የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንደጨረሱ በመምህርነት ሙያ ሰልጥነው በደንቢያ ቆላድባ በመምህርነት አገልግለዋል፤ የጎንደር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛም ነበሩ። በኋላ ደግሞ አስተዳዳሪ ሆኑ፤ ቆይተው ሕዝብን ወክለዉ የጎንደር እንደራሴ በመሆን ፓርላማ ገቡ:: በዚህ ውስጥ የጎንደር ክፍለ ሀገር መልሶ ማቋቋም እና ልማት ማኅበር (ጎልማ) መሥራችና አመራር ነበሩ፤ የጎንደር ሰላም እና ልማት ሸንጎ ሰብሳቢ ናቸው፤ የአስተዳደር ወሰን እና ማንነት ኮሚሽን አባል ሆነው ሠርተዋል፤ የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ኮሚሽን አባልም ነበሩ የተለያዩ ግዙፍ ኃላፊነቶች ላይ ተመድበው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በዕውቀት እና በብልሀት ሀገራቸውን አገልግለዋል፡- አቶ ባዩህ በዛብህ::
“የአቶ ባዩህ ከልጅነት እስከ አሁን ድረስ ግልጋሎት ሀገራችን አልተለያትም። ለልማቷ እና ለሰላሟ ታግለዋል:: ከወጣቱ ጋር ወጣት ሆኖ፣ ከምሁሩ ጋር ምሁር የሚሆን፣ ሁሉን እንደ አመጣጡ በዕውቀት፣ በብልሀት፣ በሀገር ወዳድነት እና አስተዋይነት የሚያስተናግድ ሰው ፈልጉ ቢባል በጎንደር ሕዝብ ዘንድ ቀድሞ የሚጠራ ስም ቢኖር “ባዩህ በዛብህ” የሚለው ነው:: ስለሆነም ከጎንደር ዋርካዎች መካከል አንዱ እና ዋነኛው ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም” ሲሉ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሥራት ዓፀደወይን መስክረውላቸዋል:: ከአቶ ባዩህ በዛብህ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እነሆ!
የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ኮሚሽን አባል ነበሩ፤ ዓላማው እና ተግባሩ ምንድን ነበር?
በአፍሪካ በተለይ ደግም በምሥራቅ አፍሪካ ላለው የፖለቲካ አለመረጋጋት የቅኝ ገዥዎች(ኮሎኔያሊስቶች) የኃይል የድንበር አከላለል ትልቁን ድርሻ ይይዛል! የኢትዮጵያ እና የሱዳን ጉዳይም መሰል ችግር ገጥሞታል:: ቀደምት መንግሥታት ዐፄ ምኒሊክ፣ ዐፄ ኃይለ ሥላሴም ሆኑ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም አንድም መሬት አሳልፈው አልሰጡም። በዐፄ ምኒሊክ ዘመን ሱዳን መንግሥት አልነበራትም፤ ይልቁንስ መሀዲስቶች/ደርቡሽ በተባሉ የጎጥ አስተዳዳሪዎች ስትመራ ቆይታለች፤ ከቅኝ ግዛት ነፃ ከነበሩት ሁለት የአፍሪካ ሀገሮች ኢትዮጵያ አንዷና ቀዳሚዋ ነበረች።
በዐፄ ምኒልክ ዘመን በወርሀ መስከረም ያለ መንግሥት እና የአካባቢው ሕዝብ እውቅና ሜጀር ጉኤ የተባለ የእንግሊዝ ወታደር በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል ድንበር አሰመረ:: ያሰመረው የቅኝ ግዛት መስመር ተቀባይነት የለውም። በዐፄ ኃይለስላሴ የስልጣን ዘመን ደግሞ በጠረፈኞች አማካኝነት ድንበሩን እስከ ጓንግ ጠረፍ ድረስ አስከብረውት ይኖሩ ነበር። በተጨማሪም በሁለተኛው የጃንሆይ ህገ መንግሥት ላይ ንጉሡ ሕግ መወሰኛ እና ሕግ መምሪያ ም/ቤቶችን ሳያማክሩ በድንበር ወሰን ላይ ውሳኔ ማሳረፍ እንደማይችሉ ተደንግጓል። ማንም ቅኝ ገዥ ከነፃ ሀገር መንግሥት ጋር ሳይደራደር የሚያስቀምጠው የድንበር መስመር ተቀባይነት የለውም። በአፍሪካ የሰላም አባት ተብለው በዩ ኤን ሊሸለሙ የነበሩት የአፍሪካ ህብረት መስራች ዐፄ ኃይለ ሥላሴ የድንበሩን ጉዳይ ለም/ቤቱ ሲያቀርቡት የቅኝ ገዥ ድንበር ማካለል ውድቅ መሆኑን ም/ቤቱ ወስኗል። ይህን የቅኝ ገዥ መስመር ባለ መቀበላቸውም ከዩ ኤን ይሰጣል የተባለው የሰላም የኖቬል ሽልማት ተላልፎ ለማርቲን ሉተር ኪንግ ተሰጥቷል::
በወቅቱ መንግሥት አልባ የነበረችው ሱዳን ዛሬ ላይ በመጀመሪያው የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ በቅኝ ግዛት ጊዜ በነበረው የድንበር መስመር የተከፋፈሉ ጎሳዎችን አንድ ላይ ለማሰባሰብ ስለሚቸግር በነበረው ይቆይ ተብሎ ተወስኗል በመሆኑም የጉኤ መስመር ድንበራችን ነው። የሱዳን የታጠቁ ኃይሎች በተለያየ ጊዜ ድንበር ጥሰው በመግባት በአማራ ገበሬዎች ላይ የሚያደርሱት ግድያ፣ አፈና፣ ዝርፊያ እንዲሁም ከልማት ሥራ ማደናቀፍ ተባብሶ ቆይቷል:: የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ኮሚሽን የሕዝባችንን መገፋት በመቃወም እና ሉዓላዊ ግዛታችን ለማስከበር ሲሠራ ቆይቷል::
የጎንደር የሰላም እና ልማት ሸንጎ ሰብሳቢ ነዎት፤ ሸንጎው የተቋቋመበት ዓላማ እና ሥራዎቹ ምንድን ናቸው?
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተከሰቱ አለመረጋጋቶች ነበሩ፤ ከተማውን እረፍት ለመንሳት አቅዶና አልሞ ሃይማኖትን እና ዘርን እንደ ካርድ መዞ የሚንቀሳቀስ ኃይል አለ፤ ሕዝቡን እና ከተማውን የመታደግ ተልእኮ ይዞ ነው ሸንጎው የተመሠረተው:: ሕዝባዊ አደረጃጀቶችን እና ባሕላዊ የሽምግልና እሴቶችን በመጠቀም የጎንደር እና አካባቢውን ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስ በጋራ ለመሥራት ሕዝቡ ወሰነ:: በዚህም 13 አባላት ያሉትን የሰላም እና የልማት ሸንጎ መሠረተ:: ሸንጎው ሰላም ለማደፍረስ የሚሹ ኃይሎችን ሴራ ለማክሸፍ ሕዝቡን በማሳተፍ እገዛ ያደርጋል::
ጎንደር ከተማ ሁሉም ሃይማኖቶች ተከባብረውና ተፈቃቅረው በአንድነት የሚኖሩባት ታሪካዊ ከተማ ናት፤ ከተማዋ የጥፋት ኃይሎች ኢላማ ነበረች፤ የጥፋት ሃይሎችን እኩይ ሴራ ማክሸፍ የሚቻለው የሁሉም ሃይማኖት መሪዎች እና ተከታዮች ለሰላም፣ ለውይይት እና ለእርቅ በአንድነት እና በጋራ ሲቆሙ ነው:: በዚህም ሃይማኖታዊ እሴቶችን በማስቀጠል ሸንጎው ከሌሎች አካላት ጋር በመተባበር ከተማዋን ከጥፋት ኃይሎች ታድጓል:: የእምነት አባቶች በየተቋማቸው ሃይማኖታዊ አስተምህሮትን መሠረት ያደረገ ምክርና ተግሳጽ በመስጠት በተሳሳተ መንገድ ወደ ጥፋት እና ግጭት የሚገቡ ወጣቶችን በመመለስ የተፈጠረውን የሰላም መደፍረስ ማስቆም ተችሏል::
በከተማው የተስተዋለውን የሰላም መደፍረስ እንደ ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ለዘረፋና ስርቆት እንዲሁም ስርዓት አልበኝነት እንዲነግስ የሚፈልጉ አካላት ዓላማ እንዳይሳካ ተሠርቷል:: ባህላዊ የሽምግልና እሴቶቻችንን በመጠቀም በከተማው በሃይማኖት እና በዘር ሽፋን የተፈጠረውን የሰላም መደፍረስ ለማስቆም በቀበሌ፣ በክፍለ ከተማ፣ በመንደር እንዲሁም በእድሮች ጭምር ሕዝቡን በማወያየት የከተማውን ሰላም ወደ ነበረበት መመለስ ተችሏል:: በጥፋት ኃይሎች ሴራ የከተማውን ሰላም ለማደፍረስ ተልእኮ ተቀብለው የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች እና ቡድኖችን ሕዝቡ በተደራጀ አግባብ በመታገል ሰላሙን እንዲያሰፍን ሸንጎው የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል:: የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በሚነሱ አለመረጋጋቶች እና ግጭቶች ሕዝቡ እንዳይጎዳ፣ ተፈጥረው የነበሩ አለመግባባቶችም እንዳይሰፉ በውይይት፣ በእርቅ እና በማግባባት ማለዘብ ተችሏል::
ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ጋር እንዴት እየሠራችሁ ነው?
