‘‘ቸር ተመኝ ቸር እንድታገኝ!’’

0
7

የፎክሎር ባለሙያዎች እንደሚሉት የክረምት ክብደት ልክ እንደ ምጥ ክብደት ዓይነት ነው፡፡ መስከረምም ከምጥ በኋላ እንደሚገኝና በመገኜቱ ቤቱን በእልልታ እንደሚሞላ አዲስ የተወለደ ህጻን ድምጽ ነው፤ ልክ እንደመስቀል ወፍ ልዩ ዜማ ዓይነት፡፡ ውሽንፍሩን ከባድ ምጥ ውስጥ እንዳለች እናት እና ሕይዎት ለመተካት ስትል በመካከል ስለሚፈጠር ሞት እያሰበ እንዲሁም እየተጨነቀ የህጻን ልጅ ድምጽ እንደሚናፍቅ ቤተ ዘመድ ከክረምት በኋላ ፀሐይ እና ብርሃን እንደሚመጣ መናፈቅ የተፈጥሮ ሕግ ነው፡፡ የክረምቱን ክብደት ጸንተን የምናልፈው የመስከረም መምጣት ተስፋ ስለሚሆነንም ጭምር ነው፡፡

ሰው በክረምት የመለየት እና የመረበሽ፣ የናፍቆት እንዲሁም የትዝታ አዚም ይጫነዋል፡፡ ክረምቱ ሶስት ወራት ብቻ ሳይሆን ዘላለም ይመስላል፡፡ ነግቶ የማንተያይ፣ ተለያይተን ድጋሚ  የማንገናኝ ዓይነት ስሜት ሰውን ይጫነዋል፡፡ ሰው ሲታመም ባይሆን ይህን ክረምት በከረመ ይባላል፡፡ ትዳርን ለማከም በክረምት ሰው አይፋታም፤ ባይሆን ክረምቱን አብራችሁ ክረሙ ይባላል፡፡ ከክረምት ጋር መለየት እና ናፍቆት ሲጨመር የመለየት ክብደት ከሞት እኩል የሆነ ያህል ይሰማናል፡፡

ከመስከረም ውብ ፀሐይ እና ነፋሻማ አየር ለመድረስ በከባድ ጉም፣ ጉርምርምታ፤ በመብረቅ ብልጭልጭታ፤ በቅዝቃዜ፤ በጎርፍ እና  ውኃ ሙላት ማለፍ ግድ ይላል፡፡ ክረምት ያላረሰ እና ያልዘራ፣ ዘርቶም ያላረመ እና አዝእርቱን ያልተንከባከበ ገበሬ ከክረምቱ ክብደት ጋር በረሃብ መክረም ግድ ይለዋል፡፡ በበጋ እንደልብ ለመብላት ክረምቱን ዝናብ መመታት እና መድከም ግድ ይላል፡፡

ከብዙ ውጣ ውረድ እና ድካም በኋላ እንደሚገኝ የሰው ልጅ ስኬት መስከረምም ከክረምት ብዙ ቅዝቃዜ እና ድብታ እንዲሁም  ልፋት በኋላ ከብርሃን እና ከአበባ ጋር ብቅ ይላል፡፡ ባለሙያዎች የወቅት መለዋወጥ  ከሰው ልጅ ተፈጥሮ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ስለመሆኑ የሚናገሩት ለዚህ ነው፡፡

እንደ ክረምቱ ክብደት፣ እንደ ውሽንፍሩ፣ እንደ ጉሙ፣ እንደ ብርድ ቅዝቃዜው፤ ከረምት ያልፋል ብለን ተስፋ ባናደርግ የመስከረምንም መምጣት ባንጠብቅ የክረምቱ አጭር ወራት እጥፍ ይሆንብን ነበር፡፡ ግን በምን አለፍነው? በተስፋ፡፡ ሰውም በሕይዎቱ ክረምት አልፎ መስከረም ይመጣል ብሎ ተስፋ እንደሚያደርገው ሁሉ  ከብዙ ድካም እና ውጣ ውረድ፤ ከብዙ መጨነቅ በኋላ ስኬት ይመጣል ብሎ በተስፋ ይደክማል፡፡

በመስከረም ቀጠሯቸውን እንደማያጥፉት እንደ እንቁጣጣሽ የልጅነት ትዝታ፤ እንደ መስቀል ወፍ ናፍቆት ጓጉተን ባንጠብቅ እና ይመጣል ብለን ተስፋ ባናደርግ ክረምት ከባድ ነው፡፡

አብዛኛዉ ሰዉ በአዲስ ዓመት በሕይዎቱ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ ከመመኘት ባለፈ በኑሮዉ እና በሥራዉ አንድ ርምጃ ወደፊት ለመራመድ የሚያቅድበት፤ መልካም ነገርን የበለጠ አጠንክሮ ለመቀጠል፣  የሕይወቱ አካል እንዳይሆን የሚፈልገውን መጥፎ ነገር ደግሞ ቆርጦ የመተው እና ከአሮጌዉ ዓመት ጋር ወደ ኋላ የሚጥልበትን እቅድ የሚይዝበት ነው፡፡

“ቸር ተመኝ፤ ቸር እንድታገኝ” እንዲሉ ሰው የአስተሳሰቡ ስሪት ነው፤ አዲስ ዓመት እና ተስፋ፣ አዎንታዊ አስተሳሰብ እና ስኬት ደግሞ ያስፈልጋል፡፡ አዎንታዊ አስተሳሰብ በስኬት እንዲገለጽ ከምኞት በዘለለ ሁላችንም በየተሰማራንበት የሥራ ድርሻም ሆነ በግል ሕይዎታችን  ዓመቱን ሙሉ በእቅድ እየተመራን ሥራችንን በትጋት ማከናወን ይኖርብናል፡፡

መልካም አዲስ ዓመት!።

በኲር የጳጉሜን 3 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here