የማሕጸን በር ካንሠር

0
12

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ ሴቶች በማሕጸን በር ካንሠር እየተሰቃዩ ይገኛሉ::  ይህን መረጃ የሰጡን በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የማሕጸን እና ጽንስ ትምህርት ክፍል ባልደረባ እና የልዩ አማራጭ ሕክምና ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር መሠረት ከፋለ ናቸው:: ባለሙያው የማሕጸን በር ካንሰር ምንነት፣ መንስኤ፣ ምልክቶች እና መደረግ የሚገባቸውን ጥንቃቄዎች እንዲሁም ሕክምናውን በተመለከተ ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተውናል::

መንስኤ

የማሕጸን በር ካንሠር መንስኤ ምንድን ነው ብለን እንደ መግቢያ ዶ/ር መሠረትን ጠይቀናቸዋል፤ ዶክተር መሠረት እንዳስገነዘቡት አብዛኛውን ጊዜ ካንሠር የሚባሉ በሽታዎች መነሻቸው ወይም መንስኤያቸው የማይታወቅ ነው:: ሆኖም የማሕጸን በር ካንሠር (Cervical Cancer)  ከሌሎች ካንሠሮች ልዩ የሚያደርገው  99 በመቶ በላይ የሚሆነው መነሻው ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ (HPV) መሆኑ ነው::

ባለሙያው እንዳብራሩት ለአቅመ ሔዋን ሳይደርሱ ጾታዊ ግንኙነት መጀመር (ለረዥም ጊዜ የግብረ ሥጋ ግንኙነት እንዲኖር ስለሚያደረግ) በሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ የመጋለጥ ዕድልን ይጨምራል:: የተለያዩ የጾታ ጓደኛ መኖርም ሌላው መንስኤ ነው፤ ይህ ማለት ሴቷ ከአንድ በላይ ጓደኛ ሲኖራት በቀላሉ በቫይረሱ የመያዝ ዕድል ይኖራታል:: ምክንያቱም ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ ብዙ ጊዜ የሚተላለፈው በግብረ ሥጋ ግንኙነት ነውና:: ሌላኛው ተቃራኒ ጾታ (ባል ወይም ፍቅረኛ) ከብዙ ሴቶች ጋር ግንኙነት ካለውም በሽታውን ሊያስተላልፍ ይችላል:: በተጨማሪም ሲጋራ ማጨስ ሰውነት በሽታን የመቋቋም አቅምን ስለሚያዳክም እንደ አጋላጭ ምክንያት ይቆጠራል::

እንዲሁም ኤች አይ ቪ ያለባቸው ሰዎች በተለያዩ በሽታዎች የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው:: በመሆኑም ለማሕጸን በር ካንሠር ሊጋለጡ ይችላሉ:: የዓለም ጤና ድርጅት እ.አ.አ በ2024 ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት ኤች አይ ቪ ያለባት ሴት ከሌለባት ሴት በስድስት እጥፍ በማሕጸን በር ካንሠር የመያዝ ዕድል አላት።

የማሕጸን በር ካንሠር ቅድመ ካንሠር እና ካንሠር የሚባል ደረጃ እንዳለው የገለጹት ዶክተር መሠረት ቅድመ ካንሠር የሚባለው ደረጃ ላይ በሽታው ከተገኘ ይድናል:: እንዲሁም ሂውማን ፓፒሎ ቫይረስ ከያዘ በኋላ ወደ ካንሠር ከመቀየሩ በፊት ከ10 እስከ 15 ዓመታትን ይወስዳል:: ለዚህም ነው በየአምስት ዓመቱ የማሕጸን በር ካንሠር ምርመራ የሚያስፈልገው::

