“የተደራጁ ጥቂቶች ካልተደራጁ ሚሊዮኖች የበለጠ አቅም አላቸዉ”

0
11

ሀገራዊ ሰላምን በማረጋገጥ ሕብረ ብሄራዊነትን ዕውን ለማድረግ፣ በቴክኖሎጂ እና በሌሎችም ዘርፎች ዕድገትን ለማረጋገጥ እና ተወዳዳሪ ለመሆን ሲታሰብ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ ሆኖ በቀዳሚነት ይነሳል፡፡ ከሕዝብ ቁጥራቸው ውስጥ ከግማሽ በላይ  የሚሆነው ወጣት ያላቸው እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ደግሞ በማንኛውም ዘርፍ ውጤታማ ሆኖ ለመዝለቅ አቅም አላቸው ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ወጣት የኅብረተሰብ ክፍል መብዛት በአግባቡ ካልተያዘ እና ካልተመራ የዕድገት መሠረት መሆኑ ቀርቶ የጥፋት ኀይል እንደሚሆን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በመሆኑም ትውልዱን በሥነ ምግባር መገንባት፣ በእውቀት ማብቃት፣ አትራፊ መንገዶችን  ማመላከት ላይ መሥራት ተገቢ ይሆናል፡፡

በሀገር ዓቀፍ ደረጃም ሆነ በአማራ ክልል የተቋቋሙ የወጣት አደረጃጀቶችም ዋና አላማቸው በማኅበራዊ መስተጋብር ጠንካራ ሕዝብ መፍጠር፣ በምጣኔ ሐብት ራስን መቻል፣ እንዲሁም በሁሉም ዘርፎች ውጤታማ ሆኖ ጠንካራ ሀገርን መገንባት ነው፡፡  ለዚህም የአማራ ክልል ወጣቶች ማኅበራት ፌዴሬሽንን መመልከት በቂ ነው፡፡ የአማራ ክልል ወጣቶች ማኅበር ለፌዴሬሽኑ መመሥረት መደላድል ሆኖ ይነሳል፡፡

ማኅበሩ ምስረታውን ያደረገው በ1995 ዓ.ም ነበር፡፡ ይህም ለወጣቶች መልካም ባህል መስረጽ በር የከፈተ ነበር፡፡ ከዚያም በጎ ፈቃደኝነት እና በጋራ መሰባሰብ ያለው ፋይዳ እየጎለበት መጣ፡፡ የማኅበሩን መመሥረት ተከትሎ የተለያዩ ክበባት እና ማኅበራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ ሄዱ፡፡ ማኅበራቱ ጠንካራ ሆነው እንዲጓዙ ሕብረት መፍጠር ግድ ሆነና የአማራ ወጣቶች ማኅበራት ፌዴሬሽን በወርሀ ሰኔ 2001 ዓ.ም ተመሠረተ፡፡

ፌዴሬሽኑ ጳጉሜ 2 ቀን 2017 ዓ.ም 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን  በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል፡፡ “በወጣቶች የነቃ ሰላማዊ ተሳትፎ የነገ ብቻ ሳይሆን የዛሬ ሀገር ተረካቢነታችንን እናረጋግጣለን” በሚል መሪ መልዕክት በተካሄደው ጉባኤ የተለያዩ የመንግሥት እና የፌዴሬሽን ተወካዮች እንዲሁም የወረዳ፣ የዞን እና የከተማ የወጣቶች ማኅበራት አባላት ተገኝተዋል።

የአማራ ክልል ወጣቶች ማኅበራት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኅይለሚካኤል ካሳሁን የመደራጀትን አስፈላጊነት የገለጸው “የተደራጁ ጥቂቶች ካልተደራጁ ሚሊዮኖች የበለጠ አቅም አላቸው” በማለት ነው፡፡ ይህንንም በመረዳት የክልሉ ወጣቶች ባላቸው ፍላጎት እና ዝንባሌ በተለያዩ ክበባት እና ማኅበራት ተሰባስበው በጋራ መንቀሳቀስ ከጀመሩ ዓመታት ማለፋቸውን ጠቁሟል፡፡

