ጅምላ ፍረጃ ለምን?

0
17

ምንም አይነት ድጋፍ አያገኙም። በእድሜ የገፉ መሆናቸው ደግሞ ችግራቸውን የከፋ አደረገው። በባህርዳር ከተማ አባፋሲሎ ክፍለከተማ ቀበሌ 03  በቅርብ የማውቃቸው በዕድሜ የገፉ እናት፡፡

ችግራቸው እየጠና መጥቶ ቀን ለብሰዋት የዋሏትን ቀሚስ ሌሊትም አየተጠቀሟት ከገላቸው ሳትወርድ መቀደድ ጀመረች። አማራጭ ስላልነበራቸው ቁርጥራጭ ጨርቆችን ተጠቅመው በመጠጋገን እድሜዋን ለማርዘም ጣሩ። ይህን ያጤነ አንድ ደግ ባለፀጋ ነጋዴ ለአዲስ ልብስ ማሰፊያ የምትሆን ብር ሰጣቸው፤ “ለልብስዎ ማሰፊያ ነው” ብሏቸው ስለነበር ፈጥነው ወደ ልብስ ሰፊ መደብር አመሩ።

በልብስ ስፌት መገኛ መደብሮች ካንዱ ወደ አንዱ እየተዘዋወሩ ቀልባቸው ያሰኘውን ጨርቅ አማረጡ። በአንድ መደብር ውስጥ ያዩት ጨርቅ ምርጫቸው ሆነ። የጨርቁ ሂሳብ ከነማሰፊያው ከያዙት ብር እንዳያልፍ በመስጋት ሰፊውን “ ስንት ነው ይህ ጨርቅ ከነማሰፊያው?” ሲሉ ጠየቁት። እሱም በትህትና ለጠየቁት መልስ ከመስጠቱ አስቀድሞ እኒያን የተቀዳደደ ልብስ የለበሱ አዛውንት በአኗኗራቸው ዙሪያ አወራቸው።

ምንም ዓይነት ረዳት እንደሌላቸው፤ ዛሬ ግን አንድ የፈጣሪ መልዕክተኛ የሆነ ደግ ባለፀጋ ነጋዴ ለልብስ ማሰፊያ እንዲያውሉት ብር ሰጥቷቸው ለማሰፋት እንደመጡ  አወጉት። የጨርቃጨርቅ መደብሩን ባለቤትም የሴትዮዋ ሁኔታ በጣም ሃዘኔታ ውስጥ ከተተው። በሃዘኔታ ብቻ አልተወሰነም፤ የኒያን ምስኪን  ቀልብ የሳበውን የጨርቅ ጣቃ አውርዶ የሚበቃውን በመቀሱ ቆረጠ። ሜትሩን ከላይ ወደታች፣ ከደረታቸውና ትከሻው አንዱ ጠርዝ ወደ ሌላኛው አቅጣጫ እያዟዟረ ልኬታቸውን በማስታወሻ ደብተሩ ላይ አስፍሮ አጠናቀቀ።

ልክ እንደ ቀሚሳቸው ከነተበችው መቀነት ላይ የቋጠሯትን ብር አውጥተው ለመስጠት መፍታት ጀመሩ። ያ! የጨርቃጨርቅ መደብሩ ባለቤት ግን ሃዘኔታውን በተግባር ለማረጋገጥ ውሳኔ ላይ ደርሶ ስለነበር “እማማ! እሷን ብር ለሌላ ነገር ያውሏት፤ የልብሱን ጠቅላላ ወጭ እኔ አሸፍነዋለሁ” አላቸው።

በከፋ ድህነት ኑሮን እንደነገሩ እየገፉ ያሉት እናት ድንጋጤ የታከለበት ደስታ ውስጥ ገቡ። በመቀጠልም የቻሉትን ያህል ምርቃት እሳቸውም ለደግ አድራጊው የጨርቃጨርቅ መደብር ባለቤት ለገሱ፤ ልብሱ ተሰፍቶ የሚጠናቀቅበትን ቀን ጠይቀው አረጋገጡ። ለደግ አድራጊዎች ሁሉ ፈጣሪ ጤና እና ዕድሜ እንዲቸር እየተማፀኑ ወደቤታቸው ተመለሱ።

እንደነዚህ ያሉ ለተቸገረ አዛኝ አንዳንድ ደግ ነጋዴዎች ባሉበት ዘመን ታዲያ “ነጋዴ ሲባል እኮ … !” እያሉ ደጉን ከአጭበርባሪው ባልለዬ ሁኔታ በጅምላ መፈረጅ ተገቢ እንዳልሆነ ልንገነዘብ ግድ ይላል።

የችግረኛዋን በዕድሜ የገፉ እናት እና የበጎ አድራጊ ነጋዴዎችን ደግ ተግባር ለዚህ ፅሑፍ መግቢያ አድርጌዋለሁ። የግላዊ ትዝብቴ ሃሳብ ዋና ማጠንጠኛም ይከው ነው፤ በተለያዬ ምክንያት ሃሳባችንን የምንገልጽበት የጅምላ ፍረጃ ጉዳይ ተገቢ አለመሆኑን ማስገንዘብ የዛሬው ፅሑፌ ትኩረት ሆኗል።

“የዘመኑ ወጣት እኮ … !” የሚለውም ሌላኛው የዘመኑ ጅምላ ፍረጃ መገለጫችን ነው። ቀደም ባሉት ዘመናት የወጣትነት ጥንካሬ “ወጣት የነብር እጣት” እየተባለ ይገለጽ ነበር። ታዲያ ዛሬ ሁሉም የዘመኑ ወጣት  አንድ አይነት ባህሪ፣ ችሎታ፣ እውቀት፣ … ሊኖረው እንደማይችል እየታወቀ “አይ የዘመኑ ወጣት …!” እያሉ አሳንሶ በጅምላ መፈረጅን ምን አመጣው?

