አንድ የመሆን ውጤት  – ሕዳሴ 

0
16

የዓለም ባንክ መረጃ እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ ካላት 130 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ 60 ሚሊዮኑ  የኤሌክትሪክ ኀይል ተጠቃሚ አይደለም:: የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒሥትር መረጃ የሚያረጋግጠውም ይህንኑ ሲሆን 46 በመቶው የኢትዮጵያ ሕዝብ የኤሌክትሪክ ኀይል ፍላጎቱን ለማሳካት የሕዳሴ ግድብን መጠናቀቅ አብዝቶ ይጠብቃል:: ለዚህም ይመስላል የሕዳሴ የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠ ጊዜ ጀምሮ መላው ኢትዮጵያዊ ካለው ላይ ቀንሶ ሲያበረክት የነበረው:: ለሕዳሴ ዕድሜ፣ ጾታ፣ የትምህርት ደረጃ፣ ብሔር፣ ሃይማኖት… ትርጉም አልነበራቸውም::

“የቀድሞው ጠቅላይ ሚንሥትር መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያውያንን እና የቀደሙ ነገሥታትን በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ የመገንባት  ፍላጎት ዕውን የሚያደርገውን የመሰረተ ድንጋይ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ሲጥሉ የተናገሩት ንግግር 14 ዓመታትን ሳንሰለች እንድናዋጣ አድርጎናል” ያሉን የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪው አቶ አስማረ ኀይሌ ናቸው።

«መሐንዲሶች እኛው፣ ግንበኞቹ እና ሠራተኞቹ እኛው፣ የፋይናንስ ምንጮች እና አስተባባሪዎች እኛው፣ በአጠቃላይ የሕዳሴ ጉዟችን ባለቤቶች እኛው መሆናችንን የሚያሳይ የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታችን ነው» ያሉትን ንግግር ያስቀደሙት አቶ አስማረ፤ ይህም ንግግር ለተስፋቸው ተነሳሽነትን ፈጥሮላቸው  168 ሺህ ብር ቦንድ በመግዛት የታሪኩ ተጋሪ ለመሆን እንዳበቃቸው ነው የገለጹት። “ጀምሮ አለመጨረስ የእኔም የኢትዮጵያውያንም መገለጫ አይደለም!” ያሉት ባለታሪካችን፣ “ይህም ‘አይችሉም‘ ብለው ሲዘባበቱብን የነበሩ ጠላቶቻችንን እንጥል የቆረጥንበት ሁለተኛው ዓድዋችን ነው” ብለውታል።

በበርካታ ፈተናዎች ታጅቦ ለምረቃ በመብቃቱ የተሰማቸውን ጥልቅ ደስታ ገልጸዋል። ግድቡ እንደ ሀገር የተጨማሪ ኀይቅ ባለቤት እንድንሆን አስችሎናል ያሉት አቶ አስማረ፣ ይህም በአሳ ሀብት ዘርፍ የነበረውን ተጠቃሚነት ከማሳደግ ጀምሮ የቱሪዝም መዳረሻን የሚያሰፋ እንደሚሆን እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል። ይህም ተደማምሮ ሰፊ የሥራ ዕድልን ይዞ እንደሚመጣ ነው የተናገሩት።

የግድቡ ዋና ዓላማም ሆነ የእርሳቸው ተቀዳሚ ፍላጎት በጨለማ ለሚኖረው ብርሐንን የሚገልጥ፣ በጭስ ዐይናቸው ለሚያለቅሱ እናቶችም ምላሽ የሚሰጥ እና አኗኗርን የሚያዘምን እንደሚሆን ምኞታቸው ነው::

በሕዳሴ የታየው መረባረብ በዚህ ወቅት ዋጋ እያስከፈለ ያለው ጦርነት እንዲያበቃ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል። ከጦርነት እና ከአፈሙዝ ወጥቶ ለተሻለ ፖለቲካ ምህዳር መረጋገጥ እና ኢትዮጵያውያን አሁንም ለሚፈልጓቸው ልማቶች ትኩረት መስጠት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ከለላ ወረዳ ነዋሪዋ ሰሚራ ኢብራሂም ያደረገችው የዶሮ ድጋፍም ግድቡ ከሕጻን እስከ አዋቂ፣ ከተማሪ እስከ ምሁር፣ ከአርሶ አደር እስከ ወታደር ያለ ልዩነት የተሳተፈበት ለመሆኑ ማሳያ ነው:: ሰሚራ ለሕዳሴ ብላ ያበረከተችው ዶሮ በጫራታ 17 ሺህ ብር መሸጡ ደግሞ ሕዝቡ የሕዳሴ መገንባትን ተከትሎ በሚመጡ ልማቶች ተጠቃሚ የመሆን ተስፋውን አጉልቶ የሚያሳይ ሆኖ ይነሳል:: የሕዳሴ ግድብ ለምረቃ ሊበቃ መሆኑ እንዳስደሰታት ለአሚኮ ተናግራለች::

“ዓባይ ስመ መልከም፣ ዓባይ ስመ ጥሩ፣

አንተን ሲሳይ ይዘን ስንቶች ጦም አደሩ”፤ በሚል ስንኝ ስሜታቸውን ያጋሩን ሌላው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ 50 አለቃ መንበሩ አንዷለም ናቸው::

“ዓባይ አንተ እያለህ ታላቁ ጸጋችን

እንዴት ለልመና ተዘረጋ እጃችን” ሲሉም በአግባቡ ሳንጠቀምበት መኖራችንን አጽንኦት ይሰጣሉ:: ይህ የዘመናት ቁጭታቸው እንዲያበቃ፣ በየዓመቱ የሚወሰደው አፈርም ለተጨማሪ ምርታማነት እንዲውል ጉጉታቸው ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰዋል:: ለቁጭታቸው ማብቃትም በቤተሰባቸው አባላት ቁጥር ቦንድ ሲገዙ ቆይተዋል::

የግድቡ መጠናቀቅ የሚያስደስተው አሁን ያለውን ትውልድ ብቻ ሳይሆን በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ ለመገንባት ራዕይ የነበራቸው ያለፉ ኢትዮጵያውያን እና ነገሥታት ጭምር ነውም ብለዋል:: የአባቶቹን ራዕይ የሚያስቀጥል ትውልድ እንዳለ የሚያረጋግጥ ነው ያሉት 50 አለቃ መንበሩ፤ ትውልዱ ግድቡ እውን እንዳይሆን ፈተና የሚመስሉ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጦች፣ የውስጥ እና የውጭ ሴራ እጁን ያልጠመዘዙት መሆኑንም አስገንዝበዋል::

የህዳሴ  ግድብ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ አሁን እስከደረሰበት ደረጃ በርካታ ውጣውረዶችን አልፏል:: የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) በኃላፊነት ወስዷቸው የነበሩ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች መጓተት፣ አስተዳደራዊ እና የብልሹ አሠራር ችግሮች ግድቡ ተጨማሪ ዘጠኝ ዓመታትን እንዲጠይቅ ማድረጋቸው ይነገራል::

ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ የመጣው መንግሥት (ብልጽግና) በግንባታ ፕሮጀክቱ የተስተዋሉ ችግሮችን ለይቶ ግንባታውን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ወደ ሥራ ተገባ፤ ግንባታውም ተጠናቆ ከቀናት በኋላ ለምረቃ እንደሚበቃ ጠቅላይ ሚኒሥትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) “የጉባ ላይ ወግ” በሚል ሰሞነኛ ቃለ ምልልሳቸው  አስታውቀዋል:: ግድቡ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ የመያዝ አቅም ሲኖረው እስካሁንም ከ71 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር በላይ ውኃ እንደያዘ መረጃዎች ያሳያሉ:: በ13 ተርባይኖች ታግዞ አምስት ሺህ 150 ሜጋ ዋት ኀይል ያመነጫል:: በአሁኑ ወቅትም ኀይል እያመነጨ ይገኛል:: ሀገራዊ የኀይል ችግሩን ከመፍታት ጎን ለጎን በአሳ ሐብት እና በቱሪዝም ከፍተኛ አቅም እንደሚፈጥር ይታመናል::

