የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎች…

0
24

ኢትዮጵያ ከምትከተለው የግብርና መር ፖሊሲ ዋና ዓላማዎች መካከል በምግብ እህል ራስን መቻል፣ የሀገሪቱን የግብርና ምርት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ማድረግ እና ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች በቂ ምርት ማቅረብ ተጠቃሽ ናቸው። ትርፍ አምራቹ የአማራ ክልል ደግሞ ሰፊ የሚታረስ መሬት፣ ለም አፈር፣ በመኸር፣ በበልግ እና በበጋ መስኖ ማምረት የሚያስችል ተስማሚ የአየር ንብረት ባለቤት  ነው። ክልሉ በዋና ዋና ሰብሎች ከሀገሪቱ 34 በመቶ ምርት ድርሻ እንዳለው ከክልሉ ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በመሆኑም የሰብል ልማት ዘርፋን ምርታማነት ለማሳደግ የምርት ማሳደጊያ ግብዓት በተደራጀ መንገድ ማቅረብ፣ ማሰራጨት እና መጠቀም ይገባል። የክልሉን የግብዓት አቅርቦት፣ ሥርጭት እና አጠቃቀም  በማሻሻል የአርሶ አደሩን ፍላጎት በማሟላት ምርታማነትን ማሳደግ ግድ ይላል።

ከምርት ማሳደጊያ ግብዓቶች መካከል በዋናነት  ምርጥ ዘር አንዱ ነው። ጥራቱ እና ደህንነቱ የተረጋገጠ ምርጥ ዘርን በወቅቱ፣ በበቂ መጠን እና በዓይነት ለተጠቃሚው አርሶ አደር ማቅረብ ከተቻለ ምርታማነትን ማሳደግ ይቻላል። ማሳን በወቅቱ ማረስ እና ማለስለስ፣ የሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ማዳበሪያን መጠቀም፣ ሰብልን መንከባከብ እና መጠበቅ…እንደተጠበቁ ሆኖ ምርጥ ዘርን መጠቀም ደግሞ ከ30 እስከ 50 በመቶ የምርት ጭማሪ እንደሚያመጣ ባለሙያዎች አስገንዝበዋል።

በመሆኑም የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የግብርና ምርታማነትን የሚጨምሩ የምርምር ውጤቶችን የማፍለቅ፣ የማላመድ፣ የመጠበቅ እና የማስተዋወቅ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። ተቋሙ  ከዚህ ባለፈ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ አግባብ ላለው አካል ያስተዋውቃል፤ ያሰራጫል። ለአብነትም ለኢትዮጵያ ዘር ኢንተርፕራይዝ፣ ለአማራ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይ፣ ለማሕበራት እና ለባለሀብቶች በምርምር የወጡ መነሻ ዘሮችን እና ቴክኖሎጂዎችን ያሰራጫል። በሰው ሀብት ልማትም የአቅም ግንባታ ይሰጣል። የዝናብ እጥረት ወይም ድርቅ በተደጋጋሚ የሚከሰትባቸውን አካባቢዎች በመለየት ችግሮችን ለመቀነስ ድርቅ መቋቋም የሚችሉ፣ የንጥረ ነገር ይዘታቸው የተሻሉ የሰብል ዝርያዎችን በማፍለቅ እና በማባዛት ለተጠቃሚው እንዲደረስ ጥረት እያደረገም ይገኛል።

ከሰሞኑ የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምርታማነትን እና ጥራትን የሚያሳድጉ፣ ድርቅን፣ ተባይን፣ በሽታን እና አረምን መቋቋም የሚችሉ የሰብል ዝርያዎች መልቀቁን አስታውቋል። አንድ የጤፍ፣ አንድ የምስር፣ ሁለት የአተር  እና ሦስት የማሽላ  ዝርያዎች በስሪንቃ የግብርና ምርምር ማዕከል ተለቀዋል፡፡ ሁለት የእንቁ ዳጉሳ ዝርያዎች ደግሞ በሰቆጣ ዝናብ አጠር የግብርና ምርምር ማዕከል የተለቀቁ ናቸው።

ባለፉት ሰባት ዓመታት ምርምር ሲደረግባቸው ቆይተው በሀገር አቀፍ ዘር አጽዳቂ ኮሚቴ የምርምር ደረጃዎችን ያለፉ ዘጠኝ የሰብል ዝርያዎች በ2017 ዓ.ም መለቀቃቸውን ነው የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አስማረ ደጀን (ዶ.ር) ለበኵር የተናገሩት። እነዚህን ዘጠኝ ዝርያዎች በቀጣይ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የማላመድ እና የማስተዋወቅ ሥራዎች በስፋት እንደሚከናወን አስረድተዋል። ዝርያዎቹ ከአማራ ክልል አልፎ ለሀገር የሚጠቅሙ እንደሆኑም አመላክተዋል።

ኢንስቲትዩቱ በክልሉ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ውስጥ ሆኖም በበጀት ዓመቱ ለመሥራት ካቀደው 584 የምርምር ሥራዎች ውስጥ 489 (83) በመቶ የሚሆኑትን ማከናወኑን  ዳይሬክተሩ አብራርተዋል። በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በተለይም በአንዳሳ እና በአዴት ግብርና ምርምር ማዕከላት ሥራዎችን ለማከናወን አስቸጋሪ እንደ ነበር አንስተዋል። የምርምር ሥራዎቹ ሰብል፣ እንስሳት (በግ፣ ላም፣ ዶሮ እና ንብ)፣ የዘር ብዜት፣ አፈር እና ውኃ አያያዝ፣ ደን እና የተለያዩ ምርምሮችን ያካተቱ ናቸው።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት ኢንስቲትዩቱ የምርምር ሥራዎችን እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ፣ በማባዛት እና በማስተዋወቅ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ምርምሮችን ያካሂዳል፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ያፈልቃል፣ ያላምዳል ለተጠቃሚውም ያስተዋውቃል።  የሚያወጣቸውን መስራች ዘሮችም ያሰራጫል።

በሰቆጣ ግብርና ምርምር ማዕከል ከተለቀቁ  ዝርያዎችም አንዱ “እንቁ ዳጉሳ” ነው። እንቁ ዳጉሳ በንጥረ ነገር ይዘቱ የተሻለ፣ ድርቅን መቋቋም የሚችል እና በዝናብ አጠር አካባቢዎች ፈጥኖ በመድረስ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችል  ዓይነተኛ ሰብል ነው።

ምርታማነታቸው አንደኛው የተሻሻለው ዝርያ በሄክታር 17 ነጥብ 2 ኩንታል፣ ሁለተኛው የተሻሻለው ዝርያ ደግሞ 20 ነጥብ 8 ኩንታል ምርት የሚሰጡ ናቸው። ይህም የኅብረተሰቡን ችግር በመፍታት የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ ጠቁመዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ፈጥነው የሚደርሱ፣ የተሻለ ምርት የሚሰጡ እንዲሁም የአፈር ለምነት በቀነሰባቸው (አሲዳማ አፈርን) አካባቢዎች መቋቋም የሚችሉ የሰብል ዝርያዎች ለአርሶ አደሩ እየተሰራጩ መሆኑን ገልፀዋል።

በ2017 ዓ.ም በማሽላ ሰብል ላይ በተደረገ ምርምር ኢንስቲትዩቱ ሦስት የማሽላ ዝርያዎችን የለቀቀ ሲሆን ምርታማነታቸውም ከበፊቶቹ ዝርያዎች የተሻሉ መሆናቸው ተረጋግጧል። ምርታማነታቸውን፣ ጥራታቸውን እና የአርሶ አደሩን ፍላጎት በማጥናት ለጠላ፣ ለእንጀራ እና ለገበያ የሚሆኑትን በመለየት እንዲለቀቁ መደረጉን ነው ዳይሬክተሩ ያብራሩት።

የመጀመሪያው “ስሪንቃ አንድ” የተባለው የማሽላ ዝርያ ሲሆን በሄክታር 52 ኩንታል ምርት የሚሰጥ ነው። ከበፊቱ ማወዳደሪያ ዝርያ 30 በመቶ የምርት ብልጫ አለው። ይህም ፈጥኖ በመድረስ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ይረዳል። ጨፋ፣ ቆቦ፣ ሰይዳ፣ ሸዋሮቢት፣ በለሳ እና በሌሎች ተመሳሳይ ሥነ ምህዳር ባላቸው ቦታዎች መመረት የሚችል መሆኑም ተረጋግጧል።