ዓለማችን በመረጃ መረብ ትስስር  አንድ መንደር እስከመምሰል ደርሳለች። በዚህ የተነሳም የስልጣኔ መገለጫ መስሏቸው በአውሮፓውያን ብልጭልጭ የተለከፉ እና የሃገራቸውን ወግና ባህል እየዘነጉ ያሉ አንዳንድ አልባሌ ወጣቶች መኖራቸውን አሌ ማለት አይቻልም። እንደቀደመው ዘመን መልካሙን የመከባበር በጎ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ዘንግቶ ለታላላቆቹ ተገቢውን አክብሮት የማይቸር አንዳንድ የዘመኑ ስነምግባር የጎደለው ወጣት እንዳለም ይታወቃል። ሥራ ማለት ብዙ ድካምን የማይጠብቅ እና  ጥሩ ገቢን የሚያስገኝ ብቻ ነው በሚል ደካማ አስተሳሰብም የተተበተቡ አንዳንድ የዘመኑ ወጣት ተብየዎችም አሉ።

እነዚህ አንዳንድ መገለጫዎች በአንዳንድ የዘመኑ ወጣቶች ላይ መታየታቸው ግን ሁሉንም ወጣት ሊገልፅ የሚገባው አይደለም። ምክንያቱም ከዚህ በተለየ መልኩ ሃገራችንን አሁን ከምትገኝበት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የተለያዩ ጥረቶችን የሚያደርጉ ወጣቶችም አሉና።

ከቀደመው ጊዜ በተሻለ የእውቀት ምጥቀት ደረጃ ላይ ሆነው የተለያዩ የፈጠራ ውጤቶችን ለሃገራቸው እያበረከቱ ያሉ ታታሪ ወጣቶች አሉን። ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ የሥራ መደቦች ላይ ተሰማርተውም ለሃገራቸው እድገት የሚታትሩ የዘመኑ ወጣቶች በርካቶች ናቸው። እንደነዚህ አይነት ወጣቶችን በማትጋት መጭውን ዘመን በተስፋ የተሞላ ማድረግ ከሁላችንም ይጠበቃል። ከዚህ በተቃራኒ በጅምላ ፍረጃ ወጣቱን ትውልድ ተስፋ ቆራጭ እንዲሆን ማድረግ ግን ተገቢ አለመሆኑን መገንዘብ ይገባል።

በጣም በርካታ እውቀት እና ክህሎት ኖሯቸው ከቤተሰብ ሃላፊነታቸው ባለፈ፤ በሃገራዊ ከፍተኛ የአመራር ደረጃዎች ላይ በብቃታቸው ተመድበው የዘመኑን ሴቶች ጥንካሬ በተግባር እያረጋገጡ ያሉ በርካቶች ናቸው።

ትዳራቸውን በአግባቡ ጠብቀው የዘለቁ በርካታ ሴቶች የመኖራቸውን ያህል ከትዳራቸው በላይ ወስልተው፤ መልካሙን የትዳር ህይወት በፍች እንዲጠናቀቅ የሚያደርጉም አንዳንድ ሴቶች አሉ። ይህ ድርጊት የሴቶች ብቻ መገለጫ ሊሆን አይገባውም፤ ወንዶች ላይ ከፍ ብሎ የሚታይ ነውና። በመሆኑም አንዳንድ ሴቶች ላይ የሚስተዋልን ትናንሽ ጉድለት መነሻ አድርጎ “አይ የዘመኑ ሴቶች … !” እያሉ በጅምላ መፈረጅ ተገቢ አይደለም፤ ሊታረም ይገባዋል።

ከሥራ ዘርፍ፣ ከዕድሜ እና ፆታ አንፃር ለመጥፎ የጅምላ ፍረጃ መገለጫ ይሆናሉ ያልኋቸው ከብዙ በጥቂቱ እነዚህ ናቸው። ቀሪውን እናንተም ፃፉበት።

የማይገባ ጅምላ ፍረጃ (generalization) ማለት ሰዎችን ወይም ማህበረሰብን በአንድ መለኪያ መዝኖ መግለጽ ማለት ነው። የአንዱን ባህሪ በሁሉም ላይ መጠቀም፣ የእውቀት እጥረት፣ ቅድመ አመለካከት(prejudice)፣ ማህበራዊ ስቴርዮታይፕ(stereotype) እና ፍርሃት ለማይገባ ጅምላ ፍረጃ መነሻ መሆናቸው ይገለፃል።

ያልተገባ ጅምላ ፍረጃ የግለሰቦችን ክብር ይቀንሳል፤ ተስፋንም ይጎዳል። ማህበራዊ ክፍፍልን ያስከትላል፤ የተሳሳተ ምልከታን ይፈጥራል። የማህበረሰብን ፍቅር ይቀንሳል። የማይገባ ግጭትን ይፈጥራል፤ እውነተኛ ግንኙነት እና ልማትን ያቋርጣል። በመሆኑም በጅምላ ከመፈረጅ አባዜ ልንወጣ ይገባል መልዕክቴ ነው።

(ጥላሁን ወንዴ)

በኲር የነሐሴ 26 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here