህነት  ማምለጫው ቁልፍ መንገድ ትምህርታቸውን በትጋት መማር እንደሆነ ደጋግመው ይነግሯቸው ነበር፡፡

ወላጆቻቸውን ጨምሮ ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎችን  ሕይወት ለማሻሻል የሚያደርጉትን ጥረት  አይተው ያደጉት ፍራንክ ካፕሪዮ ለሥራ፣ ለሰው ልጅ መልካምነትን የማሰብ…  የማይናወጥ እምነት አዳበሩ። የአባታቸውን ምክር ተቀብለው ከትምህርት ሳይዘናጉ ከሴንትራል ሃይስኩል እና ከፕሮቪደንስ ኮሌጅ ተመርቀዋል።

ፍራንክ ካፕሪዮ በትምህርት ዓለም ባገኙት ዕውቀት በሆፕ ሃይስኩል በቀኑ የትምህርት መርሀ ግብር  የአሜሪካን መንግሥት ታሪክ እያስተማሩ በማታ ደግሞ በቦስተን በሚገኘው የሰፎልክ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርታቸውን ይከታተሉ ነበር። ይህ የትጋትና የጽናት ጉዞ እ.አ.አ  በ1985 በዳኝነት ወንበር ላይ እንዲቀመጡ አበቃቸው። ወላጅ አባታቸውም አንድ ቀን በሕግ ተመርቀው ለድሆች እና ለተገፉት እንደሚቆሙ በሳቸው ላይ የነበራቸው ትልቅ እምነት ተሳካ፡፡

በሮድ አይላንድ ክፍለ ሀገር የከተማ ፍርድ ቤት ዳኛ በመሆን ከ1985 እስከ 2023 ለ40 ዓመታት አገልግለዋል። ብቃት ባለው የችሎት አመራራቸው፣ ለሰዎች በሚያሳዩት ርህራሔ እና በተጫዋችነታቸው ተወዳጅነትን ማትረፍ ችለዋል። በበይነ መረብ እንዲሁም በበርካታ ማህበራዊ ሚዲያ ብዙ ተከታዮችን ያፈሩት  ፍራንክ ካፕሪዮ  ነሃሴ 14 /2014 ዓ.ም ማረፋቸው ተነግሯል፡፡

እ.አ.አ በጥር 2023 ለ40 ዓመታት ከቆዩበት የዳኝነት ሥራቸው ጡረታ የወጡት ዳኛ ፍራንክ ካፕሪዮ በሕይወት ዘመናቸው በሰጧቸው ፍርዶች በሚሊዮኖች ልብ ውስጥ የማይፋቅ አሻራ ጥለው አልፈዋል። የዳኛ ካፕሪዮ መዶሻ ቢያርፍም ያስተማሩት የደግነት እና የርህራሔ ትምህርት ግን በብዙዎች ሕይወት ውስጥ ለዘላለም ይኖራል።

የፍራንክ ካፕሪዮንን የፍርድ ቤት ችሎት በቀጥታ ለተመልካች የሚያቀርበው “Caught in Providence” የተሰኘው ፕሮግራም ዳኛ ካፕሪዮ ከሳሾችን እና ተከሳሾችን የሚያስተናግዱበት መንገድ ፈጽሞ የተለየ እንደ ነበር በርካቶች ተመልክተዋል። በፊታቸው የሚቀርቡት ሰዎች የትራፊክ ጥሰት ፈጽመው አልያም ሌላ ቀላል ወንጀል ሠርተው ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ዳኛ ካፕሪዮ ከድርጊቱ ጀርባ ያለውን የሰዎቹን ታሪክ በጥሞና ያዳምጡ ነበር። የኑሮ ውጣ ውረድ የጎዳውን፣ ልጁን ለማሳከም ሲል የተቸገረውን ወይም በሕይወት አጋጣሚ ተገፍቶ ስህተት የሠራውን ሰው ሁሉ በአባትነት ርህራሔ መንፈስ ይቀበሉ ነበር።

ከቅጣት ይልቅ ምህረትን፣ ከግልምጫ ይልቅ ፈገግታን እየመረጡ ለብዙዎች ሁለተኛ እድል ይሰጡ ነበር። ችሎታቸው የሕግ መጽሐፍትን መተንተን ብቻ ሳይሆን የተሰበረ ልብን መረዳትም ጭምር ነበር። ይህ ሁሉ ርህራሔ የመነጨው ከራሳቸው የሕይወት ተሞክሮ እንደ ነበር ይገልፃሉ።

ዳኛ ፍራንክ ታዋቂ ያደረጋቸው ጥልቁ ነገር የተለያዩ ጉዳዮችን ከሕግ እና ከሰብዓዊነት አንጻር በሚሰጧቸው ፍርዶች ነበር። ዳኛ ካፕሪዮ በነዚህ ዘመናት ብዙዎችን ያስገረመ ፍርድ ከሰጡባቸው ጉዳዮች አንዱ የትራፊክ ሕግ በመተላለፍ በእርሳቸው ችሎት ቀርቦ የነበረው እና ለኛ ታሪክ ቅርብ የሆነው የኢትዮጵያዊው ሀሰን አብዲ ታሪክ ነበር። ሀሰን አብዲ በእለቱ ፍርድ ቤት የተገኘው  ባልተከፈለ የፓርኪንግ ትኬት እና በሌሊት መኪና ማቆም በተከለከለበት ቦታ ሕግን ተላልፎ ማቆሙ ነው። ዳኛ ካፕሪዮ በሀሰን አብዲ የተለያዩ የቅጣት ወረቀቶች እንደቀረበበት ከተናገሩ በኋላ፤ “ሁሉም ጥፋቶች የተፈፀሙት በሪሰርቫየር ጎዳና አካባቢ ነው፡፡   መኖሪያህ እዛ ነው?” በማለት  ጠየቁት። “አዎ!” ሲል መለሰ፤ “ለሊቱን ሙሉ እዛ ነው ያቆምከው ልክ ነኝ?”

“ትክክል ነዎት ክቡር ዳኛ! መኪናውን በዛ ስፍራ ላይ ያቆመው ልጄ ነበር፡፡”

“ልጅህ የት ነው የሚማረው?”

“ፕሮቪደንስ ኮሌጅ ነው ክቡር ዳኛ!“ “አሁን እሱ መገኘት ያልቻለው ትምህርት ስለሄደ ነው?“

“አዎ ዳኛ!” በማለት መልስ ሰጠ፡፡

ካፕሪዮ ሀሰንን እየተመለከቱ በመቀጠል “ስንት ልጆች አሉህ?“

“ሁለት”

“ሁለቱም ፕሮቪደንስ ኮሌጅ ነው የሚማሩት?“

“አዎ ክቡር ዳኛ!”

”ምንድነው ልጅህ የሚያጠናው? ትምህርቱን ሲጨርስስ ምን ለመሆን ያስባል? ሀኪም ነው? ወይም ዳኛ?” በማለት  ዳኛ ፍራንክ ጠየቁት፡፡

ሀሰን ሁለቱም ልጆቹ ፕሮቪደንስ ኮሌጅ እንደሚማሩ፤ አንደኛው ልጁ ጠበቃ መሆን  እንደሚፈልግ ነገራቸው። ዳኛ ካፕሪዮ ልጁ ጠበቃ መሆን የሚፈልግ ከሆነ ዛሬ በችሎት ቢገኝ ጥሩ ልምድ ይቀስም እንደ ነበር ከተናገሩ በኋላ በድንገት ከየት ሀገር እንደመጣና ምን ያህል ጊዜ እንደሆነው፣ ልጁ የተወለደው የት እንደሆነ አከታትለው ጠየቁት። ሀሰን አብዲ ከኢትዮጵያ እንደሄደ፤ ወደ አሜሪካ ከመጣ ደግሞ 16 ዓመታት እንዳሳለፈ እንዲሁም ልጁ በኬንያ ስደት ላይ በነበረበት ጊዜ መወለዱን ነገራቸው።