መሰባሰብ ወይም ሕብረት የተበታተነ አቅምን፣ ዕውቀትን፣ ገንዘብን እና ጉልበትን ያሰባስባል፡፡ ይህም የሚከናወኑ ሥራዎች ሁሉ ውጤታቸው ያማረ እንዲሆን ያደርጋል ሲል ፋይዳውን ገልጿል፡፡ ወጣቶች በየአደረጃጀታቸው አብረው በመዋላቸው ብቻ የሚጋሩት የሕይወት ክህሎት ልምድ በሕይወታቸው ላይ አወንታዊ ተጽእኖ እንደፈጠረላቸው ተናግሯል፡፡ በማኅበራት የሚሰጡ ልዩ  ልዩ ተግባር ተኮር ሥልጠናዎች የግንዛቤ አድማሳቸውን እንዲያሰፉ አቅም እንደሆናቸውም በተጨማሪ አበርክቶነት አመላክቷል፡፡ በየትኛውም የሥራ ዘርፍ በሚያጋጥማቸው የሥራ ስምሪት አመራር የመስጠት ልምዳቸውን እንዲያሳድጉ የሕብረት ውጤት ከፍተኛ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ተግባር እና ዕቅድን በውጤታማነት እንዲወጡም ሕብረት ትልቅ የተግባር ትምህርት ቤት መሆኑንም አስታውቋል፡፡ በጎ ፈቃደኝነት ባህል ሆኖ የክልሉ ወጣቶች መለያ ባህሪያት እንዲሆን ያደረገው መደራጀት መሆኑንም አስታውሷል፡፡

የክልሉ ወጣቶች ላለፉት 14 ዓመታት ከመላ ኢትዮጵያውያን ጋር ሆነው በፈጠሯቸው አይረሴ ንቅናቄዎች ለሕዳሴ ግድብ ብሄራዊ ጀግንነት መፈጸማቸውን ተናግሯል፡፡

ፌዴሬሽኑ የወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ከአባል ማኅበራት እና ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በርካቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ውጤታማ ሥራ ማከናወኑን በስኬት አንስቷል፡፡ ከፌዴሬሽኑ የወጡ ወጣቶች ዛሬ ላይ በትልልቅ ሀገራዊ እና ሌሎች መድረኮች ላይ መገኘታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በየጊዜው የሚያጋጥሙ አለመረጋጋቶች፣ በአደረጃጀቱም ደረጃ ተጋርጦበት የነበረው ህልውናን የማጣት አዝማሚያ፣ የአመራር መጓደል እና ብቃት ማጣት፣ የፋይናንስ እጦት እና በየጊዜው የሚፈጠሩ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ለፌዴሬሽኑ በሚፈለገው ልክ አለመጠናከር ፈተናዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ የፌዴሬሽኑ ሦስተኛ ጉባኤም እነዚህ ችግሮች ተፈትተው ፌዴሬሽኑ በሚፈለገው ልክ እንዲንቀሳቀስ መፍትሔ ለማመላከት የተዘጋጀ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ተናግሯል፡፡

ፌዴሬሽኑ የሰላም ችግር በሚገጥም ወቅት መውጫ መንገዶችን ለማመላከት፣ በተግባርም የጸና ሰላምን ለማረጋገጥ የተለያዩ መድረኮች ማዘጋጀቱን እና እያዘጋጀ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡ ሀገርን በምክክር ለማዳን በሚደረገው የሀገራዊ የምክክር መድረክም የሚጠበቅበትን እየተወጣ ያለ ፌዴሬሽን መሆኑን ተናግሯል፡፡

ሁሉም የጋራ ዓላማን ይዞ በጋራ መነሳት፣ ጥላቻ እና መናናቅን ማስወገድ፣ በሥራ መትጋት ኢትዮጵያ ከአሁናዊ ቀውሷ እንድትወጣ ማድረግ እንደሚቻል እምነቱ መሆኑን በመግለጽ የሁሉም መርህ እንዲሆን ጥሪ አቅርቧል፡፡ ሁሉም የሚኮራባት እና ሀገሬ ብሎ ሳይሸማቀቅ የሚጠራት ኢትዮጵያን ወደ ቀድሞው ከፍታዋ ለመመለስ ግን የታታሪ ወጣት እና ሕዝብ መኖር አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሷል፡፡ ሕዝብ አክባሪ መሪ እና ሕግ አክባሪ ሕዝብም ለምንፈልጋት ኢትዮጵያ ዕውን መሆን መሠረቶች ናቸው ብሏል፡፡

ለነገዋ ብቻ ሳይሆን ለዛሬዋ ኢትዮጵያ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባ ፕሬዚዳንቱ አጽንኦት ሰጥቶ ተናግሯል፡፡ ሠላም በጋራ የሚሠራ እና ጥቅሙንም በጋራ የምናጣጥመው በመሆኑ ለአስተማማኝ ሰላም ከታናሽ እስከ ታላቅ፣ ከተማረ እስካልተማረ ሁሉም ባለቤት ሆኖ እንዲሠራ ጠይቋል፡፡  በጫካ ያሉ ወገኞችም ሰላምን ላስቀደመው ውይይት አወንታዊ ምላሽ እንዲሰጡ ፌዴሬሽኑ ጥሪ አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ተወካይ ወጣት አሌክሳንደር ንጉሤ ወጣቶች ጥያቄዎቻቸውን በተናጠል ከሚያቀርቡ ይልቅ በጋራ የመጠየቅ እና የመፍታት አቅም እንዲኖራቸው የፌዴሬሽኑ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግሯል፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ማኅበራት ፌዴሬሽንም ወጣቶች በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው እና ምጣኔ ሐብታዊ ተጠቃሚነታቸውም እንዲረጋገጥ በከፍተኛ ደረጃ እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ ወጣቶች ለሀገራቸው ደጀንነታቸውን እንዲወጡ እና ለሀገር በሚጠቅም ሥራ ላይ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ በተደረገው ጥረትም መልካም ውጤቶች መመዝገባቸውን አስታውሷል፡፡

በሀገር ዓቀፍ ደረጃ በሁሉም ክልሎች የተቋቋሙ የወጣቶች ፌዴሬሽን አደረጃጅቶች በወጥነት ተጠናክረው አለመቀጠላቸውን ተወካይ ፕሬዚዳንቱ አስታውቋል፡፡ የአማራ ክልል ወጣቶች ፌዴሬሽን በመሬት ላይ የተፈጠሩ በርካታ ችግሮችን በመቋቋም የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እያደረገ ላለው ጥረት ግን ዕውቅና ሰጥተዋል፡፡

ፌዴሬሽኑን የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠል በዕውቀት፣ በክህሎት እና በሙሉ ፍላጎት መምራት የሚችሉ ተተኪ ወጣቶችን ማፍራት እንደሚገባም አስገንዝቧል፡፡ ፌዴሬሽኑ በሀገር ደረጃ ላሉ ተሿሚዎች መፍለቂያ መሆኑን ለጠንካራነቱ ማሳያ በማድረግ አንስቷል፡፡ በክልሉ የሚገኙ ባለድርሻ አካላትም ለወጣቶች ፌዴሬሽን መጠናከር የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያበረክቱ አሳስቧል፡፡

የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዘላለም አረጋ በበኩላቸው “በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ የጥፋት ጨለማ ተወግዶ ብርሐን የሚገለጠው በወጣትነት የዕድሜ ክልል ነው“ በማለት የወጣቶች ሁለንተናዊ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ወጣቶች ለአንድ ሀገር ዕድገት የጀርባ አጥንት እንደሆኑ የሚነገረው ወጣቶች በማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሐብታዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች የሚያሳርፉት ተጽእኖ ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡

ወጣቶች በአባቶቻቸው ስፍራ የሚተኩ፣ ቤተሰብን እና ሀገርን የሚዋጉትን ክፋተቶች እና እንቅፋቶች የሚቋቋሙ ጠንካራ ዜጎች  መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ስለሆነም ወጣቶችን በልዩ ልዩ አደረጃጅቶች በማሳተፍ እና በተገቢው መንገድ በማነጽ በሀገር ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር የዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ አማካሪ መስፍን አበጀ(ዶ/ር) የአማራ ክልል ሰፊ የወጣት ማኅበረሰብ ክፍል መገኛ፣ ለሀገር ትልቅ አቅም መሆን የሚችሉ  ጸጋዎች ባለቤት መሆኑን አንስተዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ብሩህ አዕምሮ ያለውን ወጣት ክልሉ ካለው ጸጋ ጋር በተሟላ ሁኔታ አስማምቶ ወደ ምርታማነት ለመቀየር ሳይቻል መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ የአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት ያልጸና ሰላም ውስጥ መገኘቱ ደግሞ ወጣቶች ዕውቀታቸውን እና አቅማቸውን ተጠቅመው ጸጋዎቻቸውን ማልማት የሚችሉበትን ዕድል እንዳሳጣ ገልጸዋል፡፡

2018 ዓ.ም ለአማራ ክልል ወጣት የቁጭት ዓመት ሊሆን እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡ የክልሉ መንግሥትም የ25 ዓመት አሻጋሪ እና የዘላቂ ልማት ዕድገት ዕቅድ ማቀዱን የገለጹት ዶ/ር መስፍን፤ ይህም ወጣቶች ነገን አሻግረው እንዲመለከቱ፣ ጸጋዎቻቸውን ለይተው እንዲያለሙ፣ ሙያዊ አቅማቸውን አሟጠው እንዲጠቀሙ የሚያበረታታ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ለዕቅዱ ተግባራዊነት እና ዕቅዱ ይዞት በሚመጣው ውጤት ተጠቃሚ ለመሆን ወጣቶች ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 ለዛ

“አመለካከትህን ቀይር፤ ከዚያም ዓለምህን ትቀይራለህ” – ኖርማን ቬንሰንት

“አትሌት በኪሰ ገንዘብ ይዞ አይሮጥም፤ በልቡ ባለው የማሸነፍ ተስፋ እና ህልም እንጂ” – ዘቶፒክ

“ከዛሬ ሃያ ዓመት በኋላ ከሠራኃቸው ነገሮች ይልቅ ባልሠራኃቸው ነገሮች ትበሳጫለህ” – ማርክ ትዌይን

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here