ቁጣን ያስከተለዉ ትርኢት

0
17

በጀርባው ላይ የድራጐን ምስል የተነቀሰ ፀጉር አልባ ውሻ በቤት እንስሳት ትርኢት ማቅረቢያ መድረክ መታየቱን ተከትሎ ከእንስሳት አፍቃሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ ማስነሳቱን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ከሳምንት በፊት ለንባብ አብቅቶታል::

በቻይና ሻንጋይ ከተማ በተካሄደው የቤት እንስሳት ማሳያ መድረክ ቻይናዊው አሳዳሪ ጀርባው ላይ በስፋት ድራጐን ምስል የተነቀሰ ውሻን በማቅረቡ በህዝቡ ዘንድ ቁጣ አስነስቷል:: የውሻው ምስል በማህበራዊ ድረ ገፆች በመለቀቁም ብዙዎችን አነጋግሯል፤ ቁጣን ቀስቅሷል፤ ውግዘት አስከትሏል::

የሜክሲኮ ዝርያ የሆነው ውሻ ጀርባው ላይ ድራጐን ተነቅሶ፣ በቀኝ እግሩ የወርቅ ሰዓት፣ የወርቅ ሀብል ወይም ወፍራም ሰንሰለት አንገቱ ላይ ታስሮ የተነሳው ፎቶግራፍ በማህበራዊ ድረ ገጽ ለእይታ በቅቷል::

የውሻው አሳዳሪ በንቅሳቱ ወቅት ምንም አይነት ማደንዘዣ አለመጠቀሙንም ተናግሯል:: ይሄን የሰሙ በሙሉ የግለሰቡን ጨካኝነት ማሳያ መሆኑን ነው በአብነት የጠቀሱት::

የውሻው አሳዳሪ ወይም ባለቤት ውሻውን በታዋቂ የንቅሳት ጠቢብ ከዓመት በፊት ማስነቀሱንም ነው የተናገረው:: የሜክሲኮ ዝርያ የሆነው ውሻው ጀርባው ፀጉር አልባ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ህመም ተቋቋሚ ወይም ለህመም ስሜት ተጋላጭነቱ አነስተኛ ነው ሲልም ሞግቷል የውሻው ባለንብረት::

ነቃሹ ጠቢብ በበኩሉ የውሻው ባለቤት (አሳዳሪ) እንዲነቅስለት ወደ መስሪያ ቦታው ሲያቀርብለት በርካታ ጥያቄዎችን አቅርቦለት እንደነበር እና አሳዳሪው ግን ደጋግሞ  እንዲነቅስለት በመጠየቅ ያስገደደው መሆኑን ነው እማኝነቱን የሰጠው:: ንቅሳቱን በውሻው ጀርባ ላይ ለመስራት አሮጌ የተጣሉ  ወይም የአገለገሉ መሳሪያዎችን መርፌ፣ ምላጭ የመሳሰሉትን መጠቀሙንም ነው በምላሽነት የሰጠው – ነቃሹ::

በማደማደሚያነት የተፈጠረውን ቁጣ እና ከተመልካች የታየውን ምላሽ መሰረት አድርጐ የትርኢት አዘጋጁ የውሻውን አሳዳሪ (ባለቤት)ከትርኢት ማስወጣቱን ሳውዝቻይና ሞርኒግ ፓስት መዘገቡን ድረ ገጹ አስነብቧል::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here