ዳኛ ካፕሪዮ ወደ አቃቤ ሕጉ እየተመለከቱ፤ ሀሰን ከዚህ በፊት በሕግ መተላለፍ ሪከርድ እንደሌለበት እና ለእሱ እና ለልጆቹ የተሻለ ሕይወት ለመፍጠር እየተጋ እንደሆነ መረዳታቸውን ገለፁለት፡፡ ወደ ፍርድ ከመሄዳቸው በፊት ሁሌ እንደሚያደርጉት የሀሰንን የኋላ ታሪክ ለማወቅ ምን እንደሚሠራ፣ ለምን ያህል ጊዜ በሥራ እንደሚያሳልፍ… መጠየቅ ጀመሩ። ሀሰን ከጥቂት ጊዜያት በፊት ሱቅ  ከፍቶ እንደ ነበር ሆኖም አሁን እንደሸጠው እና በቀን ውስጥ ለ16 ሰዓታት እንደሚሠራ ለዳኛ ካፕሪዮ አብራራላቸው።

ዳኛ ፍራንክ ካፕሪዮ ይህን እንደሰሙ ሀሰንን በአድናቆት እየተመለከቱ “ከኢትዮጵያ መጥቶ ለ16 ሰዓታት እየሠራ ሁለቱንም ልጆቹን ኮሌጅ ማስተማር መቻሉን፤ ለሌሎችም ወላጆች አርአያ መሆን በሚችል መልኩ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን በአድናቆት ተናገሩ፡፡ ቀጥለውም  የእሳቸውን የልጅነት ታሪክ በማስታወስ ስለ አባታቸው መናገር ጀመሩ። “ታውቃለህ ልጅ እያለሁ ትዝ ይለኛል አባቴ ከሌሊቱ አስር ሰዓት እየተነሳ ነበር ወደሥራ የሚሄደው።  እሱ ባለፈበት አስቸጋሪ የሕይወት መንገድ እንዳልሄድ በርትቼ መማርና ኮሌጅ መግባት እንዳለብኝ ይመክረኝ ነበር። ያንተም ልጆች አንተን እያዩ ይህንን ይገነዘባሉ፤ ለልጆችህ ጥሩ ትምህርት እየሰጠህ ነው!” በማለት የሀሰንን የሥራ ትጋት አድንቀው ሀሳባቸውን ወደ ፍርድ አሰጣጡ ሂደት መለሱ።

“እንግዲህ እዚህ ላይ መኪናውን የተከለከለ ቦታ ለቆመበት ላልተከፈለ የፓርኪንግ ትኬት ከቆመበት ቦታ የተጓጓዘበትን ጨምሮ በድምሩ የ300 ዶላር ቅጣት ተፅፎብሃል፤ ሆኖም ተምሳሌት መሆን የምትችል መልካም አባት በመሆንህ 160 ዶላር ብቻ እንድትከፍል ወስኛለሁ፡፡ ይህን መክፈል ትችላለህ?” በማለት ጠየቁት፡፡ ሀሰን በመልካሙ ዳኛ ፍርድ ተስማምቶ “አዎ መክፈል እችላለሁ!” ሲል መለሰ።

ዳኛ ፍራንክ ካፕሪዮ ሀሰን የተወሰነበትን ቅጣት መክፈል እንደሚችል ከሰሙ በኋላ በትጋቱ እና በመልካም ተምሳሌትነቱ ያደነቁትን ኢትዮጵያዊውን አባት በዚሁ መልካም ተግባሩ እንዲቀጥል መከሩት፤  መልካም ሕይወት እንዲያጋጥመውም ምኛታቸውን ገልፀው  ሸኙት።

በብዘዎቹ ዘንድ ልብ ውስጥ ከቀሩት የፍርድ ውሳኔያቸው  ውስጥ ወታደር ሆነው ሀገራቸውን ያገለገሉትን በአገልግሎት ከፍለዋል በሚል ነፃ ማሰናበታቸው፣ ለሴቶች እና ዝቅተኛ ነዋሪዎች ያላቸው ርህራሔ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ቅጣት ለመክፈል “ገንዘብ ስለሌለን፣ ሥራ ስለሌለኝ ጊዜ ይሠጠኝ” ለሚሉ ደግሞ በቂ ጊዜ መስጠት አሊያም ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ቅጣታቸውን በመሠረዝም ይታወቃሉ፡፡

“በዚህ ተግባሬ ’ፍርድ አዛብቷል፣ ግዴለሽ ነው…’ ብለው ሚተቹኝ ብዙ ናቸው፡፡” የሚሉት ዳኛ ፍራንክ እሳቸው ግን ሁሉም ሰው ስህተቱን ለማረም ድጋሚ ዕድል ሊሰጠው ይገባል ብለው በፅኑ እንደሚያምኑ ነው የሚገልፁት፡፡ በዚህም ለአንድ ሰው ደግ ባደረጉ ቁጥር ያ ሰው ደግሞ ለሌላ ሰው ደግ በመሆን እና መልካም በመሥራት ዕዳውን ይከፍላል፤ ደግነትን ይሰብካሉ የሚል እምነት አላቸው፡፡

በሙያቸው ከነበራቸው ፍትሕ እና ታማኝነት ባሻገር ፍርድ ቤት የመጡ ሰዎችን ታሪክ ሲሰሙ የሚያሳዩት ሰብዓዊነት ብሎም ለሰዎች ባላቸው ርህራሔ እና ትሕትና የበርካቶችን ቀልብ ስበዋል። ዳኛ ፍራንክ ካፕሪዮ “Caught in Providence” ከተሰኘው የቲቪ ፕሮግራማቸው ተቀነጫጭበው በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጩ ቪዲዮዎች በሚሊየኖች ዘንድ ተወዳጅነትን አትርፈዋል፡፡”በዓለም ላይ ምርጥ እና ደጉ ዳኛ!”ም አስብሏቸዋል።

በእርሳቸው ፊት የቆሙ ሁሉ ታዲያ ፍትሕን እንደሚያገኙ በልበሙሉነት ያምናሉ።  ሰዎች ዳኝነት ላይ ሲመጡ እና ከፍተኛ ፍርሃት ሲሰማቸው በመቀለድ እና በማዋዛት የፍርድ ቤት ውሏቸውን ቀላል እና የማይረሳ ያደርጋሉ፤ ሰዎች ከፍርድ በኋላ ሕይወታቸው መቀየሩንም ይከታተላሉ፤ ይጎበኛሉ፡፡

በአጠቃላይ ዳኛ ፍራንክ ካፕሪዮ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ተመልካቾች ካባ ከለበሰ ሰው በላይም ነበሩ፤ “የደግነት፣ የማስተዋል እና የሰብአዊነት ምልክት የሆኑ ዳኛ ናቸው!” ሲሉ ብዙዎች ይመሰክራሉ።

በርህራሔ፣ በትሕትና እና በሰዎች መልካምነት ላይ የማያወላውል እምነት የነበራቸው ዳኛ ካፕሪዮ በፍርድ ቤት እና ከዚያም ባሻገር በሠሩት ሥራ የብዙዎችን ሕይወት ነክተዋል። ሞቅ ባለ ፈገግታቸው እና በቀልድ አዋቂነታቸው የሚታወሱ ሲሆን ልኬት በሌለው ደግነታቸው፣ መልካም ለዋሉላቸው እና በዚህ መልካም ሥራቸው በተማረኩ ሚሊዮኖች ልብ ውስጥ ይኖራሉ።

ዳኛ ካፕሪዮ በትውልድ ከተማቸው በፕሮቪደንስ ሮድ አይላንድ በቲቪ የችሎት ውሏቸው ከመተላለፉ በፊት በሺዎች የሚቆጠሩ ጉዳዮችን ዳኝተዋል። ‘ኮት ኢን ፕሮቪደንስ’ የተሰኘውን የቴሌቪዥን ሾውን የሚያሠራጨው ኩባንያ ዴምባር ሜርኩሪ ዳኛውን ልዩ የርህራሔ ተምሳሌት እና መተሳሰብ የተሞላበት አቀራረብ የነበራቸው መሆናቸውን ገልጿል።

ኮት ኢን ፕሮቪደንስ (Caught in Providence) የተሰኘው የቴሌቪዥን ትርዒት ለዕይታ በሚበቃበት ወቅት ለሦስት ኤሚዎች ታጭቶ የነበረ ሲሆን ባለፈው ዓመት ዳኛ ካፕሪዮ ለብቻቸው በሁለት ዘርፎች ታጭተዋል። በችሎት ላይ የሚያሳዩት ያልተለመደ ርህራሔ፣ በፍርድ ሂደቱ ወቅት ልጆችን ወደ መቀመጫቸው ጋብዘው አብረዋቸው እንዲቀመጡ እና “አነስተኛ ዳኝነታቸውን” እንዲሰጡ ሲያደርጉ የሚያሳዩ አጫጭር ቪዲዮዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በሰፊው ተጋርተው ይገኛሉ።

ጥርሳቸውን ሲቦርሹ፣ ለመጽሐፋቸው አድናቂዎች ሲፈርሙ እና የራሳቸውን ቪዲዮዎች ሲመለከቱ የሚያሳዩ የቲክቶክ ቪዲዮዎች ብቻ ከ5 ሚሊዮን በላይ ተመልካች አግኝተዋል።

በአውሮፓውያኑ 2019 በሰጡት ቃለ መጠይቅ ላይ ዳኛ ካፕሪዮ “የፍርድ ቤት ውሎ በጣም አስደሳች የሆነ የሮድ አይላንድን ሕይወት ያሳያል እንዲሁም ሰዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚያጋጥሟቸውን ተመሳሳይ ጉዳዮችን ያዩበታል” በማለት ሀሳባቸውን አጋርተዋል።

ፍራንክ ካፕሪዮ ከፍርድ ቤቱ ባሻገር ለማህበረሰባቸው ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በሮድ አይላንድ የከፍተኛ ትምህርት ቦርድ ሰብሳቢ በመሆን ለ10 ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን፣ በስማቸውና በአባታቸው ስም በርካታ የነፃ ትምህርት እድል ፈንድ በማቋቋም፣ በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው አካባቢዎች ለሚመጡ ተማሪዎች የሕግ ትምህርት ተደራሽ እንዲሆን አስችለዋል።

ከተለያዩ በጎ ለጋሾች የሚያገኙትን ገንዘብም ቅጣት መክፈል ለማይችሉ ሰዎች ለማገዝ ያውሉታል፡፡

በ2023 የጣፊያ ካንሰር እንዳለባቸው ከታወቀ በኋላ ዳኛ ካፕሪዮ “በምችለው መጠን ለመታገል ሙሉ በሙሉ ዝግጁ ነኝ” በማለት ተከታዮቻቸው የሚሰጧቸውን ድጋፍ አመስግነዋል።

ዳኛ ካፕሪዮ በመጨረሻ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በለጠፉት መልዕክት በሕክምናው ላይ ችግር ካጋጠማቸው በኋላ ወደ ሆስፒታል መግባታቸውን  ተከታዮቻቸው አስታውቀው እንዲፀልዩላቸው ጠይቀው ነበር።

ዳኛ ካፕሪዮ ከባለቤታቸው ጆይስ ካፕሪዮ ጋር 60 ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ የኖሩ ሲሆን፣ አምስት ልጆችን ወልደው ሰባት የልጅ ልጆች እንዲሁም የሁለት ልጆች ቅድመ አያት ለመሆን በቅተዋል።

በቤተሰባቸውም ውስጥም ካፕሪዮ መልካም ሰውነታቸው በመልካም ባልነት፣አባትነት እንዲሁም ታማኝነት ነው ሚጠቀሰው፡፡

“እጅግ ልበቀና!” በመባል የሚታወቁት የሮድ አይላንድ ዳኛ ፍራንክ ካፕሪዮ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በ88 ዓመታቸው ነሃሴ 14 /2014 ዓ.ም ማረፋቸው በዓለም የብዙሓን መገናኛ መነጋገሪያ ሆኗል።

በዳኝነት ያገለግሉበት የነበረው ሮድ አይላንድ ፍርድ ቤት ባወጣው የኀዘን መግለጫ፣ “ለእርሳቸው ክብር ሲባል ልክ እርሳቸው ሲያደርጉት እንደኖሩት ሁሉ እያንዳንዳችን ትንሽ ርኅራሔን ወደ ዓለም ለማምጣት እንትጋ!” በማለት ጥሪ አቅርቧል።

ደይሊ ሜል፣ኢንተርቴይመንት ቱናይት፣ ሲኤን ኤን  እና ሲቢኤስ ቲቪ የመረጃ ምንጮቻችን ናቸው፡፡

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የነሐሴ 26 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here