ዛቻ ማለት በሕግ አግባብ ሲታይ ማንም ሰው በሌላ ሰው ላይ ድንጋጤን ወይም ፍርሃትን በመፍጠር ለከባድ አደጋ ወይም ጉዳት መዳረግ ነው:: ዛቻ በሕግ ያለውን ተጠያቂነት በተመለከተም በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ በሕግ ምክር ማርቀቅ እና ማጠቃለል ዳይሬክቶሬት የክልል ዐቃቢ ሕግ ባለሙያ አቶ መስፍን መኮንን ማብራሪያ ሰጥተውናል::
ባለሙያው እንደሚሉት ዛቻን የሚመለከቱ ሁለት ሕጎች አሉ:: እንዚህም የኮምፒውተር ወንጀልን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 958/2008 አንቀፅ 13 ንኡስ ቁጥር (1) እና የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ 580 ነው::
እንደ ባለሙያው ማብራሪያ በወንጀል ሕጉ 580 መሰረት ጉዳዩ የሚቀርበው በግል ተበዳይ ብቻ ነው፤ ሁለት አይነት አቤቱታ አቀራረብ ሂደት ነው ያለው ፤ አንደኛው በግል ተበዳይ አቤቱታ ማቅረብ ሁለተኛ ደግሞ በወንጀል ክስ ማቅረብ ነው::
በግል ተበዳይ ብቻ የሚቀርብ ስንል ተበደልኩ የሚለው ሰው ወደ መርማሪ ፓሊስ ሄዶ “… የሚባል ሰው መብቴን ነክቶታል“ በማለት የሚያቀርበው ክስ ነው:: ይህ ድርጊት ዛቻውን የሚሰነዝረው ሰው በቅርብ ርቀት ከመሆኑ የተነሳ አይቀሬ ለሆነ አደጋ የመጋለጥ ስጋት ስለሚኖረው የሚያቅበው ክስ ነው:: ተበዳይ ነኝ ባይ ግለሰብ ዛቻ ፈጻሚውን “በሕግ የተከለከለ ነገር እኔ ላይ አድርጓልና በምርመራ ይጣራልኝ!“ በማለት በጽሑፍ ያስገባል፣ ፓሊስ ምርመራውን ይጀምራል::
የወንጀል ክስ ሲሆን ግን የግድ ተበዳዩ ቀርቦ ማመልከት የለበትም፤ የሕዝብ መብት እና ጥቅም የሚነካ ከሆነ፣ አጠቃላይ ማኅበረሰቡን ስጋት ላይ የሚጥል ከሆነ የተበደለው ሰው ወደ ምርመራ ፓሊስ ሳይሄድ መንግሥትም በመርማሪ ፓሊስ እና አቃቢ ሕግ ምርመራ ሊጀምር ይችላል::
በግል ተበዳይ የሚቀርበው ክስ ምርመራ ተጣርቶ ወደ ፍርድ ቤት ከሄደ በኋላ የግል ተበዳይ እና ተከሳሽ ተስማምተው ከውሳኔ በፊት ጉዳያቸው በእርቅ ሊፈታ ይችላል::
በተራ ዛቻ እና በኮምፒውተር ዛቻ መካከል ያለው አንድነት በሁለቱም ዛቻ መፈፀሙ ነው፤ ነገር ግን ምክንያቱ ምንድን ነው? ብለን ስንመለከት በአፍ የሚደረገውን ዛቻ ስናይ ሰው ድንጋጤ እና ፍርሃት እንዲሰማው ለማድረገግ ከባድ አደጋ /ጉዳት/ አደርስበታለሁ ብሎ በመግለፅ ሲያስፈራራ ነው:: ለዚህ ደግሞ በወንጀል ሕጉ 580 መሰረት ከአምስት መቶ ብር በማይበልጥ መቀጮ እና ከስድስት ወር በማይበልጥ ቀላል እስራት እንደሚያስቀጣ የዐቃቢ ሕግ ባለሙያው አሳውቀዋል::
የኮምፒውተር ወንጀልን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ 958/2008 አንቀፅ 13 (1) ደግሞ ማንኛውም ሰው ሆን ብሎ የኮምፒውተር ሥርዓትን በመጠቀም በሚያስፈራራ ጽሑፍ፣ ንግግር፣ ቪዲዮ እና ስዕል አማካኝነት በተጎጂው ቤተሰብ ላይ ከባድ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ ያስፈራራ ወይም የዛተ እንደሆነ ነው::
በኤሌክትሮኒክ መልእክት የሚደረግ ዛቻ የሚባለው በቀጥታ መልእክት፣ በኢሜይል ወይም በማኅበራዊ ድረ ገጾች በኩል የሚደረገው ነው። ግለሰቡ ለደረሰው ዛቻ ካልታዘዘ ስውር ዛቻና መጥፎ መዘዞች የሚያስከትሉ አደጋዎች ይገጥሙታል የሚለውን ማስፈራሪያ ሊያካትት ይችላል።
ይህንን ላደረጉ ደግሞ ቅጣቱ ሦስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም እንደ ወንጀሉ ክብደት ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ሊሆን ይችላል::
የኮምፒውተር ወንጀል ቅጣቱ ከፍ ሊል ይችላል፤ ምክንያቱም ስርጭቱ ከፍ ያለ ስለሆነ ወደ ብዙ ሰዎች ይደርሳል ተብሎ ታስቦ የወጣ በመሆኑ ነው::
ባለሙያው በማብራሪያቸው ዛቻ በግል ተበዳይ እና በወንጀል ክስ አቅራቢነት ይቀርባል:: በግል ተበዳይ ሲቀርብ በዋናነት የሚጎዳው የግል ተበዳይን ነው:: ሁለቱ ከታረቁ ግን በእርቅ ሊዘጋ ይችላል:: ይሁን እንጅ የኮምፒውተር ወንጀልን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ የወንጀል ሕግ በመሆኑ በእርቅ አይዘጋም፤ ምክንያቱም በሕጉ በዝርዝር አልተገለፀም::
የኮምፒውተር ወንጀልን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ የዛቻ ማስረጃ ቅጅ፣ ኢሜል፣ የዛቻው ቀን እና ሰዓት እንዲሁም ዓይነቱ በቴሌግራም፣ በፌስቡክ … ቀኑ ተጠቅሶ ወደ ፍርድ ቤት ማቅረብ ይገባል::
ዛቻ ወደ ሽብርተኝነት እንደሚያድግም የዐቃቢ ሕግ ባለሙያው አስገንዝበዋል:: ከብሔር እና ሃይማኖት ጋር ከተገናኘም ከሌሎች ሕጎች ጋር ሊገናኝ ይችላል::
“ሰው የሚናገር ያሰበወውን ነው“ ያሉት ባለሙያው፤ ዛቻ የሃሳብ ክፍልን ስለሚያመለክት ከዛተ በኋላ ግድያ ቢፈፀም ግድያው እንደተጨማሪ ወንጀል ተደርጎ ይቆጠራል ::
ዛቻን ብዙ ሰዎች እንደወንጀል አያዩትም የሚሉት ባለሙያው አቶ መስፍን፤ ምክንያቱ ደግሞ ሰው የዛተውን ነገር አያደርገውም ብለው ከማሰብ የመነጨ ነው:: አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ዛቻ የተፈፀመበት ሰው የዛተበት ሰው ጉዳት ያደርስብኛል ብሎ በመፍራት ቀድሞ ወንጀል የሚሠራበት ሁኔታ አለ:: ስለዚህ የዛቻ ጉዳቱ ከባድ መዘዝ እንደሚያመጣ ሰው ቀድሞ መገንዘብ እንዳለበት የዐቃቢ ሕግ ባለሙያው አስገንዝበዋል::
ቀላል ዛቻ የሚባለው በወንጀል ሕጉ 580 ላይ የተቀመጠው በስድስት ወር ቀላል እስራት ይቀጣል:: ይሄ ሕጉ ቀላል ቢለውም ለሰው ስድስት ወራትን መታሰር እና ነፃነት ማጣቱ ቀላል ነገር አይደለም:: በመሆኑም ዛቻን እንደ ቀላል ነገር መፈፀም የለበትም::
በሌላ በኩል የኮምፒውተር ወንጀልን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ደግሞ ቀላል እስራቱ ሦስት እና አምስት ዓመት ነው:: ይህ የእርማት ጊዜም ቀላል ባለመሆኑ እንደሚያስቀጣ ማወቅ እና መጠንቀቅ ይገባል::
ሰዎች ዛቻ ሲፈፀም የሚፈፀምበትን ብቻ ሳይሆን ፈፃሚውን ጭምር ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ባለሙያው ጠቁመዋል:: በዛቻ መካከል ሌላ አደጋ ቢደርስበት እንኳን የመጀመሪያ ተጠያቂ የሚያደርግ ነገር በመሆኑ ጥንቃቄ መደረግ አለበት::
እንደ ቡድን ሆነ ግለሰብን በኮምፒውተር ከሀገር ወጥተው ዛቻ የሚፈጽሙ ሰዎችም ወደ ሀገር ከገቡ ተጠያቂ የሚሆኑበት አጋጣሚ እንዳለ ባለሙያው አስገንዝበዋል::
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የነሐሴ 26 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም