ከአቧራማ ሜዳ እስከ ግዙፉ የዓለም ዋንጫ መድረክ

0
13

እግር ኳስን ውብ እና ማራኪ የሚያደርጉት አስደናቂ ቅብብሎች፣ ድንቅ ሙከራዎች እና ልብን የሚያሞቁ ግቦች ብቻ አይደሉም። ሕግ እና ስርዓት በማስከበር ጨዋታው በፍትሃዊነት እንዲጠናቀቅ የሚተጉ ዳኞችም ጭምር እንጂ።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ስማቸው በደማቅ ከተጻፈ ጥቂት ስፖርተኞች መካከል  ዓለም አቀፉ ዳኛ ባምላክ ተሰማ አንዱ ነው፡፡ ዓለም አቀፉ ዳኛ ከሁለት ዐስርት ዓመታት በላይ የዘለቀውን የዳኝነት ህይወቱን በቅርቡ መደምደሙን በይፋ ተናግሯል።

የባምላክ ተሰማ ጡረታ መውጣት በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ እግር ኳስ ዳኝነት ታሪክ ውስጥ አንድ ትልቅ ምዕራፍ መዘጋቱን ያመለክታል። ባምላክ በሜዳ ላይ በሚያሳየው የተረጋጋ እና በራስ መተማመን የተሞላበት ብቃቱ በሀገር ውስጥ፣ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የበርካቶችን አድናቆት አትርፏል።

ባምላክ ተሰማ ወዬሳ ታህሳስ 30 ቀን 1972 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ ተወለደ። ዓለም አቀፉ ዳኛ ከእግር ኳስ  ጋር የተዋወቀው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለ ነወ፡፡ በወቅቱም ለትምህርት ቤቱ ቡድን ይጫወት እንደነበር መረጃዎች አመልክተዋል።

በኋላም የአሁኑን ኢትዮ ኤሌክትሪክን (የቀድሞውን ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን) ለመቀላቀል ሙከራ አድርጎ እንደነበር የግል የታሪክ ማህደሩ ያስረዳል፡፡ የከሸፈው ሙከራ ግን ድንገት የዳኝነት ሙያን እንዲቀላቀል አስችሎታል። እናም በትምህርት ቤት የሚደረጉ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን በዳኝነት በመምራት የዳኝነት ሙያን መለማመድ ጀመር።

ይህም ለወደፊቱ የዳኝነት ህይወቱ መሰረት እንደጣለለት የሴካፋ ኦንላየን መረጃ አመልክቷል።

ባምላክ ተሰማ መደበኛ የዳኝነት ሥራውን በይፋ የጀመረውም በ1997 ዓ.ም መሆኑን ፓን አፈሪካ ፉትቦል ዶት ኮም አስነብቧል። ስመ ጥሩው ዳኛ በአስደናቂ ብቃቱ የብዙዎችን ቀልብ ለመሳብ ጊዜ አልፈጀበትም። በ2001 ዓ.ም ደግሞ የዓለም አቀፍ የዳኝነት ፈቃድ በማግኘት  ወደ ትልቅ ምዕራፍ ተሸጋግሯል፡፡ የያዘው ዓለም አቀፍ ፈቃድም  በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ ጨዋታዎችን እንዲመራ አስችሎታል፡፡

ፊፋ ፈቃድ ከሰጠው በኋላ በጅቡቲ እና በናሚቢያ መካከል የተደረገውን የ2014ቱን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ የመራ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ባምላክ በአፍሪካ ዋንጫ፣ በቻን ወድድር፣ በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ እና በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ መድረኮች ላይ በብዛት በመሳተፍ ስሙን በአፍሪካ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ በደማቅ ቀለም አስጽፏል።

እ.አ.አ በ2018 በሩሲያ በተካሄደው የዓለም ዋንጫ አህጉራችንን ወክለው ከተመረጡ ስድስት ዳኞች አንዱ እንደነበረ አይዘነጋም። ይህም ኢትዮጵያዊ ዳኛ በዓለም ዋንጫ ላይ ሲሳተፍ ከ48 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር፡፡ ከእርሱ በፊት የቀድሞው ዓለም አቀፍ ዳኛ ስዩም ታረቀኝ በ1970 እ.አ.አ በሜክሲኮ በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ላይ ተሳትፎ እንደነበር የያሆ ዶት ኮም መረጃ ይጠቁማል።

በ2018ቱ የሩሲያ የዓለም ዋንጫ ባምላክ በቪዲዮ ረዳት ዳኝነት (VAR) እና በአራተኛ ዳኝነት ሚናዎች እንደተሳተፈ እናስታውሳለን። ክስተቱ በአፍሪካ ዳኝነት ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ሲሆን የቪዲዮ ረዳት ዳኝነት ቴክኖሎጂን ከተጠቀሙ የመጀመሪያዎቹ አፍሪካውያን ዳኞችም አንዱ እንዲሆን አስችሎታል።

ባምላክ በርካታ ብቋቱን ያስመሰከረባቸው የማይረሱ ጨዋታዎችን መርቷል። ለአብነት በ2017 እ.አ.አ በአል አህሊ እና በዊዳድ ካዛብላንካ መካከል የተካሄደው የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የፍጻሜ የመጀመሪያ ጨዋታ አንዱ ነው። ጨዋታው በከፍተኛ ውጥረት እና ፉክክር የተሞላበት የነበረ ቢሆንም ባምላክ በተረጋጋ መንፈስ ጨዋታውን በብቃት በመምራት የበርካቶችን አድናቆት አትርፏል።

ሌላው የባምላክ የዳኝነት ብስለት እና ጥበብ የታየበት መድረክ የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ነው።  በሴኔጋል እና በቡርኪናፋሶ መካከል የተደረገውን የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ በዋና ዳኝነት ሲመራ ያሳየው ብቃት እጅግ አስደናቂ ነበር። በጨዋታው ላይ ሁለት ጊዜ የፍጹም ቅጣት ምት ውሳኔዎችን በቪዲዮ ረዳት ዳኝነት (VAR) ከገመገመ በኋላ በመሻር ትክክለኛ እና ፍትሃዊ ውሳኔዎችን በመስጠት የእግር ኳስ ሕጉን ምን ያህል በጥልቀት እንደሚረዳ አስመስክሯል።  ይህ ክስተት በወቅቱ ሜል ስፖርትን ጨምሮ ሌሎችም ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን “የአፍሪካ ምርጡ ዳኛ” የሚል ቅጽል ስም ሰጥተውታል። ሜል ስፖርት በዘገባውም የፕሪሚየር ሊጉ ዳኞች ባምላክን ማየት አለባቸው  የሚል ዘገባ መስራቱ አይዘነጋም፡፡

ባምላክ በሜዳ ላይ በሚያሳየው የተረጋጋ ባህሪ በተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች እና ደጋፊዎች ዘንድ ከፍተኛ ክብርን አግኝቷል። በውጥረት የተሞሉ እና ከፍተኛ ፉክክር የሚታይባቸውን ጨዋታዎች በብቃት የመምራት ችሎታው በአፍሪካ ካሉ ምርጥ ዳኞች ተርታ እንዲሰለፍ አስችሎታል።

ከእግር ኳስ ዳኝነት ህይወቱ ጎን ለጎን በትምህርት መስክም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሶሺዮሎጂ የማስተርስ ዲግሪውን ተቀብሏል። ይህ የሚያሳየው ባምላክ በእግር ኳሱ ዓለም ብቻ ሳይሆን በሌሎች የሙያ ዘርፎችም እራሱን ያበቃ ሁለገብ ስብዕና ያለው  እንደሆነ ያመለክታል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ክፍያው አነስተኛ መሆን እና በሜዳ ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ዋነኞቹ የእግር ኳስ ዳኝነት ሙያ ተግዳሮቶቹ  ናቸው። ለሙያው ያለው  ፍቅር ግን ፈተናዎችን ተቋቁሞ ለታላቅ ክብር አብቅቶታል፡፡

ባምላክ በዳኝነት ህይወቱ በርካታ ስኬቶችን አስመዝግቧል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባዘጋጀው የ2011 ዓ.ም. የኮከቦች ሽልማት ስነ ስርዓት ላይ ከሊዲያ ታፈሰ ጋር ኢትዮጵያን በአፍሪካ መድረክ በማስጠራት ላሳዩት ድንቅ ብቃት የፌዴሬሽኑን ልዩ ሽልማት ተቀብለዋል። በተጨማሪም በምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት (CECAFA) ክልል ውስጥ ምርጥ ዳኛ ተብሎ እውቅና አግኝቷል።

ባምላክ በዳኝነት ህይወቱ ያካበተውን ሰፊ ልምድ እና እውቀት ለቀጣዩ ትውልድ ዳኞች ለማካፈል ፍላጎት እንዳለው ተነግሯል።

ለፊፋ በላከው የስንብት ደብዳቤ ባምላክ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ለአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) እና ለዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) በከፍተኛ ደረጃ እግር ኳስን እንዲያገለግል ዕድል ስለሰጡት ምስጋናውን አቅርቧል።

አሁን ላይ ምንም እንኳን  ፊሽካውን ቢሰቅልም በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ እግር ኳስ ላይ ያሳደረው በጎ አሻራ  ግን ለትውልድ ይተላለፋል።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የጳጉሜ 3 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here