ዶ/ር መሠረት እንዳብራሩት የማሕጸን ጫፍ ካንሠር ለቫይረሱ ተጋላጭነት እስካለ ድረስ የግብረ ሥጋ ግንኙነት የጀመረች ማንኛዋም ሴት የመያዝ ዕድሏ ከፍተኛ ነው:: ወደ ካንሠር ለመቀየር የሚውስደው ዕድሜ ረዥም በመሆኑ ብዙ ጊዜ ከ35 እስከ 39 እና ከ63 እስከ 65 ዓመት የሚገኙ ሴቶች ላይ ካንሠሩ ይገኛል ተብሎ ይገመታል:: ለአብነትም 20 ዓመቷ ላይ በቫይረሱ የተያዘች ወጣት ከዐሥር እና ከ15 ዓመት በኋላ ካንሠሩ ሲገኝባት ዕድሜዋ ከ30 እስከ 35 ባለው ይሆናል ማለት ነው::

ምልክቶቹ

ዶ/ር መሠረት እንደሚሉት የማሕጸን በር ካንሠር በቅድመ ካንሠር ደረጃ ላይ እያለ ምልክት አያሳይም ወይም አይኖረውም:: ምልክት ማሳየት የሚጀምረው ወደ ካንሠር ከተቀየረ በኋላ ነው:: በግንኙነት ጊዜ የሕመም እና የደም መፍሰስ የበሽታው ምልክት ነው:: ደም መፍሰሱ ከወርሃዊው የወር አበባ ዑደት በኋላም ይቀጥላል:: የወር አበባ ማየት ያቆመች ሴት ላይም (ከርጣት በኋላ) የደም መፍሰስ ይኖራታል::  ውኃማ የሆነ መጥፎ ጠረን ያለው ፈሳሽ ይከሰታል::  ካንሠሩ እየተሰራጨ ሲሄድ ከፍተኛ የሆነ የማያቋርጥ የጀርባ እና የማሕጸን አካባቢ ሕመም  ይኖራል:: እነዚህ የተለመዱ የማሕጸን በር ካንሠር  ምልክቶች ናቸው:: ካንሠሩ እየተባባሰ ሲሄድ ደግሞ ምልክቶቹ ይባባሱ እና የሽንት አለመቆጣጠር ይከሰታል፤ ለኩላሊት ሕመምም ይዳርጋል::  እግር ላይ የደም መርጋት እና እብጠትም ይታያል::

ሕክምናዎቹ

ሕክምናውን በተመለከተ ባለሙያው እንዳብራሩት በቅድመ ካንሠር ደረጃ ላይ ቀለል ያለ ሕክምና ይደረጋል፤ መውለድ የምትፈልግ እናትም ማሕጸኗ ሳይወጣ መውለድ ትችላለች:: እንዲሁም ካንሠር  ከሆነ በኋላ አራት የስርጭት ደረጃዎች ያሉት ሲሆን ደረጃ አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት እና አራት ተብለው ይከፈላሉ:: ደረጃ አንድ ላይ ከተገኘ  ካንሠሩ ብዙ ሳይሰራጭ ተገኝቷል ማለት ነው:: በመሆኑም በቀዶ ሕክምና ለማከም ይሞከራል፣ ቀዶ ሕክምናውም ማሕጸንን እስከማውጣት ይደርሳል::

ዶ/ር መሠረት እንዳሉት በካንሠር የተጠቃውን የአካል ክፍል ለማከም የሚደረገው ቀዶ ጥገና   ከባድ  በመሆኑ በማንኛውም ቦታ መከናወን አይችልም:: ለአብነትም በአማራ ክልል  የካንሠር ቀዶ ጥገና የሚሰጠው በጎንደር  እና በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ነው:: ከቀዶ ጥገናው በኋላም በሚደረግ ምርመራ ኬሞቴራፒ የሚባለው ሕክምና ሊያስፈልግ ይችላል:: ቀዶ ሕክምና የሚያስፈልገው ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ያልተሰራጨ ካንሠር ሲሆን ነው:: ከቀዶ ጥገና ካለፈ ግን ወይም ካንሠሩ ከተሰራጨ እና ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ከተዛመተ ግን በኬሞቴራፒ እና በጨረር የሚታከም ይሆናል:: ከዛ በኋላ ግን ያለው ሕክምና አጥጋቢ እንዳልሆነ ነው ባለሙያው ያብራሩት:: ሆኖም ከካንሠሩ ጋር ለመኖር ሕምም እንዳይሰማቸው እና ከማሕጸን የሚወጡ ሽታዎችን ለማስወገድ ሕክምናዎች እንደሚሰጡ ነው የጠቆሙት:: ካንሠሩ ከደረጃ አንድ  አለፈ ማለት የሚደረገው ሕክምና ሙሉ በሙሉ አያድነውም ሳይሆን ውስብስብ የሕክምና ሂደት ይኖረዋል ማለት እንደሆነም አስገንዝበዋል::