ሌላው “ወለዲ” የተባለው የማሽላ ዝርያ ደግሞ በሄክታር 47 ኩንታል የሚሰጥ ነው። ከበፊቱ የማወዳደሪያ ዝርያ ደግሞ 29 በመቶ ብልጫ አለው። ሦስተኛው “ዳግም” የተባለው የማሽላ ዝርያ ሲሆን በሄክታር 44 ኩንታል እንደሚሰጥ ተገልጿል። በስሪንቃ፣ መተማ፣ ጃሪ እና ጨፋ መመረት የሚችል ነው። እነዚህ ሁለቱ የማሽላ ዝርያዎች በመካከለኛ ጊዜ የሚደርሱ መሆናቸው ተመላክቷል።

ሌላኛው በምርምር የተለቀቀው የተሻለ ምርት መስጠት የሚችል፣ ቀድሞ የሚደርስ፣ ነጭ የዘር ቀለም ያለው “ዛቲ” የተባለ የጤፍ ዝርያ ነው፡፡ በአርሶ አደሩ ተሞክሮ በሄክታር 25 ኩንታል ምርት የሚሰጥ እና ከተሻሻለው ማወዳደሪያ ዝርያ ደግሞ 20 በመቶ የምርት ብልጫ አለው ተብሏል። በስሪንቃ፣ ጃሪ፣ ጨፋ፣ ዓለም ከተማ እና ሰቆጣ አካባቢዎች መመረት የሚችል መሆኑም ተረጋግጧል፡፡

በከፍተኛ ሁኔታ ሙከራ ተደርጎ በጥቁር አፈር ውኃን በማንጣፈፍ እና ቀድሞ በመዝራት (ሐምሌ መጀመሪያ ሳምንት አካባቢ) የተሻለ ምርት መስጠት የሚችል “የምስራች” የተባለ የምስር ዝርያ በስሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል ተለቋል። በሄክታር 19 ኩንታል ምርት የሚሰጥ እና ከአካባቢው ማወዳደሪያ ዝርያ 57 በመቶ የምርት ጭማሪ እንዳለው አመላክተዋል።

በወረኢሉ፣ ለገሂዳ፣ ጃማ፣ እነዋሪ፣ ዳውንት እና በሌሎች ተመሳሳይ የአየር ንብረት ያላቸው ቦታዎች መመረት የሚችል መሆኑም ተረጋግጧል። ቀድሞ የሚደርስ እና ድርቅን የሚቋቋም፣ የተሻለ ምርት መስጠት የሚችል “ሰርክ” የተባለ ለሽሮ መሆን የሚችል የአተር ዝርያም በስሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል በኩል ተለቋል። በሄክታርም እስከ 28 ኩንታል ምርት የሚሰጥና ከአካባቢው ማወዳደሪያ ዝርያ በ27 በመቶ የምርት ብልጫ ያለው መሆኑ ተጠቅሷል።

ሌላው በምርምር የተለቀቀው “ለኪ” የተባለው የአተር ዝርያ ነው፡፡ ቀድሞ የሚደርስ፣ ድርቅን መቋቋም እና ለክክ መሆን የሚችል የአተር ዝርያ ነው። በሄክታር  እስከ 32 ኩንታል ምርት መስጠት እና ከአካባቢው ማወዳደሪያ ዝርያ በ25 በመቶ የምርት ብልጫ አለው። በወረኢሉ፣ ጃማ፣ መቄት፣ አዴት እና ሌሎች ተመሳሳይ ቦታዎች መመረት የሚችል መሆኑም ተረጋግጧል። በቀጣይ ዓመት የተለቀቁ አዳዲስ ዝርያዎችን በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ተደራሽነታቸውን በማስፋት የማላመድ እና የማስተዋወቅ ሥራም እንደሚከናወን ዳይሬክተሩ  አመላክተዋል።

በአጠቃላይ ከውጭ ሀገር የሚመጡትን ጨምሮ የሚለቀቁ የሰብል ዝርያዎች ጤንነታቸው የተጠበቀ መሆን እንዳለበት ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የነሐሴ 26 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here