ለመፈወስ ቀዳሚዉ መድሃኒት

0
17

በእሴቶች ላይ የተመሰረተ አድማጭነት ጥሩ አካላዊ መግባቢያ ብቻ ሳይሆን አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል የጤና አጠባበቅ ስርዓትን ለውጤታማነት የሚያበቃ መሣሪያ መሆኑን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡

በአሜሪካ  የቴክሳስ የጤና ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ በመረጃ ምንጭነት እንዳስነበበው በቅርበት መገኘት፣ የማወቅ ጉጉት እና ርህራሄ   ታካሚውን ከሀኪሙ  አቀራርቦ ለውጤት ያበቃል፡፡

ባለሙያዎቹ እንዳሉት ዛሬ ላይ ባለው ፍጥነትን በሚሻው የጤና አጠባበቅ ሥርዓት ወይም የጊዜ መጣበብ በሚስተዋልበት ዘመን ሁሉም ነገር በሀኪሙ ተመርምሮ ውጤቱን መለየት አስቸጋሪ ነው፡፡ በመሆኑም ሂደቱን ለማሳጠር እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ታካሚውን ማድመጥ የተሻለ መሆኑን ነው ያረጋገጡት – ተመራማሪዎቹ፡፡

የጤና ተቋማት ወይም አብዛኛዎቹ ሆስፒታሎች፣ ታካሚዎች የበለጠ ነፃነት ተሰምቷቸው ከሀኪሙ ጋር እንዲቀራረቡ የግል ክፍሎችን እንደሚያዘጋጁ  የገለጹት ባለሙያዎቹ ታካሚዎችን በማበረታታት ለህመማቸው ፈጥኖ ፈውስ ለመሻት ማስቻሉንም አስምረውበታል፡፡

በህክምና መስጫ ተቋማት ታማሚዎችን የሚያገኙ የመጀመሪያ  ተቀባይ ሰራተኞችም በሰነድ ላይ የመፃፃፍ ሂደትን አሳጥረው አገልጋዩን እና ተገልጋዩን ማቀራረብ ቀልጣፋ ተመራጭ ስልት መሆኑን ነው ያረጋገጡት – ባለሙያዎቹ፡፡

ባለሙያዎቹ በህክምና ስርዓት  ለተሻለ እንክብካቤ ስድስት የማድመጥ ዓይነቶችን ዘርዝረዋል፡-

የመጀመሪያው ቅርበት ያለው በአካል መገኘትን የሚሻ ማድመጥ፤ ሁለተኛው በትኩረት ማድመጥ፣ ሦስተኛው  መተማመን በሚፈጥር ቅርበት ማድመጥ፣ አራተኛው  እምነት ማሳደር የሚያስችል ቦታን ይዞ ማድመጥ (በግል ክፍል)፣ አምስተኛው፣ ለለውጥ፣ ለድርጊት የሚያነሳሳ፣ ደጋፊነት ያለው ማድመጥ፣  የመጨረሻው የታማሚውን የመቻል፣ የመፈፀም አቅም የሚያጐለብት ማድመጥ  ናቸው፡፡

በመጨረሻም ተመራማሪዎቹ የጤና መርማሪው ከሌላኛው መርማሪ፣ ሀላፊው ከመርማሪው ወይም ከሌላው ባልደረባ በጥሞና ሲደማመጡ እና ሲደጋገፉ ታማሚውን ወይም ተገልጋዩን በተሻለ ደረጃ አገልግሎት መስጠት ያስችላቸዋል፡፡ ተገልጋዮችም በተንከባካቢዎቹ ላይ እምነትን አሳድረው ጥንካሬን እንደሚያዳብሩ ነው ያደማደሙት፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የነሐሴ 26  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here