መከላከያዎቹ

የማሕጸን በር ካንሠር መከላከያዎቹ አንደኛው ክትባት መከተብ ነው:: ብዙ ጊዜ ለአቅመ ሔዋን ያልደረሱ ከዘጠኝ እስከ 13 ዓመት ለሚገኙ ሴቶች  ፀረ ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ ክትባት ይሰጣቸዋል:: ሌላው ዕድሜያቸው ከ30 እስከ 49 ዓመት ለሚገኙ ሴቶች  ደግሞ መደበኛ የሆነ የማሕጸን በር ካንሠር ቅድመ ምርመራ ማድረግ በሽታውን ለመከላከል ያስችላል::

እንዲሁም ተመርምራ ውጤቷ ነጌቲቭ (ነጻ) የሆነች ሴት በየአምስት ዓመቱ   ድጋሚ መመርመር ይኖርባታል:: ይህ ምርመራ ዕድሜያቸው እስከ 50 ዓመት ለሆኑት ይሠራል:: ሆኖም ይላሉ ባለሙያው ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች ከተስተዋሉ በማንኛውም ጊዜ ምርመራ ከማድረግ ወደኋላ አለማለትን አበክረው መክረዋል::

ይሁንና የኤች አይ ቪ ቫይረስ በደሟ የሚገኝ ሴት በየሦስት ዓመቱ መመርመር እንዳለባት ነው ዶክተር መሠረት የተናገሩት:: እንዲሁም ሲጋራ አለማጨስ፣ ልቅ ከሆነ የግብረ ስጋ ግንኙነት መታቀብ፣ አንድ ለአንድ መወሰን በበሽታው ከመያዝ ያድናሉ::

የማሕጸን በር ከንሠርን ለመከላከል ሁሉም የየድርሻውን ሊወጣ ይገባል ያሉት ባለሙያው ማሕበረሰቡ የሚያጋልጡ ነገሮችን በመለየት ከመንስኤዎቹ ራሱን ከቆጠበ የማሕጸን በር ካንሠር ይቀንሳል ብለዋል:: መንግሥት በበኩሉ አሁን እያደረገ የሚገኘውን የማሕጸን በር ካንሠርን በተመለከተ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፤  ምርመራዎችን በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ማድረግ፣ መከላከያ ክትባቶችን ከእስካሁኑ በበለጠ መንገድ መስጠት እና የጤና ትምህርትን ለሕብረተሰቡ ማድረስ ተገቢ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል:: አክለውም መገናኛ ብዙኃን ስለ በሽታው እና መከላከያ መንገዶች ግንዛቤ ፈጠራ ላይ አጠናክረው መረጃዎችን ለሕዝቡ መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል:: ዩኒቨርሲቲዎችም የካንሠር በሽታን የሚያክሙ እና የሚመረምሩ ምሁራንን በብቃት እና በብዛት ማፍራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል::

በመጨረሻም ዶ/ር መሠረት እንዳሳሰቡት የማሕጸን በር ካንሠር በባሕላዊ መድኃኒት  ስለማይድን በበሽታው መያዛቸውን ያወቁ ሴቶች  በፍጥነት ወደ ዘመናዊ የጤና ተቋማት መሄድ እንደሚኖርባቸው መክረዋል:: በተለይም በባሕላዊ መንገድ ይጠፋል ብሎ ጊዜ ከመጨረስ እና ቶሎ መዳን ሲቻል ጊዜ መስጠት ወደ ውስብስብ ደረጃዎች ካንሠሩን እንዲሸጋገር በማድረግ ዋጋ እንደሚያስከፍል ነው የጠቆሙት::

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የጳጉሜ 3 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here