ያልተቋጨው ጦርነት

0
13

እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር የካቲት 24 ቀን 2022 የተጀመረው የሩሲያ – ዩክሬን ጦርነት ከባድ ውደመትን አስከትሏል። እያስከተለም ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀው ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡ አራት ሚሊዮን ገደማው በሀገር ውስጥ ሲሆን  ከስድስት ሚሊዮን በላይ ደግሞ በውጪ በጥገኝነት ይገኛሉ፡፡

የሩሲያ ኃይሎች በርካታ የዩክሬን ከተሞችን በከባድ መሳሪያ እያጠቁ ሲሆን የተወሰኑትንም በቁጥጥራቸው ስር አስገብተዋል። ከእነዚህም ውስጥ የዩክሬን ቁልፍ የወደብ ከተማ ኬርሶን አንደኛዋ ናት።

ዩክሬንን እና ሩሲያን ማን ያደራድር? በሚለው ጉዳይ ዓለም ሲመክርበት የቆየ ሲሆን አንደኛ ምርጫ ሆነው የቀረቡት የቀድሞ የጀርመን ቻንስለር አንጌላ ሜርክል ናቸው። አንጌላ እና የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በተመሳሳይ ዘመን ምሥራቅ ጀርመን ኖረዋል። አንጌላ ካልሆኑ ደግሞ የቻይናው ፕሬዝደንት ዢ ሺን ፒንግ ጥሩ ሽማግሌ ይወጣቸዋል ተብሏል።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ለአልጀዚራ ብቻ በሰጡት አንድ ቃለ ምልልስ ሀገራቸው በኃይል የያዘቻትን ክሬሚያን ከእንግዲህ ለዩክሬን እንደማትመልስ እቅጩን ተናግረዋል። ክሬሚያ የሞስኮ አካል መሆኗን ዩክሬን እየመረራትም ቢሆን ትዋጠው ብለዋል ላቭሮቭ።

የጥቃት አድማሳቸው እየሰፋ የመጣው የሩሲያ ኃይሎች የዩክሬኗን ማሪዮፖሎ ከተማን በከበባቸው ውስጥ አስገብተዋታል። ኢንተርኔት እና መብራት ተቋርጧል። ዙሪያ ገባው ገደል ሆኗል።

ሩሲያ የአውሮፓ ትልቁ የኒውክሌር ጣቢያ በእጇ መውደቁን አሳውቃ ነበር። ዛፖሪዢያ ይባላል። በዚህ የኒውክሌር ጣቢያ አንዳች ውድመት ቢከሰት በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች ከፍተኛ ጉዳት ይደርስባቸዋል። እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ወደፊት የሚወለዱ የልጅ ልጆቻቸው ጤነኛ ላይሆኑ ይችላሉ።

ይህን በይበልጥ ለመረዳት ከዓመታት በፊት እዚያው ዩክሬን ውስጥ ቼርኖቤል በተባለው የኒውክሌር ጣቢያ ላይ የደረሰውን አደጋ ማስታወስ ነው። ይህንን የቼርኖቤል የኒውክሌር ጣቢያ ላይ ከሦስት ዐሥርት ዓመታት በፊት የደረሰውን የሚያውቅ የዓለምን ስጋት ይጋራል። በዚህ ኒውክሌር ጣቢያ ላይ አንድ ነገር ቢከሰት አሉ ሳይንቲስቶች፣ ጉዳቱ ከጃፓን ሂሮሺማም የከፋ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፑቲን በሀገራቸው ብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው ምዕራባዊያን ተጨማሪ ማዕቀብ በሩሲያ ላይ እንዳይጥሉ አስጠንቅቀዋል። ይህን የተናገሩት ታዲያ የምዕራብ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በብራሰልስ ስለ ተጨማሪ ማዕቀብ እየመከሩ በነበረበት ወቅት ነው። ፑቲን ለሕዝባቸው ባስተላለፉት መልዕክት በዩክሬን ላይ የተከፈተው ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ በታቀደለት መልኩ እየሄደ ነው፤ በጭራሽ አታስቡ ብለዋል፡፡

