የጨነቀ ዕለት

0
20

በቻይና ጂንዢ ግዛት በከተማ አቅራቢያ በመንግሥት በሚሰራው ባለሁለት መም አውራጐዳና በተቀየሰው ቦታ መካከል ቀደም ብሎ የተሰራ ባለሁለት ፎቅ መኖሪያ ቤት ባለቤት በካሳ መጠን ባለመስማማቱ፣ ቤቱ ባለበት  የመንገድ ስራው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ቤቱን ለቆ መውጣቱን ኦዲት ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን ለንባብ አብቅቶታል::

በያዝነው ዓመት በየካቲት ወር በካሳ ክፍያ ያልተሰማሙትን ባለንብረት  ውሳኔያቸውን በማክበር ቤቱ ባለበት ሳይነካ የግዛቱ አመራር በዙሪያው መንገዱ ተከፍሎ እንዲሰራ በወሰኑት መሰረት አውራ ጐዳናው ተሰርቶ ተጠናቋል::

በወቅቱ የቀረበላቸው የካሳ ክፍያ 223 ሺህ ዶላር ሲሆን ተከፍሎ የሚጠናቀቀውም በሁለት ጊዜ  መሆኑ ነበር የተነገራቸው:: ባለንብረቱ ግን ክፍያው በአንድ ጊዜ ይሁን፤ መጠኑም ከፍ ማለት አለበት በሚል ሳይስማሙ ይቀራሉ::

የግለሰቡ ቤት ባለበት በዙሪያው አውራ ጐዳናው ለሁለት ተከፍሎ እንደምስማር መካከል ላይ እንደተቸነከረ ሥራው ተጠናቆ ጐዳናው ለትራፊክ አገልግሎት ክፍት ሆኗል:: ውሎ አድሮ ግን ቤቱ ምንም   ዓይነት የድምፅ መከላከያ የሌለው መሆኑ ኗሪውን ሳይቸግራቸው እንዳልቀረም ነው አስተያየት ሰጪዎች የጠቆሙት::

በዙሪያቸው የነበሩ ባለንብረቶች በሙሉ መንግሥት በወሰነላቸው ካሣ ተስማምተው በአቅራቢያ ወደ ሚገኝ ከተማ ለቀው ገብተዋል::

ባለንብረቱ እና ቤተሰባቸው በተለይም ከከባድ ተሽከርካሪዎች የሚወጣው ድምፅ የሚፈጥረው ሁካታ እና ንዝረት አሰቃቂ እና አስደንጋጭነቱን ችለው ጥቂት ወራት ታግሰው መቆየት ችለዋል::

በቅርቡ ግን በአውራ ጐዳና መካከል እንደ “አይን” ተቸንክሮ የቀረው መኖሪያ ቤት መስኮቶቹ ተሰባብረው፤ ዙሪያውን አረም  ውጦት ተስተውሏል::

በአካባቢው ካሉ የዜና አውታሮች እንደተሰማው የቤቱ ባለቤት እና ቤተሰባቸው ከአውራጐዳናው በሚሰማው የማያቋርጥ የትራፊክ ድምፅ የተረጋጋ ህይወት መምራት ተስኗቸዋል:: በመጨረሻም  በአቀራቢያው ወደ ሚገኝ  ከተማ ተከራይተው ለመኖር ቤታቸውን መልቀቃቸው ነው የተረጋገጠው::

በያዝነው ዓመት በየካቲት ወር በዚሁ ዓምድ የጂንዢ  ግዛት የሚያሰራውን አውራ ጐዳና እና በካሣ ክፍየ ያልተስማሙትን ባለንብረት መዘገባችን ይታወሳል::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የነሐሴ 26  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here