በሩዋንዳ ሰሜናዊ ክልል የመጥፋት አደጋ ያንዣበበባቸው ጐሬላዎች መጠበቂያ ቀጣና ነው:: ፓርኩ በኮንጐ የቬሩንጋ ብሔራዊ ፓርክ እና ከኡጋንዳው ማጋሂንጋ ጎሬላ ብሔራዊ ፓርክን ይዋሰናል::
በብሔራዊ ፓርኩ አስሪ ሁለት የጐሬላ መንጋዎች ወይም ቡድኖች መገኛ በመሆኑ ጥበቃ የሚደረግለት የጐብኚዎች መዳረሻ ሆኗል::
የብሔራዊ ፓርኩ ስፋት 160 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ተለክቷል:: በፓርኩ ቀጣና የካሪሲምቢ፣ ቢሶክ እና ሙሃቡራ የተሰኙ ተራራዎች ይገኛሉ:: በተራራዎቹ ላይ ጐብኚዎች ወጥተው ዙሪያውን መቃኘት ስለሚያስችላቸው በአብዛኞቹ ተመራጭ ቀጣና ነው::
የሩዋንዳው የእሳተ ገሞራ ብሔራዊ ፓርክ ጐሬላዎችን ለመጐብኘት ከሌሎቹ አዋሳኞች ጐብኚዎችን የበለጠ መሳብ ችሏል:: ለዚህም ከኪጋሊ አውሮኘላን ማረፊያ እስከ ፓርኩ የሦስት ሰዓት የተሽከርካሪ ጉዞ በኋላ መደረሱ እና የተጠናከረ ጥበቃ መደረጉ ነው በምክንያትነት የተጠቀሰው::
በ1990ዎቹ በአገሪቱ የነበረው የርስ በርስ ጦርነት እና አደን በቱሪዝም እንቅስቃሴው ላይ አጥልቶበት ቆይቷል:: ሆኖም ከ2005 እ.አ.አ ወዲህ ለሚወለዱ የጐሬላ ግልገሎች ስም የማውጣት ስነስርዓት እንደ ታላቅ በዓል የማስተዋወቅ ስራ በመስራቱ ዘርፉ መነቃቃቱን ድረገፆች አስነብበዋል::
በፖርኩ ከጐሬላዎች ባሻገር ባለ ወርቃማ ቀለም ጦጣዎች፣ ነጠብጣባማ ወይም ዥንጉርጉር ጅብ ከዓዕዋፍም 178 ዝርያዎች እንደሚገኙ ተመዝግቧል::
በፓርኩ ጐብኚዎች ቀደም ብሎ ኘሮግራም አስይዘው በቁጥር የተወሰኑቱ ብቻ የጐሬላ መንጋዎችን ቀርበው እንዲመለከቱ እንደሚያደርግ ወይም ፈቃድ እንደሚሰጥ በወጣው ደንብ አስተዋውቋል- የፓርኩ አስተዳደር:: ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ቮልካኖሱ ናሽናልፓርክ፣ ቮልካኖስ ናሽናል ፓርክ ሩዋንዳ እና ቪዚት ሩዋንዳ ድረገፆችን ተጠቅመናል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም