“ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ አንጡራ ሀብት”   – በዓለማየሁ ዋሴ (ዶ.ር)

0
8

የኢትዮጵያ አንጡራ ኃብት፣ ከፈጣሪ የተቸራት ገጸ በረከት፣ የጉስቁልና ዘመን ማክተሚያ ትዕምርት!

ታላቁ የዓባይ ግድብ በስኬት መጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ከዓድዋ ድል በኋላ የተጎናፀፈችው ግዙፍ ታሪካዊና ስትራቴጅካዊ ድል ነው::

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን በየዘመናቱ በርካታ ገድላትን የፈጸሙ ባለታሪኮች ቢሆኑም የዓድዋ ድልና ታላቁ የዓባይ ግድብ ስኬት ግን በሰማይ ላይ እንዳለ ችቦ ከኢትዮጵያ አልፎ በዓለም አደባባይ የሚታዩ አኩሪ ገድሎች ናቸው::

የሕዳሴ ግድብ በስኬት መጠናቀቅ ከዓድዋ ድል ጋር የሚያመሳስለው ብዙ ጉዳዮች ቢኖሩም ሦስት መሠረታዊ ነገሮችን ግን መጥቀስ ተገቢ ነው::

፩. የዓድዋ ጦርነትን እና የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ኢትዮጵያ ያለማንም ረዳት፣ አጋዥ፣ ለጋሽ፣ አባዳሪ እና አይዞሽ ባይነት ብቻዋን የተወጣችውና የተጐናፀፈችው ድል መሆኑ፤

፪. የዓድዋ ጦርነትና የግድቡ ግንባታ ኢትዮጵያዊያን አመላቸውን በጉያቸው፣ ልዩነታቸውን በጓዳቸው ትተው ገንዘባቸውን፣ ዕውቀታቸውን፣ ጊዜያቸውን፣ ላባቸውን፣ ደማቸውን አዋጥተውና አስተባብረው ያከናዎኑትና በድል የተወጡት ዘመን ተሻጋሪ አኩሪ ተግባር መሆኑ፤

፫. የዓድዋ ድልና የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የሰው ልጆች ሁሉ በሀገራቸውና በሉዓላዊ ግዛታቸው በነጻነት የመወሰን፣ ሦስተኛ ወገን ያወጣውን ሕግ መሰል ቀንበር፣ ውል መሳይ እግረ ሙቅ ያለመቀበል ጀግንነትን ያስተዋወቀ፣ በጥቅሉ የቅኝ ገዢዎችን ቀንበር የሠበረ፤ ፍትሕን በራስ አቅም ያስከበረ ለመላው ታዳጊ ሀገር ሕዝቦች ትምህርት የሆኑ ድንበር ተሻጋሪ ድሎች መሆናቸው ነው::

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ፋይዳዉ እንደሌሎች ኘሮጀክቶች ነጠላ ትርክት የሚተረክለት፣ ውስን ጠቀሜታ ያለው አይደለም:: ታላቁ የሕዳሴ ግድብ እጅግ የገዘፈ ፋይዳና ስትራቴጅካዊ ጠቀሜታን ለኢትዮጵያ

የሚያበርክት መሆኑ ጎላ ብሎ ሊነገር ይገባል:: ከመሠረታዊ ፋይዳዎቹና ጥቅሞቹ ጥቂቶቹን ለመግለጽ፤

፩. ፖለቲካዊ ጥቅም፡- ኢትዮጵያ በሉዓላዊ ግዛቷ ውስጥ ያለ ማንም ፈቃድና ድጋፍ የተፈጥሮ ሀብቷን በማልማት ከድህነት መላቀቅ የምትችል ሀገር መሆኗን መሠረት ጥሎ አልፏል:: በተጨማሪም የፖሊሲ ነጻነት ያላት ሀገር፣ በየትኛውም ዘመን ቢሆን መብቶቿንና ጥቅሞቿን ለማስከበር ወደ ኋላ የማይሉ ዜጎችና መንግሥት ያሏት ሀገር መሆኗን የመግለፅ ትልቅ ፋይዳን አጎናጽፏል፤

፪. ኢኮኖሚያዊ ጥቅም፦ የዓባይ ግድብ የሚያመነጨው ኃይል የኢንዱስትሪ መሠረት፣ የኑሮ ማሻሻያ ግብዓት፣ የቱሪዝም መዳረሻ፣ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ሆኖ ኢኮኖሚዋን ያነቃቃል፤ የጀርባ አጥንት ሆኖ ይደግፋል፤ ታላቅና አዲስ ሐይቅ ፈጥሮ ለአካባቢው የተረጋጋ ሥርዓተ ምህዳር በማበርከት በርሃማነትን ለመቋቋም ደጀንና ጸጋ ይሆናል።

፫. የደህንነትና የፀጥታ ጥቅም፤ ኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች አሏት ከተባለ በዋነኝነት የጠላትነት ሰበብ ሆኖ የሚጠቀሰው የዓባይ ውኃ ነው:: ኢትዮጵያ ከበለፀገች ዓባይን ትገድባለች፤ ስለዚህ

‘ሠላምና መረጋጋት አግኝታ ለኢኮኖሚዋ ዕድገት ወሳኝ ሊሆን የሚችለውን ዓባይን እንዳትገድብ በውስጥም በውጭም ሰላሟን እንንሳት’ የሚል ኋላቀርና ክፉ አስተሳሰብ ነበር:: አሁን የፈሩት ይደርሳል የጠሉት ይወርሣል ነውና በዓባይ ወንዝ ላይ ሊገነቡ ከሚችሉት ግድቦች መካከል ትልቁ የሆነው የሕዳሴው ግድብ ተጠናቅቆ ውኃ ተሞልቶ ታሪክ መታጠፊያው ላይ መድረስ ግዴታ ሆኗል:: ይህ ስኬት የጠላቶቿን ሰበብ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያመከነ ስለሆነ ጠላቶቿ የመጨረሻ ሞኝ ካልሆኑ በስተቀር ከዚህ ቀደም የሚከተሉትን ፖሊሲ መከተል ፋይዳ የሌለው፣ አዋጭ ያልሆነ መናኛ ሀሳብ መሆኑን ትምህርት የሠጠ ሆኗል::

ስለሆነም ከእንግዲህ ግድቡን በማስቆም ሰበብ ኢትዮጵያን ማወክ ጊዜ ያለፈበት ተግባር ብቻ ሣይሆን ግድቡን መተናኮልም የኒውክሌር ማብላያን ጋንን ሸንቁሮ የራስን ትውልድና ሀገርን እንደማጥፋት ይቆጠራል:: እናም የሕዳሴ ግድብ ለእናት ሀገሩ ኢትዮጵያ በልጆቿ የተበረከተ የሠላምና የደኅንነት ዘብ ሆኖ የቆመ ስትራቴጅካዊ የኒኩሌር ኃይል ነው::

፬. የዲኘሎማሲ ጥቅም፦ ኢትዮጵያ ግድቡን ስትጀምር የማንንም ጥቅም ለመጉዳት ሣይሆን በመተባበር መንፈስ ራስን የማልማት ኘሮጀክት እንደሆነ አበክራ ስትገልጽ ቆይታለች:: ‘ከዚህ ቀደም በተናጠል ተፈረሙ የተባሉት የቅኝ ገዥዎች ውሎች ትብብርን የማያስጠብቁ፤

በወንደማማች ሕዝቦች መካከል መጠራጠርንና መቃቃርን የሚፈጥሩ፣ በጥቅሉ ከሞራል የወረዱ ውሎች ናቸው’ በማለት ስትሟገት ቆይታለች:: በዚህ አቋሟ አሁን በተግባር የውኃው ፍሰት ሳይቀንስ፣ በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ላይ ጉዳት ሳያስከትል ግድቡ በውኃ ተሞልቶ መጠናቀቁ

‘ሀበሾቹ ፍትሕ ያውቃሉ’ የተባለውን ቀደምት ቃል ዳግም ያስመሰከረ ኢትዮጵያ ለእውነትና ፍትሕ የቆመች ሀገር መሆኗን የሚያሳይ በወርቅና በአልማዝ የተከፈፈ የዲኘሎማሲ ካባ የሚያጐናፀፋት ይሆናል።

፭. የመንፈስና የሥነ ልቦና ልዕልና ማጎናጸፍ፦

የዓባይ ወንዝ ወይም ጊዮን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት አራት ወንዞች አንዱ ሲሆን ይህም ወንዝ ‘ኢትዮጵያን ይከባል’ ተብሎ ተጽፏል:: የዓባይ ወንዝ እስከ ዛሬ ድረስ ለሺህ ዓመታት ከኢትዮጵያ ተነስቶ ኢትዮጵያን ከፍሎ ሲጓዝ እንጅ ሲከባት አልታየም ነበር:: የፈጣሪ ቃል አይታበልምና ከእንግዲህ የዓባይ ወንዝ በፍካሬያዊ ትርጉሙ ወደ ኃይል ተቀይሮ በኢትዮጵያ ምድር ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ይዘዋወራል:: በየቤታችን ራትና መብራት ሆኖ ይገባል፣ የመኪኖቻችን፣ የባቡሮቻችን ጉልበት ሆኖ በየጋራውና በየሸንተረሩ፣ በየሜዳውና በየከተማው ይዘዋወራል::

ዓባይ በበረከቱ ኢትዮጵያን ይከባል:: የፈጣሪን ቃልኪዳን በዘመናችን እውን ሆኖ አየን፤ እንደተነገረልን የአማኞች ሀገር፣ ጉስቁልና የማይገባን፣ በተፈጥሮ የታደልን ሕዝቦች መሆናችንን እንድናምን

ወደላይ ተስፈንጥረን እንድንዘል አንችልም፣ አይሆንልም የሚልን አዚምን የሰበረ፣ከዚህ በላይ የሥነ ልቦና ከፍታን የሚፈጥር፣ የትንሣኤ ምልክትስ ምን ይኖራል?!

ይህ እውን እንዲሆን ላስቻሉ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ምስጋና ይድረሳቸው! እንድናከናውን ለፈቀደልን ፈጣሪም ክብር ሁሉ ለእርሱ ይሁን!

በኲር የጳጉሜን 3 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here