ሕዳሴ አሁን ካለበት ደረጃ ለመድረስ አድካሚ፣ አታካች፣ አጨቃጫቂ እና ከዓላማ የሚያዛባ  ሂደትን ማለፉን ጠቁመዋል:: የኢትዮጵያ ሕዝብ በሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ኢ ፍትሃዊ በሆነ ዓለም ውስጥ ፍትሕን በመጠበቅ በእጅጉ መፈተኑን እና በምሬት የተሞላ ጊዜ ማሳለፉን አንስተዋል:: የውኃው ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ እንደ ሌባ እና እንደ ጥፋተኛ የታየችበት ጊዜ መሆኑንም አስታውሰዋል:: በግድቡ ምክንያት ወደሌሎቹ የተፋሰሱ ሀገራት የሚወጣው ውኃ ካልተቋረጠ እና ሌላውን የማይጎዳ ከሆነ ኢትዮጵያ ኃይል ማመንጨቷ እንደ ችግር ተቆጥሮ ጫና መብዛቱ እንድንተክዝ የሚያደርግ ጉዳይ ሆኖ መቆየቱንም አብራርተዋል::

የጸጥታው ምክር ቤት በዓባይ ላይ በሚገነባው ግድብ በተደጋጋሚ መክሯል:: የተለያዩ አካላትም በግድቡ ጉዳይ መምከራቸውን አስታውሰው፣ ኢትዮጵያ ግድቡን መገንባት እንድታቆም ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎች እና ማስፈራሪያዎችን አስተናግዳለች ብለዋል:: “በግድቡ ምክንያት በየዕለት ተዕለት ሥራዎቻችን ላይ ጫና ሲደረግብን ነበር” ብለዋል::

የዓለም ተቋማት የአንድን ሀገር ገጽታ እና ልማት በእጅጉ ለሚያሻሽለው፣ የሀገሬውን ሕዝብ የኅይል ፍላጎት ለመፍታት ከፍተኛ አቅም ለሚፈጥረው ግድብ ብድር እና እርዳታን ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልነበሩ ሌላኛው ፈተና አድርገው አንስተዋል:: ይህም ከፍላጎታቸው ጋር የሚጣጣም ሃብት የሌላቸው ሀገራት በሃብት ውስንነት ምክንያት ታስረው ከተወዳዳሪው ዓለም ውጭ እንዲሆኑ የሚያደርግ እንደሆነ ጠቅሰዋል::

ዓባይ ለዘመናት ውኃችንን፣ አፈራችንን እና አሳዎችንን ሲወስድ  ኖሯል:: ከዚህም በላይ ወርቅን ይዞ ሲወጣ መቆየቱን እንደተረጋገጠ ተናግረዋል:: ይህ ተጨማሪ ቁጭት ሆኖ ለግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ  ማበርከቱን ተናግረዋል::

ግድቡ አሁን ወርቅ እና አፈራችንን እንድናስቀር  ከማድረጉም በተጨማሪ ብዙ ጨለማ ለወረሰው  ሕዝባችን ብርሐንን መፈንጠቁን ጠቅላይ ሚኒሥትሩ ገልጸዋል:: ሕዳሴ የኢትዮጵያን ሕዝብ ጽናት እና ብቃት የሚያሳይ፣ በመሰናሰል እና በመደመር ማሳካት የማይቻል ነገር እንደማይኖር ትምህርት የሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል::

“ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል” የሚለው ታሪክ ማብቃቱ በእያንዳንዱ ቤት ሊነገር ይገባል ብለዋል:: ግድቡ ባለፉት ዓመታት 74 ትሪሊየን ሊትር ውኃ መያዙን ጠቁመዋል:: ከግድቡ የሚመነጨው ዓመታዊ ገቢም አንድ ቢሊየን ዶላር እንደሚጠጋ አረጋግጠዋል:: ዓሣዎቻችንን የማጥመድ፣ ወርቆቻችንን የመለየት እና ኢነርጃችንን (ኅይል) የማምረት ሥራ የጋራችን ነው ሲሉም ተናግረዋል::

በታላቁ ዓባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለውን የሕዳሴ ግድብ ተከትሎ ያጋጠሙ ፈታኝ ችግሮች ለነገዋ ኢትዮጵያ ስሪት ትምህርት የሚሰጡ ልምዶች የተወሰዱበትም ነው:: “የዓባይን ውኃ እንዳንጠቀም ብዙ ሴራ ቢሸረብብንም ያንን ሁሉ አልፈን የወሰንነው ውሳኔ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እርምጃ ነው” ሲሉ የተናገሩት የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሪዚዳንቱ ዛዲግ አብርሐ ናቸው:: ከአካዳሚው የማኅበራዊ ትስስር ገጽ (ፌስቡክ) የተገኘው መረጃ አጽንኦት እንደሚሰጠው ግድቡ ኢትዮጵያ ልማቷን ለማረጋገጥ የምትሄድበትን ርቀት በግልጽ ያሳየ ነው:: “ጀምሮ ያለመጨረስ ታሪካችን የሁልጊዜም አለመሆኑን በሕዳሴ ማረጋገጥ እንደተቻለም ተናግረዋል::

የአሁኑ ትውልድ የቀደሙ ኢትዮጵያውያን እና ነገሥታት በዓባይ ላይ ግድብ የመሥራት ህልማቸውን እውን ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል:: ይህንንም አስቀጥሎ ለትውልድ ማስተላለፍ ከተቻለ ኢትዮጵያ ሁልጊዜም የታላላቅ ጅምሮች እና የታላላቅ ፍጻሜዎች ሀገር ሆና ትጓዛለች ሲሉ አስገንዝበዋል::

ጠቅላይ ሚኒሥትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ እስካሁን ባለፈችባቸው ጊዜያቶች ሁሉ ትልቁ ፈተና ከትልቁ ዓባይ ጋር የተያየዘ መሆኑን ተናግረዋል:: የዓባይ ጉዳይ ከሌሎች ችግሮቻችን በሦስት ምክንያቶች እንደሚበልጥም አሳይተዋል:: “በግድቡ መገንባት ‘እንጎዳለን‘ ብለው የሚያስቡ ወንድሞቻችን እንደማይጎዱ በተግባር የሚያረጋግጡ በመሆኑ በእስካሁን የግንባታው ሂደት ተፈጥሮ የነበረው ነገር እንዲረግብ በር የሚከፍት ነው” በማለትም እምነታቸውን  ተናግረዋል:: በባዕዳን መላክ ሱሳቸው የሆኑ ኀይሎችም ባዕዳዎቹ ረገብ ሲሉ በሚቀጥሉት ዓመታት እንደ ሕዳሴ ግድብ አይነት ትላልቅ ፕሮጀክቶች እንደሚጀመሩ ማረጋገጫ እንደሚሆን አጽንኦት ሰጥተዋል::

የሕዳሴ መጠናቀቅ ጀምረን መጨረስ እንደምንችል ያሳየንበት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒሥትሩ፤ ትልቁ ዓባይ ላይ መሠራት የነበረበትን ማሳካት እና ችግሩን መፍታት ከቻልን ሌሎች ትንንሽ ችግሮችን መፍታት እንደምንችል ማረጋገጫ የሰጠ ነው ብለዋል:: ይህም ኢኮኖሚያዊ ቦታችንን እንዲስተካከል በማድረግ ኢትዮጵያ የበለጸገች፣ ፍላጎቶቿን የምታስከብር፣ ከዓለም ስንዴ እና ፍትሕ የምትለምን ሳትሆን እራሷ የምታረጋግጥ እንደምትሆን አስገንዝበዋል::

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የጳጉሜ 3 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here