አሜሪካ  በሩሲያ  የገንዘብ  ተቋማት  እና  ቁልፍ  ኢንዱስትሪዎች  ላይ  እያነጣጠረች  ነው።  የአውሮፓ ሕብረትም  በሩሲያ  የፋይናንስ  ገበያ  ላይ  አተኩሯል።  ዩናይትድ  ኪንግደም (እንግሊዝ)  “በክሬምሊን  እና  በዙሪያው ያሉ ሁሉ የሚደበቁበት  ቦታ  አይኖራቸውም”  በማለት  አስጠንቅቃለች።

ዋነኛው  የኢኮኖሚ  ዒላማ  የሩሲያ  የባንክ  ሥርዓትን  ከዓለም  አቀፉ  የስዊፍት  የክፍያ  ሥርዓት  ማለያየት ነው።  ይህ  ግን  መልሶ  በአሜሪካ  እና  በአውሮፓ  ኢኮኖሚ  ላይ  መጥፎ  ተጽዕኖን   አሳድሯል።

ሩሲያ  ከኔቶ  ጋር  ያላትን  ግንኙነት  እንደገና  ለማደስ  የማይቀያየር ፍላጎቴን  እወቁልኝ ብላለች።  ሦስት  ፍላጎቶቿ ደግሞ  ጉልህ  ናቸው። የመጀመሪያው  ኔቶ  ከዚህ  በላይ  እንደማይስፋፋ  ሕጋዊ  አስገዳጅ  ስምምነት  እንዲደረስ  ትፈልጋለች።  “ዩክሬን  መቼም  የኔቶ  አባል  እንደማትሆን  ማረጋገጥ  ሙሉ ግዴታችን  ነው”  ሲሉ  ምክትል  የውጭ  ጉዳይ ሚኒስትር  ሰርጌ  ሪያብኮቭ  ተናግረዋል።

ፑቲን  ደግሞ  ሩሲያ “ ከዚህ  በላይ  ማፈግፈግ  የምትችልበት  ቦታ  የላትም።  ዝም  ብለን  የምንቀመጥ ይመስላቸዋል?”  ብለዋል።

ሩሲያ  እ.አ.አ  በ1994 የዩክሬንን  ነፃነት  እና  ሉዓላዊነት  ለማክበር  ስምምነት ተፈራርማለች። ዩክሬን  ኔቶን  ከተቀላቀለች  ሕብረቱ  ክሬሚያን  መልሶ ለመያዝ ሊሞክር ይችላል ሲሉም  ፕሬዝዳንት  ፑቲን የሩሲያን ስጋት አስቀምጠዋል።

ሌላኛው  አንኳር  ጥያቄ  ኔቶ  በሩሲያ  ድንበር  አቅራቢያ  የጦር  መሣሪያ  እንዳያሰማራ  እና  እ.አ.አ ከ1997  ጀምሮ ሕብረቱን  ከተቀላቀሉ  አባል  ሀገራት  ጦሩን  እና  ወታደራዊ  መሠረተ  ልማቶችን  እንዲያስወግድ  ነው። ይህም  መካከለኛው  አውሮፓ፣  ምሥራቅ  አውሮፓ  እና  ባልቲኮች  (ላቲቪያ፣ ኢስቶኒያ፣ ሊቱዋኒያ)  ማለት  ነው።  ይህ  የሚያሳየው  ኔቶ  ወደ ቅድመ  1997 ድንበሩ  እንዲመለስ  ሩሲያ  መፈለጓን  ነው፡፡

ኔቶ  የመከላከያ  ጥምረት  ሲሆን  ለአዳዲስ  አባላት  በሩን  ክፍት  የማድረግ  ፖሊሲ  ያለው  ነው፡፡  በዚህ  ዙሪያ  30ዎቹም አባል ሀገራቱ  ምንም  ለውጥ  እንደማይኖር  ጽኑ  አቋም  አላቸው።

የዩክሬኑ  ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ኔቶን  ለመቀላቀል  ግልፅ  የሆነ  የጊዜ ገደብ  እንዲኖራቸው  ጥሪ  ማቅረባቸው ይታወሳል፤  የጀርመኑ  ቻንስለር ፍሬድሪክ ሜርዝ  በግልፅ  እንዳስቀመጡት  ግን  በረዥም  ጊዜ  ሊሳካበት  የሚችልበት  ዕድል  የለም ስለማለታቸው የቢቢሲ ዘገባ ያመላክታል።

የሩሲያው የዜና ማሰራጫ አር ቲ አር (RTR) እንደዘገበው ምዕራባውያን  እ.አ.አ  በ1990  ኔቶ  “ወደ  ምሥራቅ  አንድ  ኢንች”  እንደማይሰፋ ቃል  ቢገቡም  አልተገበሩትም። ይህ  የተባለው  ከሶቪየት  ሕብረት  መፍረስ  በፊት ነበር። በወቅቱ  ለሶቪየት ሕብረት ፕሬዚዳንት  ሚካኤል  ጎርባቾቭ  የተገባው ቃል  የሚያመለክተው  ምሥራቅ  ጀርመንን  ከግምት  በማስገባት  እንደገና  ስለተዋሃደችው  ጀርመን  ነው። ጎርባቾቭ  በኋላ  ላይም  “ስለ ኔቶ መስፋፋት ርዕሰ ጉዳይ  በጭራሽ  አልተነጋገርንም” ብለው ነበር።

ፈረንሳይ  ፑቲንን  እና ባይደንን ለማሸማገል  ያደረገችው ሙከራ የተሳካ  አልነበረም። ማንኛውም  ስምምነት  በምሥራቅ ያለውን  ጦርነት  እና  የጦር  መሣሪያ  ቁጥጥርን  ያካትታል። አሜሪካ  የአጭር  እና  የመካከለኛ  ርቀት  ሚሳኤሎችን  በመገደብ  እንዲሁም  በአህጉር  አቀፍ  ሚሳኤሎች  ላይ  አዲስ  ስምምነት  ላይ  መነጋገር  ለመጀመር ሃሳብ  አቅርባ ነበር። ሩሲያ  ደግሞ  ሁሉም  የአሜሪካ  የኒውክሌር ጦር  መሣሪያዎች  ከግዛቷ  ውጭ  እንዳይሆኑ  ትፈልጋለች። ሩሲያ  አክላም  በሩሲያ፣  በሮማኒያ  እና  ፖላንድ  በሚገኙ  የሚሳኤል  ማዕከሎች  ላይ  በጋራ ለመፈተሽ  የተያዘው  “ግልጽነት”  ላይ  አዎንታዊ  ሃሳብ  አላት።

ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ ቅድመ ሁኔታዎች በሁሉም ወገን በጥርጣሬ የሚታዩ ናቸው፤ ይህም ተግባራዊ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ የአካባቢውን ሰላም ለመመለስ የሚደረገው ጥረትም ውጤት ሳያስገኝ ጦርነቱ እንደቀጠለ ነው፡፡

ይህ በአንዲህ እንዳለ ዩክሬናዊያን ልጆቻቸውን ከመሬት ውስጥ በተሠሩ ትምህርት ቤቶች ማስተማር መጀመራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ ለሦስት ዓመታት ልጆቻቸው በጦርነት ምክንያት ከትምህርት ገበታ የራቁባቸው ዩክሬናዊያን በመሬት ውስጥ ለውስጥ ተቆፍረው በተሠሩ ትምህርት ቤቶች ለማስተማር በመወሰን ፈጽመውታል፡፡ በዚህም በካርኪቭ ብቻ 17 ሺህ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመልሰዋል፡፡ እስካሁን ሰባት የመሬት ውስጥ ትምህርት ቤቶች የተገነቡ ሲሆን ተጨማሪ መሰል ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት እና ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይስተጓጎሉ ለማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው የካርኪቭ ከንቲባ ተናግረዋል፡፡

በዩክሬን ጦርነቱን ተከትሎ ከአራት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ተስተጓጉለዋል፡፡ ቀሪዎቹ የቤት ውስጥ ትምህርት በመከታተል አሊያም ከከተሞች ራቅ ወዳሉ ስፍራዎች በመሄድ ትምህርታቸውን ለመከታተል እየሞከሩ ነው፡፡

ሦስት ዓመታትን የተሻገረው ጦርነቱ በርካታ ጥረቶች ቢደረጉም የሚጨበጥ ውጤት አልተገኘም፤ በቅርቡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን በአሜሪካዋ አላስካ ግዛት መገናኘታቸውን ተከትሎ ጦርነቱን ለመቋጨት ተስፋ ተጥሎበት ነበር፤ ይሁን እንጂ ጦርነቱ ተባብሶ እንደቀጠለ ነው፡፡ ዩክሬናዊያንም የጦርነቱ እሳት ሰለባ ሆነው ቀጥለዋል፡፡

 

(ቢንያም መስፍን)

በኲር የጳጉሜ 3 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here