ርብርብ የሚጠይቀዉ ሥራ

0
14

ሄቨን በሪሁን በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ ሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ ዓድዋ ድል አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ7ኛ ክፍል ተማሪ ናት። የክረምቱን ወቅት በበጎ ፈቃደኛ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመላሽ ወጣቶች ሲሰጥ የነበረውን የማጠናከሪያ ትምህርት ስትከታተል ቆታለች። ይህም በአዲሱ የትምህርት ዘመን ለማስመዝገብ ላቀደችው የተሻለ ውጤት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያግዛት ተናግራለች።

ተማሪ ሄቨን በሪሁን ለ2018  የትምህርት ዘመን ቀድማ መመዝገቧን ተናግራለች። በአሁኑ ወቅትም ራሷን ለትምህርት ዝግጁ ከማድረግ ጀምሮ አስፈላጊ የትምህርት ቁሳቁሶችን በማሟላት ላይ ናት።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ260 ሺህ በላይ ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ዕቅድ ተይዟል:: በሁሉም ወረዳዎች የተማሪ ምዝገባ እየተከናወነ እንደሚገኝ መምሪያው ለአሚኮ አስታውቋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በተከሰተው የሰላም እጦት  የትምህርት እንቅስቃሴያቸው በከፍተኛ ሁኔታ ከተስተጓጎለባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ የምዕራብ ጎጃም ዞን ነው። በእነዚህ ዓመታት ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ እንደሆኑ የመምሪያው ኃላፊ የስጋት ደሴ አስታውቀዋል። በ2018 የትምህርት ዓመት ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሁሉንም ተማሪዎች መዝግቦ ማስተማር በዕቅድ ተይዟል። ከ426 ሺህ በላይ ተማሪዎች ወደ መደበኛ ትምህርት ለማምጣት ትኩረት መደረጉም ተመላክቷል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ያለፈውን ዓመት እቅድ በገመገመበት እና የመጭውን ዓመት የተማሪ ምዝገባ የንቅናቄ መድረክ ባካሄደበት ወቅት የተገኙት የደቡብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የትምህርት መምሪያ ኃላፊው ደስታ አስራቴ እንዳስታወቁት በትምህርት ዘመኑ ከ811 ሺህ በላይ ተማሪዎች ይመዘገባሉ:: እስከ ነሐሴ 29 ቀን 2017 ዓ.ም የተመዘገቡት ተማሪዎች ቁጥር የዕቅዱ 31 በመቶ ነው:: ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ቢሆንም ከዘንድሮው ዕቅድ አኳያ ግን ዝቅተኛ እንደሆነ ነው የተናገሩት።

በቀጣይም የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን በማሳተፍ ማኀበረሰቡን በማነሳሳት የታቀደውን እቅድ ለማሳካት በትኩረት እንደሚሠራ አሳውቀዋል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ጌታሁን ፈንቴ በበኩላቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ800 በሚበልጡ ትምህርት ቤቶች ትምህርት ተቋርጦ መቆየቱን ተናግረዋል። ችግሩ ልጆች ወደ አልባሌ ድርጊቶች እንዲገቡ፣ ለማኅበራዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጫና እንዲዳረጉ ማድረጉንም ገልፀዋል።

ችግሩ ወደ ሌላ ሦስተኛ ዓመት ተሸጋግሮ ሀገርን እንደ ሀገር የሚያስቀጥል ትውልድ እንዳይታጣ ለ2018 የትምህርት ዘመን በከፍተኛ ንቅናቄ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ከ790 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ መታቀዱን የገለጹት ኃላፊው አሁናዊ አፈጻጸሙ ግን ከ10 ነጥብ አምስት በመቶ የተሻገረ አለመሆኑን አመላክተዋል። ይህም አፈጻጸም በቀጣይ የትምህርት ማኅበረሰቡ እና መላው ሕዝብ ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባ የማንቂያ ደወል መሆኑን አስገንዝበዋል።

የአማራ ክልል የተማሪ ወላጆች ኅብረት ፕሬዝዳንት አዱኛ እሸቴ በበኩላቸው ተማሪዎችን ከትምህርት ውጪ እንዳይሆኑ በጋራ ቆሞ “በቃ!” የሚባልበት ጊዜው አሁን እንደሆነ አስገንዝበዋል። በግጭቱ ትምህርት ቤቶች ለጉዳት እየተዳረጉ ነው፤ በየዓመቱ መማር የነበረባቸው ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ ሆነው ለተመሰቃቀለ ሕይወት እየተዳረጉ ነው፤ በትምህርት ሥራው ላይ እየደረሰ ያለው መስተጓጎል ሁሉም ነገ የሚጠብቃት ኢትዮጵያ ዕውን እንዳትሆን፣ ሕዝቡ ከድህነት አዙሪት እንዳይወጣ በማድረግ ሀገር ከዓለም አቀፍ የውድድር መድረክ እንድትወጣ ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ አሉታዊ ተጽእኖውን መረዳት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

የሰለጠነ፣ ብቁ፣ ተወዳዳሪ እና ችግር ፈቺ ትውልድ የሚፈራው በምንም የማይደናቀፍ የትምህርት ሥራ ሲኖር ነው የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፣ በመሆኑም ትምህርት ቤቶች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተከፍተው ሁሉም ተማሪዎች ወደ መማር ማስተማር እንዲመለሱ ማድረግ ከሁሉም የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

በየትምህርት ቤቶች የተዋቀረ የወላጅ እና መምህራን ኅብረት መኖሩን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባም አሳስበዋል። በተለይም የተማሪ ወላጆች ልጆቻቸውን በወቅቱ በማስመዝገብ ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ መበርታት እንዳለባቸው ፕሬዝዳንቱ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከዚህ በፊትም መስዕዋትነት እየከፈሉ የልጆቻቸው ትምህርት እንዳይቋረጥ ያደረጉ ወላጆች መኖራቸውን ጠቅሰው ይህ ተግባር ከልጆቻቸውም በላይ ለሀገርም ትልቅ ውለታ እንዳለው አስገንዝበዋል።

“ታጥቀው በጫካ ያሉ ወጣቶችም የኛው ልጆች ናቸው፤ ሰላም ወርዶ መልካም ኑሮን እንዲኖሩ እንፈልጋለን፤ እነዚህ ታጣቂዎች የተማሪዎችን የከፋ አዋዋል በውል ተገንዝበው ለትምህርት ቤቶች መከፈት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ማድረግ እንጅ ማደናቀፍ ማብቃት አለበት” በማለትም ጠይቀዋል።

ያሳለፍነው የትምህርት ሥብራት ይበቃል፤ የፈረሱ ትምህርት ቤቶችን ለመጠገን፣ ከትምህርት ርቀው የቆዩ ልጆችን በሥነ ልቦና ለመደገፍ፣ በቀጣይም ያለማቋረጥ እንዲማሩ በጋራ መሥራት እንደሚገባ ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል:: “በያለፈው ሊቆጨን ይገባል፤ ጥፋትን መድገምም የለብንም፤ የተከፈቱ ትምህርት ቤቶች እና በዕውቀት ገበታቸው ላይ የሚውሉ ልጆችን ብቻ ማየት እንሻለን!” በማለትም መልዕክት አስተላልፈዋል::

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ነሐሴ 29 ቀን 2017 ዓ.ም የተጠናቀቀውን በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ እና የ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል። በመድረኩ ላይ የተገኙት ቢሮ ኃላፊዋ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) የሰላም መደፍረሱ በትምህርት ሥራው ላይ ያደረሰው ጫና አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት ብቻ ከአራት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት እንደራቁ ማሳያ አድርገው አንስተዋል።  ችግሩ በትውልድ ላይ የማይመለስ ክፍተት ፈጥሮ የሚያልፍ እንደሆነ የጠቆሙት ኃላፊዋ፤ በዚህም ክልሉ የተማረ የሰው ኀይል እንዲያጣ በማድረግ በሁለንተናዊ ዘርፍ ከውድድር ውጪ የሚያደርገው እንደሚሆን አስገንዝበዋል።

የጸጥታ ችግሩ እየፈጠረ ያለው አሉታዊ ተጽእኖ እንዲያበቃ የትምህርት ባለድርሻ አካላት ዋነኛ አጀንዳቸው አድርገው እንዲሠሩ፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ወላጆች፣ ተማሪዎች፣ ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች እና  ማኅበረሰቡ ችግሩን በሚገባ ተገንዝበው ለመፍትሑው በጋራ እንዲቆሙ  በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲሱ የትምህርት ዓመት ሰባት ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎችን ለመመዝገባ መታቀዱ ይታወሳል። እስከ ነሀሴ 29/2017 ዓ.ም ከሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ተመዝግበዋል። “ትምህርት ከፖለቲካ ነጻ ነው። ሁሉም አካላት የነገን ትውልድ በማሰብ ክልሉ በተማረ የሰው ኅይል እጦት ምክንያት ወደ ኋላ እንዳይቀር በርብርብ መሥራት ይገባል” በማለትም ቢሮ ኃላፊዋ ጥሪ አቅርበዋል።

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የጳጉሜን 3 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here