ዓለም እና ረሃብ

0
20

ረሃብ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየቀነሰ ቢገኝም  በአፍሪካ እና በምዕራብ እስያ ግን ጨምሯል:: የዘንድሮው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም የምግብ ዋስትና እና የተመጣጠነ ምግብ ሁኔታን ሪፖርት ሲያደርግ በቅርብ ጊዜ የተከሰተውን የምግብ የዋጋ ግሽበት መንስኤ እና መዘዝንም መርምሯል::

 

እ.አ.አ በ2024 ወደ 673 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ረሃብ ያጋጠማቸው ሲሆን ይህ አሃዝ እ.አ.አ በ2023 ከነበረው በስምንት ነጥብ አምስት በመቶ እና እ.አ.አ በ2022 በስምንት ነጥብ ሰባት በመቶ መቀነሱን የሚያመላክት ነው::

ለረሃብ መንስኤዎች ከሆኑት መካከል ግጭት በዋነኝነት ተጠቃሽ ሲሆን   ሰብአዊ እርዳታን በማደናቀፍ ለረሃብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል። በተለይ እንደ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ያሉ ሀገራት በእጅጉ ተጎድተዋል። ሌላው የአየር ንብረት ለውጥ ሲሆን ድርቅን በማስከተል በርካቶችን ለረሃብ ዳርጓል::  እንዲሁም ድህነት አንዱ የረሃብ መንስኤ ነው::  ታዲያ ይህም ሆኖ  በዓለም ደረጃ ረሃብ እንደቀነሰ ነው እየተነገረ ያለው::

ረሃብ መቀነሱ ይፋ የተደረገው በጎርጎሮሲያኑ ሐምሌ መጨረሻ (ሐምሌ 28/2025) በአዲስ አበባ በተካሄደው ሁለተኛው የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ሥርዓት ጉባኤ ላይ ነበር::

ማሽቆልቆሉ ጥሩ ቢሆንም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ያለው ከፍተኛ የምግብ ዋጋ ግሽበት ለምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ አስተዋፅዖ ማድረጉ ነው ይፋ የተደረገው።

 

በጉባኤው እንደተነገረው በደቡብ እስያ እና በላቲን አሜሪካ ጉልህ መሻሻሎች ታይተዋል:: እንደ አለመታደል ሆኖ ይህ አወንታዊ አዝማሚያ በአፍሪካ እና በምዕራብ እስያ ካለው የማያቋርጥ የረሃብ መጨመር ጋር በእጅጉ ይቃረናል:: በ2024 በአፍሪካ ለረሃብ የተጋለጠዉ የሕዝብ ቁጥር ከ20 በመቶ በላይ ሲሆን 307 ሚሊዮን ሕዝብም ጉዳት ደርሶባቸዋል:: በምዕራብ እስያ 12 ነጥብ ሰባት በመቶው ሕዝብ ወይም ከ39 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በ2024 ረሃብ ገጥሟቸው ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (FAO)፣ ዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ (IFAD)፣ የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት ኤጀንሲ (ዩኒሴፍ)፣ የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) እና የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) በጋራ እንዳስጠነቀቁት በረሃብ የተጎዱ ሰዎች ቁጥር ቢቀንስም አፋጣኝ ረሃብን የሚቀለብስ ርምጃ ካልተወሰደ ዓለም ትልቅ ቀውስ ውስጥ ትገባለች::

 

እ.አ.አ. በ2030 512 ሚሊዮን ሰዎች ሥር የሰደደ የምግብ እጥረት ሊገጥማቸው ይችላል ተብሎ ይጠበቃል። ይህም የተባበሩት መንግሥታትን የዘላቂ ልማት ጎሎች ከሆነው ውስጥ በ2030 ረሃብን ሙሉ በሙሉ (ዜሮ ረሃብ) የማጥፋ እቅዱን የሚያደናቅፍ ነው:: ይህ ብቻ ሳይሆን ባለፉት አስርት አመታት ረሃብን ለማጥፋት በተከናወኑ ሥራዎች እና ፍጥነት አንጻር ከ130 ዓመት በኋላም ዓለም ዝቅተኛ የረሃብ ደረጃ ላይ አትደርስም የሚል ድማዳሜ ላይ ተደርሷል::

ይሁንና አንዳንድ ከረሃብ ጋር የተያያዙ ችግሮች እየቀነሱ እንደሆነ ማሳያዎች አሉ:: ለአብነትም ከአምስት ዓመት በታች ባሉ ሕጻናት የመቀንጨር ስርጭት እ.አ.አ. በ2012 ከነበረበት 26 ነጥብ አራት በመቶ በ2024 ወደ 23 ነጥብ ሁለት በመቶ ቀንሷል:: ይህም የዓለም እድገትን ያሳያል።

 

ከስድስት ወር በታች ጡት ብቻ የሚጠቡ ሕጻናት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል:: እ.አ.አ. በ2012 ከነበረበት 37 በመቶ በ2023 ወደ 47 ነጥብ ስምንት በመቶ ከፍ ብሏል:: ይህም የሚያስገኘው የጤና ጥቅም እውቅና እያደገ መሆኑን ያሳያል።

የፋኦ ዋና ዳይሬክተር ኪዩ ዶንግዩ “በዓለም አቀፍ ደረጃ የረሃብ መጠን መቀነሱን ማየታችን አበረታች ቢሆንም ግስጋሴው ያልተመጣጠነ መሆኑን መገንዘብ አለብን ብለዋል:: በ2025 ሁሉም ሰው በቂ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኝ ለማድረግ ጥረቶችን ማጠናከር እንዳለብን ወሳኝ ማሳሰቢያ ሆኖ ያገለግላል ነው ያሉት::

የዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ (IFAD) ፕሬዝዳንት አልቫሮ ላሪዮ በበኩላቸው “የምግብ ዋጋ መናር ሲያጋጥም እና የዓለም እሴት ሰንሰለቶች በሚስተጓጎሉበት ወቅት ኢንቨስትመንታችንን በገጠር እና በግብርና ለውጥ ላይ ማጠናከር አለብን”። ሲሉ ነው መፍትሔ ያስቀመጡት::

 

የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ራስል እንዳሉት አሁንም ከ190 ሚሊዮን በላይ ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት በምግብ እጦት ተጎድተዋል:: ይህም በአካልና በአዕምሮ እድገታቸው ላይ አሉታዊ መዘዝ ያስከትላል። የምግብ ዋጋ መናር በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ቤተሰቦች የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ሊያባብስ ይችላል::

ለችግር የተጋለጡ ቤተሰቦች በተመጣጣኝ ዋጋ በቂ ምግብ ለሕጻናት እንዲያቀርቡ ለማድረግም ከመንግሥት፣ ከግሉ ሴክተር እና ከማሕበረሰቡ ጋር በትብብር መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል::

 

ይህ በእንዲህ እያለ የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም በምዕራብ እና መካከለኛው አፍሪካ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለረሃብ የተጋለጡ መሆናቸውን ከሁለት ወር በፊት ባወጣው ሪፖርት ማስጠንቀቁን ልብ ይሏል:: ግጭት፣ መፈናቀል፣ የኢኮኖሚ ችግር ተደጋጋሚ የአየር ንብረት ለውጥ ቀጣናውን ወደ ከፍተኛ ቀውስ እየገፋው ነው:: ከ36 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ሰዎች  መሠረታዊ የምግብ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት እየታገሉ ይገኛሉ:: ይህ ቁጥር እስከ ነሀሴ መጨረሻ ባለው የዝናብ ወቅት ከ52 ሚሊዮን በላይ ሊጨምር እንደሚችል ተተንብዩአል:: በመሆኑም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስከ ጥቅምት ወር መጨረሻ ድረስ የሕይዎት አድን ሥራውን ለመደገፍ 710 ሚሊዮን ዶላር ይፈልጋል::

የዓለም የምግብ ድርጅት ጦርነት፣ የምግብ ዋጋ ግሽበት፣ እና የጎርፍ መጥለቅለቅ በምዕራብ እና በመካከለኛው አፍሪካ ረሃብን ከሚያባብሱ ምክንያቶች መካከል መሆናቸውን ተናግሯል:: በቻድ፣ ካሜሩን ሞሪታኒያ እና ኒጀር ውስጥ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ስደተኞችንና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ጨምሮ በክልሉ ውስጥ ተጋላጭ ከሆኑት መካከል ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል::

 

በኢትዮጵያም እየተከሰቱ ባሉ ግጭቶች  ቀጣናዊ አለመረጋጋት፣ መፈናቀል፣ ድርቅ እና የኢኮኖሚ ቀውስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በቂ አልሚ ምግብ እንዳያገኙ አድርጓል::  ረሃብም እየጨመረ መምጣቱን የዓለም የምግብ ፕሮግራም ሚያዚያ 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስጠንቅቋል::

ድርጅቱ በመግለጫው እንዳስታወቀው በኢትዮጵያ  ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለረሃብ እና ለተመጣጠነ ምግብ እጥረት ተጋልጠዋል:: ከነዚህም መካከል በግጭት እና በአስከፊ የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት  ከቤታቸው የተፈናቀሉ ሦስት ሚሊዮን ሰዎች ይገኙበታል::

 

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ገብረእየሱስ በበኩላቸው “ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዓለም የመቀንጨር ችግርን በመቀነስ እና ጡት በማጥባት ረገድ ጥሩ መሻሻል አሳይቷል:: ነገር ግን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከምግብ እና የተመጣጠነ ምግብ እጦት ሸክም ለማቃለል አሁንም ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል::

ይህ በእንዲህ እንዳለ በጋዛ ፋኦ፣ ዩኒሴፍ፣ የዓለም የምግብ ፕሮግራም እና የዓለም ጤና ድርጅት በረሃብ እና በተመጣጠነ ምግብ እጦት የሚደርሰውን ሞት ለመግታት አፋጣኝ የተኩስ ማቆም እና ያልተቋረጠ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደረግ በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል::

ከሰሞኑ አዲስ የተቀናጀ የምግብ ዋስትና ደረጃ ምደባ (IPC) ትንታኔ እንደሚያመለክተው በጋዛ ውስጥ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ለረሃብ ተጋልጠዋል:: በሚቀጥሉት ሳምንታት ረሃቡ ከጋዛ አድማሱን በማስፋ ወደ ዲር አል ባላህ እና ካን ዮኒስ ግዛቶች ሊሰራጭ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።

 

የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (FAO)፣ ዩኒሴፍ፣ የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) እና የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) በጋራ በሰጡት መግለጫ  በቋሚነት በጋዛ ከረሃብ ጋር በተያያዘ  ምክንያት ሰዎች እየሞቱ ነው:: አጣዳፊ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተከሰተ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የምግብ ፍጆታ ደረጃ እያሽቆለቆለ በመሄድ ላይ ይገኛል::

በጋዛ ሕጻናት ላይ  የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በአስከፊ ሁኔታ እየተስፋፋ ነው:: በሐምሌ ወር ብቻ ከ12ሺህ  በላይ ሕጻናት የከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዳጋጠማቸው ታውቋል::

የአይፒሲ የግንቦት ወር   ትንተና እንደሚያሳየው በሰኔ 2026 መጨረሻ ላይ በምግብ እጥረት ለከፋ ሞት ይጋለጣሉ ተብሎ የሚጠበቁ ሕፃናት ቁጥር ከ14ሺህ 100 በሦስት እጥፍ አድጓ ወደ 43ሺህ 400 ከፍ ብሏል ።

በተመሳሳይ በምግብ እጥረት የሚሰቃዩ የነፍሰ ጡር እና የሚያጠቡ እናቶች ቁጥር  በግንቦት ወር ከነበረው 17 ሺህ  በሦስት እጥፍ አድጓ 55ሺህ ይደርሳል።

 

ከሐምሌ ጀምሮ ወደ ጋዛ የሚገቡት የምግብ እና የእርዳታ አቅርቦቶች በትንሹ ጨምረዋል:: ይሁንና ከፍላጎት አንፃር በጣም በቂ ካለመሆኑ በላይ ወጥነት የሌለው እና ተደራሽ አይደለም።

የእርዳታ ስራዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየተስተጓጎሉ ይገኛሉ:: አብዛኛዎቹ የተባበሩት መንግሥታት የጭነት መኪናዎች  ተዘርፈዋል። የምግብ ዋጋ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው:: እንዲሁም ለማብሰያ የሚሆን በቂ ነዳጅ፣ ውኃ፣ መድሃኒት እና የሕክምና አቅርቦቶች የሉም::

 

አሁን አሁን በግጭቶች እና በጦርነቶች ውስጥ ረሃብን እንደጦር መሳሪያ መጠቀም እየተለመደ መጥቷል:: እርዳታዎችን መከልከል፣ የእርሻ ቦታዎችን ማውደም የውኃ ምንጮችን ማበላሸት የተለመደ ሆኗል:: እነዚህ ድርጊቶች የጅምላ ሞትንና መፈናቀልን ስለሚያስከትሉ በጦር ወኝጀል ሕግ ያስጠይቃሉ:: ሆኖም እስካሁን በዚህ ድርጊት የተሳተፉ ቡድኖች ርምጃ ሲወሰድባቸው አልታየም::

በተያያዘም ሕጻናት በረሃብ ምክንያት ትምህርታቸውን እያቋረጡ መሆኑ ነው የተነገረው:: የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) እንዳስታወቀው በአውሮፓዊያኑ 2025 መጀመሪያ አካባቢ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በሰሜን አፍሪካ 30 ሚሊዮን ሕጻናት ከትምሕርት ገበታ ውጪ ሆነዋል::

የቻይናው ዥንዋ እንደዘገበው በኢትዮጵያም  በግጭት ምክንያት ሰባት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ተስተጓጉለዋል::

(ሳባ ሙሉጌታ )

በኲር የነሐሴ 26  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here