ምክክር የእውነት ፍለጋ ሂደት በመሆኑ ለኮሚሽኑ ተልዕኮ መሳካት ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የግል እና የጋራ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል። ኮሚሽኑ የአካታችነት፣ የአሳታፊነት፣ የግልጸኝነት እና የተአማኒነት እሴቶችን መርህ በማድረግ ሀገር ጸንታ እንድትቀጥል ሀገራዊ እና ታሪካዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት እየሠራ ነው። ሀገር በቀል እውቀትን መሠረት በማድረግ በእውቀት እና በጥበብ የታገዘ ብሔራዊ ምክክር ከታችኛው እርከን ጀምሮ ለማካሄድ የሚያስችሉ ዝግጅቶች ኮሚሽኑ እያደረገ ይገኛል። በበርካታ የዓለም ሀገራት የተካሄዱ ምክክሮች ለሀገራቸው ሰላምና እድገት መሠረት የጣሉ ናቸው፤ በኢትዮጵያም ሀገራዊ ምክክሩ ሰላምን፣ አብሮነትን እና አንድነትን ለማጠናከር ትልቅ ሚና አለው።
ሀገራዊ ምክክር የኢትዮጵያውያን አጀንዳ በመሆኑ የጋራ መግባባትን በመፍጠር ዘላቂ ሰላምና ልማት እውን ለማድረግ ወሳኝ ነው:: የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚሽን ለዘመናት ምላሽ ሳያገኙ እና መግባባት ላይ ያልተደረሰባቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች በማጥናትና በመለየት ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር ትልቅ የሰላም መሳሪያ ነው።
ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የሕዝቦችን አብሮነትና አንድነት በማጠናከር በሀገሪቱ ለተፈጠሩ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለማስቀመጥ ያግዛል የሚል እምነት አለን:: ሀገራዊ ምክክሩ በአካታችነት፣ ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች እና በገለልተኛ አካል የሚመራ በመሆኑ ውጤታማ ይሆናል ብለን እናምናለን:: በመሆኑም ከአጀንዳ ማሰባሰብ ጀምሮ ተለያዩ ድጋፎችን ለኮሚሽኑ እናደርጋለን:: በዚህ መልኩ ተደጋግፈን ሀገራዊ አንድነትን እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በጋራ እየሠራን ነው::
በሀገራችን የተፈጠረው ችግር ኢትዮጵያዊ የመከባበር እሴቶች የአመራሩ ቁርጠኝነት ማነስ እና ስሜታዊነት ናቸው። የሰው ሕይወትን የቀጠፈው ግጭት አነሳሱ ኢትዮጵያውያን ያዳበሯቸው የፍቅር እና የአንድነት እሴቶች በመሸርሸራቸው፣ የእምነት አባቶችም ፈጣሪ የሰጣቸውን የመቻቻል እና የመፈቃቀር ሥራ ትተው በፖለቲካ በመጠመዳቸው ነው:: እነዚህን እየጠፉ የመጡ የመቻቻል፣ የአንድነት እና የመፈቃቀር እሴቶችን መመለስ ያስፈልጋል:: ሁሉም ሐይማኖቶች ክፋትን አያስተምሩም፤ ይልቁንም የችግሩ ፈጣሪዎች በሐይማኖት ካባ የተወሸቁ ፖለቲከኞች ናቸው:: ወጣቱም ነገሮችን በምክንያት መጠየቅ እና መረዳት እንጂ በስሜት መጓዝ አይገባውም:: የተፈጠረውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ውይይት እና ሽምግልና ወሳኝ ነው::::
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የጳጉሜን 3 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም