በግሏ ዘጠኝ የሙዚቃ አልበሞችን ሠርታለች::
ከአዱኛ ቦጋለ߹ ደረጀ ደገፋው߹ አስናቀ ገብረየስ እና ጸጋየ እሸቱ ጋር አራት የሙዚቃ አልበሞችን አውጥታለች። በተለያዩ ጊዜያት ነጠላ ዜማዎችን አቅርባለች:: ከባለቤቷ አበበ ብርሀኔ ጋርም ዘፍናለች:: ብዙዎች ያልታደሉት ስርቅርቅ ድምጽ ባለቤት ናት::
ፍቅርአዲስ ጥላሁን ገሰሰ በ1997 ልዑል አስወደደኝ አልበምን ስታወጣ አድናቆት ከቸራቸው ዘፋኞች ቀዳሚዋ ናት:: “በጣም አሪፍ ስራ ነው የሰራሽው ኮርቼብሻለው ብሎ ደውሎ ሲያመሰግነኝ ለመናገር ራሱ አልቻልኩም ነበረ:: እውነት በጣም ነበር ደስ ያለኝ እሱ ሲደውልልኝ” ስትል የጥላሁንን አድናቆት ታስታውሰዋለች::
ወላንሳየ߹ የቆሎ ተማሪ߹ ሳብ በለው߹ ልዑል አስወደደኝ߹ እምቢ߹ ምስክር አልበሞች ፍቅርአዲስ ነቅዓጥበብ በሙዚቃው ዘርፍ ውስጥ ተወዳጅ አሻራዎችን ያተመችባቸው ናቸው::
ከሰሞኑ ደግሞ “ደህና ሰው” በሚል ዘጠነኛ አልበሟን ለአድማጭ አድርሳለች:: የተወለደችው ከጎንደር ሰላሳ አምስት ኪሎ ሜትር በምትርቀው ደንቢያ ወረዳ ቆላድባ ከተማ ነው:: ዘፈን ባለበት ፍቅርአዲስ ነበረች:: በጣም ከፍተኛ የሙዚቃ ፍላጎት ነበራት። ዘፈን በተዘፈነበት ቦታ ሁሉ እየሄደች መዝፈን ደስ ይላታል። እንዲያውም ስሟ ካላት ሙዚቃ ፍቅር አንጻር “ከበሮ ጠራኝ ነበር የምባለው ሀገር ቤት” ስትል የልጅነት ዘመኗን ታስታውሳለች::
ከበሮ ሲጠፋ ደረቷን እየመታች ነበር ሰዎች እስክስ እንዲሉ ታደርግ የነበረችው:: ተማሪ ሆና በመጀመሪያ የታዳጊ ኪነት߹ ቀጥሎ በቀበሌ ኪነት እንዲሁም በደንቢያ ወረዳ ኪነት ውስጥም ሠርታለች:: በቀበሌ እና ወረዳ ኪነቶች ሰርታለች:: የወረዳው አስተዳዳሪ ያደንቋት ስለነበር ተዋዘዋዥ ሆና በአስራ አራት ዓመት እድሜዋ የሰሜን ምዕራብ እዝ ኪነትን እድትቀላቀል ወሰዷት:: ልጅ ብትሆንም “እኛ እናሳድጋታለን” ብለው ወደ ጎንደር ከተማ ወሰዷት::
አበበ ተካ እና አዱኛ ቦጋለ ጋር የሰሜን ምዕራብ እዝ ኪነትን ተቀላቀለች:: በዚህም በእዙ ስር የስድስት መቶ ሶስተኛ ኮር ኪነት አባል ሆነች:: በወቅቱ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነበረች:: “ከነዩኒፎርሜ ከነደብተሬ ከትምህርት ቤት ተጠርቼ ተቀላቀልሁ” ትላለች:: በመቶ ሰማንያ ሁለት ደሞዝ ብር በሲቪል ተቀጠረች:: እጅጋየሁ አብዲሳ አጋ የምድር ጦር ኦርኬስትራ ዳንሰኛ እና አሰልጣኝ በነበረችበት በአንድ አጋጣሚ ወደ ጎንደር ታቀናለች:: ወደ ጎንደር ባቀናችበት ጊዜ በወቅቱ የሰሜን ምዕራብ እዝ ኪነት ተወዛዋዥ የነበረቸውን ፍቅርአዲስን አገኘቻት::
አንቺ ዘፋኝ ነው መሆን ያለብሽ ብላ መከረቻት:: በዚህ መነሻነትም ሙዚቃን ሙሉ በሙሉ መቀላቀል ቻለች:: ዛሬ ድምጻዊት እያልን እንድንጠራት ያ ጊዜ የሽግግር ምእራፍ ሆነላት:: የአረጋኸኝ ወራሽ ባደለሽ ጸባይ እና የአስቴር አወቀ ልቅም እንደ ስንዴ የሚሉ ዘፈኖችን በማንጎራጎር ጎሮሮዋን አሟሸች:: የመጀመሪያ አልበም ከአዱኛ ቦጋለ ጋር ነበር የሰራቸው:: የግሏን የሙዚቃ ካሴት ለመስራት አዲስ አበባ መጣች:: ወልላንሳየ በ1982 ዓ.ም አልበም ተሠራ:: የሰራዊት ቤቱን እንዳትከዳ ብለው ወታደሮች አዲስ አበባ ሄደው ወደ ጎንደር ወሰዷት::
ስትመለስ በራሷ ጥረት ክፍሉን ያስጠራች ተብላ የአስር አለቃ ማእረግ ተሰጣት:: በ1983 ዓ.ም የመንግሥት ለውጥ ሲመጣ አዲስ አበባ አብራ ገባች:: ከይሁኔ በላይ እና እያዩ ማንያዘዋል ጋር በ1983 የጋራ ካሴት አላት:: ከአስናቀ ገብረየስ ጋር በ1984 ዓ.ም የጋራ አልበም ሠራች:: ዝም እላለሁ የሚለው ዘፈኗ ተወዳጅ ሆነላት:: ከደረጀ ደገፋው ጋር በ1985 ዓ.ም ካሴት ሠራች:: ከጸጋየ እሸቱ ጋርም በ1986 ዓ.ም የጋራ አልበም አላት::
ፍቅርአዲስ አዲስ አበባ እንደሄደች ነጋዴ ባል አገባች:: ሁለት ልጆችም ወለደች። የአዲስ አበባን የምሽት ክለቦች ባህሪ መላመድ ከበዳት:: ባለቤቷ ሊረዳት አልቻለም:: የሙዚቃ ጉዞዋ በአጀማመሯ ልክ አልሄደላትም:: የልጆቿ አባት ባለቤቷ በሞት ተለያት::
“አምጡልኝ ከጎንደር ማር እሸት ቆርጣችሁ
አምጡልኝ ከአገሬ ማር ሸት ቆርጣችሁ
ዓባይና ጣና ወንዙን ተሻግራችሁ”
በሚል የናፍቆት ዜማዋ በስፋት ተሰማ:: ፍቅርአዲስ ከብዙ አድማጭ አፍ ውስጥ የማይጠፉ ዘፈኖችን የሠራችው በ1989 ባወጣችው ሳብ በለው በሚለው ካሴት ነው:: ለዚህ ደግሞ ተወዳጁ የዜማ እና ግጥም ደራሲ አበበ ብርሀኔ ጋር የፍቅር ግንኙነት መጀመራቸው እና እሱም በዚህ ካሴት ላይ መሳተፉ ነበር የሚሉ አሉ::
በኋላም አበበ ጋር የተጠነሰሰው ፍቅር አድጎ ሁለቱ በትዳር ተጣምረው አብረው መኖር ጀመሩ:: ከዚያ በኋላ ዝናዋ እየጨመረ መጣ:: ተጋብተው ሶስት ልጆች ወለዱ:: የቆሎ ተማሪ 1993፣ ልዑል አስወደደኝ 1997፣ እምቢ 2003፣ ምስክር 2008፣ ደህና ሰው በ2017 ተከታታይ አልበሞች አውጥታለች::
ደህና ሰው አልበም እንዴት ነው? 14 ዘፈኖች ተካተውበታል:: ከወጣት እስከ አንጋፋ የኪነ ጥበብ ሰዎች የተሳተፉበት አልበም ነው:: ሰላም ለኪ የሚል መጠሪያ የተሰጠው ዘፈን ብዙ አነጋግሯል:: ክርክሩ ብዙም ውኃ የሚያነሳ ሆኖ አላገኘሁትም:: የጎንደርን በዘመናት ያልደበዘዘ ገናና ታሪክ እና ስልጣኔ ለማሳየት የሞከረችበት ዘፈን ነው::
ሰላም ለኪ የሚለው ቃል ለቦታ መዋል የለበትም የሚል ክርክር ሰላም ላንቺ አትበይ እንደማለት ነው:: ቃሉ ለምን ግእዝ ሆነ ከሚል ሐሳብ በቀር:: ተስፋ ብርሀን በግጥም አበበ ብርሀኔ ደግሞ በዜማ ተሳትፈውበታል:: ዋናው የሙዚቃው ሐሳብ ቃላት በመሸንሸን ተሸፍኖ አልፏል::
“ጎንደር ወይዘሪት
ውብ እመቤት
ሰላም ለኪ ሰላም ልበልሽ
አዲስ ልጅሽ
ጎንደርም ጎንደር ናት ሰውም ያው ጎንደሬ
የተለየ ነገር ምን መጣና ዛሬ
ተዋልዶ ተዛምዶ በፍቅር የኖረ
አንተ አንቺ ሚያባብል ምን ጉድ ተፈጠረ?”
ከሰላምታዋ በኋላ ምርር እያለች በዜማ የምትጠይቀው ፍቅርአዲስ ቀደምቱን አንድነት በመፈለግ ላይ ናት:: ምነው በመካከላችን የገባ? የሚል ቁጭት ያዘለ ዜማዋን እንሰማለን::
“በጌምድር ተወልዶ አንተ እንዲህ እኔ እንዲያ
ተው ያስተዛዝባል ነገ ከነገ ወዲያ
ዓይናችን አቧራ ካልጋረደው በቀር
ሁላችን ተጓዠ ነን ሀገር ነው የሚቀር”
ለሰላም ለኪ ከልጅ ለእናት ምልጃ የሚደረግበት ዘፈን ነው:: ልጆቿ ከአንድነት ይልቅ መለያየትን፣ ከፍቅር ይልቅ ጠብን፣ ከነገ ይለቅ ዛሬን በማስቀደማቸው ፍቅርአዲስ እባካችሁ የምትልበት የአንድነት እና እርቅ ጥሪ ነው::
አባቶች ችግሮች ሳይገጥሟቸው ቀርቶ አይደለም:: ለሀገር ሲሉ እነሱ ተሸንፈው ሰላምን እና አንድነትን አስቀድመዋል:: አቧራው የሀሰት ወሬ እና ጥላቻ ነው:: በአንድነት የተሳሰሩ ወገኖች ግን ባለመግባባት የት ነህ፣ የት ነሽ መባባላቸው ግራ አጋቢ ነው::
ዘራፍ ያሰኛል ዘፈን በአልበሙ ውስጥ ከተካተቱት መካከል ተወዷል:: አቤት አቤት ብላ ለአምላክ ምልጃዋን በማሰማት ነገር እንዲርቃት ትለምናለች::
“ዘራፍ ያሰኛል ዘራፍ ያስመኛል
ሁለቴ አታጥቃኝ አንዱም አሞኛል
አሁን ምን ያደርጋል ቢሉት ፍቅር ፍቅር
የለፉበት ሁሉ ከቀረ እንዲህ ባጭር
ህመም ነካህ እንዴ የሚያደርግ ድንብርብር
ሲመጡ ሚያስረሳ የወጡበትን በር”
ፍቅር ሁሉን የሚያስቀኝ ስሜት ነው:: ፍቅር ጦርነት ነው:: በመስጠትም ብቻ አይሰራም:: ደግ መዋልም ለፍቅር ዋስትና አይሆንም:: ዋጋ መክፈልም ፍቅርን አያጸናውም:: እንዲያውም እንደ ጅል ያስቆጥራል:: መጀመሪያ በፍቅሩ ጎዳት ቀጥሎ ደግሞ በመክዳት ጎዳትና ነው ሁለቴ አታጥቃኝ የምትለው::
ፍቅሩን ገፍቶ የሄደ ሰው ለልመና ተመልሶ ለምልጃ ሲመጣ ዘወር በል ብላ ነው የምትሸልለው:: ሸልይ የሚለው ዘፈን የተፈቃሪውን ሰብእና ከማጉላት ባሻገር እንተያይ፣ ይዋጣልን የሚል ፉከራ ነው:: “ዘንድሮ አንላቀቅም” ብላ ትፎክራለች::
ብትወድም ባትወድም ማርከኸኝ አትሄድም
ማርኮ መሄድ የለም ገሎ መሄድ የለም
ወይ ትጥለኛለህ ወይ እጥልሃለሁ
ዘንድሮ በዋዛ መች እፋታሃለሁ
እንደ አሞራ ብረር፤ እንደሰው ተራመድ
ቀላል እንደሆነ ልብን ማርኮ መሄድ
ታጥቄያለሁ ብትል የተፈሪን ሱሪ
የእኔም የእቴጌ ነው የዛች ጥበብ ሰሪ
ለፍቅር ለመውደድ ታጥቀው ሲሰለፉ
ክንድ ላይ አይደለም መንፈስ ላይ ነው ሰልፉ”
በፍቅር መማረክ ቀላል አይደለም:: በጉልበት፣ በጥበብ ወይም በአቅም አይደለም የሚልን አገላለጽ በዚህ ሙዚቃ ውስጥ እናደምጣለን:: በፍቅር ማሸነፍ ከመንፈስ ጥንካሬ ብቻ የሚመጣ እንጂ በጉራ አይደለም:: አንተ የለበስከው የተፈሪ ሱሪ ቢሆንም እኔም የእቴጌዋ ትጥቅ አለኝ ስትል እንሰማለን:: የቀደምት ሴት ንግሥቶችን ጉልበት እና ወኔ ወርሳለች:: ዳዊት ጎሊያድን ያሸነፈበትን የመንፈስ ጥንካሬ እናያለን::
ኃያላን በአናሳዎች የተሸነፉበት የመንፈስ ብልጫ ስለተወሰደባቸው ነው:: አንተ ከታጠቅኸው የፍቅር ጦር የበለጠ እኔም አለኝ ነው ሽለላው:: ልታታልለኝ እና የፍቅር ትጥቄን ልታስፈታኝ አትሞክር:: አውቃለሁ ትላለች::
“ቁመቱ እንደ አባይ ነው ትግስቱ እንደ ጣና
አውቆ ትቶት እንጂ መቼ ይበለጥና”
ዓባይ የኢትዮጵያዊያን ቅኔ መቋጠሪያ ውል ነው:: ያመኛል ዘፈን የሚያሳየው ይህን ገሀድ ነው:: ይህቺ አፍቃሪ የዓባይ ማዶን ሰው አፍቅራለች:: አዲስ አበባ ሆና ነው እየዘፈነች ያለቸው:: የጎጃም ሰው ማፍቀሯን እንስማማ:: የተፈቃሪው ሰው ሰብእና ግሩም በሆኑ ስንኞች ቀርቧል::
“ውሀ በውሀ ላይ በሄደበት ሀገር
እኛም አይሳነን ተግባብቶ ለማደር”
የዓባይ ማዶ ልጅ አስተዳደጉ ያስታውቃል:: ትእግስትን ዓባይ ወንዝ በጣና ሐይቅ ላይ ሲሄድ በማየት አድጓልና እሱ ጋር መኖር አልቸገርም በሚል ታዜማለች:: አማራው ሲመርቅ እንደ ጣና ስፋ፤ እንደ ዓባይ ተጋፍ ይላል:: ጉልበት ቢኖረውም ትእግስት አለው:: መታገሱ እንጂ መሸነፉ እንዳልሆነ ያውቃል:: ጣና ሆደ ሰፊ ነው:: ልብን ይወክላል:: ዓባይ ኃይልና ጉልበት ነው:: ሁሉን ማድረግ የሚችል አቅም ቢኖረውም ከጣና ትእግስትን ተምሯል:: አስተዋይነት እና ጥበብን ተምሮ ማደግ ከዚህ ተፈጥሮ የሚማረው ነው::
እያንጎራጎረ ዘፈን ትዝታን ያጭራል:: ሕይወት የፊት ጊዜን በተስፋ፣ ያለፈውን ደግሞ በትዝታ ታስቃኛለች:: የፍቅርአዲስ የዚያ ዘመን ከልጅነት እስከ አሁን ድረስ በትዝታ ተቃኝቶበታል:: ሰው ምንም ቢመቸው በትናንት የታሰረ ፍጥረት ይመስላል:: ትዝታ ደግሞ ትናንት ነው:: የቀድሞ ፎቷችን ከዛሬ ይልቅ የበለጠ የሚያስደስተን ከዚህ የሰው ልጆች በትናንት ከመታሰር ባህሪ በመነሳት ነው::
“አልሆንልሽ ቢለኝ ናፍቆቱን መላመድ
ጭሬ እሞቀዋለሁ የትዝታን አመድ”
ትናንት አልፏል:: ማጠንጠኛ ካሴቱ ትዝታ ነው:: ሰፈሩ፣ ሰዉ፣ ሙዚቃው፣ ስሜቱ ሁሉ ይለወጣል:: በጊዜ ተሸሽጎ ያልፋል:: ፍቅርአዲስ በልጅነቷ ገብታ ቤተሰብ የመሰረተችባት መዲና እንደ ትናንቱ አይደለችም:: ተለውጣለች:: የዋለችበት ሰፈር ተቀይሯል:: ቢኖር እንኳን ስሜት አልባ ይሆናል:: መዲናዋ እርቃን ሆና ትታያታለች:: የዛሬዋ መልክ አይጥማትም::
“እንዳንቀጣጠር ለሳቅ ለጨዋታ
ከቦታውም የለ የምናውቀው ቦታ
የጥንቷን አውልቃ በጣለች መዲና
ምልክትም የለኝ ዝም ብለህ ወዲህ ና”
ምልክት የሌለው ሰው በደፈናው የት ይሄዳል? በቃ በትዝታ መጋለብ ብቻ:: ሕይወት ይቀጥላልና በሀሳብ መጓዝ ብቻ::
አበቃሁ::
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም